Saturday, 07 March 2020 12:29

ኢትዮጵያና ግብፅ 5 ጉዳዮች ላይ ተደራድረው መግባባት ይጠበቅባቸዋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(14 votes)

     -  ኢትዮጵያና ሱዳን የአረብ ሊግን ውሣኔ ተቃውመዋል
                          
በህዳሴው ግድብ ጉዳይ ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ በ5 ወሳኝ ጉዳዮች ላይ ተደራድረው መግባባት እንደሚጠበቅባቸው የተገለፀ ሲሆን ችግሩን ለመፍታት ከድርድር ውጪ ሌላ አማራጭ እንደሌለ የኢትዮጵያ መንግስት አስታውቋል፡፡
እ.ኤ.አ በ2015 በተፈረመው የመርሆ መግለጫ ስምምነት መሠረት፤ ከሰሞኑ አሜሪካና የአለም ባንክ ጣልቃ የገቡበት የድርድር ሂደት መጀመሩን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የህግ አማካሪ አምባሳደር ረታ አለሙ አስረድተዋል፡፡ በመርሆ ስምምነቱ አንቀፅ 5 መሠረት፤" የግድቡ የውሃ ሙሌትን፣ የግድቡን አሠራር ሂደት ወይም የውሃ አለቃቀቅ በሚመለከት ከሁለቱ ሀገራት ጋር ስምምነት ላይ እንደምትደርስ ተደንግጓል” ያሉት አምባሳደር ረታ፤ በዚህ መሠረት ወደ ድርድር መገባቱን አውስተዋል፡፡
የተጀመረው ድርድርም የህዳሴውን ግድብ አሞላልና አለቃቀቅ የሚመለከት መሆኑን፣ በዚህም 5 ስምምነት ላይ ሊደረስባቸው የሚገቡ ጉዳዮች ተለይተው ወደ ድርድር መገባቱን አስረድተዋል - አምባሳደሩ፡፡ እልባት ያላገኙትና በድርድር ሂደት ላይ የሚገኙት አምስቱ ጉዳዮችም የስምምነቱ የተፈፃሚነት ወሰን፣ የአፈፃፀምና የክትትል ሥርዓቱ እንዲሁም የአሞላልና የውሃ አለቃቀቅ ስርአትን የሚመለከቱ ድንጋጌዎች፣ የመረጃ ልውውጥ ስርአት፣ ክርክር ቢነሳ መፍትሔ የሚሰጥበት አሠራር እንዲሁም አምስተኛው የማጠቃለያ ድንጋጌዎች ናቸው ተብሏል፡፡
የተፈፃሚነት ወሰንን በተመለከተ በኢትዮጵያ በኩል የቀረበው የድርድር ሃሳብም፡- አንደኛ ድርድሩ በህዳሴው ግድብ ላይ ብቻ የታጠረ እንዲሆን፣ ሰነዱ የውሃ ክፍፍልን ወይም ድርሻን የማይመለከት መሆኑን እንዲሁም የቀድሞ የቅኝ ግዛት ስምምነቶችን የማይመለከት መሆኑ በግልጽ እንዲቀመጥ በድርድር ሃሳብነት መቅረቡን አምባሳደሩ አስረድተዋል፡፡
በውሃ አለቃቀቅና ሙሌት ጉዳይ እንደ ሁኔታው ተለዋዋጭ ሊሆን ስለሚችል በሰነዱ ላይ መጠንን የሚገልፁ ቁጥሮች እንዳይቀመጡ በመጠየቅ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን ሊያስጠብቅ የሚችል ሃሳብ ማቅረቧንና ጉዳዩም ገና በድርድር ሂደት ላይ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
የመረጃ ልውውጥን በተመለከተም ኢትዮጵያ የሰጥቶ መቀበል መርህን የመጠቀም ፍለጐት እንዳላት አቋሟን ማሳወቋን፣ ይህም ጉዳይ ገና በሶስቱ ሀገራት መግባባት ያልተደረሰበት መሆኑ ተመልክቷል፡፡
በሶስቱ ሀገሮች መካከል ክርክር ቢነሳ የሚፈታበትን መንገድ በተመለከተ ኢትዮጵያ የዲፕሎማሲና ድርድር መንገድን መከተል የሚል ማቅረቧን በግብፅ በኩል ደግሞ የሽምግልና ስርአትና የግድ ውሣኔ የሚሰጥበት አሠራር እንዲኖር ሃሳብ መቅረቡንና ገና በድርድር ሂደት ላይ ያለ ጉዳይ መሆኑም ተገልጿል፡፡
በድርድር ላይ ያለው መመሪያዎችንና ደንቦችን የተመለከተው የስምምነት ሰነድ ከ10 ዓመት በላይ ሊያገለግል የማይችል መሆኑና በሂደት የሚከለስበት አማራጭ እንዲኖር ኢትዮጵያ ተጨማሪ ሃሳብ ማቅረቧንም አምባሳደሩ አስረድተዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ገዱ አንዳርጋቸው በበኩላቸው፤ በቀጣይም በግድቡ ጉዳይ መግባባት ላይ ለመድረስ ብቸኛው አማራጭ ድርድር ብቻ መሆኑን ነገር ግን የሚካሄደው ድርድር የኢትዮጵያን ጥቅም እስካስከበረ ድረስ ብቻ ኢትዮጵያ ተሳትፎዋን እንደምትቀጥል አስታውቀዋል፡፡
በዚሁ ጉዳይ የተለያዩ ምሁራን የራሳቸውን ምልከታና ምክረ ሃሳብ እያቀረቡ ሲሆን የኢንሼቲቭ አፍሪካ መስራቹ አቶ ክቡር ገና በፌስ ቡክ ገፃቸው ባቀረቡት ምክረ ሃሳብ፤ ኢትዮጵያ በድርድሩ ውስጥ ለመቆየት የተቻላትን ጥረት ማድረግ እንዳለባትና ጉዳዩ የሶስቱንም ሀገር ጥቅም ባስከበረ መልኩ በመግባባት መቋጨት የሚችልበትን መንገድ መፈለግ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡  
በድርድሩ መቆየት የመጀመሪያው አማራጭ ሊሆን ይገባል የሚሉት ሌላው የአባይ ጉዳይ ተንታኙ አቶ ፈቄ አህመድ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ሌሎች ተጨማሪ አሸማጋዮችን ወደ ድርድር ማዕቀፉ በመሳብ የአሜሪካንና የአለም ባንክን ጫና መገደብ ይኖርባታል ሲሉ ምክረ ሃሳብ ያቀርባሉ፡፡ በተጨማሪም ኢትዮጵያውያንን በሙሉ ከግድቡ ጐን በማሳለፍም፣ ለዲፕሎማሲያዊ ጥረቱ እንደ አጋዥ መሣሪያ መጠቀም ያስፈልጋል፣ መንግስት በዚህ በኩል ጠንካራ የህዝብ ንቅናቄ መፈጠር አለበት ይላሉ አቶ ፈቄ፡፡
የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ሙሼ ሰሙም ህዝብን ለአንድ አላማ በማሰለፍ ጉዳይ ይስማማሉ፡፡ “ለሠላምና ለጋራ ጥቅም የሚደራደር ማንነት እንጂ ድፍረት የተሞላበትና ሉአላዊነታችንን የሚፃረር ትዕዛዝ ለመቀበል ዝግጁ የሆነ ኢትዮጵያዊነት እንደሌለብን በጋራ በመቆም ማስመስከር አለብን›› የሚሉት አቶ ሙሼ፤ኢትዮጵያም ግድቡን አጠናቃ ውሃ ከመሙላት የሚያግዳት ሀይል እንደሌለ ማሳየት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
አንዳንድ የአሜሪካ ባለሥልጣናትም ከወዲሁ የአሜሪካ ግምጃ ቤት ጣልቃ ገብነትንና ተፅዕኖን መቃወም ጀምረዋል፡፡ የአሜሪካ ኮንግረስ አባሉ ስቴቪን ሆርስፎርድ እንዲሁም በኢትዮጵያና በቡርኪናፋሶ የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩት ዴቪድ ሺን፤ የአሜሪካ መንግሥት በድርድሩ ለግብፅ እያደላ ነው ሲሉ በግልፅ ወቅሰዋል፡፡ አሜሪካ ሶስቱን አገራት ለማደራደር ከፈለገች የገለልተኝነት መርህን እንድትከተል፤ ይህን ካደረገች ኢትዮጵያ ወደ ድርድሩ ለመመለስ እንደማትቸገር ኮንግረስማን ሆርስፎርድ ገልጸዋል፡፡
በተመሳሳይ አምባሳደር ሼንም አገራቸው በኢትዮጵያ ላይ የምታሳርፈው ጫና ሊታረም ይገባል ብለዋል፡፡
ግብፅ በበኩሏ በአባይ ወንዝ ላይ ያላትን ጥቅም ለማስከበር ማንኛውንም አማራጭ እንደምትጠቀም፣ ለዚህም ከጎኗ በርካታ ደጋፊ አገራት እንዳሉ በመግለጽ፣ ኢትዮጵያ በአሜሪካ የቀረበውን የስምምነት ሰነድ እንድትፈርም አስጠንቅቃለች፡፡ አያይዞም የአገሪቱ መንግሥት የአረብ ሊግ በአባይ ጉዳይ ከግብፅ አቋም ጎን እንዲሰለፍ ከትናንት በስቲያ ጥሪ ያቀረበች ሲሆን የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚ ሹክሮ ኢትዮጵያ ስምምነቱን እንድትፈርም የአረብ ሊግ ተፅዕኖ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡
ኢትዮጵያ በ2015 የተፈረመውን የመርሆዎች መግለጫ ስምምነትን በመጣስ የግድቡን ስራ በማከናወን ላይ ትገኛለች ስትልም ግብፅ ለአረብ ሊግ ባቀረበችው የድጋፍ ጥያቄ አመልክታለች፡፡ የአረብ ሊግም ግብፅ በአባይ ውሃ ላይ ያላትን መብት ኢትዮጵያ እያሳጣቻት ነው በማለት ኢትዮጵያን የሚኮንን ውሳኔ ማሳለፉ የተገለፀ ሲሆን የአረብ ሊግ አባል የሆነችው ሌላኛው አገር ሱዳን በበኩሏ፤ የውሳኔ ሀሳቡ ኢትዮጵያን የሚያስቀይም ከመሆኑም በላይ የአገሯን ብሄራዊ ጥቅም የሚጋፋ መሆኑን በማመልከት ሀሳቡን እንደማትቀበለው አስታውቃለች፡፡
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ፤ የአረብ ሊግ በግድቡ ዙሪያ እየተደረገ ያለውን ድርድር ቁልፍ እውነታዎች ሳያገናዝብ በውሳኔ ሀሳቡ የሰጠው ጭፍን ድጋፍ እንዳሳዘነው አመልክቶ ሱዳን ያሳየችውን አቋም አድንቋል፡፡ የሊጉ ውሳኔም ተቀባይነት የሌለው ነው ሲል መንግሥት ውድቅ አድርጎታል፡፡
ይህ ሁሉ የግብፅ ማስጠንቀቂያ፣ ማሳሰቢያና አቤቱታ እያለ ግን የህዳሴው ግድብን አሁንም በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ ግንባታው እየተፋጠነ መሆኑን መንግስት ያስታወቀ ሲሆን 71 በመቶ የግንባታ አፈፃፀም ላይ መድረሱንም ለማወቅ ተችሏል፡፡ በቀጣይ ክረምትም 4.9 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ እንደሚገደብ እንዲሁም በመጋቢት 2013 የመጀመሪያ የሙከራ ሀይል ማመንጨት እንደሚጀመርም የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ አስታውቀዋል፡፡

Read 15266 times