Saturday, 30 June 2012 12:41

ፍቅር እስከ… መቃብር” ፊልም በባለሙያዎች ተገመገመ

Written by  መልካሙ ተክሌ (melkamutekele@gmail.com)
Rate this item
(1 Vote)

ምስል የትያትር እና ፊልም ፕሮዳክሽን በደራሲና አዘጋጅ ኤልያስ ገብረክርስቶስ ያሰራውን ”ፍቅር እስከ… መቃብር” ፊቸር ፊልም ባለፈው ማክሰኞ በባለሙያዎች አስገመገመ፡፡ ፒያሳ በሚገኘው የራስ ቴአትር ስቴርዮ አዳራሽ የተከናወነው የግምገማ ውይይት፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ትያትር ጥበባት ትምህርት ክፍል ጋር በመሆን የተሰናዳ ሲሆን የትምህርት ክፍሉ ሊቀመንበር መምህር ነብዩ ባዬ፤ የመነሻ ሀሳብ አቅርበው በጋዜጠኛ ፍቅር ይልቃል መድረክ መሪነት ውይይቱ ተካሂዷል፡፡ አቶ ነብዩ ባዬ በዚሁ ወቅት ባቀረቡት አስተያየት፤ ፀሃፊው የሩቅ ምሥራቅና የምስራቅ አውሮፓን በተለይ የሩሲያን ሥነፅሁፍ በደንብ ያነበበ ነው ሲሉ  አድንቀውታል፡፡ ታዋቂው ጋዜጠኛና ፀሐፌ ተውኔት ቴዎድሮስ ተክለአረጋይ በበኩሉ፤ “አሁን ያሉ ብዙ ፊልሞች ማደንዘዣ ናቸው፡፡ የዚህ ፊልም ርእስ ግን ያንስበታል” ብሏል፡፡ በመጪው ሐምሌ በስፋት መታየት የሚጀመረው ፊልሙ፤ በማቲ ሲኒማ ካለፈው ሰኞ ጀምሮ መታየት የጀመረ ሲሆን ሕሊና ሲሳይ፣ ሞገስ ወልደዮሃንስ፣ እንግዳ ጌታቸው፣ ሱራፌል ተካ አና ሌሎች ተውነውበታል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ ቢፈዋቃ ፊልሞች “ሄሉ ኢትዮጵያ” የተሰኘ አዲስ ልብ አንጠልጣይና ማህበራዊ ሕይወትን የሚያሳይ ፊልም ነገ ቦሌ መድኃኔዓለም አካባቢ በሚገኘው ሐርመኒ ኢንተርናሽናል ሆቴል ያስመርቃል፡፡ ዮሐንስ ፈለቀ ፅፎ ያዘጋጀውን የ90 ደቂቃ ፊልም ለመስራት ሰባት ወራት የፈጀ ሲሆን አርቲስት ሜሮን ጌትነት፣ ተስፋ ብርሃኔ፣ ጣሊያናዊው ተዋናይና ጋዜጠኛ ግርሃም ማርሽ፣ ዳንኤል ታደሰ (ጋጋኖ)፣ ዮሐንስ ተፈራ፣ ሰለሞን ታሼ (ጋጋኖ) እና ሌሎች ኢትዮጵያውያን እና የውጭ ሀገር ዜጐች ተውነውበታል፡፡ ፊልሙን ደራሲ እና አዘጋጅ ከኢዮኤል አበራ ጋር ፕሮዱዩስ አድርገውታል፡፡

በሌላም በኩል ኢያሪኮ ማስታወቂያና ፊልም ፕሮዳክሸን “ቢንጐ” የተሰኘ ፊልም አቀረበ፡፡ ነገ የሚመረቀውን የ105 ደቂቃ ፊልም ፍቅሩ ፍሬው ፅፎ ያዘጋጀው ሲሆን ደረጀ ደመቀ፣ አልያስ ወሰንየለህ፣ ሚካኤል ታምሬ፣ ነብያት መኮንን፣ ዮሐንስ ተፈራ፣ ካሳሁን ፍስሃ (ማንኤላ) ወይንሸት በላቸው፣ ኒና መለሰ፣ ብርሃን ክፍሌ፣ ቤተልሄም ታዬ እና ሌሎችም ተውነውበታል፡፡ ፊልሙ የሚመረቀው በአዲስ አበባ እና በክልሎች በሚገኙ ሲኒማ ቤቶች ነው፡፡

 

 

Read 2970 times Last modified on Saturday, 30 June 2012 12:46