Print this page
Saturday, 07 March 2020 13:01

‹‹ኮሮና ቫይረስ” በኢትዮጵያ በተከሰተ ማግስት፣ ምን ይፈጠራል?

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(7 votes)

 - መንግስትን የሚፈትኑ፣ በዘፈቀደና በተዝረከረከ አሰራር ለከፍተኛ ጥፋት ሊዳረጉ የሚችሉ ጉዳዮች ምንድን ናቸው? በማግስቱ ከመደናበርና ከመቃወስ፣ - አስቀድሞ ማሰብና ጠንቅቆ መዘጋጀት ይበጀዋል፤ ይበጀናል፡፡
- ብዙ ሰዎች መልካምነትን በመመኘት ወደ ሃይማኖት ተቋማት ይጎርፋሉ፡፡ ይሳለማሉ፤ ይጨባበጣሉ፤ ይሳሳማሉ:: እነዚህ ቀና ተግባራት፣ በሽታን የሚያዛምቱ ሰበቦች ሊሆኑ አይገባም፡፡ የሃይማኖት መሪዎች ምን አስበዋል?
- የኮሮና ቫይረስ በተከሰተ ማግስት፣ ምንጩ እስኪጣራ ድረስ፣ ለጥንቃቄ የከተማዋን ትምህርት ቤቶች መዝጋት፣ ብልህነት ነው፡፡ ብዙ አይጎዳም፡፡ - ትራንስፖርትን ማስተጓጎል ግን ጉዳቱ ያመዝናል፡፡ እጥረት ሲፈጠር፣ በሽታን የሚያዛምት መተፋፈግ ይከተላል፡፡
- የጥንቃቄ ውሳኔዎች የእለት ጉርስን የሚያሳጡ፣ የነገን ኢኮኖሚ ጭራሹን የሚያንኮታኩቱ ከሆነ፣ ከቫይረሱ የከፋ ጥፋትን ያመጣሉ፡፡ የሰዎችን የኑሮ አማራጭ ይባስኑ ማጥበብ፤ የነገንም ተስፋ ማደብዘዝ ጎጂ ነው፡፡
                  

        የኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ ቢከሰት፣ ምን ለማድረግ አስበናል? ለማግስቱስ ምን አቅደን ተዘጋጅተናል?
በአእምሯችን የሚመጣልን ምላሽ፣ ‹‹በመንግስት ታስቦበት ይሆናል››፤ ‹‹መንግስት አቅዶ ሳይዘጋጅበት አይቀርም›› የሚል ቀሽም ምላሽ ብቻ ከሆነ፤ ራሳችንን ለከባድ አደጋ እናጋልጣለን፡፡
ሁሉንም ነገር በብዥታ ለመንግስት አስረክቦ መደንዘዝ፣ ከመዘዝ አያስጥልም፡፡ የኋላኋላ፣ አገር ምድሩ ተዝረክርኮ፣ በጭፍን የመደናበር አስቀያሚ ትርምስ ላይ ይጥለናል፡፡ ሀሳብን ሁሉ በመንግስት ላይ ጥሎ ያለ ሀሳብ ለመኖር መመኘት፣ መጥፎ የኋላ ቀርነት ጠባሳ፣ አደገኛ የአቅመ ቢስነት በሽታ ነው፡፡ ብዙ በሽታዎችንም ጐትቶ ያመጣብናል፡፡
ኮሮና ቫይረስ በቀላሉ የሚዛመተው፣ ሕዝብ በብዛት በሚሰበሰብባቸው አካባቢዎች እንደሆነ፣ እስከ ትናንት ያስተዋልናቸው እውነታዎች ይመሰክራሉ፡፡ ጥናቶችም ያረጋግጣሉ፡፡ ታዲያ ይህን በማገናዘብ ምን ምን ታስቧል? ምንስ ታቅዷል?
የሃይማኖት ተቋማት፣ በተለይ በአገራችን፣ ከህፃን እስከ አዋቂ በብዛት የሚያዘወትሯቸው ቀዳሚ ቦታዎች ናቸው፡፡ በየእለቱ ለፀሎትና ለምስጋና እጅግ ብዙ ሰው የሚሰበሰብባቸው የአምልኮ ስፍራዎች፣ የጤና ባለሙያዎችን አነጋግረው፣ ምን አይነት የዝግጅት ምክር እየሰጡ ነው? ቫይረሱ በኢትዮጵያ ከተከሰተስ፣ ምን አይነት የጥንቃቄ ዘዴ ለመከተል፣ ምን የተለየ አማራጭ መንገድ ለመጠቀም አስበዋል?
ወይስ፣ መንግስት፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጥቶ ትዕዛዝ ካልሰጠ፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ ስለኮሮና ቫይረስ ሁሉንም ነገር ሰምተው ምንም እንዳልሰሙ ሆነው ለማለፍ ያስባሉ? እንዲህ ካሰቡ፣ በጣም አሳዛኝ ነው፡፡ ፀሎትና ምስጋና በቤት ውስጥ ብቻ እንዲካሄድ መንግስት በአዋጅ ካልወሰነ በቀር፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ ‹‹ምንም እንዳልተፈጠረ›› እያስመሰሉ ለመቀጠል ይሞክራሉ? መሞከር የለባቸውም፡፡
ይሄ፣ የሕግና የመንግስት ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ የኮሮና ቫይረስ አደጋን የመከላከል ጉዳይ፣ እውነተኛ መረጃና ትክክለኛ ሀሳብ የመያዝ ጉዳይ ነው፡፡ የሰውን ህይወት በቅንነት የማክበርና ለእውነት የመታመን፣ ቀና የሥነ ምግባር ጉዳይ ነው - ነገሩ፡፡
ሰዎች፣ ለብርሃናማ እውነት፣ ለቀና መንገድና፣ ለንፁህ ህይወት ያላቸውን ልባዊ ምኞትና ክብር ለመግለጽ፤ መንፈሳቸውንም ለማደስ የሚያዘወትሯቸው የሃይማኖት ስፍራዎች፤ የበሽታ አደጋን ለመከላከል የሚያግዙ እንጂ፣ ለቫይረስ መዛመትና ለበሽታ መስፋፋት ሰበብ እንዳይሆኑ መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል፡፡
ሰዎች፣ በየጊዜው በስህተት፣ በድክመትና በጥመት የተለያየ ጥፋት ቢሰሩ እንኳ፣ ለመታረም እንደሚፈልጉ፣ ንፁህ ሕይወትን እንደሚመኙ ለመግለጽ ወደ እምነት ቦታ ይጐርፋሉ፡፡ ይሳለማሉ፡፡ ይጨባበጣሉ፡፡ ይሳሳማሉ፡፡
እነዚህ ቀና ተግባራት፣ የቫይረስ መዛመቻ ሰበቦች ሊሆኑ አይገባም፡፡ ይህም የሃይማኖት ተቋማት ኃላፊነት ነው፡፡ የሃይማኖት መሪዎች እንዲሁም የእያንዳንዱ ሰው የስነምግባር ኃላፊነትም ነው፡፡  
አዎ፤ መንግሥትም ትልልቅ ሕጋዊ ሃላፊነቶች አሉበት፡፡ ለበሽታ ስርጭት የተጋለጡ ቦታዎችን በጥበቃ ውስጥ የሚገቡበትን፣ ግልጽ መመዘኛና ስርዓት አለማሰናዳት ምን ያህል ዝርክርክነትን፣ ዝብርቅርቅ ውሳኔዎችንና ውዝግቦችን እንደሚያስከትል አስቡት፡፡ ይሄ ራሱ ሌላ በሽታ ይሆናል፡፡
የማቆያ ስፍራዎችን በአግባቡ ማሰናዳትም፣ ሌላው የመንግስት ሕጋዊ ሃላፊነት ነው፡፡ ልዩ የህክምና ቦታዎችን ለመፍጠር ከወዲሁ ካልተዘጋጀም ኃላፊነቱን መዘንጋት ይሆናል:: በባለሙያና በቁሳቁስ የማደራጀት፣… በተለይ የኢትዮጵያን ሁኔታ በማገናዘብ፣ ከመደበኛዎቹ የጤና ተቋማት ውጭ፣ ለመኖሪያ አካባቢዎች ያልተጠጉ የማቆያ እና የህክምና ተቋሞችን ማዘጋጀት ወይም ማቀድ አለበት፡፡
የግድ ትልቅ ሕንጻ፣ የተራቀቀ ቴክኖሎጂ መኖር አለበት ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን፣ የህክምና ባለሙያዎች ስራቸውን በብቃት ማከናወን እንዲሁም ሕይወታቸው ለአደጋ እንዳይጋለጥ መጠንቀቅ የሚችሉበት ቦታ መሆን ይገባዋል - የማቆያ ወይም የህክምና ተቋም፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፡፡
ወደማቆያ ስፍራ የሚገቡ ተመርማሪዎች፣ በአብዛኛው ከቫይረሱ ነፃ እንደሚሆኑ ይታወቃል፡፡ እናም፣ የመቆያ ስፍራው፣ ሰዎችን አጉሮ ለቫይረስ የሚያጋልጥ ቦታ እንዳይሆን መጠንቀቅ፣ የመንግስት ሕጋዊ ሃላፊነት ነው - አለበለዚያ፣ ከባድ ተጠያቂነትን የሚያስከትል ይሆናል፡፡  ቀላል የሚመስሉ ጉዳዮችም አሉ:: ከወዲሁ ካልታሰበባቸው ግን ትልቅ ችግር ይሆናሉ፡፡ ለመቆያ ስፍራዎች፣ በቂ ምግብ፣ መኝታ፣ ውሃ፣ ቅያሪ ልብስ አለማዘጋጀት፣ የተሳከረ ዝርክርክነትን፣ የውንጀላና የማስተባበያ ንትርክን ያስከትላል፡፡ ለክፉ ቀውስና ለትርምስም ሰበብ ሊሆን ይችላል፡፡ ይሄ አንድ ምሳሌ ነው፡፡
የመንግስት ኃላፊነት ብዙ ነው፡፡ በመንግስት ስር የሚገኙ ተቋማት እጅግ ብዙ በመሆናቸው፤  በርካታ ሃላፊነቶችን ለመሸከም ይገደዳል፡፡ ትምህርት ቤቶች በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ፡፡
የኮረና ቫይረስ በኢትዮጵያ በተከሰተ ማግስት፣ በዚያ ከተማ የሚገኙ የመንግስት ትምህርት ቤቶች ለሳምንት ተዘግተው እንዲቆዩ ማድረግ፣ የመንግስት ድርሻ ነው፡፡
በእርግጥ አንድ ከውጭ አገር የመጣ ሰው፤ ገና ከአውሮፕላን ሳይወርድ ወዲያውኑ የቫይረሱ ተጠቂ እንደሆነ ከታወቀ፣ የስርጭት መንገዶቹን ለመዝጋትና ለመቆጣጠር ቀላል ነው፡፡ አደጋው የዚያን ያህል አስጊ ላይሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ሁልጊዜ እንዲህ ቀላል ስላልሆነ ነው፤ በደቡብ ኮሪያ፣ በኢራንና በጣሊያን፣ ቫይረሱ በስፋት ሲዛመት የታየው:: ስለዚህ፣ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ ትምህርት ቤቶችን ለሳምንት ያህል ያህል መዝጋት፣ የቫይረስ ስርጭት ለመከላከል ይጠቅማል እንጂ ብዙ ጉዳት የለውም፡፡
በተቃራኒው የትራንስፖርት አገልግሎትን ማቋረጥ ወይም ማስተጓጎል፣ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡
የትንስፖርት እጥረትን መፍጠር መተፋፈግን ያስከትላልና፡፡ ከትምህርት ቤት ወይም ከትራንስፖርት በላይ፣ ከፍተኛ ትኩረት የሚያሻቸው ሌሎች ተቋማትም አሉ፡፡ የሕግ አስከባሪና የፀጥታ ተቋማት፣ ስራቸውን ከወትሮ ከፍ ባለ ብቃትና ስርዓት እንዲያከናውኑ በጥንቃቄ መምራት ቀዳሚውና ትክክለኛው የመንግስት ሃላፊነት ነው፡፡
የውሃ አቅርቦት በመንግስት ስር የተያዘ ስራ በመሆኑም፤ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ንፁህ የመጠጥ ውሃ - ለመደበኛ ህልውና ብቻ ሳይሆን የቫይረስ ስርጭትን ለመከላከልም የግድ ያስፈለጋል፡፡ መብራትና ስልክ የመሳሰሉ አገልግሎቶችም እንዲሁ፡፡
የግል ተቋማትስ? ማንኛውም የጥንቃቄ ሃሳብና ውሳኔ፣ የእለት ጉርስን የሚያሳጣ፣ የነገን ሕይወት ለረሃብ የሚያጋልጥ መሆን የለበትም፡፡ ዳቦ ቤትና እህል በረንዳ፣ የባንክና የትራንስፖርት አገልግሎቶች እንዲሁም ሌሎች የምርት ተቋማት፣ ከጥንቃቄ ጋር፣ ከሞላ ጎደል፣ የዘወትር ስራቸው መስተጓጎል የለበትም፡፡
በአመዛኙ፣ የእለት ጉርስን የማያጎድሉ፣ የነገን ኢኮኖሚ የማያቃውሱ፣… ግን ደግሞ ብዙ ሕዝብ የሚሰበሰብባቸው፣ ለምሳሌ ፊልም ቤቶች ወይም ጭፈራ ቤቶች፣ ስራቸውን ለአጭር ጊዜ ዘግተው ለማቆየት ቢወስኑ ተገቢ ነው፡፡ ስታዲዮሞችም እንዲሁ፡፡
የሃይማኖት ስነ ሥርዓቶች፣ የትምህርትና የኪነ ጥበብ፣ የፌሽታም ሆነ የመታሰቢያ ስብሰባዎች፣ የድጋፍም ሆነ የተቃውሞ ሰልፎች… እነዚህን የመሳሰሉ ክንውኖችን ማለዘብ ወይም ለጊዜው ማስቀረት፣ ከእያንዳንዱ አስተዋይና ቀና ሰው የሚጠበቅ ተገቢ የሥነ ምግባር ውሳኔ ነው - ኮሮና ቫይረስ በተከሰተ ማግስት፡፡
የቫይረሱ አደጋ፣ በግልጽ ወደ አስገዳጅ አዝማሚያ የሚሄድ ከሆነ፣ በመንግስት የሚወጣ የአስቸኳይ ጊዜ ትዕዛዝ፣ የግድ አስፈላጊ ይሆናል፡፡ እስከዚያው ግን በእያንዳንዱ አስተዋይና ቀና ሰው፤ እንዲሁም በግል ተቋማት፣ ሊከናወኑ የሚገባቸው ነገሮች እጅግ የላቁና የበዙ መሆናቸውን እንገንዘብ፡፡ በተለይ በተለይ የጤና ባለሙያዎች ኃላፊነት በጣም ከባድ ነው፡፡
‹‹ፈዋሽ መድሃኒት አውቃለሁ››፣ ‹‹መከላከያ ክትባት ሰርቻለሁ›› እያሉ፣ በባዶ አእምሮ የኖቤል ተሸላሚ፣ በተሳከረ የምናብ ዓለም ውስጥ ተዓምረኛ አምላክ የሆኑ የሚመስሏቸው፣ እጅግ የተናጉ ሰዎች ይኖራሉ:: የባሱም አሉ፡፡ በትልቁም በትንሹም፣ በበጎም ላይ በክፉም ላይ፣ የመዘባበትና የማላገጥ ሱስ የተጠናወታቸው ቀሽም ሰዎች ሞልተዋል፡።
ሁሉም ነገር የአሉባልታ ሰበብ ሆኖ የሚያስጎመጃቸው፤ ከአእምሯቸው መቀጨጭና መጥበብ ጋር፣ እንደ ማካካሻ ‹‹አለምን በስፋት የሚያጥለቀልቅ፣ ግዙፍ የፖለቲካ ድብቅ ሴራ እንደተጎነጎነ ደርሼበታለሁ›› ብለው ለመናገር የሚሽቀዳደሙም አሉ፡፡ መበሻሸቂያና መወነጃጀያ የፖለቲካ ጉዳይ ቢሆንላቸውማ ደስታቸው ነው፡፡ እነዚህን ሁሉ መከላከል፣ የእያንዳንዱ አስተዋይና ቀና ሰው ሃላፊነት ነው - በተለይ ደግሞ የጤና አዋቂዎች፡፡

Read 7340 times