Print this page
Saturday, 29 February 2020 12:12

ዓለምን ስጋት ላይ የጣለው ኮሮናቫይረስ ኢትዮጵያንም ያሰጋታል

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(13 votes)

    - በሽታው ወደ ኢትዮጵያ ቢገባ ጉዳቱ እጅግ አስደንጋጭ እንደሚሆን የጤና ባለሙያዎች ተናገሩ
         - በሽታው ካሉባቸው አገራት አራት ሺ ሰዎች ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል
         - በ25 ቀናት ውስጥ 60 ጥቆማ ደርሶ፣ በ17 ሰዎች ላይ የበሽታው ምልክት ታይቷል
         - ስለበሽታው ምንነትና ቅድመ ጥንቃቄዎች በቂ ግንዛቤ አልተሰጠም
         - በቻይና የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩን ተማፀኑ
                

             መነሻውን ከቻይናዋ ሁዌይ ግዛት ውሃን ከተማ አድርጐ፣ ከ26 በላይ የአለማችንን አገራት ያዳረሰው የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ 19) የዓለም ስጋት መሆኑ አሁንም ቀጥሏል፡፡ አልጀሪያ በአፍሪካ ሁለተኛውን የኮሮኖ ቫይረስ በሽታ ታማሚ ማግኘቷን አረጋግጣለች፡፡ አሜሪካ እስካሁን 61 ተጠቂዎችን የመዘገበች ሲሆን፤ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ምክትላቸውን ማይክ ፔንሰን የኮሮና ቫይረስ ተከላካይ አድርገው ሾመዋቸዋል፡፡ የበሽታውን ስርጭት ለመቆጣጠርም ከፍተኛ ገንዘብ መመደቡን ተናግረዋል፡፡
አሜሪካ፣ ጣሊያን፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ኢራንና ጃፓን በበሽታው የተያዙ ሰዎች ከተገኙባቸው አገራት መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
በአፍሪካ ግብጽና አልጀሪያ በበሽታው የተያዙ ሰዎችን ማግኘታቸውን ይፋ አድርገዋል::
በሽታው ዓለምን በስጋት እየናጣት መሆኑን ተከትሎ፣ በአገራችን በሽታውን ለመከላከል እየተወሰደ ያለው እርምጃ እጅግ አነስተኛ መሆኑንና በሽታው ቢከሰት በአገሪቱ ሊያስከትል የሚችለው አደጋ ከሚታሰበው በላይ እንደሚሆን የጤና ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
የኮሮና ቫይረስ በሽታ ስጋት ይፋ ከተደረገ በኋላ በርካታ የዓለማችን አገራት የበሽታው መነሻ ወደሆነችው ቻይና የሚያደርጓቸውን በረራዎች በየተራ ማቋረጣቸው ይታወቃል:: በአንፃሩ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አገሪቱ ለ35 ዓመታት የዘለቀ ደንበኝነት ያላት አገር ከመሆኗ አንፃር አሁን ክፉ ጊዜ ገጠማት ብለን በረራ ማቋረጥ አይገባንም፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ወደታይላንድ የሚደረጉ በረራዎችም እስካልተቋረጡ ድረስ ቻይናውያን መንገደኞች በታይላንድ በኩል መግባታቸው አይቀሬ ነው፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ አየር መንገዱን የሚጠቀሙና ከሌሎች አየር መንገዶች ወደሌሎች የተለያዩ አገራት የሚጓዙ ሰዎች ስለሚኖሩና መንገደኞቹ ትራንዚት ሲያደርጉ በአገሪቱ በኩል ማለፋቸው ስለማይቀር ወደ ቻይና የሚደረጉ በረራዎችን በማቋረጥ የበሽታውን ስርጭት ለመግታት አይቻልም ብሏል፡፡ በዚህ ምክንያትም አየር መንገዱ በሳምንት ለ30 ጊዜያት ወደ ቻይና የሚያደርገውን በረራ እንደቀጠለ ነው፡፡
የበሽታው መከሰት ይፋ ከተደረገበት ጊዜ ጀምሮ ላለፉት 25 ቀናት 5400 በላይ ሰዎች ወደ አገሪቱ መግባታቸው ታውቋል:: እነዚህ ገቢ መንገደኞች የመጡት በሽታው እንደተከሰተባቸው ሪፖርት ካደረጉ አገራት ነው፡
የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት በቦሌ ዓለምአቀፍ አየር ማረፊያ ውስጥ ሁሉንም ገቢ መንገደኞች የሰውነት ሙቀት የመለካት ስራ እየሰራ እንደሆነ ገልጿል፡፡
ኢንስቲቲዩቱ በሰጠው መግለጫ ላይም፤ እስካሁን በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ከ220ሺ ለሚበልጡ ገቢ መንገደኞች የሙቀት መለካት ስራ መስራቱንና ከእነዚህ መካከል 5400 ሺ የሚበልጡት የመጡት የበሽታው ስርጭት ይፋ ከተደረገባቸው አገራት መሆኑን አመልክቷል:: ባለፉት 25 ቀናት ውስጥ 60 የሚደርሱ የበሽታው ጥቆማዎች እንደደረሰው ያስታወቀው ኢንስቲትዩቱ፣ ከእነዚህ መካከል 17 ያህሉ የበሽታው ምልክት እንደታየባቸውና ተለይተው እንዲቆዩና ተጨማሪ ምርመራ እንዲደረግላቸው ተደርጐ ከበሽታው ነፃ መሆናቸው መረጋገጡን አስታውቋል፡፡
የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት በአየር ማረፊያው የሚያደርገው የገቢ መንገደኞች የሙቀት ልኬት፣ በሽታው ወደ አገራችን ከመግባት ሊያግደው እንደማይችልና በአየር ማረፊያ ለገቢ መንገደኞች የሚደረገው ጥንቃቄ እጅግ አነስተኛ እንደሆነ የጤና ባለሙያዎች ይገልፃሉ፡፡
ሁለት እህቶቹን ከቻይናዋ ሁቤይ ግዛት ወደ አገሩ ይዞ መምጣቱን የተናገረው ዮሴፍ ታረቀኝ፤  በሽታው መቀስቀሱ ከተገለፀበት ጊዜ ጀምሮ ቤተሰቦቻቸው እጅግ ለከፍተኛ ስጋት ተዳርገው እንደነበር ጠቁሞ፤ ወደ ቻይና ተጉዞ እህቶቹን ይዞ ለመምጣት መወሰኑን ያስረዳል፡፡  ከሁለት ዓመት ለበለጠ ጊዜ ኑሮአቸውን በቻይና አድርገው በመማር ላይ የነበሩትን  ሁለቱን እህቶቹን ይዞ  ወደ አገር ውስጥ በገቡበት ወቅት የመግቢያ ቪዛ በሚሰጥበት ስፍራ ላይ የሙቀት ልኬት መታየታቸውንና ከዚህ የዘለለ የጥንቃቄ እርምጃ ሲወሰድ አለማየቱን ተናግሯል፡፡
በአየር ማረፊያው ውስጥ የበሽታውን ስርጭት ለመከላከል የሚያስችል የጥንቃቄ እርምጃ ሲወስድ እምብዛም አለመታየቱ የብዙዎችን ስጋት ጨምሮታል፡፡
ሁኔታው ከቁጥጥር ውጪ ከመሆኑ በፊትም ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ያሉት የህብረተሰብ ጤና ባለሙያው ዶ/ር ተስፋዬ ሰለሞን፤ የአለማየችን ቁንጮ የሆኑት የሰለጠኑት አገራት መቋቋም ያልቻሉትንና ያላመለጡትን ወረርሽኝ፣ እኛ በዚህ ጥንቃቄና የመከላከል እርምጃ ልናመልጠው እንችላለን ማለት የማይታሰብ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡
የህብረተሰቡ ማህበራዊ አኗኗር እርስ በርሱ በጣም የተሳሰረና የተጣበበ ከመሆኑና በቂ የንጽህና መጠበቂያ ሁኔታዎች ካለመኖራቸው አንፃር በሽታው ወደ አገራችን ቢገባ ሊከሰት የሚችለው ከፍተኛ አደጋ ሊያሳስበን ይገባል ያሉት ዶ/ር ተስፋዬ፤ ህብረተሰቡም ስለ በሽታውና መከላከያው በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው ለማድረግ ሰፊ ስራ ሊሰራ ይገባል ብለዋል፡፡
በኢኮኖሚ ደረጃቸው የላቁ የአለማችን  አገራት ሊከላከሉትና ሊያስቆሙት ያልቻሉትን ወረርሽኝ እኛ በወደቀ የኢኮኖሚ አቅምና በደከመ ቴክኖሎጂ ልንቆጣጠረው እንችላለን ማለቱ በእጅጉ የማይመስል ጉዳይ ነው ይላሉ - ዶ/ር ተስፋዬ፡፡  በሽታው እስካሁንም በአገራችን አለመከሰቱ የተአምር ያህል ያስገርመኛል ብለዋል - ሃኪሙ፡፡
የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት ከትናንት በስቲያ በሰጠው መግለጫ፤ በሽታው ከተከሰተባቸው አካባቢዎች የመጡ ገቢ መንገደኞችን የሙቀት ልኬት ሥራ መስራቱን ጠቁሞ፣ በበሽታው የተጠረጠሩ 17 ሰዎች በለይቶ ማቆያ ውስጥ ለ14 ቀናት እንዲቆዩ ተደርገው የቆይታ ጊዜያቸውን ሳይጨርሱ ከቤተሰብ ጋር እንዳይገናኙ መደረጉንም አመልክቷል:: ኢንስቲቲዩቱ ትኩሳት፣ ሳልና የመተንፈስ ችግር ያጋጠመው ማንኛውም ሰው በአፋጣኝ ወደ ህክምና ተቋማት መሄድ እንደሚገባውና በሚያስሉበትና በሚያስነጥሱበት ወቅት አፍና አፍንጫን መሸፈን እንደሚገባ አመልክቷል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሳምንት ለ30 ጊዜያት ወደ ቻይና የሚያደርገውን በረራ እንደቀጠለ ሲሆን በሽታው ከተቀሰቀሰበት ውሃን ከተማ የሚገቡ ሁሉም መንገደኞች ለ14 ቀናት ተገልለው የሚቆዩበት የማቆያ ስፍራ ማዘጋጀቱንና ለእነዚህ መንደገኞች በተለየ መስኮት ለብቻቸው አገልግሎት እየሰጠ እንደሆነም ተናግሯል፡፡
እስካሁን ድረስም በአገሪቱ በቫይረሱ የተያዘ ሰው አለመገኘቱን ጠቁሟል - ኢንስቲቲዩት፡፡ በተያያዘ ዜናም በዚህችው የኮሮና መነሻ በሆነችው የቻይናዋ ውሃን ከተማ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ወደ አገራችን መልሱን ሲሉ የተማፅኖ ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚ/ሩ ጽፈዋል፡፡
በ26 የአለማችን አገራት የተከሰተው የኮሮና ቫይረስ በአገራችን ቢከሰት የሚያስከትለው ጉዳት እጅግ የከፋ እንደሚሆን ቀደም ሲል የተናገሩት የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም፤ አገሪቱ ያላት አቅም የበሽታውን ስርጭት ለመግታት የሚያስችል አለመሆኑን  መናገራቸው አይዘነጋም፡፡
በአሁኑ ወቅት የበሽታው መነሻ በሆነችው ቻይና የበሽታው ስርጭት እየቀነሰ የመጣ ሲሆን፤ ከትናንት በስቲያ 394 አዳዲስ የበሽታው ተጠቂዎች ተመዝግበዋል፡፡ ከሶስት ቀናት በፊት ግን በአንድ ቀን ብቻ 1749 አዳዲስ የበሽታው ተጠቂዎች ተመዝግበው ነበር፡፡
ስርጭቱ ከቀን ወደ ቀን እየቀነሰ የመጣ ቢሆንም አሁንም በሽታው የአለማችን ትልቁ አደጋና ስጋት እንደሆነ ቀጥሏል፡፡


Read 13632 times