Saturday, 07 March 2020 12:30

“ግብፆችን ወደ ጦርነት የሚመራቸው በቂ ምክንያት የላቸውም”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

 ግብፅ፣ ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን በጋራ የመሰረቱትን የናይል ትብብር መድረክ የምስራቅ ናይል ጽ/ቤት ይመራሉ፡፡ ‹‹የናይል ትብብር መድረክ›› ትብብርን የሚያጠናክሩ ወሰን ተሻጋሪ ፕሮጀክቶች የመለየትና የማዘጋጀት እንዲሁም ለአገራቱ የማቅረብ ስራ ይሰራል፡፡ መድረኩ ካዘጋጃቸው የትብብር ፕሮጀክቶችም መካከል የሱዳንና ኢትዮጵያ የሀይል አቅርቦት፣ የመስኖ ፕሮጀክቶች እንዲሁም ሶስቱ አገራት በጋራ ሊተገብሩት የነበረው የዘርፈ ብዙ የጋራ ፕሮጀክት ይጠቀሳሉ፡፡
የዚህ ፕሮጀክት አስተባባሪና የምሥራቅ አፍሪካ የውሃ ፖለቲካ ተንታኝ የሆኑት አቶ ፈቄ አህመድ፤ የአባይ ድርድር ከምን ተነስቶ እዚህ ደረሰ? ለምን አሜሪካ ጣልቃ ገባች? በቀጣይ መፍትሄው ምንድን ነው? በሚሉና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ እንደሚከተለው አነጋግሯቸዋል፡፡  


                 በዓባይ ግድብ ላይ እስከ ዛሬ ሲካሄዱ የነበሩ ውይይቶችና ድርድሮች ምን መልክ ነበራቸው?
ከግብፅ ጋር ያደረግነው ትልቁ ድርድር፤ በናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት፣ በዘጠኝ አገራት መካከል ከ1997 እ.ኤ.አ እስከ 2010 የተካሄደው ነው፡፡ ይህም ድርድር በዋናነት የውሃ ሀብት አጠቃቀም፣ ልማትና እንክብካቤ ጥበቃ ላይ ያተኮረ ነው:: ይህ ድርድር ሲካሄድ በአብዛኛው ብዙም ልምድ አልነበረንም፡፡ ግብፆች ይሄ የልብ ልብ ሰጥቷቸው ነበር እዚህ ነገር ውስጥ የገቡት፡፡ ሌሎች አገራት አቅም የላቸውም፤ እኛ በበላይነት ድርድሩን እንመራለን ብለው ተማምነው ነበር፡፡ ነገር ግን አንደኛ ኢትዮጵያ በወቅቱ የመደራደር አቅም ገንብታለች፤ የመደራደር አቅም መገንባት ብቻ ሳይሆን ሌላ ትልቅ አቅም ነበራት፤ እሱም የመልክአ ምድር አቀማመጡ ነው፡፡ የላይኛው ተፋሰስ አገር ነን፡፡ የላይኛው ተፋሰስ አገር መሆን ሁሌም የመደራደር አቅምን ከፍ ያደርጋል። ምክንያቱም ውሃው እሱ ጋ ስላለ፣ ውሃውን ለመጠቀም የሌሎችን በጎ ፈቃድ አይጠብቅም፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ የመልክአ ምድር አቀማመጧን እንደ መደራደሪያ አቅም ተጠቅማበታለች፡፡ ሌላኛው ኢትዮጵያ በወቅቱ ያደረገችው የላይኛው ተፋሰስ አገራትን አስተባብራ ጥምረት መፍጠር ነው:: ምክንያቱም የላይኛው የተፋሰሱ አገራት ውሃውን የመጠቀም ተመሳሳይ ፍላጎት አላቸው፡፡ የላይኛው የተፋሰሱ አገራትን አጋርነት በመፍጠር ድርድሩን በሁለት ጎራ የተከፈለ ማድረግ ተችሎ ነበር፡፡ በመጀመሪያ በሙሉ የላይኛው የተፋሰሱ አገራት ከግብፅ ጋር ነበሩ፤ በኋላ ግን በተሰራው ዴፖ ማሳያ ስራ አጋርነታቸው ወደ ኢትዮጵያ ሊሆን ችሏል፡፡ በዚህ ሂደት ድርድሩን በሁለት ጎራ ሆነው መደራደር ጀመሩ:: የላይኛውን ተፋሰስ ኢትዮጵያ ስትመራ፣ የታችኛውን ግብፅ እየመራች ድርድራቸውን ቀጠሉ፡፡ የላይኛው ተፋሰስ አገራት በወቅቱ 7 ነበሩ፤ የታችኛው ደግሞ (2) ግብፅና ሱዳን ነበሩ:: ድርድሩ በአብዛኛው የላይኛውን ተፋሰስ አገራት ብሄራዊ ጥቅም የሚያስጠብቅ፣ የታችኛውን ተፋሰስ አገራት የማይጎዳ ስምምነት ሆኖ ነበር የተጠናቀቀው። ነገር ግን መጨረሻ ላይ ግብፅ ከድርድሩ ጥላ ጠፋች፡፡ ሱዳንም ተከተለቻት:: ከድርድሩ ብቻ ሳይሆን ከናይል ተፋሰስ አገራት ትብብርም ጥለው ወጡ፡፡ ሱዳን በ2013 እ.ኤ.አ ወደ ትብብሩ ተመልሳለች፡፡ ግብፅ ግን እስካሁንም አልተመለሰችም፡፡
ግብፅ ጥላ መውጣቷን ተከትሎ ነው የህዳሴ ግድብ የተጀመረው ማለት ነው?
የኢትዮጵያን የህዳሴ ግድብ ከወለዱት በርካታ ምክንያቶች አንዱ፤ ይሄ ድርድርና ውጤቱ ነው፡፡ ለ13 አመታት ተደራደሩ፤ በመጨረሻ ግብፅ ጥላ ጠፋች፡፡ ስለዚህ እስከ መቼ ነው የሚጠበቀው በሚል ነው ወደ ግድቡ ሥራ የተገባው፡፡ ሌላው በትብብሩ ውስጥ ሶስቱ አገራት አብረው በጋራ ለመተግበር የተዘጋጁ ፕሮጀክቶች ነበሩ፡፡ በተለይ (Joint Multipurpose project) የዘርፈ ብዙ ጥምር ፕሮጀክት ነበር፡፡  
ፕሮጀክቱ ምን ነበር?
ኢትዮጵያ ውስጥ ለግዙፍ የግድብ ፕሮጀክት የሚሆኑ ጉዳዮችን በመለየትና በማጥናት በጋራ ተጠቃሚ የመሆን ፕሮጀክት ነበር፡፡ ከዚህ ፕሮጀክትም አንዱ የህዳሴ ግድብ ነበር፡፡ ግብፆች ከትብብሩ ሲወጡ ይሄን ፕሮጀክትም ትተው ወጡ፡፡ ስለዚህ ግብፆች ትተው ሲወጡ የኢትዮጵያ መንግሥት በራሱ ስራውን ሄደበት:: በነገራችን ላይ የዚህ ግድብ ቅድመ ጥናቱ በዝርዝር የተሰራው በጋራ ነው፡፡ ሦስቱ አገራት በጋራ ነው የሰሩት፡፡ ከዚያ ወደ ትግበራ ሊገባ ሲል ነው ሁለቱ ትተው የወጡት፡፡  የኢትዮጵያ መንግሥት ግድቡን አስጀመረ፡፡ በግድቡ ጅማሮ ላይ እነሱም ነበሩበት ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡
ግድቡ የግብፅን አብዮት ከለላ አድርጎ ነው የተጀመረው የሚባለውስ?
ይሄ ውሸት ነው፡፡ ከግብፅ አብዮት ቀድሞ ነው ለግድቡ ግንባታ ቅድመ ዝግጅት ሲካሄድ የነበረው፡፡ የግብፅ አብዮት ከመነሳቱ ከ7 ወር በፊት ነው የግድቡ ዝግጅት የተጀመረው፡፡ ይሄ ግድብ እንደተጀመረም ሲካሄድ የነበረው ድርድር ሳይሆን ውይይት ነበር፡፡ ድርድር ውስጥ አልተገባም ነበር፡፡ ግድቡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ለድርድርም አልቀረበም ነበር፡፡
ምን አይነት ውይይት ነበር ሲካሄድ የነበረው?
የቴክኒክ ውይይት ነው ሲካሄድ የነበረው:: ለምሳሌ በ2010 እ.ኤ.አ ግንባታ ላይ የግብፅ ዲፕሎማቲክ ቡድን አባላት ወደ ኢትየጵያ መጥተው ነበር፡፡ 26 አባላት ያሉት ነበር:: እነሱ በወቅቱ መረጃ የለንም፤ መረጃ ይሰጠን ነበር ያሉት፡፡ ጠ/ሚኒስትር መለስም “መረጃ ማግኘት ከፈለጋችሁ ወደ ናይል ትብብር ማዕቀፍ ተመለሱና፣ በዚያ በኩል ታገኛላችሁ” ነበር ያሏቸው፡፡ እነሱም ወደ ናይል ትብብር ለመመለስ አሁን አንችልም፤ ገና መንግሥት የለንም፤ በሦስት ወር ውስጥ ፓርላማ እናቋቁማለን፤ ያ ፓርላማ እስኪወሰን ድረስ አንደኛ ኢትዮጵያ ያኔ የትብብር ስምምነቱን የማፅደቅ ስራ ጀምራ ነበር፤ አሁን ግን ይዘግይልን፡፡  ሁለተኛ መረጃ የማግኘቱ ሥርዓት በናይል ትብብር በኩል ሳይሆን ሌላ መድረክ ይፈጠርልን የሚል ጥያቄ ጠየቁ፡፡ በዚያ አመት ግንቦት ላይ የወቅቱ የግብፅ የሽግግር መንግሥት ጠ/ሚኒስትር የነበሩት ሆሳም ሻራፊ መጥተው ነበር፡፡ እሳቸውም ተመሳሳይ ጥያቄ ነበር የጠየቁት፡፡ መስከረም 2011 ደግሞ ጠ/ሚ መለስ ግብፅን ለመጎብኘት ችለው ነበር:: እዚያም የተጠየቁት ተመሳሳይ ጥያቄ ነበር:: በወቅቱም ጠ/ሚኒስትሩ አዎንታዊ ምላሽ ነበር የሰጡት፡፡ የማፅደቁን ሂደት እንደውም እነሱ ከጠየቁት 3 ወር በላይ አዘግይታ በሁለት ዓመት አዘጋጀች።  መረጃ የማግኘቱም ሥርዓት፤ የኤክስፐርቶች ፓናል በማቋቋም በዚያ በኩል የሚፈልጉትን መረጃ እንዲያገኙ፣ ኢትዮጵያም ባለችበት የጥናት ሰነዶችን በጋራ እንዲመረምሩና አስተያየት እንዲያቀርቡ ተደረገ፡፡ ከአንድ ዓመት በኋላም በኤክስፐርቶች ፓናል የተዘጋጀው ሪፖርት ወጣ:: ሪፖርቱ ሲወጣ ሱዳንና ኢትዮጵያ ተቀበሉት:: ኢትዮጵያ እንደውም ለሷ የተሰጧትን ምክረ ሀሳቦች ተቀብላ፣ ከተሰጧት ሀሳቦችም አልፋ ሄዳ ነው ማሻሻያዎች ያደረገችው፡፡
ምንድን ናቸው እነዚህ ምክረ ሀሳቦች?
ምክረ ሀሳቦቹ ለምሳሌ አቃፊ ግድብ (ሳድል ዳም) የሚባለው በመጀመሪያ ኮር በሚባል መልክ ይሰራ ነበር የተባለው:: በቀረበው ምክረ ሀሳብ ግን አስፓልት ይሁን ተባለ፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ ከዚህም አልፋ ኮንክሪት ነው ያደረገችው:: ኮንክሪት ከአስፓልት በጣም የተሻለ ነው:: ምክንያቱም አስፓልት በሙቀት ሊቀልጥ ይችላል፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ ከምክረ ሀሳቡ በላይ ተራምዳ ነው ማሻሻያ ያደረገችው፡፡ ሌላው የዋናው ግድብ የአናቱ ስፋት ነበር:: የመጀመሪያ ዲዛይን ላይ 4 ሜትር ነበር፡፡ ኢንተርናሽናል ፓናሉ 6 ሜትር ቢሆን ብሎ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ወደ 8 ሜትር ከፍ አድርጋ ነው ያሻሻለችው፡፡ መስከረም 2014  ላይ ደግሞ የግብፅና የሱዳን ሚኒስትሮች ግድቡን ጎብኝተውት ነበር። በወቅቱ የነበሩት የግብፅ የውሃ ሚኒስትር ለማመን ነበር የተቸገሩት:: ለጋዜጠኞች ቃል ሲሰጡም፤ ‹‹ይሄ ግድብ እየተካሄደበት ያለው የቴክኒክ ብቃት በጣም አስደምሞኛል…›› ነበር ያሉት፡፡ ወዲያው ግን የህዳሴውን ግድብ እያደነቁ መሆኑ ሲገባቸው ‹‹ይሄ አሁን የተናገርኩት ሀሳብ፣ እንደ አንድ የውሃ መሀንዲስ ነው እንጂ እንደ ግብፅ ሚኒስትር አይደለም›› አሉ፡፡ በወቅቱ እንግዲህ በግድቡ የግንባታ ጥራት እነሱ ራሳቸው ተደንቀውበት ነበር፡፡ እነዚህ በሙሉ ግን ድርድር ሳይሆኑ ውይይቶች ነበሩ:: በኋላ ላይ ነው የምርምር ቡድን የሚባል ከአስታራቂ አገራት አምስት ተሳታፊዎች ያሉበት ቡድን የተቋቋመው፡፡ ይሄ ቡድንም ሲያደርግ የነበረው ውይይት እንጂ ድርድር አልነበረም:: ድርድር የተጀመረው አሁን አሜሪካ ከተሄደ በኋላ ነው፡፡
ግብፅ በአባይ ጉዳይ ከኢትዮጵያ በተሻለ ጠንካራ የዲፕሎማሲ ስራ እየሰራች ነው፤ በዚህም ውጤታማ እየሆነች ነው የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ እርስዎ ጉዳዩን በጥልቀት እንደሚያውቅ ባለሙያ ምን ይላሉ?
ግብፅም ኢትዮጵያም በየራሳቸው ዲፕሎማሲያዊ ስራዎችን ይሰራሉ፡፡ ዋናው ነገር ዲፕሎማሲ መስራቱ ሳይሆን አብዛኛው ወገን የሚባሉት በአንድ ጉዳይ አቋም ሲይዙ የራሳቸው ፍላጎት ይኖራቸዋል። የመብለጥ ያለመብለጥ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የእነዚያ ሶስተኛ አካላት ፍላጎት፣ ከኛ ፍላጎት ጋር የተጣጣመ ነው ወይ የሚለው መታየት ያለበት ይመስለኛል። በግብፅ በኩል እንደምናስተውለው፤ ሁልጊዜ ሰለባ ነኝ የሚል ነው የምታቀርበው፡፡ አንድ አካል ደግሞ ሰለባ ነኝ ካለ ትኩረት ማግኘቱ አይቀርም፡፡ ግን ከዚህም ባሻገር አሜሪካም ሆነ የአውሮፓ አገራት ግብፅ ላይ ፍላጎት አላቸው፡፡ አሜሪካ በተለይ የግብፅን ፍላጎት ለማስጠበቅ የሚያስገድዷት ነገሮች አሉ። ለምሳሌ የካምፕ ዴቪድ ስምምነት በ1979 እ.ኤ.አ ሲፈረም፣ በግብፅና በአሜሪካ መካከል የጎንዮሽ ስምምነት ነበር፡፡ በዚያ ስምምነት ውስጥ አሜሪካ በናይል ላይ ግብፅ ያላትን ፍላጎት ለመጠበቅ ቃል የገባችበት ሁኔታ አለ፡፡ ይሄ የስምምነት ሰነድ በጣም በሚስጥር የሚጠበቅ ነው:: ማንም አያየውም፤ ግን በተለያየ መልኩ ይሄ መረጃ ወጥቷል። ስለዚህ አሜሪካ በዓባይ ጉዳይ ገለልተኛ ነች ብሎ ለመናገር በጣም ነው የሚያስቸግረው፡፡ ሌላው የመካከለኛው ምስራቅ ጉዳይ አለ፡። ግብፆች ደግሞ የመካከለኛው ምስራቅ ትልቋ አገር ነን ብለው ነው የሚወስዱት፡፡ አሜሪካ ደግሞ እዚህ ውስጥ ፍላጎት አላት፡፡ የነዳጅ ጉዳይ፤ የእስራኤል ጉዳይ አለ፤ ብዙ ኢንቨስትመንት አላቸው፡፡ ስለዚህ ግብፅን የማባበል ስራ ሲሰሩ ይታያሉ፡፡ በአብዛኛው  ምዕራባውያን ለግብፅ ሲያደሉ ነው የሚታየው፡፡ አለም ባንክም ለግብፅ ነው የሚያደላው፡፡ ነገር ግን እነዚህ አካላት ኢትዮጵያን አይፈልጉም ማለት አይደለም:: ሆኖም ሁለቱን አገራት የሚያዩበት መንገድ መጠኑ ይለያያል:: ግብፆች በዚያ ላይ ቀን ከሌት ነው ዲፕሎማሲ የሚሰሩት፡፡ የሀሰት መረጃ ሁሉ ሆን ብለው ይለቃሉ፡፡ እነሱ በሚሄዱበት ደረጃ እኛ እየሄድን ያለን አይመስኝም፡፡
አሁን ድርድር ውስጥ እንዴት ልንገባ ቻልን?
በመጀመሪያ ደረጃ ወንዙ ድንበር ተሻጋሪ መሆኑ በራሱ ድርድርን ይጋብዛል፡፡
መደራደርን ግዴታ የሚያደርጉ አለማቀፍ የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች የስምምነት ማዕቀፍ አለ?
ኢትዮጵያ አልፈረመችም እንጂ በ1997 እ.ኤ.አ የተባበሩት መንግሥታት ያወጣው የባህር ላይ መመላለሻን የማያካትት የውሃ ስምምነት አለ፡፡ ይሄን ስላልፈረመች ኢትዮጵያ ላይ አስገዳጅ አይሆንም፡፡ ነገር ግን እንዲሁ የዘልማድ አካሄድ አለ፡፡ ሁሉም አገራት ድንበር ተሻጋሪ ለሆኑ ወንዞች መደራደርን ነው መግባቢያ የሚያደርጉት፡፡ ይሄ ማለት ግን አስገዳጅ ውይም የሚያስከስስ ሕግ አለ ማለት አይደለም፡፡ ለሰላም ሲባል በበጎ ፈቃድ የሚደረግ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የፈረመችው የናይል ትብብር ማዕቀፍ ነው:: ይሄን ማዕቀፍ 4 አገራት አፅደቀውታል:: በቀጣይ ሁለት ተጨማሪ አገራት ካፀደቁት ስምምነቱ አለማቀፍ ይሆናል ማለት ነው:: ነገር ግን ሁልጊዜም መደራደር ተመራጭ ነው መሆን ያለበት፡፡
ለአሜሪካ ጣልቃ መግባት በር የከፈተው በ2015 የተፈረመው የመርሆዎች ስምምነት ነው የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ ስምምነቱ ምን ነበር?
ይሄ ስምምነት በሱዳን ካርቱም ነው የተፈረመው፡፡ በዚህ ስምምነት አንቀፅ 10 ላይ፤ በስምምነቱ አተረጓጎም ላይ ልዩነት ከተፈጠረ በመመካከር በመወያየት ሊፈቱት ይሞክራሉ፤ በዚያ መልኩ ሊፈቱት ካልቻሉ ግን የሶስተኛ አካላትን ሽምግልና ወይም የሶስቱን አገራት ርዕሳነ ብሄራት እገዛ ሊጠይቁ ይችላሉ ነው የሚለው:: ይህ ስምምነት በአስገዳጅ ሁኔታ የታሰረ አይደለም፡፡ ስለዚህ አሸማጋይ አንፈልግም ማለት ይቻላል፡፡ በነገራችን ላይ አሁን ተግባራዊ እየሆነ ያለው ይሄ አንቀፅ አይደለም፡፡
የአሁኑ ታዲያ ምንድን ነው? አሜሪካንን ወደ ሶስቱ አገራት ጉዳይ ያመጣት ምንድን ነው?
አሁን የተከሰተው ሁለት ነገር ነው:: አንደኛው የአሜሪካ መንግሥት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ህዳር 2019 ዋሽንግተን እንዲገኙ ለሦስቱ አገራት ነው ግብዣ የቀረበው፡፡ በዚሁ መካከል ደግሞ ራሺያ  ሶቺ ላይ የራሺያና የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች ፎረም ስብሰባ ነበር፡፡ እዚያ ላይ የሦስቱ አገራት መሪዎች ተገናኝተው ውይይቱ ይቀጥል የሚል ነገር ያነሳሉ፡፡ በዚህ ግብዣ መሰረት አሜሪካ መሄዱም አስፈላጊ ነበር:: እዚያ ሄዶ ውይይት የሚደረግበት ቦታ መገኘት ጥሩ ነው:: አላስፈላጊ መረጃዎች ካሉ ለማስተካከል ዕድል ይሰጣል፡፡ የኛ ልዑካንም በወቅቱ ለፕሬዚዳንት ትራምፕ፣ በኢትዮጵያ በኩል ያለውን እውነት አሳውቀዋል:: እሳቸው ራሱ የተሳሳተ መረጃ ነበራቸው፤ ያንን ማስተካከል ተችሏል፡፡ ከዚያ በፊት ፕሬዚዳንት አልሲሲ በኒውዮርክ በተካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ስብሰባ ወቅት ትራምፕን አሸማግሉን ብለው ጠይቀዋቸዋል፡፡ እንደገና በህዳር 2019 የሦስቱ አገራት ውይይት ከመካሄዱ በፊት ፕሬዝዳንት አልሲሲ ለትራምፕ ስልክ ደውለዋል፡፡ አግዙን ብለው ጠይቀዋል:: በሌላ በኩል ደግሞ የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ስብሰባው ከመካሄዱ ሁለት ቀን ቀደም ብለው አሜሪካ ደርሰው ወሳኝ ያሏቸውን ሰዎች፣ የፕሬዚዳንቱ ልጅ ባለቤት ዴቪድ ኩሽራርን ጨምሮ ሲያናግሩ ነበር:: የግምጃ ቤት ሃላፊውን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩንና የተለያዩ ሰዎችን ሲያናግሩ ነበር፡፡ ከዚያ ወደ ስብሰባው ተገባ፡፡ አሜሪካና የአለም ባንክም ታዛቢ ነን ብለው ገቡ፡፡ በምን ማዕቀፍ እንደገቡ እኔ አሁን መረጃ የለኝም፡፡
መግባታቸው ትክክል ነው ግን?
ይሄን በሁለት መልኩ ማየት ይቻላል፡፡ እንደ አንድ ባለሙያ፤ የተባለውን ትብብር ስናየው፤ መግባት የለባቸውም ብሎ መውሰድ ይቻላል:: ምክንያቱም ሶስቱ አገራት ግልጽነትና ቀናነት ካለ መፍታት የሚችሉት ጉዳይ ነው፡፡ ሶስቱም አገራት ፍላጎትና ስጋታቸውን እርስ በእርስ በሚገባ ይተዋወቃሉ፡፡ ሶስተኛ አካል ሲመጣ ግን ሁልጊዜ የራሱን ፍላጎት ጭምር ይዞ ነው የሚመጣው፡፡ እኛ ሶስታችን ግን እጣ ፈንታችን አስተሳስሮናል፡፡ ሦስተኛው አካል ግን ይሄን እጣ ፈንታችንን አይረዳም:: የራሱን ፍላጎት ነው ይዞ የሚመጣው፡፡ ስለዚህ ባይገቡ ይመረጥ ነበር:: ነገር ግን የኛ መንግሥት አሜሪካንን የአለም ባንክን በታዛቢነት የተስማማበት የራሱ አሳማኝ ምክንያቶች ሊኖሩት ይችላሉ፡፡ እኔ አሁንም በታዛቢነቱ ላይ ብዙም ችግር የለብኝም፡፡ ነገር ግን ታዛቢ ብለው ከገቡ በኋላ፣ ከታዛቢነት ወደ አደራዳሪነት፣ መጨረሻ ላይ እንደውም የድርድሩ አካል ሆነው ራሳቸው ስምምነት ማርቀቅ ድረስ ሄደዋል። ይሄ አካሄድ ግን መፈቀድ አልነበረበትም ባይ ነኝ፡፡ ከሁለት አመት በፊት የአለም ባንክ በአሸማጋይነት እንዲገባ ግብፅ ጠይቃ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ግን አልቀበልም ብሎ ውድቅ አድርጎታል። አሁንም አሜሪካ እንድትገባ የጠየቀችው ግብፅ ነች፡፡ ስለዚህ ሁለቱም ላይ ፍላጎት ያላት ግብፅ ነች:: ስለዚህ የኛ መንግሥት በሩን ክፍት አድርጓል ማለት ነው፡፡ በሌላ በኩል ግን ታዛቢ ሆነው ሲገቡ፣ ታዛቢ የሆነው አካል ድርድሩ ላይ ያለውን ተሳትፎ የሚወስን መመሪያ መዘጋጀት ነበረበት:: በሕግ መስማማትና መፈራረም ይገባቸው ነበር፡፡ ወደ ፊርማ ሲመጣ ግን እርግጠኛ ነኝ ግብፅ እኛ ብላ አትፈርምም ነበር፡፡ ይህ ሲሆን ደግሞ ታዛቢ የተባሉትን አንፈልግም ማለት ወይም ስብሰባውን መተው ወይ መቀጠል ነው አማራጩ፡፡ መቀጠሉ የተሻለ ነው፡፡ ምናልባት ማድረግ የሚቻለው እነሱ ከታዛቢነት ወጥተው ወደ ማሸማገል ሲመጡ ማስቆም ይቻል የነበረ ይመስለኛል። ይሄ የእናንተ ሚና አይደለም ብሎ ማስቆም ይቻል ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ በጉልበት ሊመጡ ይችላሉ፤ ያኔ ስብሰባውን ማቋረጥ ይቻል ነበር፡፡
አሜሪካና ግብፅ አጋርነታቸው ምን ያህል ነው?
በሚስጥር የሚጠበቀው የካምፕ ዴቪድ ስምምነት እንዳለ ሆኖ፣ አሜሪካ ግብፅ በአባይ ላይ ያላትን መብት ዋስትና ከመስጠት አልፋ እንድትከላከል ራሱ የጦር መሳሪያ ድጋፍ እየሰጠቻት ነው:: በአመት የ1.3 ቢሊዮን ዶላር ያህል የጦር መሳሪያ ነው የምትሰጣት፡፡ እነዚህ ሲታዩ ሚዛኑ የደፋ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ መጠን ውግንና ያሳያሉ የሚል ግምት አልነበረኝም፡፡ በማይጠበቅ ሁኔታ ነው በሉአላዊነት ጉዳይ ጣልቃ የገቡት። አሜሪካንን የሚያክል ትልቅ አገር እንዲህ ያለ መግለጫ ይሰጣል ብሎ ማንም አይጠብቅም፡። ነገሩ ያልተጠበቀ ነው፡፡
በሦስቱ አገራት ጉዳይ ላይ የሱዳን ፍላጎትና ተፅዕኖ ፈጣሪነት ምን ድረስ ነው?
ሱዳን ግድቡን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ስትደግፍ ነው የቆየችው፡፡ ይሄን ደግሞ የሚያደርጉት ከራሳቸው ጥቅም አኳያ ነው:: ኢትዮጵያን ለመጥቀም ብለው ሳይሆን የራሳቸውን ብሄራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ሲሉ ነው የግድቡን ግንባታ የሚደግፉት፡፡ ከግድቡ ሱዳኖች ከኢትዮጵያ የበለጠ ሊጠቀሙበት ይችላሉ፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠር ሄክታር መሬት በግድቡ ሊያለሙበት ይችላሉ። አሁን ትንሽ የተለወጠ ነገር የሚመስለው ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ ‹‹ግብፅን የሚጎዳ ነገር አናደርግም›› ማለታቸው ነው፡፡ ግን ያን ያህል ገፍተው የሄዱበት ጉዳይ አይደለም:: ግብፆች በፊት ከነበራቸው ቁርጥ አቋም ትንሽ ላላ ያሉበት ነገር አለ፡፡ ዋናው ነገር ግን ሱዳን ከግድቡ ተጠቃሚ ነች፤ የግድቡ ተጠቃሚም የምትሆነው ደግሞ ከኢትዮጵያ ጋር ስትተባበር ነው፡፡
ከሰሞኑ አሜሪካ ያቀረበችውን ሀሳብ ተከትሎ ምን ሊፈጠር ይችላል?
ምንም አይፈጠርም፡፡ የድንበር ተሻጋሪ የውሃ አጠቃቀምን በተመለከተ ሁለት አስተሳሰቦች አሉ፡፡ አንደኛው አስተሳሰብ የውሃ አጠቃቀም ላይ አገራቶች ካልተስማሙ ወደ ጦርነት ያመራሉ፤ የወደፊቱ የአለም ጦርነት በውሃ ላይ ነው የሚል ነገር አለ፡፡ በአብዛኛውም የግብፅ መሪዎች የሚያቀነቅኑት አስተሳሰብ ነው:: ሌላው ግን በወሰን ተሻጋሪ ውሃ ላይ ትብብርና ግጭት አብሮ አለ የሚል አመለካከት አለ፡፡ ይሄ ማለት በውሃ አጠቃቀም ላይ ያለመስማማት ይኖራል፤ ፍጥጫ ይኖራል፤ ወደ ግጭት ሊያመሩም ይችላሉ፤ ከዚያ ግን ወደ ትብብር ነው የሚመለሱት፡፡ ይሄኛው ነው ትክክለኛ አመለካከት፡፡ ስለዚህ ግብፆች ወደ ጦርነት የሚያመሩበት ምክንያት የለም:: ወደ ግጭት የሚወስዳቸው በቂ ምክንያት የላቸውም፡፡ ያለምክንያት ደግሞ ወደ ግጭት ማምራታቸው ከትርፉ ኪሳራው እንደሚያመዝንባቸው ያውቁታል። ወደ ግጭት ለመግባት ምክንያት ያስፈልጋል፡፡
ኢትዮጵያ ወደ ውሃ መሙላቱ የምትሄድ ከሆነ ለግጭት ምክንያት አይሆንም?
ኢትዮጵያ ውሃውን ስትይዝ ግብፅ ላይ የሚደርስ ጉልህ ጉዳት የለም፡፡ ጥናቶች ያንን ነው የሚያሳዩት፡፡ እንደ ተፅዕኖ የሚነሳው፣ አስዋን ግድብ ላይ ውሃው ዝቅ ሊል ስለሚችል የሚመነጨው ሀይል መጠን ዝቅ ይላል የሚል ነው፡። በዚያ የተነሳ የሚቀንሰው ሀይል ካጠቃላይ ምርቱ  ከ7 እስከ 10 በመቶ ብቻ ነው:: በአሁኑ ጊዜ አስዋን ግድብ የሚያመነጨው 2100 ሜጋ ዋት ነው፤ 10 በመቶ ቀነሰ ቢባል እንኳ 210 ሜጋ ዋት ነው የሚቀንስባት፡፡ ግብፅ ደግሞ በአሁኑ ወቅት 40 ሺህ ሜጋ ዋት ነው የምታመነጨው:: ስለዚህ የምታጣው የሀይል መጠን 0.07 በመቶ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ ምንም አትጎዳም ማለት ነው፡፡ ግድቡ በተለቀቀ ቁጥር ደግሞ የቀነሰው አስዋን ይሞላላቸዋል። ሌላው ወደ ጦርነት የሚያመሩበት ምክንያት ከትርፉ ኪሳራው ያመዝንባቸዋል፡፡
ስለዚህ ወደ ግጭት አትገባም ማለት ይቻላል?
አዎ፤ ምክንያት የላትም፤ ምክንያቷ ግጭቱ ከሚያመጣባት ጣጣ ጋር ለንፅፅርም የሚቀርብ አይደለም፡፡ በሌላ በኩል ውሃው ከላይ ወደ ታች መፍሰሱ አይቆምም። ነገር ግን ወደ ግጭት የምትገባ ከሆነ አንድ ነገር ላይመለስ ይለወጣል:: አሁን ኢትዮጵያ ለታችኛው ተፋሰስ ያላት ሀዘኔታ፣ ክብርና የሞራል ግዴታ ይለወጣል፤ ያውም ላይመለስ፡፡ ስለዚህ ግጭት ውስጥ ቢገቡ ራሳቸው በሰሩት ስራ ተመልሰው የእድሜ ልክ ሰለባ ነው የሚሆኑት፡፡ በዚህ የተነሳ ወደ ግጭት ይሄዳሉ የሚል እምነት የለኝም፡፡
ድርድሩ መስመሩን እንዲስት መነሻ የሆነው ስህተት ምንድን ነው?
እዚህ ጋ ወይም እዚያ ጋ ስህተት ተሰርቷል የሚለው ብዙም አይጠቅምም:: ነገሩ ውስብስብ ነው፡፡ የተለያዩ ጫናዎች አሉ፡፡ ስለዚህ ዋናው እንዴት ከዚህ እንውጣ የሚለውን ማሰብ ላይ ትኩረት ማድረግ ነው፡፡
በእርስዎ በኩል መላው ምንድን ነው ይላሉ?
አንደኛው፤ በግድቡ ዙሪያ ላይ የኢትዮጵያን ሕዝብ በአንድነት ማሰለፍ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ግድቡ ሲጀመር እንደነበረው አሁንም ለግድቡ ደጀን መሆኑን ማሳየት አለበት፡፡ በገንዘቡም በሞራሉም በፀሎቱም ከግድቡ ጎን ነበር፡፡ ያንን አጠናክሮ መመለስ ያስፈልጋል፡፡ ጥቃቅን ስህተቶች ተሰርተው ነው የህዝቡ ድጋፍ የቀነሰው፡፡ የግድቡ አስተዳደር ላይ የተሰሩ ስህተቶች አሉ፤ ያንን ለማሳወቅ ሲባል በተሰራ ስህተት ለግድቡ የነበረ ድጋፍ ቀንሷል፡፡ ስለዚህ ይሄን የሕዝብ እምነት መመለስ ያስፈልጋል:: ይሄን መመለስ ከተቻለ የውጭ ጫና በጣም ነው የሚቀንሰው። ለተደራዳሪዎቻችንም ትልቅ አቅምና ግብዓት ነው የሚሆነው፡፡ ሌላው ትልቅ የአለማቀፍ ዲፕሎማሲ ስራ መሰራት አለበት:: ምክንያቱም የተሰራው ስራ ኢ ፍትሃዊ ነው፡፡ በአንድ አገር ሉአላዊነትና መብት ውስጥ ገብቶ እንደዚህ አይነት መግለጫ ማውጣት ተገቢ አይደለም፡፡ ይሄን ኢ-ፍትሃዊ አካሄድ ለአለም ገልፆ፤ ከኢትዮጵያ ጎን እንዲቆም ማድረግ ይቻላል፡፡ ይሄን ለማድረግ በመጀመሪያ በናይል ተፋሰስ ላይ መሠራት አለበት፡፡ ቀጥሎ የአፍሪካ ህብረት፣ አፍሪካዊ ድርጅቶች ላይ መሠራት አለበት፡፡ ምዕራባዊያንና እስያ አገራትም ላይ መሰራት አለበት፡፡ በሶስተኛ ደረጃ ደግሞ የውስጥ ጉዳያችንን ማስተካከል ነው፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ድርድሩ መቀጠል አለበት፡፡
በምን መልኩ?
ለዚህ ሁለት ትይዩ ሥራዎች መሰራት አለባቸው። አንደኛው፤ የራሳችንን የድርድር ሂደት በደንብ አጠናክረን መቀጠል አለብን። ጎን ለጎን ደግሞ ግድቡ ቶሎ አልቆ ውሃ የሚይዝበትን ሁኔታ ማዘጋጀት መቻል አለብን፡፡ ሀገራዊ አቋሞቻችን ግልፅ መሆን መቻል አለባቸው:: ሶስተኛ አካል አንዴ ገብቷል፤ ለመቀጠልም ፍላጎት አላቸው:: እሱንም በታዛቢነት የሚቀጥሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነው፡፡ በሌላ ጎን፤ የእነሱን ተፅዕኖ መቀነስ የሚችሉ አፍሪካዊ ድርጅቶችን የታዛቢነቱ አካል ማድረግ ይቻላል:: ለምሳሌ የናይል ትብብር መድረክንም የአፍሪካ ህብረትንም ወደ ታዛቢነቱ መሳብ ይቻላል፡፡ በዚህ መልኩ የእነዚህን ጫና ማላላት ይቻላል:: ሌሎች ሀያላን ይግቡበት ከተባለም እነ ቻይና ሩሲያ አሉ፤ እነሱንም ማምጣት ይቻላል፡፡ እነዚህን በማድረግ ራሳችን ድርድሩን መምራት የምንችልበትን ብቃት ልንጎናፀፍ ይገባል:: ለሕዝቡ ሁሉንም ነገር በማሳወቅ ከጎን ማሰለፍ ይቻላል፡፡ ይሄ ተደርጎ ካልተስማሙ ግን ግድቡ ውሃ እንዲይዝ ማድረግ ነው፡፡ ግድቡ ውሃ መያዙ ጉዳት እንደማያመጣ በተግባር ማሳየት ይቻላል፡፡                                   


Read 14151 times