Saturday, 07 March 2020 12:54

ሲያልቅ አያምር!

Written by  አብይ ተስፋዬ አሳልፍ
Rate this item
(2 votes)

በቀጠሯችን መሰረት ከጓደኛዬ ጋር ቁጭ ብለን እያወራን እያለ ድብርት በሞላበት ፊቱ እየተመለከተኝ ‹‹…እና አቢሳንም አፍቅሪያለሁ ነው የምትለው!?›› ሲል ጠየቀኝ፡፡
‹‹አዎ!›› አልኩት እየፈራሁ፡፡ ስሜቱን ልጎዳው አልፈለግሁም፡፡ እውነቱንም ልደብቀው አልሻም፡፡ ‹‹አንተ አፍቅረሃት ከሆነ ግን ይቅርብኝ፣ መቼም አለም ልትሰጠን የምትችለው ብዙ አለና በዚህ ላስቀይምህ አልፈልግም!›› ስል በዳርዳርታ አስታወቅሁት፡፡ በርግጥ አዎ አፍቅሪያታለሁ! ካለኝ ለመተው ወስኜ ነበር፡፡
ትንሽ ከፈዘዘ በኋላ .. ‹‹በጭራሽ!…›› ሲል አረጋገጠልኝ፡፡ ‹‹በመጀመሪያ ግን የንጉስ ዳዊትን ታሪክ ስለጻፍኩት ከውሳኔህ በፊት እንድታነበው እፈልጋለሁ፡፡ ያንን ልታደርግልኝ ትችላለህን?!›› ሲል ጠየቀኝ፡፡
ፈገግ ብዬ ‹‹ የሚያገናኘው ነገር ካለ፣ እሺ ደስ እንዳለህ!›› ስል አረጋገጥኩለት፡፡
***
ከፍቅረኛዬ ከአቢጊያ ጋር ከተለያየን ሶስት ወር ሞልቶን ነበር፡፡ በዚህ ሁሉ ጊዜ ውስጥ ብቻዬን ነበርኩ፡፡ ከእርሷ በፊት ከቤርሳቤህ ጋር ለወራት ቅልጥ ያለ ፍቅር ውስጥ ነበርኩ:: አሁን ደግሞ አቢሳ የምትባል ጉብል አፈቀርኩና ተሰቃየሁ፡፡ አቢሳ የማለፊያ መንገዱን እንድጓዝበት ያሳየችኝ ቢሆንም አልሄድኩበትም፡፡ በሁለት ነገር ሀሳብ ገብቶኝ ነበር፡፡  አንደኛ ከፍቅረኛዬ ጋር ከተለያየን ገና ቅርብ የሚባል ግዜ ስለነበር፣ ስለ ምን ቶሎ ፍቅር እንደያዘኝ ግራ ተጋባሁ:: (የበፊቷን አላፈቀርኳትም ወይስ አሁን ፍቅር አልያዘኝም ወይስ ምን ሆኜ ነው እያልኩ ከራሴ ጋር በየቀኑ እጨቃጨቃለሁ፡፡) ሁለተኛ ደግሞ አቢሳን ጓደኛዬ ያፈቅራት ስለነበር (ይመስለኝ ስለነበር!) የመንጠቅ ያህል ተሰምቶኝ እስክንነጋገርበት ብዬ ነበር::  
መቼም በህይወት መንገድ ለሁሉም ነገር ተደጋጋሚ ዕድል ይኖራል፡፡ ፈፅሞ የማይደገም ነገር ምን አለ? እነዚህ ከላይ የተገለፁት ነገሮች ደግሞ ብዙ ግዜ ተደጋግመው ይከሰታሉ ብለን እናስባለን፡፡
በእርግጥ ከቀድሞ ፍቅረኛዬ ፍቅር ይዞኝ ነበር፡፡ እናንተ እንደምትሉት አይነት ፍቅር ግን አይደለም፤ ምክንያቱም አላበድኩም፣ እንቅልፍ አልከለከለኝም፡፡ አልጠቆርኩም (ምናልባት ጥቁር ስለሆንኩ ይሆናል)፣ አልከሳሁምም (ምናልባት ቀጭን ስለሆንኩ ይሆን!?) ግና በደምብ አፍቅሬ እንደነበር አውቃለሁ፡፡ በምኞት መንደድና ፍላጎት ማሳየት፤ በሆኑ ሰዓታት መዳፍ እስኪያልብ እጆቼን እያፋተጉ በሃሳብ መንጎድ፣ በብርሃንና በጨለማ እጅ ለእጅ ተያይዞ መጓዝ:: በየአደባባዩ ሃፍረትን ጥሎ ተቃቅፎ መዞርን ሁሉ አድርጌ ነበር፡፡  (በእርግጥ ከዚያም በፊት አድርጌዋለሁ!)
እና ታዲያ አብሮነት እንደነበር ሁሉ መለያየት መቼም አዲስ አይሆንምና (ጨለማ ካለ ብርሃን ይኖራልና!) ተለያየን፡፡ በመለያየት ሰዓት ወደ ጥልቁ ባትወድቅም ይደብርሃል፣ ትበሳጫለህ፣ ግና ብርቱ ከሆንክ በግዜ አፈርህን አራግፈህ ትወጣለህ! ከቆነጃጅቱ ጋር በድጋሚ መሳሳቅ ይኖርብሃልና መነሳትህ ግድ ነው! ሁሉ ነገር በዙሪያዬ አጥር ሊያስቀምጥብኝ እንደሚፈልግ እገነዘባለሁና የነዚህን ነገሮች ቀንበር ከራሴ ላይ አስወግዳለሁ ብዬ ለራሴ ቃል ገባሁ፡፡ ራሴን ለማገዝና ለማዘዝ ጥረት ጀመርኩ፡፡ ለማን ይድላው ብዬ ነው በብቸኝነት የምሰቃየው! የተፈጠርኩት ከእነርሱ ጎን እንድሆን ነው፡፡
***
በማግስቱ ጓደኛዬ ‹ተነስ፣ ታጠቅ፣ ዝመት!› የሚል ርዕስ ያለው በኮምፒውተር የተተየበ ፅሁፍ ሲሰጠኝ ተቀበልኩትና ምንም መልስ ሳልመልስለት በአካባቢዬ ወደሚገኘው ካፌ ጎራ ብዬ፣ ቶሎ ቶሎ ማንበብ ጀመርኩ:: (ምን ሊነግረኝ እንደፈለገ ግራ ገብቶኝ ስለነበር ለማንበብ በጣም ጓጉቼ ነበር፡፡)
ገፅ - 1
ተነስ!
ንጉስ ዳዊትን እወደዋለሁና የሱን ታሪክ ደጋግሜ አስተውላለሁ፡፡ (ከእረኝነት እስከ ቤተ መንግስት … ከዚያ በየጦር አውድማና በየጓዳው አየዋለሁ...)፡፡ ከታሪኮቹ ለመማር ብዙ ጥረት አደርጋለሁ፡፡
ዳዊት ሺ ቆነጃጅትን አቀፈ! (ይገርማልኮ!) ማንም የከለከለው የለ! በዚያ ሁሉ ግዜ ግን ልበ አምላክ ነበረ፡፡ (እኔ ታዲያ አንዲትን ወጣት መከተል የሚከለክለኝ ህግ ከየት ወደቀብኝና ነው ጥቅሻ ባየሁና በጠቀስኩ ቁጥር አዕምሮዬ የሚከሰኝ! ወደሃታል ባሉኝስ ቁጥር ለምን ይሆን የሚጨንቀኝ?)
አቢጊያ የሃብታሙ የናባል ሚስት ነበረች፣ ቆንጆና ባለትልቅ አዕምሮ ሴት ናት፡፡ … ታዲያ ዳዊት ለእርሱና በበርሃ ለሚኖሩ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ከባሏ ስጦታ እንዲላክለት ቢጠይቅ … ባለቤቷ ይህ ደግሞ የማን ኩታራ ነው፤ አላውቀውም በሉት ሲል መለሰለት:: ዳዊት በእግዚአብሔር ስም እየማለና እየተገዘተ፣ ባሏን ሊያጠፋው መዝመቱን አቢጊያ ሰማች:: ቀድማ ምግቡንም መጠጡንም ይዛ ተደብቃ መጣችና አራት መቶ ባለ ሰይፎችን አስከትሎ የዘመተውን ዳዊትን እጅ ነሳችው፡፡ ውብ ነበረች፣ ደግሞም ሰው አክባሪና አርቆ አስተዋይ:: ለመነችው፡፡ በውበቷና በአክብሮቷ ተመስጦ ነበርና ልመናዋን ሰምቶ ተመለሰ፡፡ እግዜሩም አርቦሹ አይደል! ነገሮች የተመቻቹለት ሆነ፡፡ ባሏ ሰክሮ ይጨፍር ነበር፤ በነጋታው ስካሩ ሲለቀው ብትነግረው እንደ እምነበረድ ሃውልት ክው ብሎ ነበር የደረቀው፡፡ እናም በቀናት ውስጥ ተፈጥሯዊ በሆነ ሁኔታ ሞተ:: ዳዊት ሞቱን ሲሰማ ቆንጆዋን አቢጊያን  አገባ፡፡ (ይሁና!) … ዘይገርም ነገር! እና ታዲያ ምን ይደረግ!? ምንም!
እኔ የሚገርመኝ የራሴ አዕምሮ ለምን እንደሚከሰኝ ነው፡፡ ለምን!?  መውደድን ማን ነው የሚከለክለኝ? ለአንዱ ወደ ፊት መቀጠል አንዱ ወደ ኋላ ይቀራል፣ ያገባ ይፈታል፣ የፈታም ያገባል፡፡ መዐዛዋንም.. ትዝታዋንም መተው ይቻላል፡፡ በህይወት ጎዳናህ ሌላ መዓዛና ሌላ ትዝታ መጨመርም  … መተካትም ይቻላል፡፡ ግና የመነጠቅ ህመሙ ያሰቃያል፡፡
ዳዊት ግን ይገርመኛል … ሺ ቆነጃጅትን ማቀፍ ተፈቅዶለት እያለ የሚመኘው የሌሎችን ሚስቶች ነበር፡፡ መንጠቅና መውሰድ ይወድ ነበር ማለት ነው! ለራሴ ደግሞ እላለሁ … በል ተነስ! … ወደ ምኞትህ ተራመድ፡፡ ሌሎች ውድህን ሳይነጥቁህ ጠንክረህ ተራመድ፡፡ ግና ምን ያደርጋል? የሚሳካው ለጮሌዎች ብቻ ነው፡፡
ታጠቅ!
ከእለታት አንድ ዕለት ዳዊት ከቤተ መንግስቱ ሰገነት መስኮት ላይ ሲንጎራደድ (ምናልባት ደክሞት እየተዝናና ይሆናል፣ ምናልባት ከቁባቶቹ ከአንዷ ጋር ተቃቅፎ ሲያበቃ ንፋስ ሊወስድ ይሆናል፣ ምናልባት ደግሞ የጦርና የልማት ዕቅዱን ሊያስብበት እየተከዘ ይሆናል፣ ምናልባትም ሌላ…፡፡)
እናም በመስኮት ብቅ ማለት ሐጢያት አልነበረም፤ መዝናናትም ሐጢያት አልነበረም፤ ብቅ ሲል የያው ግን ቤርሳቤህ ስትታጠብ ነበር:: እጅግ መሰጠችው፣ ግና ወይዘሮ ቤርሳቤህ የሚወደው የጦር ጄነራሉ የኦርዮን ሚስት ነበረች፡፡ ዳዊት ሺህ ቆነጃጅት ነበሩት፣ ኦርዮን ግን አንድ ቤርሳቤህ ብቻ ነበረችው፡፡ (ምስኪን እኔ!)
ዳዊት አንዱን ባለሟል ጠራና አናገረው ‹‹...ያቺ ጉብል ማናት!?››
‹‹ወይዘሮ ቤርሳቤህ ጌታዬ!››
‹‹…እንዲች ያለች ጉብል በድፍን ከተማዬ አላየሁም፤ ስለ ምን ደበቃችሁኝ? … እስኪ ጥራልኝ…››
‹‹የጀነራል ኦርዮን ሚስት ናትኮ ጌታዬ?…››
ዳዊትም ጥቂት አሰበና … ‹‹…ቢሆንም ጥራት…›› … ተጠራች፡፡ መጣች፡፡ ከዳዊት ጋር መተኛትም ደጋገመች፡፡ (ምን እንደተባባሉ ማን ያውቃል!? ብቻ መሰራረቁን ቢደጋግሙ ግዜ እግዜሩም ምልክቱን በማህፀኗ አስቀመጠ፡፡)
አንድ ቀን ቤርሳቤህ እንዲህ አለች “...ጌታዬ አርግዣለሁ መሰለኝ! የወርሃዊ አበባ ምልክቴ ቀርቷል፤ ምን ተሻለኝ ይሆን? ባሌ ኦርዮን ከጦር ሜዳ ሲመጣስ ምን አወራለሁ?!››  
ዳዊት ጥቂት አሰበበትና እንዲህ አለ (መሰለኝ!) ‹‹ከጦር ሜዳ ቶሎ አስመጣዋለሁ! … ከዚያ አብረሽው መተኛት ትጀምሪያለሽ … እናም ከእርሱ ታረግዢያለሽ!››
የኤልያብ ልጅ ኬጢያዊው ኦርዮን ከጦር ሜዳ ተጠርቶ መጣ፡፡ ንጉሱን ካነጋገረ በኋላ ወደ ቤትህ ሒድ ተባለ፡፡ ሆኖም ከንጉሱ ደጅ ተኝቶ አደረ፡፡ ከሚስቱ ጋር ሊተኛ አልፈቀደም፡፡ አሃ! ምነው? ቢሉት ‹‹…ጓዶቼ በግንባር ላይ እየሞቱ እኔ ከሚስቴ ጋር አልተኛም!…›› … ብሎ ግግም አለ፡፡
በማግስቱ ዳዊት እስኪሰክር አጠጣውና ሒድ አለው፡፡ ኦርዮን ግን… ‹‹ በህይወትህና በህያው ነፍስህ እምላለሁ! አላደርገውም›› ብሎ ከዚያው አደረ፡፡ (ወይ እውነት? ወይ መታመን? ወይ ፈተና! አልን፡፡)
ገጽ - 2 (የመጨረሻው ገጽ…)
ዝመት!
ንጉሱ ያሰበው እንዳልተሳከለት አየ… “..በቃ ተመልሰህ ሂድ፡፡ የአገርህና የንጉስህ ክብር ተደፍሯልና ዝመት! ›› አለው፡፡ እናም ደብዳቤ ፅፎና በእጁ አስይዞ ላከው፡፡
ደብዳቤው እንዲህ የሚል ነበር፡- ‹‹ፅኑ ሰልፍ ባለበት በፊተኛው ስፍራ አቁሙት፣ ተመትቶም ይሞት ዘንድ ከኋላው ሽሹ!›› ኦሪዮን ከፊት ዘመተ፡፡ ከወዳጆቹ ጋርም በክብር ተሰዋ! የዳዊት ተንኮል ግን ፈጣሪውን በጣም አበሳጨው፡፡
አምላኩ ናታንን ላከበትና ዳዊትን እንዲህ አለው፡- ‹‹በእስራኤል ላይ አንግሼ ቀባሁህ፣ ከሳኦልም እጅ አዳንሁህ ፣ የጌታህንም ቤት ሰጠሁህ፣ የጌታህንም ሚስቶች በብብትህ ጣልሁልህ፣ የእስራኤልንና የይሁዳን ቤት ሰጠሁህ፣ ይህም አንሶ ቢሆን ኖሮ ከዚህ የበለጠ እጨምርልህ ነበር፡፡ አንተ ግን በፊቴ ክፋትን ሰራህ…››
ዳዊት ወደ ልቦናው ሲመለስ በሰራው እጅግ አፈረ፡፡ ውቅያኖስ ሙሉ ተሰጥቶት ሳለ፣ የሰው ባልዲ ውሃ ሰረቀ! እናም አዘነ:: ተጸጸተ፡፡ አልቅሶ ወደ ፈጣሪው ለመነ:: ለእርሱ የመጣው ሞት ከቤርሳቤህ የተገኘውን ፅንስ በመውሰድ ተፈጸመ፡፡ ቢሆንም ቤርሳቤህን ከማግባት መች ቀረ? ህይወቷ ከእርሱ ጋር ታስሯልና አገባት፡፡
ዳዊትም በሚቀጥለው ልጅ ተባረከ:: ከቤርሳቤህ ጥበበኛው ሰለሞን ተወለደ:: እናም ይህንን ታሪክ ስታውቅ ልብህ ‹ብታዝንም አታመንታ! … ተነስ … ታጠቅ … ዝመት!› ይልሃል፡፡ (አስታውስ፤ ዘሙት ግን አይልህም! ምክንያቱም መጨረሻህ አያምርም፡፡)
ሲያልቅ!
የጉብዝናና የጉልምስና ወራት ያልፋሉ … የድካምና የመዛል ግዜ መምጣቱ አይቀርም:: ዳዊት ሸመገለ፡፡ ቆነጃጅትን በማቀፍና ጠላቶቹን በመጣል ጠንካራ የነበሩ ክንዶቹ ዛሉ፡፡ ልብስም ደረቡለት አይሞቀውም፤ ወዳጆቹም እንዲህ አሉ ‹‹ድንግል እናምጣለት፤ ታገልግለው፣ በብብቱም ተኝታ ታሙቀው ዘንድ…››
እንደ አለንጋ የምትለመጠውንና እንደ እንቁ የምታበራውን ድንግል፣ አቢሳን አመጡለት፡፡ አገለገለችው፡፡ በፍፁምም ታዘዘችው፡፡ ሆኖም … አንዴም ቢሆን ጭኗን አልገለጠም ነበር፡፡ ከአቢሳም የተለየ ቁንጅና፣ ድንግልናና ውበት ከየት ይመጣ ነበር? ሁልጊዜም ነገሩ ሲያልቅ አያምር እንደሚባለው ሆኖ ነው’ንጂ፡፡
***
ፅሁፉን አንብቤ ስጨርስ ለደቂቃዎች ደንዝዤ ተቀመጥኩ፡፡ ጓደኛዬ ምን ሊለኝ እንደፈለገ ስለገባኝ፣ ምን ማድረግ እንዳለብኝ ወሰንኩ፡፡ እናም ‹ከአቢሳ አጠገብ አልደርስም!› ስል ማልኩ፡፡Read 601 times