Saturday, 29 February 2020 11:40

ዋ!---ያቺ ዐድዋ

Written by  በታደለ ገድሌ
Rate this item
(3 votes)

           “በኢትዮጵያውያን የአንድነት ጽንዓት ጀኔራል አልቤርቶኒ ሲማረክ፣ ሶላቶ ሁሉ በኢትዮጵያውያን ክንድ ተደቁሶ ተዝለፍልፎ ሲወድቅ፣ ነፍሴ አውጭኝ ብሎ ሶላቶ ሲሸሽ፣ ሲፈረጥጥ ጀኔራል አርሞንዲ፤ ኮሎኔል ጋሊያኖ፤ ካፕቴን ፍራንሲ፤ ማጆር ቶዚሊ ሲገደሉ፤ በአጠቃላይም በዚያ ሕገ ወጥ ጦርነት ኢጣሊያ ካሰለፈቺው 14 ሺህ ያህል ሠራዊቷ ሰባት ሺህ ሲያልቅባት፤ ኢትዮጵያ የስድስት ሺህ ሰው ደም ገብራለች፡፡”
          
             በዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ አዋጅ  አስነጋሪነት፣ በጦር አበጋዞቻቸው አዝማችነትና በጀግኖቻቸው ተዋጊነት፣ ከወራሪዋና ከቅኝ ገዥዋ ኢጣሊያ ጋር ዓድዋ ላይ የተደረገው ጦርነት ምን ያህል አስከፊና ወሳኝ እንደነበር ባለቅኔ ሎሬት ጸጋየ ገብረ መድኅን፣ በዚህች ቃለ አንክሮን፤ ቃለ ትውስታን፣ቃለ ትዝብትንና እምቅ ሐሳብን  በያዘቺው ሥራው በዓይነ ኅሊና ወደ ኋላ ተጉዘን፣ ዘመኑን እንድንቃኝ፣ እንድንስታውስ ያደርገናል፡፡
ዋ!---
ዓድዋ ሩቅዋ
የዓለት ምሰሶ አድማስ ጥግዋ
ሰማይ ጠቀስ ጭጋግ ዳስዋ
ዓድዋ---
የአድዋን ጦርነት ወይም የአድዋን ድል፣ ዓድዋ ሩቅዋ ከሚለው ስንኝ ጋር በዓይነ ልቡና ተጉዘን ስናስታውሰው ከመቶ ዓመት በላይ ሆኖታል፡፡ ግን ይህ በዘመን የሚለካ ሳይሆን ዓድዋ የመጠቀ፤ የማይደረስበት የታሪክ ክንውን የተፈጸመባት መሆኑዋን ይነግረናል፡፡ ዓድዋ ሩቅዋ ሲባል ለእግረ መንገድ ትርቃለች ማለት ሳይሆን የታሪክ ከፍታዋን ለማሳየት ነው፡፡ በቅኝ አገዛዝ ዘመን ለነጻነት መሥዋዕትነት የተከፈለባት ታሪካዊት ምድር፣ በዓለምም ይሁን በአፍሪካ አናገኝም እንደ ማለት ነው፡፡ ለምን ቢሉ፣ ነጭ ሁልጊዜ አሸናፊ፤ ጥቁር ተሸናፊ ተደርጎ በሚታይባት በዚህች ዓለም፤ ኢትዮጵያ የሀገር ፍቅር ወኔን ብቻ አንግባ ዘመናዊ ጦር የታጠቀውን የኢጣሊያ ወራሪ ኃይል ዓድዋ ላይ በአሳፋሪ ሁኔታ ደምስሳ ስለአሳፈረቺው ነው፡፡
የዓለት ምሰሶ አድማስ ጥግዋ
የሚለው ተምሳሌቱ በዓድዋ የገዘፉና ሰማይ ጠቀስ የሆኑ የሶሎዳ፣ የራዮ፣ ደራርና ናስራይ የተባሉ ተራራዎች እንደሚኖሩ፤ እነዚህም ተራራዎች ለኢትዮጵያውያን የጥንካሬና ጀግንነት የአይበገሬነት ተምሳሌቶች እንደሆኑ፤ በተራራዎች አናትና ጥጋጥጉን እንደነ ማርያም ሸዊቶ፣ እንደነ እንዳ አባ ገሪማ፣ እንደነ እንዳ ኪዳነ ምሕረት የመሳሰሉ ታሪካዊ ቦታዎች መኖራቸውን ባለቅኔው በምዕናባዊ ምሥጢሩ ያሳየናል:: የዓለት ምሰሶ የማይወድቅ ነው፡፡ ይህም ሀገሪቱ የእምነት፣ የአንድነት፣ የነጻነት መሠረት ያላት መሆኗን ያበሥረናል፡፡
ሰማይ ጠቀስ ጭጋግ ዳስዋ
የሚለው ሐረግ ከላይ የተጠቀሱት የገዘፉ ተራራዎች፣ ዳመናና ጭጋግ እንደማይለያቸው የሚያመለክት መስሎ በሁለቱም ወገን ጦርነቱ እንደተከፈተ፤ ሰማይና መሬት የተገለባበጡ እስኪመስል ድረስ በ87 ምድብ በየተራሮች ላይ የተጠመዱት 56 የጣሊያን መድፎች ሲያጓሩ፣ መትረየሶች እሳት ሲተፉ፣ ዘመናዊ ጦር የታጠቀውና በቁጥር ከ14 ሺህ በላይ የሆነው የኢጣሊያ ሠራዊት በሚተኩሰው እሩምታ፣ የኢትዮጵያ ጀግኖችም  በጥይት፣ በሳንጃ፣ በጎራዴ ከወራሪው ጋር ሲሞሻለቁ በተነሣው አቧራ በአድዋ ሰማይና ተራራዎች ላይ  እንደ ጉም፤ እንደ ዳመና እንደ ዳስ፣ እንደ ጃንጥላ እየሆነ ምድሪቱን ጭጋግ የሸፈናት መሆኑን ያመለክታል፡፡
በአንቺ ብቻ ሕልውና
በትዝታሽ ብፅዕና
በመሥዋዕት ክንድሽ ዜና
አበው ታደሙ እንደገና
የኢትዮጵያ ጀግኖች ጣሊያንን ድባቅ መምታት የጀመሩት ገና ወደ ዋናው ጦርነት ሳይገቡ አምባላጌ ላይ ነው፡፡ በራስ መኮንን የበላይነትና በፊታውራሪ ገበየሁ ጎራ አዝማችነት ወደ ሰሜን የተመመው ቀዳሚ ጦር፣ በሜጀር ጀኔራል ቶዚል መሪነት አምባላጌ ላይ መሽጎ ይጠባበቅ የነበረውን ወራሪ ድባቅ መታው፤ የሞተው ሞቶ የቀረው ፈረጠጠ፡፡ ጀግናው የኢትዮጵያ ጦር ወደ መቀሌ እንዳ ኢየሱስ ገስግሶ፣ በእቴጌ ጣይቱ ብልኃት ጣሊያን ይጠቀምበት የነበረውን የውኃ ጉድጓድ ተቆጣጥሮና ወግቶ ወደ ኋላው እንዲሸሽ አደረገው፤ እዳጋሐሙስ አዲግራት ሲድበለበል የነበረውን ወራሪ እያባረረ ጦሩ ዓድዋ ደረሰ፡፡
ዋ!
ዓድዋ የዘር ዐፅመ ርስትዋ
የደም ትቢያ መቀነትዋ
በሞት ከባርነት ሥርየት
በደም ለነጻነት ስለት
አበው የሰውብሽ ለት
ይህ ግጥም ሕዝብ  በዓድዋ ጦርነት ዘር፣ ጎሳ፣ ሃይማኖት ሳይለየው ለሀገሩ ሉዓላዊነትና ፍቅር ሲል የደም መሥዋዕትነት ከፍሎና ሞቶ ከባርነት እንደወጣ፣ ነጻነቱን እንዳስከበረ ያሳያል፡፡
ዓድዋ!
የኩሩ ትውልድ ቅርስዋ
የኢትዮጵያዊነት ምስክርዋ
ዓድዋ
ዓድዋ የኩሩ ትውልድ ቅርስና የኢትዮጵያዊነት ምስክር ለመሆን የበቃቺው በዘመኑ ጀግኖች መሥዋዕትነት ስለተከፈለባት ነው፡፡
የኩሩ ደም ባንቺ ጽዋ
ታድማ በመዘንበልዋ
ዐፅምሽ በትንሣኤ ነፋስ
ደምሽ በነጻነት ሕዋስ
ሲቀሰቀስ ትንሣኤዋ
ተግ ሲል ሲንር ትቢያዋ
ብር ትር ሲል ጥሪዋ
ድው እልም ሲል ጋሻዋ
ሲያስተጋባ ከበሮዋ
ሲያስገመግም ዳኘው መድፍዋ
ያባ መቻል ያባ ዳኘው
ያባ ነፍሶ ያባ ቃኘው
ያባ በለው በለው በለው
በለው በለው በለው በለው
ዋ!---ዓድዋ
ያንቺን ጽዋ ያንቺን አይጣል
ማስቻል ያለው አባ መቻል
በዳኘው ልብ በአባ መላው
በገበየሁ በአባ ጎራው
በአባ ነፍሶ በአባ ቃኘው
በለው ብሎ፣ በለው- በለው!
ዋ!---ዓድዋ---
የትላንትናዋ
ተማምለውና የኢትዮጵያዊነትን ጽዋ ጠጥተው በአንድነት ነጋሪት እጎሰሙ፤ ከበሮ እየተመተሙ፤ ሴቱ በእልልታ፤ ወንዱ በሆታ፤ አዝማሪ በእልልታ ወደ አድዋ ተምመው፣ በኮራው ደማቸው የምድሪቱን አፈር ያቀለሙት፤ በዐጥንታቸው የነጻነት ዓለት ያቆሙት የምጽዓት ቀን የደረሰ እስኪመስል ድረስ በጋሻና በጎራዴ፣ በመድፍና በጦር ወኔ ተዋግተው መሆኑን የግጥሙ ስንኝ ይነግረናል፡፡
በጦርነቱ ላይ የተሰለፉት የኢትዮጵያ የጦር አበጋዞች በፈረስ ስማቸው ጭምር አባ ዳኘው (ምኒልክ)፣ አባ መቻል፤ አባ መላ (ሀብተ ጊዮርጊስ)፣ አባ ቃኘው (ራስ መኮንን)፣ ገበየሁ አባ ጎራው፣ ባልቻ አባ ነፍሶ፣ አባ በለው እየተባሉ የተጠቀሱት  ከጀግንነታቸው የተነሣ ነው፡፡
የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ከንጋቱ ጀምሮ ተራራ ላይ የተጠመደው 56 የጠላት መድፍ ሲያጓራ ከቁብ ያልቆጠረውና ከባርነት ተላቅቆ ነጻነቱን ለማስረገጥ በዓድዋ ማኅጸን የከተተው የኢትዮጵያ ጦር በወኔ ተሞላ:: በዚያ ወቅት በራስ መኮንን የተመራው የሐረርጌ ጦር ወደ ከተማዋ ተመመ፤ በራስ ሚካኤል ሥር የነበረው የወሎ ጦር ጀኔራል አልቤርቶኒ ያሸመቀበትን  የሶሎዳን ተራራ ከበበ፤ በንጉስ ተክለ ሃይማኖት የተመራው የጎጃም ጦር  ፊት ለፊት ሄዶ ከጠላት ጋር ተጋፈጠ፤ በራስ መንገሻ ዮሐንስ የተመራው የትግራይ ጦር አዲአቡንን ከበበ፤ በዓፄ ምኒልክ፤ በእቴጌ ጣይቱ፤ በራስ ወሌና በዋግሹም ጓንጉል ሥር የተደራጀው ጦር በደጀንነት ተሰለፈ፤ ምርጥ የሸዋ ፈረሰኞች ጣሊያን እንዳይጠቀምበት ከ13 ኪሎ ሜትር ጀምሮ የምንጭ ውኃ ያለበትን ጉድጓድ ሁሉ ከበቡ፡፡
በጦርነቱ ምድር ቀውጢ ስትሆን፤ አቧራው ወደ ሰማይ ሲጎን፣ ደም ከዐፈር ጋር ሲቀላቀል፣ አጥንት በመድፍ ጥይት ሲገነተል፣ ዛፍ ቅጠሉ ሲረግፍ ቆይቶ ጠላት ሲርበተበት፤ ግጥሙ በሥዕላዊ መንገድ ያስረዳናል፡፡ እናም በኢትዮጵያውያን የአንድነት ጽንዓት ጀኔራል አልቤርቶኒ ሲማረክ፣ ሶላቶ ሁሉ በኢትዮጵያውያን ክንድ ተደቁሶ ተዝለፍልፎ ሲወድቅ፣ ነፍሴ አውጭኝ ብሎ ሶላቶ ሲሸሽ፣ ሲፈረጥጥ ጀኔራል አርሞንዲ፤ ኮሎኔል ጋሊያኖ፤ ካፕቴን ፍራንሲ፤ ማጆር ቶዚሊ ሲገደሉ፤ በአጠቃላይም በዚያ ሕገ ወጥ ጦርነት ኢጣሊያ ካሰለፈቺው 14 ሺህ ያህል ሠራዊቷ ሰባት ሺህ ሲያልቅባት፤ ኢትዮጵያ የስድስት ሺህ ሰው  ደም ገብራለች፡፡ ይህንን ሁሉ የምታሳየን ዓድዋ ናት፡፡
ዋ!---ያቺ ዐድዋ
ክብር ለጀግኖቻችን ይሁን!


Read 1738 times