Saturday, 07 March 2020 12:25

በዘንድሮ ክረምት 5 ቢሊዮን ችግኞች እንደሚተከሉ ጠ/ሚኒስትሩ አስታወቁ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

     በመጪው ክረምት 5 ቢሊዮን ችግኞችን በመላ ሀገሪቱ ለመትከል መታቀዱን ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ አስታወቁ፡፡ ባለፈው ክረምት በተከናወነው ሀገር አቀፍ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር፣ በአጠቃላይ በመላ ሀገሪቱ ከ4 ቢሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸውና አብዛኞቹ ችግኞችም አስፈላጊው እንክብካቤ እየተደረገላቸው መሆኑ ተመልክቷል፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ የኮካ ኮላ ኩባንያ ሊቀ መንበርና ዋና ስራ አስፈፃሚን አግኝተው ማነጋገራቸውን በጠቆሙበት የፌስ ቡክ ገጽ መልዕክታቸው፤ ኮካኮላ ኩባንያ በሸገር ፓርክና በእንጦጦ ፓርክ ፕሮጀክቶት ላይ ተሳታፊ እንደሚሆን ጠቅሰው፤ በመጪው ክረምት ለተያዘው 5 ቢሊዮን ችግኞችን የመትከል እቅድ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል፡፡
በቀጣይ ክረምት 5 ቢሊዮን ችግኞችን የመትከል እቅዱን ለማሳካትም ከወዲሁ ድጋፍ አድራጊ አካላትን የማስተባበር ስራ እየተሠራ መሆኑም ተመልክቷል፡፡
ባለፈው ዓመት የክረምት ወራት የተተከሉ ችግኞችን ህብረተሰቡ እንዲንከባከብ በተደጋጋሚ ጥሪ የሚያቀርቡት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ራሳቸውም በአዲስ አበባ የተለያዩ ቦታዎች የሚገኙ ችግኞችን በየጊዜው ውሃ በማጠጣት አርአያ ለመሆን እንደሚጥሩ ይታወቃል፡፡    

Read 957 times