Saturday, 29 February 2020 12:13

ምርጫ 2012 183 ቀናት ቀረው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

    የኢዜማ የቅድመ - ምርጫ ማስጠንቀቂያና ማሳሰቢያ

             ሥርዓት ዓልበኝነት ዘርፈ ብዙ ተግዳሮቶች - የሥልጣን ጥመኞች
               
            የኢትዮጵያ ዜጐች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ሁለት አመት ገደማ ያስቆጠረውን የለውጥ ሂደት በገመገመበት ሪፖርቱ የቀጣዩ ምርጫ ሀገራዊ ፋይዳና በሀገሪቱ የተደቀኑ ያላቸውን አደጋዎች ለኢትዮጵያ ህዝብ በዝርዝር አድርሷል - በሳምንቱ መጨረሻ፡፡
የኢዜማ መሪ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ባቀረቡት ሠፊ ግምገማ፤ የለውጡ የእስካሁን ሂደት፣ የቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ እንዲሁም ሀገሪቱ እንደ ሀገር ወደ ዲሞክራሲያዊ ስርአት ለመሻገር በምታደርገው መፍጨርጨር የተደቀኑባት ፈተናዎችን ዳሰዋል::
ኢዜማ ይህን የግምገማ ሪፖርቱን ያዘጋጀው ከተለያዩ ምንጮቹ ከሚሰማቸው መረጃዎች በተጨማሪ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የዘረጋውን የፓርቲ መዋቅር በመጠቀምና በተለያዩ አካባቢዎች ካደረጋቸው ህዝባዊ ውይይቶች ያገኛቸውን ግብአቶች መሠረት በማድረግ መሆኑን አስታውቋል፡፡
“ሶስቱ ሃይሎች”
በሀገሪቱ እየተከናወነ ያለው ለውጥ እንዲደናቀፍ ጥረት እያደረጉ ነው ያሏቸውን ሶስት ሃይሎች ፕሮፌሰሩ በንግግራቸው አስቀምጠዋል፡፡ አንደኛው ሃይል፤ “ይህ ለውጥ በእርግጥ ወደ ዲሞክራሲያዊ ስርአት ከሄደ እስካሁን በስልጣን ላይ በመሆን ያገኘነውን ጥቅም እናጣለን ብለው የሚሠጉ የቀድሞው ስርአት ዋነኛ ተጠቃሚዎችን የያዘ መሆኑን፤ እነዚህ ሃይሎችም ከህዝብ የተዘረፉ ከፍተኛ ገንዘብ ያላቸው፣ ከዚያም በላይ ከቀድሞ ስርአት ጋር ተያይዘው የመጡና እስካሁን ያልፈረሱ ለየክልሉ ዘውግ ታዛዥ የሆኑ ወታደራዊና የአካባቢ መንግስት አስተዳደር እንዲሁም የሚዲያ ተቋማት ያላቸው መሆናቸውን ፕ/ሩ ይገልፃሉ፡፡
ሁለተኛው ሃይል፤ ለውጡን የሚፈልግ ሃይል ነው፡፡ ይህ ሃይል የሚፈልገው ደግሞ መንግስትን ለመግራትና አገራዊ ዲሞክራሲያዊ ስርአት ለመመስረት ሳይሆን የቀድሞውን ዘውጌያዊ ስርአት ተክቶ እሱ ባለተራ ሆኖ፣ ሀገሪቱንና የሚያዘውን ክልል እንደፈለገው አድርጉ፣ ትናንሽ ነፃ መንግስታትን በመመስረት ደካማ ማዕከላዊ መንግስት የሚፈጠርበትን አካሄድ የሚከተል ነው፡፡ ይህም በዋናነት በአክራሪ ዘውጌ ፖለቲከኞችና በስሜት የሚጋልቧቸው የዘውጌ የህብረተሰብ ክፍሎችን ያካተተ መሆኑን የፕ/ሩ ሪፖርት ይጠቁማል፡፡
ሶስተኛው ሃይል ደግሞ እንደ ሁለቱ ሃይሎች በተግባራዊ እንቅስቃሴው ጠንካራ ባይሆንም፣ የለውጥ ሃይሉን በፍፁም የማያምን፣ በመሠረታዊ መልኩ ከዚህ በፊት ከነበረው አቋም የተለየ ነገር ይዞ መምጣት የማይችል፣ አገራዊ ዲሞክራሲያዊ ስርአት እመሠርታለሁ ብሎ ቃል የገባውም ህዝብን ለማታለልና በአዲስ ጭምብል የቀድሞውን ስርአት ለማስቀጠል የሚፈልግ ሃይል ነው ብሎ የሚያምን ነው፤ ይህ ሃይል የለውጥ ሃይሉ በደንብ ከመደላደሉ በፊት በመቃወም፣ የህዝብን ተቀባይነት እንዳያገኝ በማድረግና ለውጡን ለማስኬድ ብቃትም ሆነ ተአማኒነት የለውም በማለት የተጀመረውን ለውጥ ከግቡ ለማድረስ ከሁሉም የተውጣጣ የሽግግር መንግስት ይፈጠር በሚል የራሱን አጀንዳ ለማራመድ የሚሞክር ነው ይላሉ - ፕ/ሩ፡፡
እነዚህ ከላይ የተመለከቱት ሶስት ሃይሎች የሚያመሳስላቸውም የሚያሠራጩት ፀረ መንግስት ፕሮፖጋንዳና መንግስትን የማዳከም ፍላጐታቸው መሆኑንና የቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ ዋነኛ ስጋትም ከእነዚህ ሃይሎች እንደሚመነጭ የፕ/ሩ መልዕክት ይጠቁማል፡፡
ቀጣዩ ምርጫ እና ተግዳሮቶቹ
በነሐሴ ሊካሄድ ቀጠሮ የተያዘለት ሀገራዊ ምርጫ ከዚህ ቀደም ከነበሩት ምርጫዎች በባህሪው የተለየና የሀገሪቱን የወደፊት እጣ ፈንታ የሚወስን መሆኑን የገለፁት ፕ/ር ብርሃኑ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ በህዝብ ቅቡልነት ያለው መንግስትን የመመስረቻ ወሳኝ ሂደትም ነው ብለዋል፡፡
የሀገሪቱን የተጠራቀሙ ችግሮች በሰለጠነ መንገድ መፍታት የሚቻለውም ቀጣዩ ምርጫ የተሳካ መሆን ሲችል ብቻ ነው ያሉት የኢዜማ መሪ፤ ይህን እንደ ሀገር ማሳካት ካልተቻለ ግን ሀገሪቱ ባለፉት 18 ወራት ካሳለፈቻቸው ዘርፈ ብዙ ችግሮችም ወደተወሳሰበ አጠቃላይ ሀገራዊ ቀውስ የምትገባበት ሁኔታ መፈጠሩ አይቀሬ ነው ብለዋል፡፡
አሁን የሚታየው የሶስት ሃይሎች መጓተት፣ የህግ የበላይነትና የስነ ስርዓት ጉድለት፣ የተካረረ የዘውጌ ብሔርተኝነት ተጠናክሮ ከቀጠለና ምርጫው ሁሉም በሚያስበው መልኩ የማይካሄድ ከሆነ፣ ውክልናቸው በህዝብ ያልተረጋገጠላቸው “ወኪል ነን” ባይ ድርጅቶች፤ “ውክልናቸውን ለማረጋገጥ ሊሄዱበት የሚችሉት ብቸኛ መንገድ ጉልበትና አመጽ ብቻ ይሆናል - ይላሉ - ፕ/ሩ፡፡
ይህ አመጽ ደግሞ አንድ ሃይል ወይም አንድ ወገን ብቻ የሚያካሂደው አመጽ ሳይሆን ሁሉም ሁሉንም የሚፈራበት፣ ሁሉም ከፍርሃቱ ለመውጣት ሲል ቀደም ልቅደም በሚል ራሱን ለአመጽ የሚያዘጋጅበት፣ ተዘጋጅቶም “ጠላቴ” የሚለውን ሃይል ለማጥፋት የሚንቀሳቀስበት፣ የዘውጌ ክልሎች አንዱ ካንዱ ጋር ለውጊያ የሚነሳሱበት፣ በዘውጌ ክልሎች ውስጥ (ህገ መንግስቱ ባመጣው መዘዝ “ነባር ነዋሪ የክልል ባለቤቶች” በሚባሉና “መጤ” በሚባሉ ኢትዮጵያውያን መካከል ግጭት መቀስቀሱ አይቀርም”” በየአካባቢው ባሉ “ጊዜው የኛ ነው ባይ ጉልበተኞች” የሚመሩ ቡድኖች የበላይነት ለማግኘት የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ የሚገቡበት፣ እልም ያለ ስርአት አልበኝነት የሚነግስበት ሁኔታ መፈጠሩ አይቀሬ ነው ባይ ናቸው፡፡
በስልጣን ለይ ያለው መንግስት ደግሞ “የፖለቲካ ሃይሎች ሀገርን ትርምስ ውስጥ ሲከቷት እጄን አጣጥፌ አላይም” በሚል በጉልበትና በሃይል ስልጣን ላይ ለመቆየት ሲል ወደ ለየለት አምባገነናዊ ባህሪ ሊቀየር እንደሚችልም ፕ/ሩ ግምታቸውን ያስቀምጣሉ፡፡
ተመልሰን ወደ ጨለማ እንዳንሄድ ከፊታችን ምርጫ መካሄዱ የግድ አስፈላጊ ነው የሚሉት ፕ/ር ብርሃኑ፤ ምርጫውም አይቀሬ መሆኑ ከተረጋገጠ ከወዲሁ ምርጫው ምን አይነት መስፈርቶችን ማሟላት እንዳለበት፣ ምርጫውን ተዓማኒ ለማድረግስ ከፊት ለፊት የተጋረጡ ፈታኝ አገራዊ አደጋዎች ምንድን ናቸው? የሚለው በሚገባ መጤን አለበት ይላሉ፡፡
ቀጣዩ ምርጫ በሠላማዊ መልኩ እንዲካሄድ ለማድረግም፣ ለማንኛውም ተወዳዳሪ ሃይል የመንግስት አካላትና አስፈፃሚው ወግነው እንደማይቆሙ ማረጋገጥና ዋስትና መስጠት ቀዳሚው ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር ህዝብ በምርጫ የሰጠው ድምጽ በትክክል እንደሚቆጠርና እንደማይጭበረበር ማረጋገጥና የህዝቡን እምነት ማግኘት አለበት ያሉት ፕ/ሩ፤ ለዚህም ምርጫ ቦርድ ፍፁም ነፃና ገለልተኛ እንደሆነ፣ በምርጫው ሂደት መሠናክሎች ቢገጥሙ በማንም ሳያዳላ የሚይይና የሚፈርድ ተአማኒነት ያለው የዳኝነት/ፍትህ ስርአት እንዳለ ማረጋገጫ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ለዚህ ምርጫ በዋናነት አደጋ ሊሆኑ ይችላሉ ተብለው በኢዜማ መሪ የተጠቀሱትም፤ በየክልሉ ያሉ በየብሔር የተደራጁ ጽንፈኛ ሃይሎችና በስራቸው የተሰባሰቡ ኢ-መደበኛ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ በየክልሉና በተለይ በታችኛው እርከን ያሉ የመንግስት አስተዳዳሪዎችና የፀጥታ ሃይሎች የሚፈጥሯቸው እክሎች፣ በከፍተኛ የመንግስት አካላትና በገዥው ፓርቲ እውቅና የሚፈፀሙ እንቅፋቶች መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
እነዚህ ችግሮች ታውቀው ምርጫው የተሳካና ዲሞክራሲያዊ ስርአት የሚዋለድበት ይሆን ዘንድ ሁሉም ባለድርሻዎች፤ የየራሳቸውን በጐ ሚና እንዲጫወቱ ያሳሰቡት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፤ መንግስትም ህግና ስርአትን የማስከበር ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡


Read 3198 times