Print this page
Monday, 09 March 2020 00:00

ሣሙኤል ታፈሰ ከሕይወት የተማሯቸው 10 ነገሮች

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

    የቀጠሮን ሰዓት በአግባቡ መጠቀም፡፡
ማለቅ ያለበት ከሆነ ሥራህን በዕለቱ ጨርስ፡፡
ጊዜን ያከበረ አሉ፤ ራሱ የተከበረ ይሆናል፡፡ ያላከበሩት ጊዜ በጭንቅ ወቅት እንዲደርስልህ መጣራት አግባብ አይደለም:: ያላከበርከው ጊዜ፣ የውርደት ጉድጓድዎችን ይቆፍርልሃል እንጂ ከማጥ አያወጣህም፡፡
ማደር የሌለበት ሥራህን ለሚቀጥለው ቀን አለማስተላለፍ ቀንህን ብሩህ ያደርገዋል:: የተደላደለ ሕይወት እንድትመራ ጥርጊያ መንገድ ያመቻችልሃል፡፡
አንዳንዶች “MISTER TODAY!” ይሉኛል፡፡ “MISTER TODAY”/ሚስተር ቱዴይ መባል መባረክ ነው፡፡ ሣሙኤል የዛሬ ሰው ነው እንደማለት ነው፡፡ መጠርያው በትክክልም እኔን ይገልጸኛል ብዬ አምናለሁ:: ሰው የሚሳካለት የጊዜ ባርያ ሲሆን ነው፡፡
ጠዋ፣ ጐኅ ሲቀድ እነሳለሁ፡፡ “ጂም” እሠራለሁ፡፡ ሰውነቴን ሳላፍታታ፣ አዕምሮዬን ሳላዝናና ወደ ሥራ ገበታዬ አልሰማራም፡፡ ከጥዋቱ ሁለት ሰዓት እስከ ስድስት ሰዓት ቢሮዬ ነኝ፡፡ ምሳ ለመብላት ቤት እሄዳለሁ:: እመለሳለሁ፡፡ ባለ ጉዳይ እቀጥራለሁ:: የቀደመ ቀጠሮ ካለኝ አስተናግዳለሁ:: አመሻሹን ማርዮት ሆቴል ነኝ፡፡ ለየት ያሉ ጉዳዮችን የምጨርሰው እዚህ ሆቴል፣ የቀጠርኳቸውን ሰዎች እራት እየጋበዝኩ ነው፡፡
የምንቀሳቀሰው በአጀንዳ ነው፡፡ ቀጠሮ ካለኝ አምስት ደቂቃ ባላረፍድ ደስ ይለኛል:: የዛሬ ሰው ነኝ፡፡ መሥራት እየቻልኩ ለነገ የማሳድረው ነገር የለኝም፡፡ የዛሬን ዛሬ፡፡ ከዛሬ ትናንት ይሻላል፡፡
ትናንት የሠሩት ሥራ ከብዙ ነገር ይጠብቅዎታል፡፡ ዛሬ ነገ ሲሉ፣ ሊሠሩት ካሰቡት ጋር የተያያዘ ሌላ አዋጅ ወጥቶ ዕቅድዎ ሊሰናከል ይችላል፡፡
የሰን ሻይን ኮንስትራክሽን ሠራተኛ ሁሉ ጉዳይ ይዞ እፊቴ ሲቀርብ ወይም ፈልጌው ሲመጣ አጀንዳ ይዞ ነው፡፡ በየአመቱ፣ አዲስ አመት በመጣ ቁጥር 1ሺ500 ቅጂ አጀንዳ በሰንሻይን ድርጅት ስም ይታተማል:: አጀንዳ እወዳለሁ፡፡ መቼ ከሀገር ውጭ እንደምሄድ ቀድሜ አውቃለሁ፡፡ አንድ ሰው ጊዜዬን ከሚያበላሽብኝ ገንዘቤን ወስዶ ሳይመልስልኝ ቢቀር ይሻለኛል፡፡
ስለ ጊዜ በቂ ግንዛቤ ሲኖርህ ዛሬ ላይ ቁጭ ብለህ፣ ነገ ሥራህ ምን ሊገጥመው እንደሚችል መረዳት ትችላለህ፡፡
ማለቅ ያለበት ከሆነ ሥራዎትን በዕለቱ መጨረስ፡፡
ማደር የሌለበት ሥራዎትን ለሚቀጥለው ቀንም አለማስተላለፍዎ ቀንዎን ብሩህ ያደርገዋል፡፡ የተደላደለ ሕይወት እንዲመሩ ጥርጊያ መንገድ ያመቻችልዎታል፡፡ “MISTER TODAY!” (ሚስተር ቱዴይ) መባልዎ መባረክ ነው፡፡
በተቻለ መጠን በደንብ የምታውቀውን ብቻ ሥራ፡፡
ሁላችንም ያለን የተመጠነ ዕድሜና የተመረጠ የሥራ ዓይነት ነው፡፡ ያየነው ሁሉ ሊያምረን አይገባም፡፡ የማናውቀውን ስንሞክር ሕይወታችን ግራ በመጋባት የተሞላ ይሆናል፡፡ በአጭሩ ይህን በማድረግህ ከብት ባልዋለበት ኩበት እንዳትለቅም ያደርግሃል፡፡
እኔ በበኩሌ የማውቀው ነገር ላይ ነው፣ ልቤን ማሳረፍ፣ ጊዜዬን ማሳለፍ የምፈልገው:: እርሻ ላይ ቢጥሉኝ የትኛው ስንዴ፣ የትኛው የገብስ አዝመራ እንደሆነ ስለማላውቅ፣ ሌላው ገብቶ አተረፈበት፣ ወይም ስም አገኘበት ብዬ ዘልዬ ለመግባት አልፈልግም፡፡
በማውቀው ስራ ላይ ካተኮርኩ ሌላው ቢቀር ራሴን አልጐዳም፡፡ ሆስፒታል ብከፍት የዶክተሮቹ ታዛዥ ነው የምሆነው:: ቋንቋውን ሙያውን አላውቀውም፡፡ የእኔ ቁርኝት ከመሀንዲሶች ጋር ነው፡፡ የሚሉት ይገባኛል፡፡ የምለው ይገባቸዋል፡፡ ስለዚህ እንተጋገዛለን፡፡ ተልዕኮአችንን እናውቀዋለን:: አዲሱን ነገር እስክለምደው ድረስ ጊዜ ይፈልጋል፡፡ ያን ለመልመድ የሚፈጅብኝን ጊዜ ደግሞ እኔ አጥብቄ እፈልገዋለሁ፡፡
ያ ማለት ደግሞ አዲስ የቢዝነስ አማራጮችን ለመሞከር እፈራለሁ ማለቴ አይደለም፡፡ ለምሳሌ ወደ ሆቴል ሙያ ስገባ ተፈትኜ ነበር፡፡ እየዋልኩ እያደርኩ ግን የሥራውን ሂደት ተረዳሁት፡፡ የሆነ ጊዜ፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ዘንድ ተጋብዘን ቀርበን ነበር:: የቀረብንበት ምክንያት በሪል ስቴት ሥራ ላይ ተሰማርተን የነበርን ኢትዮጵያውያን ክስና ወቀሳ ቀርቦብን ነው፡፡ አቶ መለስ፣ በንግግራቸው እኛን ሸንቆጥ አደረጉን፡፡ እኛም፤ “ምንድነው ያጠፋነው?” አልናቸው::
እሳቸውም፤ “ያጠፋችሁት ነገር የለም፤ የእናንተ ሥራ ማለትም የሪል ስቴት ሥራ “ፋስት መኒ” ነው፡፡ አሁን ተዘርቶ፣ አሁን በቅሎ፣ አሁኑኑ ውጤቱ የሚገኝ፡፡” አሉን፡፡
“ታዲያ ሰርቶ ማደር ወንጀል ነው ወይ?”
“እኛ የምንፈልገው ብዙ ሠራተኞችን የሚያሳትፍና የሥራ አጡን ቁጥር የሚቀንስልን ነው፤ ለምን ግብርና፣ ወይም ኢንዱስትሪ ላይ አትገቡም? ወደዚህ ሙያ እንድትገቡ ደግመን ደጋግመን ነገርናችሁ፤ ዕድሉን አመቻቸንላችሁ፤ በቁጣም በማባበልም ሞከርናችሁ፤ እናንተ ግን ልትሰሙን አልቻላችሁም” አሉን፡፡
እኔም ነገርኳቸው፤ “ክቡርነትዎ! እኔን ወደ ሆነ ማሳ ወስደው የትኛው ስንዴ፣ የትኛው ጤፍ ነው? ብለው ቢጠይቁኝ ለመመለስ የምቸገር ሰው ነኝ:: እድገቴም ብቃቴም ኮንስትራክሽን ላይ የተመሰረተ ነው እንጂ ለግብርና ባዶ ነኝ፡፡ ወድጄው ፈቅጄው ካልተሰማራሁበት ደግሞ አትራፊ አልሆንም፡፡ ለዜጋው የረባ ለውጥ አላመጣም፡፡ አስተዳደጌ ነው፡፡ ከየት አመጣዋለሁ? ለአንዳንዱ በግብርና ላይ መሰማራት እጅግ በጣም ቀላል ነው:: እኔ ግን አይሆንልኝም፡፡ ኢንዱስትሪው የሕይወቴ መሰረት ነው፡፡ ሀገሬን መለወጥ፣ ሙያዬን ማሳደግ የተሰማራሁበትን መስክ ማዘመን በምፈልግበት ጊዜ እንዲህ ዓይነቱ ሞራል የሚነካ ነገር መሰማት ቅር ያሰኘኛል:: እንዴት አርባ ሃምሳ ባለሐብት በአንድ ጊዜ ወደዚህ ሙያ እንዲገባ ግዴታ ይጣልበታል? ለሚፈልጉት ግን መንገድ ይከፈትላቸው፤ መንገድ ይዘርግላቸው” አልኳቸው፡፡
ከዚያ በኋላ በዚህ ጉዳይ ዳግም አልተሰባሰብንም፡፡
በተንቀሳቃሽ ስልክ ላይ የሚደውልልዎት ሰው ስለሚኖር በተቻለ መጠን ሁሉንም ስልክ ለማንሳት መሞከር፡፡
አንዷ ስልክ ምን ይዛ እንደመጣች ወይም ልትመጣ እንዳሰበች የምታውቀው ነገር ስለሌለ፣ ስልክ ለመመለስ መሞከር ተገቢ ነው፡፡
5- የሚሰሩትን ሥራ በተቻለ መጠን ጥዋት
    በመግባት ይፈጽሙ፡፡
ይህን በማድረግዎ፣ ቀኑ አለአግባብ እንዳይባክን ያግዝዎታል፡፡ በነቃና በተደራጀ አመለካከት ሥራዎትን እንዲሰሩ ያበረታታዎታል፡፡
የሚሰሩት ሥራ ከአቅም በላይ እንዳይሆን ይሞክሩ፡፡
በሚችሉት አቅም ብቻ በመሥራት በወቅቱ ለመጨረስ መሞከር ተገቢ ነው፡፡
የሚያደርጉት የኢንቨስትመንት ሥራ በአቅም የተደገፈ ይሁን፡፡
በቶሎ የሚመለስ ኢንቨስትመንት ሥራ ላይ አቅምዎትን ከደገፉ በኋላ ለረጅም ጊዜ የሚደረግ ኢንቨስትመንት ለቤተሰብና ለሀገር ስለሚጠቅም፣ ለመስራት ይሞክሩ፡፡
8- እየኖሩ ለመሞት ይሞክሩ!
“ለወደፊት ማለትም አቅሜ ከጠነከረ በኋላ ነው የምደሰተው፣ ወይም የምዝናናው” ብለው ለራስዎ ደስታ የቀጠሮ ጊዜ አያስረዝሙ፡፡ ራስን በመጉዳትና ስሜትን አለቅጥ በመጨቆን ነገን ማፍካት አይቻልም:: እናም ለራስዎ ጊዜ ሰጥተው፣ ለእናቴ ልጅ ነኝ ለማለት ሞክሩ፡፡
በተቻለ መጠን ለሚሠሩ የድርጅቱ ባልደረቦች ሃላፊነት እየሰጡ እንዲሠሩ ይምረጡ፡፡
ሁሉም ሥራ በራሴ ብቻ ነው የሚከናወነው ብለው አይመኑ፡፡ በአንድ እጅ አይጨበጨብም፡፡ እርስዎ የድርጅቱ አንድ እጅ ነዎት፤ ሠራተኞቹ ደግሞ ሌላኛው እጅ፡፡ ቤተሰብዎም በሥራዎና በውጥንዎ እንዲካተት ያድርጉ፡፡
10- እንደገና ሞክር፣ አሁንም እንድገና ሞክር!
በአንድ ወቅት የግል ሄሊኮፕተር ለመግዛት እንቅስቃሴ ውስጥ ገባሁ:: ይህን የሰሙ ብዙዎች ተደናገጡ፡፡ የድንጋጤያቸው ምንጭ ይገባኛል፡፡ እኛ አገር የግል ሄሊኮፕተር መግዛት የተለመደ አይደለም፡፡ እኛ አገር ባይለመድም በውጭ አገር ግን አንድ ባለሐብት ጊዜውንና ምቾቱን ለመጠበቅ ሲል የግል ሄሊኮፕተርና ጄት ይኖረዋል፡፡ ይህን የምለው ስለ አውሮፓና አሜሪካ ባለሐብቶች አይደለም፡፡ ደቡብ ሱዳን ብትሄድ ባለሐብቱ ሠፋፊ እርሻዎቹን የሚያስጐበኝህ በግል ሄሊኮፕተር እያዟዟረ ነው፡፡
እናም፣ እኔም እንደሚያስፈልገኝ አሰብኩ:: ቢኖረኝ ጊዜዬን እጅጉን ይቆጥብልኛል፡፡ ጠዋት ተነስቼ መኪና ይዤ ሰሜን ወሎ የሚገኘውን የመንገድ ፕሮጀክት ለመከታተል ብነሳ፣ መንገዱ ብቻ ሦስት ቀን ይፈጅብኛል፡፡ በአንድ ቀን አጠናቅቄ መመለስ የምችለውን ነገር ሦስት ቀን ከወሰደብኝ፣ ይህን ለማቅለል የግል ሄሊኮፕተር ብገዛ ምንም ማለት አይደለም:: ዛሬ የአንድ የግል ሄሊኮፕተር ዋጋ ዘመናዊ ከሚባል መኪና ጋር ተቀራራቢ ነው፡፡
ሆኖም፣ ለመግዛት ወሰንን፡፡ ሄሊኮፕተር ማሳረፊያ ዱከም ቦታ ከወሰድን በኋላ፣ ደብረዘይት ሌላ ማሳረፊያ ስላለ ተቀራራቢ ቦታ መሆን የለበትም አሉን፡፡ አሁንም ግን አማራጭ መንገዶችን እየፈለግን ነው:: እንሞክራለን፤ እንደሚሳካልንም ጥርጣሬ የለንም፡፡   
(ከሣሙኤል ታፈሰ “ተግባር፤ እኔና ሰንሻይን ከትናንት እስከ ዛሬ” መጽሐፍ፤ የሰንሻይን ኢንቨስትመንት ግሩፕ ባለቤትና ፕሬዚዳንት)

Read 1139 times
Administrator

Latest from Administrator