Sunday, 01 March 2020 00:00

የማይነጥፈው ኢትዮጵያዊነት!

Written by  ሔኖክ ገለታው
Rate this item
(3 votes)

ወቅቱ የሽግግር መንግሥት ነበር፡፡ ከዚህም ከዚያም የቆሙ የጎሳ ድርጅቶች ሐገርን በቅርጫ ለመከፋፈል ሙዳ ሥጋ እንዳየ አሞራ ያሶመሶሙበት፡፡  የወሬው መቀሰቻ ሁሉ የሐገሪቱ ህልውና በመበታተን አደጋ አካፋይ መስመር ላይ ስለመቆሙ ሆኗል፡፡ ለዘመናት የኢትዮጵያ አካል ሆኖ የኖረ አንድ ክፍልም በይፋ መነጠሉ እውን መሆኑ ተቃርቧል፡፡  የሒደቱን ፈለግ ተከትለው ‹‹ነጻ ሐገር እንመሰርታለን!›› በሚል ተምኔት ውስጥ እንደ ዝሆን ራሳቸውን ያገዘፉ ድርጅቶችም የ”ጨቋኝ ተጨቋኝ” ትርክቱን በሰፊው ማስጮሁን ተያይዘውታል፡፡ ጎጠኝነት ጅማታቸው ድረስ ዘልቆ የሚያንገበግባቸው ኃይሎች ጊዜ ቀን ያወጣላቸው ይመስላል፡፡ ያሻቸውን ተናጋሪ፣ የፈቀዱትን አሳሪ ከሆኑ ሰንብተዋል:: ኢትዮጵያ በሥም፤ ኢትዮጵያዊነት ደግሞ በግብር አልቦ ሆነዋል፡፡ በዚህ አስፈሪና አሳዛኝ የታሪክ አጋጣሚ መሃል ግን አንድ ድርጅት በጊዜው “አሸናፊ” የመሰለውን የማርክሲስት ተረክ በጥሶ  ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን የማዳን ተልዕኮውን በአደባባይ ይዞ ተከሰተ፡፡ ‹‹የሀገራችን በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ መገኘት፣ የጎሳ ፖለቲካ አደገኛነት፣ የሰከነ ፖለቲካ አመራር አስፈላጊነትና ሌሎችም…›› ዓላማዎችን  በማንገብ በበርካታ ስመጥር አባላት የተዋቀረ ‹‹የኢትዮጵያዊነት ድርጅት›› የተባለ ሐገር በቀል የሲቪክ ማኅበር መቋቋሙ በይፋ ተበሰረ፡፡
ይህ ድርጅት መጋቢት 19 ቀን 1985 ዓ.ም ዓላማውን ለህዝብ ሲያስተዋውቅ ምንም ያህል የፖለቲካው አየር ከመንደራቸው በላይ ማሰብ በተሳናቸው ጽንፈኛ ኃይሎች የነጋ ጠባ “ጨቋኝ ተጨቋኝ ፤ ልነጠል ልገንጠል” ልፈፋ ቢከረፋም ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ ግን ላይለያይ የተሳሰረ፤ ላይነጣጠል የተጋመደ በመሆኑ ‹‹ኢትዮጵያዊነት›› የዘመኑ ደዌ ፍቱን ፈውስ መሆኑን ለአፍታም ባለመጠራጠር ነበር፡፡ ይህ የኢትዮጵያዊነት ድርጅት ለታሪክ ማስረጃነት ትውልድ መለስ ብሎ ይመረምረው ዘንድ የወቅቱን መንፈስና የጊዜውን ኃይላት ኢትዮጵያ ጠል ቄሳራዊ ዓላማ ‹‹ኢትዮጵያዊነት›› በሚል ርዕስ በወራት አሳትሞ በሚያሰራጨው  የንድፈ ሃሳብ መጽሔቱ አስፍሮልን አልፏል:: ያ ጊዜ ምን ያህል የኢትዮጵያን ሕልው ሆኖ መቆየት በአደጋ ንፍቀ ክበብ ውስጥ ለማቆየት የሚጥሩ ወገኖች ላይ ታች ይሉ እንደነበር ከተከታዩ ቅንጭብ ሓሳብ ስንረዳ በአናቱም ዛሬ ከቆምንበት ሌላኛው የታሪክ ፈተና ጋር ያለውን ምስስሎሽ አስተውለን ትጥቃችንን እንድናጠባብቅ ገፊ ምክንያት ይሆነናል፡፡
‹‹ዛሬ በኢትዮጵያ የመገንጠልን ጥያቄ ሕገ መንግሥቱ ውስጥ ለማስገባት የሚያቀነቅኑ ግለሰቦችም ሆኑ ድርጅቶች የአገሪቱን የወደፊት ሕልውና በመመልከት ከእሳት ጋር እንደሚጫወቱ ቢረዱት መልካም ይመስለናል፤ በውይይት ደረጃ ብቻ ሳይሆን በድርጊት የአንድ ሉዓላዊ ሐገር ክፍል ለመገንጠል መሞከር፣ ማነሳሳት፣ ማደፋፈር፣ … በከፍተኛ ወንጀል ሊያስጠይቅ ይችላል…››  ይህ ሃሳብ ውስብስብነት የለውም፡፡ በ”እስከ መገንጠል›› ስሌት የማንነት ፖለቲካ ላይ ተቸንክረው በዚሁ አፍራሽ ቀመር የሰፉት የዛሬው ሕገ መንግሥት ሃያ ዓመታትን ተሻግሮ ሀገርንም ሆነ ሕዝብን ከመለያየት አደጋ መታደግ ተስኖት (በፕሮፌሰር መስፍን አማርኛ የወጣበትን ቀለምና ወረቀት እንኳ መመለስ አቅቶት) ኢትዮጵያዊነት ዳግም እውነትም መንገድም መሆኑ ላይ ሁለቴ ማሰብ ሳያስፈልገን እንድንረዳ አስችሎናል:: ዛሬም ግን አዙሪቱ ተመልሷል፡፡ የመደብ ትግሉ ቀበኛ ካርል ማርክስ ‹‹History repeats itself; first as tragedy, second as farce›› እንዳለው ታሪክ ራሱን መድገሙም ሆነ ኢትዮጵያ ትናንት ያደሟት የታሪክ ዲቃሎች መልሰው የመብቀላቸውን እውነታ ‹‹ቧልት›› አድርጎ ማለፍ የሚጠይቅበት ትክክለኛው ጊዜ ሆኗል፡፡ ለዚህ ደግሞ ዘመኑም ሆነ ጊዜው የሚጠይቀውን ‹‹ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት›› መነሻም መድረሻም ማድረግ ምርጫ የማይኖረው ጉዳይ ይሆናል፡፡
ኢትዮጵያዊ ‹‹ብሔርተኝነት››?
በአማርኛ መድብለ ቃል ውስጥ ለትርጉም አሻሚና አወዛጋቢ ከሆኑ ቃላት መካከል ‹‹ብሔር፣ ብሔርተኝነትና ብሔራዊ›› የሚሉትን በግሌ መጥቀስ እችላለሁ። ቃላት በዘመን ሂደት ውስጥ የትርጉም ስፋትና ጥበት ሊኖራቸው እንደሚችል የዘርፉ ምሁራን ቢናገሩም ‹‹ብሔር›› የሚለው ቃልን ያህል ፈጣን በሆነ ሁኔታ የአንድምታ ልውጫ (Shift) ያመጣ አለ ብዬ አልገምትም፡፡ የዚህ ጥሬ ቃል ትርጓሜ ወደ “አንድ የራሴ ቋንቋ፣ ባህል፣ ሥነ ልቦናዊ አንድነት አለኝ” ብሎ የሚያስብ ማኅበረሰብ መጠርያነት መጥበቡ ‹‹ብሔራዊ›› የሚለውን ውልድ ሥም ሳይቀር በጎሰኝነትና ሀገራዊ ስያሜ የሽሚያ ቅርቃር ውስጥ እንዲገባ ምክንያት እንደሆነው አሁን አሁን መታዘብ ይቻላል፡፡ ለአብነት እንኳን ‹‹ብሔራዊ ስሜት›› የሚለው ሀረግ ለሁለት የፖለቲካ ወገን ክፍት የሆነ ትርጉም እንደያዘ መቀጠሉን ማጤን ይቻላል፡፡ በግሌ ግን ‹‹ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት›› የሚለውን ጽንሰ ሃሳብ ለገዘፈ ስብዕናም ይሁን ሕብረ ብሔራዊ አስተሳሰብ ቅቡል ሳደርገው ‹‹ብሔር›› የሚለውን ቃል ‹‹ሐገር›. ከሚለው አንድምታ መነሻ በማድረግ ነው፡፡ አፈወርቅ ታረቀኝ ‹‹አንጋረ ምሳሌ ግዕዝ›. በተባለው መጽሓፋቸው ‹‹ወለእመ ሆርከ ብሔረ ባዕድ ኩን ከማሆሙ (የማታውቅ ሐገር ብትሄድ እንደነሱ ሁን)›› በማለት ብሔር ሥርወ መነሻው ‹‹ሐገር›› የሚለውን ቃል ለመወከል ጥቅም ላይ እንደዋለ ጽፈዋል፡፡ ታላቁ ሊቅ ተስፋ ገብረሥላሴም ‹‹ዘብሔረ ቡልጋ›› የተሰኘች መጠርያቸውን መጽሔተ አዕምሮ በተባለ መጽሐፋቸው ደግሞ ‹‹ዘሀገረ ቡልጋ›› በማለት ብሔር ማለት ሐገር ፤ ሀገር ማለትም ብሔር መሆኑን አስምረውልን አልፈዋል፡፡
አንዳንዶች ‹‹ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት›› የሚለውን ሐረግ ላዩን እያዩ ከኦሮሞ ወይም ከአማራ አልያም ከትግራዋይ ብሔርተኝነት በመጠኑ ሰፋ ይል እንደሆነ እንጂ በድንበር የተከተረ፤ ከሱዳንና ኬንያ ብሄርተኝነት ራሱን የነጠለ በመሆኑ “ለሰውነት ውሃልክ”  የቀረበ ማንነት መሆኑ ላይ በገደምዳሜ ትችት ይወረውሩበታል፡፡ ላይ ላዩን ሲታይ ትችቱ እውነት ቢመስልም ጽንሰሃሳቡን ለመረዳት ግን ‹‹ብሔር እና ብሔርተኝነት›› የሚሉትን ቃላት ሀገር ከምትባለው አቃፊ ዋርካ ጋር አሰናስሎ ጥቅም ላይ ማዋልን ይሻል:: ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት ሌላ ሳይሆን ሀገርና ሀገራዊነትን ታሳቢ ያደረገ በሀገራችን ውስጥ የቋንቋና የባህል ልይይቶችን ያለ አድሎ ማቀፍ የሚችል ሰፊ ጫንቃ ያለው ማንነት መሆኑን መገንዘብ አስፈላጊ ነው፡፡ እናም ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት ሰማንያውንም የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ሰብሳቢ በመሆኑ ሠውን ሁሉ ያለ አንዳች ገደብና ልዩነት በእኩል የመውደድና የማስተናገድ መንደርደሪያ ዕሳቤ ነው፡፡ ይህ አቃፊ ማንነት ትከሻው እየደነደነ ግለሰብን በሰውነቱ ብቻ ለመቀበል ከየትኛውም የጎሳ አደረጃጀት  ተመራጭ መሆኑ የተሻለና ገዢ የፖለቲካ ማታገያም ያደርገዋል።
ኢትዮጵያዊነት እንደ ጨፍላቂነት?   
ሩሲያዊው አሳሽ አሌክሳንደር ቡላቶቪች ‹‹ከአጼ ምኒልክ ሠራዊት ጋር›› በተሰኘው የ1892 ዓ.ም መጽሓፉ በወቅቱ የነበረው የኢትዮጵያን ግዛት ዳግም የመመለስ (Reunification) ዘመቻን አብሮ በመሳተፍ የደረሰበት ድምዳሜ ኢትዮጵያዊ ማንነት ለሳላድ ቦውል ኀልዮት (Salad Bowl theory) የቀረበ፣ ከሁሉም የተውጣጣ የጋራ ማንነት የመፍጠር እንጂ አንዱን በአንዱ የመጨፍለቅ አለመሆኑን፤ የኢትዮጵያዊያን(ሀበሾች) ባህልም እንዳልሆነ በሚከተለው አጭር አንቀጽ አረጋግጧል፡፡
‹‹ኢትዮጵያዊን ቀስ በቀስ የተቀበሏቸው የአውሮፓ ሥልጣኔዎች አልጎዷቸውም:: ኢትዮጵያ ከነዚህ ሥልጣኔዎች ጠቃሚ ነገሮችን ወርሳ በበኩሏ የጎረቤት ጎሳዎችን ድል እያደረገችና ወደ ግዛቷም እያዋሀደች የራሷን ባህል በመሃላቸው ስታስፋፋ አንድም ጎሳ ከምድረ ገጽ ያላጠፋች ከመሆኗም ሌላ ሁሉም ግላዊ ባህሪያቸውን ጠብቀው እንዲቆዩ ዕድል ሰጥታለች›› ይህ የቦላቶቪች ድምዳሜ መሰረቱን ያደረገው በወቅቱ  አውሮፓውያን በምን ያህል ዕቅድና ትግበራ የአፍሪካውያንን ማንነትና ባህል በማጥፋት ላይ የተመሰረተ ቅኝ የመመስረት ፍላጎት እንደነበራቸው የአሜሪካና የህንዶች ጨርሶ የመጥፋት አመክንዮን እንደ አባሪ በማንሳት ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን አንዳችን በአንዳችን ውስጥ ተሳስረን የምንኖር፤ ባህላችን የተቀየጠ፤ የኑሮ ይትበሃላችን የተዛነቀ መሆኑ የጋራ ሀገር ይዞ ለመቀጠል ከየትኛውም ሐገር ያላነሰ በጎ ዕድል የተቸርን ህዝቦች ስለመሆናችንም ቡላቶቪች ይጠቅሳል፡፡ ለኢትዮጵያውያን ቋንቋ ዘለል የሆነ የወል ማንነትን ማዳበርና በዚያ ጠለልም  ሥር መኖርም እንግዳ አለመሆኑን የሚጠቅሱ ሌሎች ምሁራንም አልጠፉም፡፡
ዶ/ር ሀሰን አዳል መሐመድ በ2009 ዓ.ም ባሳተሙት ‹‹ቋንቋ እና ብሔርተኝነት››  በተባለው መጽሓፋቸው ደጋግመው የሚያነሱትም ይህንኑ ሀቅ ነው፡፡ እንደርሳቸው አመለካከት “ወሎዬነት”  በቋንቋ ልዩነት ያልተገደበ የአምስት ማኅበረሰቦች የወል ማንነት ነው፡፡ አማርኛ፣ አገውኛ፣ አሮምኛ፣ አፋርኛና ራይኛ ተናጋሪ የወሎ ሕዝብ ልሣነ ብዙሓነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ራሱን እንደ ወሎዬ የሚገልጽና የሚኮራ መሆኑ ከቋንቋና ከባህል ልዩነት ከፍ ያለ የጋራ ሠፊ ማንነትን ማዳብር ፤ በኢትዮጵያ ልማድ ውስጥ ለጨፍላቂነት የሚጠጋ ዳራዊ ትርጉም እንደሌለው አስረጂ አድርገው ይናገራሉ፡፡ የኢትጵያዊ ብሔርተኝነት የከፍታው ልኬትም በቋንቋ ልዩነት አጥር አበጅቶ ከተወሰነ (Specific) ማኅበረሰብ ጥቅም የተሻገረ ለሁለም ዜጋ  በእኩል የመታገል ፣ የኢትዮጵያ የሆነ ሁሉ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ይዞታ የሚሆንበትን አግባብ የሚያመቻች ርዕይ ነው፡፡ ‹‹ቀልቀሎ ስልቻ፤ ስልቻ ቀልቀሎ›› በማለት የጋራ ማንነትን በምሳሌያዊ አነጋገር እያዛነቁ  መገንባትን ገንዘቡ ባደረገ ሕዝብ ኢትዮጵያዊነት የወል ማንነት እንጂ ማንም በማን የመጨፍለቅያ (Assimilation) መድረክ አልነበረም፤ አይኖርምም፡፡
ኢትዮጵያ’ኒዝም’ እንደ ርዕዮት
በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ በዛሬይቱ ደቡብ አፍሪካ ጥቁሮች የተጫነባቸውን የባዕድ ባህልና አስተሳሰብ ለማራገፍ፣ ብሎም አፍሪካዊ ሥነ ልቦናን፣ ለማዳበር ያግዝ ዘንድ መሃሉ ኃማኖታዊ ይዘት የነበረው ዳሩ ግን አፍሪካን በአዲስ የአስተሳሰብና የለውጥ ፍኖት መምራት ያስችላል የተባለ የ‹‹ኢትዮጵያኒዝም›› እንቅስቃሴ ተጀመረ:: ቤንት ሱድክለር የተባለ አጥኚ ‹‹Bantu prophets in south Africa›› በሚለው መጽሓፉ የሚያወሳን ይህ የኢትዮጵያኒዝም አዲስ ፍልስፍና ነጻ አፍሪካዊ ቤተክርስቲያናት መመስረትን ታክኮ አፍሪካንና አፍሪካውያንን ነጻ ለማውጣት ዕሳቤ (Assumption) ያለው ሆኖ በርዕይነት መቀረጹን ነው:: የወቅቱ የዌስሊያን ማቶዲስት ቤተ ክርስቲያን ተጠሪ የነበረው ማንጌና ሞኬኔ ስለ ኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አስፈላጊነት በሚያሰማው ስብከቱ ዘወትር የሚጠቀማት ‹‹አፍሪካ ለአፍሪካውያን›› የተሰኘች መፈክሩ የኋላ ኋላ ለተመሰረተው Universal Negro Improvement Association And African Communities League (UNIA – ACL) አዕማድ ሆኖ ነበር:: የኢትዮጵያኒዝም የትግል ኀልዮት ከአፍሪካ ሀገራት የነጻነት ፍኖት መሆንነት አልፎ የራስ ተፈሪያን ንቅናቄ መሰረትም የነበረ ሲሆን ዊሊያም ዴቪድ ስፔንሰር ‹‹DREAD JESUS›› በሚለው መጽሓፉ ያሰፈረውና ኋላ ላይም ማርክስ ጋርቬይ በስፋት ያሳወቀው ‹‹ፈጣሪ ጥቁር ነው››  የሚለው ሥነ መለኮታዊ ሐሳብም መነሻው የኢትዮጵያኒዝም አስተሳሰብ መሆኑን በርካታ ምሁራን አምነው ጽፈውበታል፡፡ ኢትዮጵያኒዝም የችግሮች መፍትሔ ማግኛ የተዋጣለት ሥነ ዘዴ መሆኑን በርካታ አፍሪካውያንና የነጻነትን ዋጋ የተረዱ ሕዝቦች ሁሉ የሚስማሙበት ሲሆን አይደለም ኢትዮጵያችንን ሰፊዋ አህጉራችንን ማሻገር የቻለ ገዢ አስተሳሰብ መሆኑ ዛሬም የሙጥኝ እንለው ዘንድ መግፍዔ ይሆነናል፡፡
ዛሬም ኢትዮጵያዊነት!  
በመደባዊና ብሔራዊ ጭቆና ትርክት መሰረቱን ከአርባ ዓመት በፊት የጣለው ቆሞ ቀሩ የሀገራችን የፖለቲካ ትግል ማንነትና ቋንቋ ላይ ተቸንክሮ የማኅበረሰቡን የዳቦ ጥያቄ ባላየ ማለፉን ቀጥሎበታል፡፡ የድህነትና የሥራ አጥነት ጥያቄዎች የሀገሩን ጣርያ በጥርቀው ቢወጡም ለችግሮቹ ሳይንሳዊ ዘዴን የተከተለ የኢኮኖሚ ፖሊሲን በአማራጭነት ለማስቀመጥ የደፈረ ኃይል ብዙም አልተገኘም፡፡
ለትንሹም ለትልቁም የሀገሪቱ ጉዳይ የጎሳ ፖለቲካ ብቻ ሆኗል:: “ማንነት” ይሉት ፖለቲካ አዋጭ ሸቀጥ መሆኑ ዕለት ከዕለት ጨምሯል፡፡ ስለ ጋራ ቤቱ ካስማ መነቅነቅ ግድ የማይሰጠው ቁጥሩ ተበራክቷል፡፡ ‹‹የኔ እንጂ ያንተ ርስት አይደለም›› ሙግት የሰርክ ፖለቲካዊ ዲስኩር በመሆኑ በካራ እንጂ በክርክር የሚፈታ አይመስልም፡፡ በዚህ ሁሉ መሃል ግን እንደ ሰው  አከባብሮ የሚያኗኑረን አቃፊ ማንነት የቱ ነው? ለሚለው ጥያቄ ሁሉም መላምቱን በኪሱ ከመያዝ የዘለለ ለምሁራዊ ተዋስዖ (Intellectual Discourse) የቀረበ  መፍትሔን ያስቀመጠ አካል ብዙ አይደለም::
እኛ ግን እንላለን - ዛሬም ኢትዮጵያዊነት የጭንቁን ዘመን ለማሻገር ብርቱ ጉልበት አለው፡፡ ዛሬም ኢትዮጵያዊነት በመንደር ሥነልቦናችን ምክንያት ‘ርቆ በከፍታ የተሰቀለ ማንነት ሆኖብን እንጂ ቀና ብለን መንጠራራት ከጀመርን ደርሰን የምንደምቅበት ጌጣችን ነው፡፡
በመግቢያችን የጠቀስነው “የኢትዮጵያዊነት ድርጅት” ዋና ጸሐፊ የነበሩት አቶ ሳሙዔል ዓለማየሁ ‹‹ኢትዮጵያዊነት ሁላችንም በዘር፤ በባህልና በቋንቋ መወራረስ በሕብረትና በፍቅር ሰንሰለት አያይዞ እስካሁን ያቆየን ትልቅ ማንነት ነውና እርሱን መጠበቅ ህልው ሆኖ ለዘመናት የቆየን ማንነት የመታደግ አንድ እርምጃ ነው›› በማለት የዘመኑን (የጊዜውን) ፈተና ‹‹ለጋራ ህልውና፣ ለጋራ ጥቅም፣ ኢትዮጵያዊነትን የደግፉ!›› በሚል የጠራ መፈክር ተጋፍጠውታል፡፡ የኔታ መስፍን ወልደማርያም ደግሞ በ1986 ዓ.ም በጻፉት ‹‹ኢትዮጵያ ከየት ወዴት?›› መጽሓፋቸው ‹‹ኢትዮጵያዊነትን መካድ የራስን ማንነት መካድ ብቻ አይደለም ፤ አባቶችና እናቶችን; ቅድመ አያቶችን ከነቅርሳቸው መካድ ነው:: በእንደዚህ ዓይነቱ ክህደት ላይ የተመሰረተ ማንነት የት ይደርሳል? ከበሽታ በቀርስ ትርፉ ምን ይሆናል? ክህደት ራሱን የቻለ በሽታ ሲሆን ማስካድ ደግሞ የባሰ ነው፡፡ ክዶ ማስካድ ታምሜያሁ ታመሙ እንደማለት ነው፤ አስታማሚ እንኳን እንዳይገኝ የማድረጉ ጥረት የበሽታውን ምለዓትና ጽናት ያሳያል::›› በማለት የጊዜያቸውን ሳይሆን የጊዜያችንን መከራ እንደ ነቢይ (ወሊይ) ቀድመው አስቀምጠውልናል፡፡
እኔ ጨረስኩ ፤ ፕሮፌሰር ግን ይቀጥላሉ ‹‹ሆኖም የኢትዮጵያ ታሪክ ሊያስተምረን እንደሚችለው ኢትዮጵያዊነት እንደ ላስቲክ ነው፤ ሲስቡት ይሳባል፤ ሲለቁት ይሰበሰባል:: ማለት ይሳብና ይሳሳል እንጂ አይበጠስም::”
ትንሣዔ ለኢትዮጵያዊነት!
ቸር ያቆየን!

Read 1981 times