Tuesday, 10 March 2020 00:00

ቱራየቭ በብራና መጻህፍቶቻችን ላይ ያደረገው ጥናት

Written by  ታደለ ገድሌ ጸጋየ (ዶ/ር)
Rate this item
(2 votes)

  በርካታ የውጭ አገር ዜጎች በኢትዮጵያ የብራና መጻሕፍት ላይ ከፍተኛ ጥናትና ምርምር አድርገዋል፡፡ ለአብነትም  አውገስት ዲልማን፣ ኢኒሪኮ ቸሩሊ (በጣሊያን ወረራ ወቅት በደብረ ሊባኖስ መነኮሳት ግድያ እጁ ያለበት)፣ አሌሳንድሮ ጎሪ፣ ኢኖ ሊትማን፣ ካርሎ ኮንቲ ሮሲኒ፣ ስቲቸን ስትሬልሲን፣ ኢኞሲዮ ጉይዲ፣ አንቶን ዲ አባዲየ፣ ኤድዋርድ ኡሌንዶርፍ (ለኤርትራ መገንጠል የጥላቻ መደላድል የሠራ እንግሊዛዊ)፣ ጳውሎ ማራሲኒና ሌሎች  በብራና መጻሕፍት ላይ ትኩረት አድርገው ለኢትዮጵያ ጥናት ተቋም የላቀ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ በተመሳሳይ ሩሲያዊው ቦሪስ አሌክሳንድሮቪች ቱራየቭም እንዲሁ በዘመኑ  በኢትዮጵያ ብራና መጻሕፍት ላይ የላቀ ጥናትና ምርምር አድርጎ፣ ወጥ የሆኑ  ልዩ ልዩ ሥራዎቹን ለኅትመት አብቅቷል፤ ነገር ግን በሀገራችን የፊሎሎጂ ጥናት ክፍል ብዙም ያልታወቀና ስሙ  እምብዛም የማይጠቀስ  ሳይንቲስት ነው፡፡
በቀድሞዋ ሶቭየት ኅብረት በቫሮኔዥ ስቴት ዩኒቨርሲቲ በትምህርት ላይ በቆየሁባቸው ዓመታት፣ ስለ ቦሪስና ስለ ቡላቶቪች ሥራዎች ከሩሲያውያን አስተማሪዎቼ ሰምቼ በመደነቅ፣ በሩሲያኛ የታተሙ ኢትዮጵያዊ መጽሐፎቻቸውን ገዝቼ ለማንበብ እድሉ ገጥሞኛል፡፡ እነዚህ የኢትዮጵያ ባለውለታዎች የሆኑ የሩሲያ ዜጎችን ለማስተዋወቅ በተለይ ስለ ቡላቶቪች በተደጋጋሚ በጋዜጣና በመጽሔት ላይ መጻፌ ትዝ ይለኛል፡፡ ሞስኮ ያደገውና የበለጸገ የሩሲያ ቋንቋ አዋቂ የሆነው ዶክተር አምባቸው ከበደም የዚህን ሰው  ሁለት ሥራዎች ከምንጩ ከሩሲያኛው ተርጉሞ በማሳተም ባለውለታችን ሆኗል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፊሎሎጂ የትምህርት ክፍል፣ የሦስተኛ ዲግሪ ጥናት በማደርግበት ጊዜ፣ በተለይም የዚህን ሳይንቲስት ስም (ቱራየቭን) ጠቅሰው፣ ‘በመጽሐፈ ሰዓታት ላይኮ ሠርቷል  እስቲ እየው’ ብለው ያነሣሡኝ  ፕሮፌሰር ሺፈራው በቀለ ናቸው፡፡ ቱራየቭ ጥናትና ምርምር ያደረገባቸውን የኢትዮጵያ የብራና መጻሕፍት በዳግማዊ ዓፄ  ምኒልክ ዘመን  ከሀገራችን ወደ ሩሲያ ፒተርስበርግ ከተማ በመርከብ ጭኖ የወሰዳቸው  አሳሹ፤ የጦር መኮንኑና ሐኪሙ አሌክሳንደር ቡላቶቪች ነው፡፡
በ19ኛው  መቶ ክፍለ ዘመን ከኢትዮጵያ ጋር መልካም ግንኙነት ከነበራቸው የአውሮፓ አገራት ውስጥ አንደኛዋ ሩሲያ ናት፡፡ ለዚህም  ሁለት ዋና ምክንያቶችን ለመጥቀስ ይቻላል፡፡ አንደኛው፤ ሩሲያ በአፍሪካ ቅኝ ግዛት የሌላት ሀገር በመሆኗ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ኢትዮጵያ ልክ እንደ ሩሲያ የክርስትና እምነት ተከታይና የታላቁ ኢትዮ-ሩሲያዊው ባለቅኔ የአሌክሳንደር ፑሽኪን ቅድመ አያቶች ሀገር በመሆኗ ነው፡፡ በተጨማሪም እንደነ አሌክሳንደር ቡላቶቪች፤ እንደነ ፎን ሊዎንቲቭና ቱራየቭ የመሳሰሉት ተመራማሪዎች ስለ ኢትዮጵያ በሚያወጧቸው ጽሑፎች፣ ሩሲያውያን ኢትዮጵያን ለማወቅ ጉጉት ስለነበራቸው ጭምር ነው፡፡
የጦር መኮንኑ፤ አሳሹና ሐኪሙ
 አሌክሳንደር ቡላቶቪች
በተለይ በሩሲያውያን ዘንድ የከፋ መሐንዲስ እስከ መባል የደረሰውና የቀይ መስቀል አባል ሆኖ ወደ ሀገራችን የመጣው አሌክሳንደር ቡላቶቪች፣ የዐድዋ ጦርነትን ጨምሮ በዓፄ ምኒልክ በተመሩ ሦስት ዘመቻዎች ተሳትፏል፤ ራስ ወልደ ጊዮርጊስ (በኋላ ንጉሥ) እንግሊዞችንና ፈረንሳዮችን ያስጨነቀውን  16 ሺህ ሠራዊት ይዘው ወደ ጂማ ከፋና ወደ ሩዶልፍ ሐይቅ፣ ወደ ቱርካናዎች ምድር ዘምተውና ከቅኝ ገዢዎች ቀድመው ሩዶልፍ ሐይቅ ላይ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በተከሉበትና ዳር ድንበራችንን ባስከበሩበት ወቅት  አውራ መንገድ ሠሪና ቀያሽ፤ የኢትዮጵያን መልክዓ ምድር አጥኚና ፎቶግራፍ አንሺ፤ የጦሩ ዜና መዋዕል ጸሐፊ፤ተመራማሪና አሳሽ  ሆኖ ሠርቷል፡፡ ለዚህም አበርክቶው ከዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ የወርቅ ጋሻና ሰይፍ እንዲሁም ሌላም ሽልማት  ተበርክቶለታል፡፡ ወደ ሀገሩ ከተመለሰ በኋላም፤ ከዓፄ ምኒልክ ሠራዊት ጋር፤  ከእንጦጦ እስከ ባሮ፣  ኢትዮጵያውያን በሩሲያውያን እይታ፡ የጥቁር ሕዝቦች ዓለም (ቾርኒ ፊኒክስ) የሚሉና ሩሲያውያን ስለ አፍሪካና ድንቂቱ  አቢሲኒያ የማወቅ ፍላጎት እንዲኖራቸው የሚያነሳሱ መጻሕፍትን አሳትሞ ባሰራጨበት ጊዜ፣ በአድናቂዎቹ ‘የኢትዮጵያ ሊቪንግስተን’ ፤‘የከፋ መሐንዲስ’፣ ‘የሩዶልፍ ሐይቅና የቱርካና ምድር አምባሳደር’ እስከ መባል ደርሷል፡፡
ይህም ሥራው ከሩሲያ የጂኦግራፊ ማኅበረሰብ  ዘንድ  ከፍተኛውን የብር ሜዳሊያ ሽልማት አስገኝቶለታል:: እናም ቡላቶቪች በዘመኑ ወደ ሀገሩ ባሻገራቸው የብራና መጻሕፍት ላይ ትኩረት ያደረገው ቱራየቭ፤ በሩሲያ የምሥራቅ ሀገሮችና  የኮፕቲክ ሥነ ጽሑፍ ተወካይ (ኦሬንታሊስት)፣ በሩሲያ የጥንት ታሪክ፣ የሳይንስ አካዳሚና የፊሎሎጂ ትምህርት ተቋም መሥራች፣ የሴም ቋንቋዎች ተመራማሪ፣ የአፍሪካና የመካከለኛው ምሥራቅ ሀገሮች ማለት የግብጽ፣ የኢትዮጵያ፣ የሶርያ፣ የአሶራውያን፣ የዑርና የባቢሎን፣ የሱሜራውያንና የከለዳውያን ጥንታዊና ሴማዊ ቋንቋዎችና የብራና መጻሕፍት ጥናት ቋሚ ተጠሪ ተደርጎ ይታያል፡፡
የብዙ መጻሕፍት ደራሲ፣ በኢትዮጵያ ታሪክና የመካከለኛው ዘመን  የቤተ ክርስቲያናችን ታሪክ ተመራማሪ የሆነው ቱራየቭ የተወለደው እ.ኤ.አ ኦገስት 5 ቀን 1868  ኖቮግሩዶክ በተባለና በቤሎሩስ ግዛት በሚገኝ ቦታ ነው፡፡ ያረፈው ደግሞ እ.ኤ.አ ኦገስት 23 ቀን 1920 በፒተርስበርግ ነው፡፡
በልጅነቱ ቪልኖ ጊምናዚየም ገብቶ የተማረ ሲሆን  ቆይቶም  በፒተርስበርግ ዩኒቨርሲቲ ኢምፔሪያል አካዳሚ የታሪክና የፊሎሎጂ  ትምህርት ክፍልን ተቀላቅሎ፣ በእነ ፕሮፌሰር  ኦስካር ሌም  ቮን  አስተማሪነት የግብጽ ቋንቋን አጥንቷል፡፡ እ.ኤ.አ በ1891 ትምህርቱን እንደጨረሰ  ለአንድ ዓመት  ከፍተኛ ትምህርቱን እንዲያጠና ወደ ውጭ አገር ተላከ፡፡ በወቅቱ በእስክንድርያና በሌሎች ቦታዎች ታዋቂ በነበሩ ምሁራን በእነ አዶልፍ ኢ ማንና ኢንጉኔ  ማስፔሮ  አስተማሪነት የኮፕቲክን፣ የሶርያንና የግእዝን ቋንቋዎች አጥንቶና በበርሊን፣ በእንግሊዝ፣ ፈረንሳይና በጣሊያን ሙዚየሞች ውስጥ ተመድቦ ሠርቷል፡፡ በውጭ አገር እያለም ለማስትሬት ዲግሪው የሚያግዙ ግብአቶችን  አሰባስቧል፡፡
የቅዱስ ፒተርስበርግ ኢምፔሪያል ዩኒቨርሲቲ  
ቱራየቭ እ.ኤ.አ በ1896 ወደ ሀገሩ ከተመለሰ በኋላ የቅዱስ ፒተርስበርግ ኢምፔሪያል ዩኒቨርሲቲ ረዳት ፕሮፌሰር ሆኖ  የኮፕቲክ ጥንታዊ  ኦሬንታል  ታሪክና ቋንቋ አስተምሯል፡፡ እ.ኤ.አ በ1898 በጥንታዊ የግብጽ ቋንቋና አጠቃላይ ባህል ላይ ጥናት አድርጎ  የማስትሬት ዲግሪውን ተቀበለ፡፡ ጥናቱ የኢትዮጵያ ጥንታዊ ቋንቋ  በሆነው ግእዝ ላይ ሰፋ ያለ ምርምር እንዲያደርግ አነሣሣው፡፡ የመጀመሪያ የኅትመት ሥራው የሆነውን “መጽሐፈ ሰዓታት” እ.ኤ.አ በ1897  ያሳተመው በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ላይ ትኩረት አድርጎ  ነው፡፡ በመቀጠል ዛሬ እንደ ልብ በሀገራችን የማይገኙትን የቀዳማዊ ዐምደ ጽዮንንና የዓፄ ዘርዓ ያዕቆብን፣ የዓፄ ልብነ ድንግልን፣ የዓፄ ገላውዴዎስንና የዓፄ ሚናስን ዜና መዋዕሎች ከግእዝ ወደ ሩሲያኛ ተርጉሞ አሳትሟቸዋል፡፡ እነዚህ የኢትዮጵያ ነገሥታት የግእዝ ዜና መዋዕሎች እ.ኤ.አ በ1936  በታዋቂው ተመራማሪ በክራስኮውስኪ በአርትኦት ሥራ ጭምር እንዲብራሩና  እንዲበለጽጉ ተደርገዋል፡፡
ቱራየቭ የዶክትሬት ዲግሪ ጥናቱን የሠራውም በኢትዮጵያ ዋና ዋና ቅዱሳን ገድሎች ላይ ነው፡፡ በአጠቃላይ የኢትዮጵያን ገድሎች ፈትሽዋል፡፡ በዚህም ስለ ደብረ ሊባኖሱ መጽሐፈ ፊሊጶስ፣ ስለ ሳሙኤል ዘዋልድባ፣ ስለ አሮኑ ኤዎስጣቴዎስ ወዘተ አጥንቷል፡፡ ሥራዎቹንም  ‘ሞኑሜንታ ኤቲዮጵየ  ሃጊዮግራፊካ’ እና ‘ ስክሪፕቶረም ክርስቲያኖረም  ኦሬንታሊየም’  በተሰኙ  ዓለም አቀፍ የምሁራን  የጥናት ኅትመት ሰነዶች ላይ አሳትሟቸዋል፡፡ እ.ኤ.አ በ1904 የኢትዮጵያ ፊደሎች ማስታወሻ (Pamiatniki efiopsko pismennosti,  ‘Monuments  of Ethiopian letters’) በሚል  ሁለተኛ ሥራውን በግእዝና በሩሲያኛ አሳትሟል፡፡ እ.ኤ.አ በ1906 በፒተርስበርግ ለኢትዮጵያ ታሪክና ለግእዝ ሥነ ጽሑፍ መሠረት የሆኑ የኢትዮጵያ የብራና መጻሕፍትን ዝርዝር ሠርቶ  አቅርቧል፡፡ በቱራየቭ ዝርዝር ውስጥ ከሚገኙት የብራና ጽሑፎች  ውስጥ እነርሱ ‘ማጂክ ’እያሉ የሚጠሩት  ባለ ጠልሰሙ  የግእዝ ጽሑፍ አንዱ ነው፡፡ ቱራየቭ በተጨማሪ የገዳም ሥነ ጽሑፍ የሆነውን ተአምረ ሥላሴን፣ የቅዳሴ መጻሕፍትን፣ ሐተታ ዘዘርዓ ያዕቆብን፣ ብዕለ ነገሥትን፣ የአስማት ሥነ ጽሑፎችን  አጥንቷል፡፡
ቱራየቭ  ከታዋቂው ምሁር ከዶርን ቀጥሎ በሩሲያ ዩኒቨርሲቲ ግእዝን በማስተማር የመጀመሪያው ፕሮፌሰር ነው፡፡ የኢትዮጵያን ታሪክና ሥነ ጽሑፍ ማስተማር የእርሱ ግዴታና ኃላፊነት እንደሆነ ይሰማው ነበር፡፡ ቱራየቭ  ቭላድሚር ጎልንቺሆቭ ያሰባሰባቸውን 6ሺህ ልዩ ልዩ የግብጽ ብራና መጻሕፍትን ከካይሮ ወደ ሞስኮ በመውሰድ እንዲጠበቁና በኋላም እ.ኤ.አ በአፕሪል 1911 ወደ ሞስኮ ሙዚየም ተዛውረው ፋይን አርትስና ካታሎግ በተሰኘው ክፍል እንዲቀመጡ አድርጓል፡፡ ይህንን የቱራየቭን ጥረት የተመለከተው የሩሲያ መንግሥትም የእነዚህ ውድ ቅርሶች የበላይ ጠባቂ እንዲሆን ሾመው፡፡ ቱራየቭ ግን የመጻሕፍቱ የበላይ ጠባቂ መሆን ያለበት በሙዚየሙ ውስጥ የተመደበው የግብጽ ሥነ ጽሑፍ ክፍል ኃላፊ እንጂ እኔ አይደለሁም ብሎ ተቃወመ:: ቱራየቭ እ.ኤ.አ በ1912 የዩኒቨርሲቲ ሥራውን ለቅቆና በኢትዮጵያ ጥናት ላይ አተኩሮ የምሥራቅ ሀገሮች ጥንታዊ ታሪክ በሚል በሁለት ቅጽ ያዘጋጀውን መጽሐፍ አሳተመ:: ይህም ሥራው በሩሲያ መንግሥት ዘንድ ከፍተኛ እውቅናን ስላስገኘለት እ.ኤ.አ በ1913  የሩሲያ ኢምፔሪያል ሳይንስ አካዳሚ የወርቅ ሜዳሊያ ሸልሞታል፡፡ በዚህም የሳይንስ አካዳሚው  ቃል አቀባይና የቋሚ ኮሚቴ  አባል ሆኖ እንዲሠራ  አስችሎታል፡፡
ባለ ጠልሰሙ  የግእዝ ጽሑፍ
ቱራየቭ ጽኑዕ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት አማኝ የነበረ ሲሆን እ.ኤ.አ በ1917 በነበረው የጥቅምት ሶሺያሊስት አብዮት ወቅት በእጅጉ ይበሳጭ ጀመር፡፡ ምክንያቱም የሩሲያ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት፣ እምነትና ማተብ በሌላቸው ኮሙኒስቶች እጅ ወድቃ ስትሠቃይ ስላየ ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር ጸሎት የሚያደርግበት፤ የአምልኮ ሥርዓቱን የሚፈጽምበትና በሚሠራበት ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ይገኝ የነበረው ቤተ ክርስቲያን በእምነተ ቢሶች እንዲዘጋ በመደረጉ የበለጠ ተናደደ፡፡ ሃይማኖትና መንፈሳዊ ባህል ለታሪክ እድገት መሠረቶች ናቸው የሚለው ቱራየቭ ፤ ብርዛቪያ በተባለው የዩኒቨርሲቲው መንገድ ዳር፣ የራሱን ቤተ ክርስቲያን መሥርቶ ከፈጣሪው ጋር በጸሎት መገናኘት ጀመረ፡፡
ሞስኮ  ኢምፔሪያል ሳይንስ አካዳሚ
ከ1917 የጥቅምት ሶሺያሊስት ሪቮሉሽን በኋላም ቱራየቭ፣ ፔትሮግራድ፣ በያኔዋ ፒተርስበርግ ሥነ መለኮት ኮሌጅ ውስጥ ሆኖ ለሁለት ዓመታት ምሁራዊ ጥናቱን  አጠንክሮ ይሠራ  ጀመር፡፡ ስቪር ቼምትሱቭ (ኢንሳይክሎፔዲያ ኢትዮፒካ ቅጽ 4.2010.፤ 1002) ስለ ቱራየቭ የመጨረሻ የሕይወት ዘመኑ ሲያትት፤ ‘ ከአብዮቱ በኋላ በመላ የሩሲያ ሕዝብ ላይ ከባድ እንቅልፍ ወደቀበት፤ የትም ቦታ የሚኖረው  የእያንዳንዱ ሰው ሕይወት ተናጋ፤ በዚህም ቱራየቭ በአካልም፤ በመንፈስም፤ በሥነ ልቡናም መሠቃየት ጀመረ፡፡ በመጨረሻ  በሩሲያ በሆነው ነገር ሁሉ ነፍሱ ተጨንቃ ሞተ፤ በፒተርስበርግ ከተማ በሚገኘው በኒኮልስኮየ ገዳም  ውስጥ በሚገኘው የመቃብር ቦታም ተቀበረ ’ ብሏል፡፡


Read 7593 times