Saturday, 29 February 2020 11:44

የፈርኒቸርና ቤተ ውበት አውደ ርዕይ ሐሙስ ይከፈታል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

  በፕራና ኢቨንትስና በኢቲ መባቻ ኤቨንትና ቢዝነስ ሶሉሽን ትብብር የተዘጋጀው የፈርኒቸርና የቤተ ውበት አውደ ርዕይና ጉባኤ የፊታችን ሐሙስ ረፋድ ላይ ለሁለተኛ ጊዜ በሚሊኒየም አዳራሽ ይከፈታል፡፡
ለ3 ቀናት በሚካሄደው በዚህ አውደ ርዕይና ጉባኤ የፈርኒቸር፣ ቤተ ውበትና የግንባታ አጨራረስ ምርቶች፣ የቤት፣ በቢሮና በኢንዱስትሪ ፈርኒቸር ዘርፍ የተሰማሩ፣ የውስጥና የውጭ የቤት ማስዋቢያ ምርቶች፣ መብራቶች፣ መጋረጃ አምራቾችና አከፋፋዮች እና ልዩ ልዩ ግብአቶች ለእይታ ይቀርባሉ ተብሏል፡፡
ከአውደ ርዕዩ ጎን ለጎንም ዘርፉን ለማሳደግ በሚቻልባቸው ሁኔታዎችና ጉዳዮች ላይ ሰፊ ጥናትና ምርምር ባደረጉ ባለሙያዎች በሚነሱ ሀሳቦች ላይ ውይይትና ምክክር ይደረጋልም ተብሏል፡፡ በአውደ ርዕዩም ላይ ከ50 በላይ የውጭና የአገር ውስጥ አምራቾች አቅራቢዎችና አገልግሎት ሰጪዎች ይሳተፋሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ከ5 ሺህ በላይ ጎብኚዎችም ይጎበኙታል ተብሏል፡፡
አውደ ርዕዩ በዋናነት የጋራ መኖሪያ መንደሮችን፣ ቤቶችን፣ የፋይናንስ ተቋማትን፣ የሕክምና ማዕከሎችን የትምህርት ተቋማትን፣ የገበያና የመዝናኛ ማዕከላትንና ሱፐርማርኬቶችን በመገንባት የእርስ በርስ የገበያ ትስስር ለመፍጠር ጥሩ አጋጣሚ ነው ያሉት አዘጋጆቹ በአውደ ርዕዩ ላይ ከጀርመን፣ ከኬንያና ከቱርክ ከተወከሉ ድርጅቶች ጋር መስራት የሚችሉበት ሁኔታም ይፈጠራል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከ5 ቢ ዶላር እና ከ1.3 ሚ በላይ የሥራ እድል መፍጠር የሚችል እንዲሁም የአፍሪካ 67 በመቶ ከዓለም 7 በመቶ የቀርከሃ ምርት ባለቤት ስትሆን በምሥራቅ አፍሪካ ሁለተኛዋ ግዙፍ የፈርኒቸር ገበያ እንዲሁም በምሥራቅ አፍሪካ 5ኛዋ የውጭ አገራት የፈርኒቸር ምርቶች መዳረሻ እንዲሁም የመንግሥት የፈርኒቸር ግዢ ዓመታዊ ወጪ ከ10 ቢ.ብር በላይ ስለመሆኑ የወርልድ ባንክን ጥናት ዋቢ አድርገው አዘጋጆቹ ገልፀዋል፡፡  

Read 2976 times