Print this page
Sunday, 01 March 2020 00:00

ህዝባቸውን የማያከብሩ ፖለቲከኞች ዕድሜ የላቸውም!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(3 votes)

   ሮዛ ፓርከር የተባለች የአርባ ሶስት ዓመት የዕድሜ ባለፀጋ፣ በአሜሪካ ለተቀጣጠለው የነፃነት ጥያቄ መነሻ ሆናለች፡፡ የእርሷን ችቦ የተቀበለው የቤተ ክርስቲያን መጋቢ ማርቲን ሉተር ኪንግ ደግሞ የሚታወቀው ሕይወቱን ለትግሉበመሰዋት ነው፡፡ ሆኖም በመላው ዓለም እስከ ዛሬም ድረስ በሰላማዊ ትግል አቀንቃኝነቱ ይጠቀሳል፡፡
ማርቲን ሉተር ኪንግ ትግሉን ሲያካሄድ ታዲያ የሚታገልለትን ሕዝብ እያከበረ፣ አንዳንዴም ‹‹የኔ የመብት ትግል ትክክለኛው መም ላይ ነውን?›› በሚል ራሱን እየገመገመም ነበር፡፡ ለአንዴም እንኳን ለግል ጥቅሙ ሲል “እታገልለታለሁ” ያለውን ሕዝብ ሲያዋርድ፣ ሲያስጠቃና ሲያሳጣ የታየበት ጊዜ የለም፡።
አንዴ እንደውም ‹‹ዘ ሞንት ጎመሬ አድቨርታይሰር›› የተባለ ጋዜጣ፤ ትግላቸውን በዘረኝነት ፈርጆ ሲያወጣ፣ ኪንግ እሁድ ከሰዓት ቤቱ ገብቶ፣ በመደርደሪያው ላይ ያሉትን መጻሕፍት መፈተሽ ያዘ፡፡ በተለይ ከሃይማኖት፣ ከፍልስፍናና ከሥነ ምግባር ጋር ተያያዥ የሆኑ መፃሕፍት አግኝቶ አነበበ:: በኋላም የኮንኮርዱ ፈላስፋና ደራሲ ሄኬ ዴቪድ ቶሮው ጋ ደረሰ:: ቶሮው እንዲህ ይላል፡- ‹‹ሰዎች መገዛት ያለባቸው በራሳቸው ህሊና ነው፤ ፍትሀዊ ያልሆኑ ሕጎችን መቃወም አለባቸው፡፡”
ኪንግ፤ ወደ ራሱ መለስ አለ፡፡ ነጮች ጥቁሮችን ከወንበራቸው አስነስተው መቀመጣቸው ግፍ ነው፣ ጥቁሮችም ነጮችም ሰው ናቸው። ከዚያ በኋላ ማርቲን ሉተር ኪንግ የነፃነት ጎዳናውን ተያያዘው፡፡ ታዲያ ኪንግ ከምንም በላይ ለሚታገልለት ሕዝብ ክብርም፣ ጆሮም ነበረው፡፡ እኔ ያልኩት ካልሆነ ሞቼ እገኛለሁ ብሎ ሕዝቡን ሌላ ቀለም አልቀባም፡፡
ይህንን ታሪክ ያነሳሁት ሰሞኑን ከጽንፈኛ ፖለቲከኞች የተነሱት የማላዘን ድምጾች ኮርኩረውኝ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ኪንግን እንደ ትግላቸው መሪና አርአያ እንደሚቆጥሩት የሚናገሩ፣ በእምነታቸውም እንደሱው የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ ነኝ የሚሉ አንድ ፖለቲከኛ፤ የሰሞኑን የኦሮሚያ ክልል ሕዝባዊ ሰልፍ ከሸቀጥና ጋር ለማያያዝ መሞከራቸው በእጅጉ አሳዝኖኛል፡፡
ለመሆኑ ሕዝብ የደገፈን የመሰለን ጊዜ እውነተኛ፣ ከእኛ የተለየ ሀሳብ የያዘ ጊዜ ደግሞ “ሙሰኛ” ሊባል ይገባል እንዴ? በየትኛው መመዘኛ?
ከዚህ ቀደም በተለይ በለውጡ፣ በኦሮሚያ ክልል የሚቀሰቀሱ ግጭቶችን እንደ ፈንጠዝያና እንደ ስልጣን መወጣጫ የሚያዩ ፖለቲከኞችን ሲታዘብ ቆይቶ፤ ግራና ቀኙን መዝኖ፣ ግጭቶች የሚያመጡትን ጣጣና የሚፈጥሩትን ጥፋት አጢኖ ‹‹የለውጥ መሪዎቹ ይሻሉናል፤ ደግሞም መሪያችንን አትስደቡብን ‹ኦሮሞ መሪውን ያከብራል እንጂ አይሳደብምም!›› በማለቱ ሊከበር ሊወደስ አይገባም ነበር?! ጭራሽ ይህንን ትልቅ ሕዝብ፣ ይህንን የሰለጠነ ዴሞክራሲ ባለቤት ዝቅ አድርጎ በመመልከት ‹‹ሰልፉ የተደረገው ከመንግሥት በተሰጠ ገንዘብ ነው›› ብሎ በድፍረት መናገር ነውር አይደለምን... ሰልፉ ላይ የምናየው እነዚያ ባጌጡ ፈረሶች ተሰልፈው፣ ጥሩር ለብሰው፣ ጦርና ጋሻ የያዙ አባቶች፤ በገንዘብ የሚሰሩት ድራማ ነው ማለት ከባድ ድፍረት ነው:: ምነው! አድዋ ላይ በተደረገው ጦርነት ገንዘብ ተከፍሎት ሳይሆን ነፍሱን ከፍሎ የጦርነቱ እሳት ውስጥ የገባውን የሰላሌ/ኦሮሞ ፈረሰኛ እንዴት ረሱት?... የዚያ ጀግና ሕዝብ ደም ያለበት ትውልድ፤ ለእነርሱ ሥልጣን መሰላል አልሆንም ስላለ ብቻ ማራከስና ማጣጣል የታሪክን ገፆች መፋቅ ነው የሚሆነው፡፡
ለስልጣን ስግብግብነቱም ከሆነ፤ የኦሮሞ ሕዝብ በአባ ገዳ ስርዓት፣ በውድድር መሸነፍና ሽንፈትን መቀበልን እንዲያስተምር፣ ከእኔ በበለጠ እኒሁ ጽንፈኞች የሚያውቁት ይመስለኛል፡፡ እኔም ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ተ/አረጋይ ‹‹ፍልስምና›› በተሰኘ መጽሐፉ ውስጥ የዕጩ ዶክተር ተፈሪ ንጉሴን አነጋግሮ ያሰፈረውን መጥቀስ እችላለሁ፡፡ እንዲህ ይላል::
“አባ ገዳ ካልሆንኩ፣ ካልመረጣችሁኝ የሚል ማስፈራራትም ሆነ ካልተመረጠ አሻፈረኝ ማለት በዚህ ሥርዓት ውስጥ ታይቶ አያውቅም። ካልተመረጡ የእሱ ‹‹ሂርያ›› (የዕድሜ አቻዎቹ) ሥልጣን ላይ ስላሉ፣ እሱም ሥልጣን ላይ እንዳለ አድርጎ ነው የሚሰማው:: የእሱ ጊዜ ‹‹የእሱ ገዳ›› ይባላል::  የዚያ ገዳ አባላት በሙሉ በአንድ ፓርቲ ውስጥ ስለሆኑ የእኔነትም የአንድነትም ስሜት አላቸው፡፡ ስለዚህ ተወዳድሮ የተሸነፈውም ሆነ ያልተወዳደሩት፣ የእኔ ገዳ ጥሩ እንዲሆን ትላልቅ እቅዶችን ወደ ማቀድና ወደ ማስፈጸም ነው የሚሄዱት::” እንግዲህ ልብ በሉ፡፡ ይህን ሥርዓት የተከለው የኦሮሞ ሕዝብ ነው፡፡ አሁን ደግሞ “ገንዘብ ተከፍሎት ሰልፍ ወጥቷል” የተባለውም ይኸው የኦሮሞ ሕዝብ ነው:: እንዴት አንድ ለኦሮሞ ሕዝብ እኩልነትና ፍትህ እታገላለሁ የሚል ፖለቲከኛ፤ ሕዝቡን እንዲህ ቁልቁል በንቀት ይመለከታል?
እነዚህን ሰዎች ከእስር ለማስፈታት ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወገኖቹ ጋር እንዲያውም ግንባር ቀደም ሆኖ በስናይፐር ግንባር ግንባሩን የተመታውና የሞተው ገንዘብ ተከፍሎት ነው እንዴ? የአምቦ ሕዝብ ነው ወይስ የሰላሌ ያለእምነቱና ፍላጐቱ በገንዘብ ሰልፍ የሚወጣው? ነገሩን ስናጋንነው በዘመነ ወያኔ፣ ድንጋይና ዱላ ይዞ ያንን ግዙፍ ሰራዊት ወደ ኋላ የመለሰው ገንዘብ ተከፍሎት ነው? በእውነቱ ከባድ ድፍረት ነው፡፡ እንደውም ጽንፈኞች ንገሩን ካሉ፤ ትናንት ወንደሞቻቸውን በጥይት የደፉ፣ እናትን በልጇ ሬሳ ላይ አስቀምጠው የገደሉ ሰዎችን፤ እንደ ፍትህ ተከራካሪ ቆጥሮ የፈሰሰውን የሕዝብ ደም ረግጦ፣ መቀሌ ስብሰባ ላይ መታደም፤ ይበልጥ ለክፍያ ይቀርባል ብዬ አስባለሁ፡፡ በእንዲህ ያለው ጉዳይ ከሕዝቡ ይልቅ መጠርጠር ያለባቸው ራሳቸው የሥልጣን ጥመኛ የሆኑት ፖለቲከኞች ናቸው፡፡ ሕዝብን ከሕዝብ አጋጭቶ፣ በሕዝብ እንባ የተድላ ታንኳ ላይ ለመቀመጥ ነገሮችን ማመቻቸት ያሳፍራል እንጂ አያኮራም፡፡
የማርቲን ሉተር ኪንግ አድናቂ ወደ መምሰል የሚጠጉት አቶ በቀለ ገርባም ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት አስተያየት፤ የኦሮሞን ሕዝብ “ገንዘብ ተከፍሎት ነው የወጣው” ሲሉ ዓይናቸውን በጨው አጥበው መቅረባቸው ያስተዛዝባል:: ስንቱ ሰው ይሆን የተከፈለው? ለይተው ስለተወሰኑ ካድሬዎች ቢነግሩን፣ ወያኔ ያስተማራቸው ትምህርት በልባቸው የሰረፀ ደካሞች ናቸው ብለን እናልፈው ነበር፡፡… ድፍን የጂማን ሕዝብ፣ ድፍን ሰላሌን፣ ድፍን ሐረርጌን፣ ድፍን ኦሮሚያን… በገንዘብ እንደሚነዳ መቁጠር ግን እንታገልለታለን ያሉትን ሕዝብ ሥነ ልቦናና ማንነት ያለማወቅ ይመስለኛል፡፡ የእነ ጀነራል ታደሰ ብሩ፣ የእነ አቢቹ፣ የእነ ደጃዝማች ባልቻ አባነፍሶ፣ የእነ ሀብተ ጊዮርጊስ ዲንግዴ… ሀገር እኮ ነው፡፡ እነዚህ ፖለቲከኞች አንድም ተሳስተዋል? አሊያም ዞሮባቸዋል… ማለት ነው?! አቶ በቀለ ገርባ ‹‹ወንጌል አውቃለሁ›› የሚሉ እነ ቄስ ጊዳዳ፣ እነ ሮሮ ዋጣ፣ የበቀሉበት አገር በቅለው ሳለ፣ የዚህ ዓይነት ድፍረት መድፈራቸው ለኔ ግራ ነው የሆነብኝ፡፡ መቼም ሰይጣን አሳሳተኝ አይሉ ነገር!.. ለነገሩ ይሁዳም ሰይጣን ገብቶበት ነው ተብሏል፡፡ ግን ከበደል አያነፃምና ራሳቸውን ማረምና ሕዝብ ላይ የሚቀቡትን ጭቃ ወደ ኋላ መመለስ ያለባቸው ይመስለኛል፡፡
ገጣሚ አበረ አያሌው እንዲል፡-
ዘመኑ ድፍርስ ነው - ምንም የማይጠራ
ለጠያቂው ሕመም - ለመላሹ ግራ፡፡
ስምህን የጠራ ‹‹የቤትህ ጠበቃ›› - ሽሮ ነው ቀለቡ
‹‹የከዳህ ይሁዳ›› - ለድሆች ያለቅሳል -
ገራገር ነው ልቡ
ይህንን ግልብጥብጥ - ትመልስለት ዘንድ
አንተን ያያል ሕዝቡ!
በእኔ እምነት ሕዝቡ ላይ የዚህ ዓይነት የድፍረት ቃል የሚናገሩ ሰዎች፤ ሕዝቡን ክደውታል፤ ህዝቡን ንቀውታል፤ ወይም ደግሞ ሸጠውታል፡፡ … ይሁዳም ጌታው ላይ ያደረገው ይህንኑ ነው?
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አወዛጋቢ እየሆኑ የመጡትና ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያዊነታቸው አይደራደሩም የሚባሉት ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና፤ ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ ፈተናዎች፡ የሚጋጩ ሕልሞች…›› በሚል ርእስ ባሳተሙት መጽሐፍ ላይ የተጠቀሱት ሀሳብ ከዛሬው ጽሑፌ ጋር የሚስማማ ስለመሰለኝ ጥቂት እዋሳለሁ ምናልባትም ሁላችንንም የሚጠቅመን ሀሳብ ሊሆን ይችላል፡፡
‹‹የቡዳ ፖለቲካችንን ከሁሉም በላይ አስቸጋሪ የሚያደርገው ሁሌም ጥፋተኞች እነዚያ ናቸው ብለን ስለምንደርቅ ነው፡። እዚህ ላይ ፈረንጆች የሚበልጡን በሁለት መሰረታዊ ጉዳዮች ነው፡፡ አንደኛው፤ ጥይት መቀበልን እንደ ሞት አያዩትም፡፡ ሁለተኛው፤ ሥልጣንን የሙጡኝ በማለት አጥፍቶ መጥፋትን በባህላቸው አስወግደዋል ወይም የኋላ ቀሮች አስተሳሰብ አድርገውታል፡፡ ቢያንስ ከሂትለር ወዲህ የአብዛኞቹ ጉዞ በዚህ አቅጣጫ ነው…”
ይህ የፕሮፌሰሩ መጽሐፍ፤ የኦሮሞ ጽንፈኞችን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም የሚመለከት ነው፡፡ እኛ አገር በአደባባይ ቅጥፈት ማውራት፣ ሌሎችን ማዋረድ… እንደ ጀግንነትም ይታያል:: አንደበትን ሳይገቱ አፍ እንዳመጣ መናገር የተለመደ ሆኗል፡፡ ሁልጊዜ ወደ ሌሎች መጠቆም እንጂ ወደራሱ መመልከት የሚታሰብ አይደለም፡፡ ስለዚህም አሁን እንደምንሰማው፣ አንዳች አማራጭ የፖሊሲ ሀሳብ የሌለው ፖለቲከኛ ሁሉ፤ የዶክተር ዐቢይን ሕፀፅ በመልቀም ላይ ሲባትል እናየዋለን፡፡ አዲስ ሀሳብና ሥራ ከመስራት ይልቅ በዚህ ሁሉ ጣጣ ውስጥ በሥራ የተጠመዱትን የጠ/ሚኒስትሩን እንከኖች ለመንቀስ አበሳቸውን ይበላሉ፡፡
ምናልባትም ግርግሩን አጡዘው፣ በግርግር የሽግግር መንግሥት ተመስርቶ፣ የሆነች ወንበር ላይ ለመንጠልጠል፣ አፋቸውን በስድብ ሲያሟሹ እያየን ነው፡፡ እውነት ለመናገር፤ አሁን በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ዋነኛ ተዋናይ ነን የሚሉ ሰዎች፤ በአብዛኛው የአእምሮ ጤንነታቸው ሁሉ የሚያጠራጥር ይመስለኛል፡፡ ባለፈው ሥርዓት በካድሬ የተደበደቡ፣ የታሰሩና ከሩቁም ቢሆን በፍርሃት እየራዱ የኖሩ በመሆናቸው አንዳች መቅበዝበዝ ይታይባቸዋል፡። ሌሎቹ ደግሞ በቀደመው የግፍ ዘመን ስምና ቢሮ ይዘው፣ ውጭ ሀገር ለሚሄዱ ሰዎች የፓርቲያቸውን መታወቂያ ሲሸጡ እንደከረሙ ይታወቃል፡፡
ብዙዎቹም ግርግሩንና መለያየቱን እንደ መልካም አጋጣሚ ለመጠቀም ቀዳዳዎች ሲያጨልቁ ታዝበናል፡፡ በዚህ ሁሉ መሀል ግን በየጎጣቸውና በየጥጋጥጋቸው ከመቆም ይልቅ “የሚያዋጣው የሀገር አንድነትና ሰላም ነው በሚል በያቅጣጫው የሚሰነዘርባቸውን ያልተገባ ዘለፋና የስድብ ናዳ ታግሰው፣ አገር ለማዳን ዋጋ የሚከፍሉ የአገር ልጆች መኖራቸው የሚያኮራና የሚያፅናና ጉዳይ ነው፡፡
አሁን ያለው መንግሥት የቀድሞውንና ህዝቡ አናት ላይ ተፈናጥጠው የነበሩ ጨካኞችን ካስወገደ በኋላ ህዝብን የማድመጥ፣ የመቅረብና ችግሮችን በውይይት የመፍታት ዝንባሌና ዝግጁነት እያሳየ ነው፡፡ በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አካባቢ የሚስተዋለው ቅንነትና ለዜጐች ያለው ከበሬታ ይደነቃል፡፡ እንደኔ ሕዝብን እንደ ሕዝብ የሚያከብር መሪ ለማየት ከፍተኛ ጉጉት ለነበረው ኢትዮጵያዊ፤ ዶ/ር ዐቢይ ለዜጐች የሚሰጡት አክብሮት ያስተደስተዋል፡፡
ከዚህ ቀደም የነበሩትመ ሪዎች ሀገር መምራትን ከኮስታራ ግንባር፣ ከቁጣና ከዛቻ ጋር አያይዘው ያሸማቀቁትን ህዝብ ፈገግታ ማጥገብ፣ አቅፎ መሣም፣ ከታሠረበት ማስፈታት፣ በስደት ባለበት ሀገር ሄዶ በአይዞህ” ማለት የሚነዝር ወገናዊ ስሜት የሚፈጥር ይመስለኛል፡፡
ይሁንና ጉድለቶተ የሉበትም አንልም:: በምንም መመዘኛ ግን የሀገርን አንድነት ለመጠበቅ ባለው ቁርጠኝነት የተመረጠ ነው፡፡ ሀገር እንደሀገር አንድ ሆና እንድትቀጥል እንጂ በየጐጡ የተበታተነ በጠላትነትየ ሚተያይ ህዝብ እንዳይኖር እየሠራ ነው፡፡
በሁላችንም ውስጥ ያለች አንድ ጥያቄ ግን አለኝ፡፡ ከረዥም ዓመታት በፊት ቪድፎርስት ከተባለው ጋዜጠኛ ጋር ቃለ ምልልስ የማርቲን ሉተር ኪንግ የቅርብ ወዳጅ የነበረው ክላረክ መንግስትን አስመልክቶ በተናገረው ነገር እጨርሳለሁ እንዲህ Government has to concede the diginity of its citizens If government can’t protect its citizens with fairness, we ‘re in real trouble, aren’t we?

Read 11526 times