Saturday, 29 February 2020 11:15

ትናንሽ በጐ ተግባራት ለውጥ ያመጣሉ!

Written by  ሂሮዬ ሹማቡኩሮ
Rate this item
(5 votes)

      በቅርቡ በዚሁ ጋዜጣ ላይ ባቀረብኩት ጽሁፌ፤ በአዲስ አበባ፣ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የፈጸምኳቸውን በርካታ ትናንሽ በጐ ተግባራት ለእናንተ ለውድ አንባቢያን አካፍዬአችሁ ነበር፡፡ ብዙዎችም አንብበው አድናቆታቸውንና ምስጋናቸውን ስለገለጹልኝ በእጅጉ ተደምሜአለሁ፡፡ ተደምሜ ግን ቁጭ አላልኩም፡፡ በተከታዩ ወርም፣ ሌሎች በጎ ተግባራትን አከናውኛለሁ - ትናንሽ ቢሆኑም፡፡ በዛሬው ጽሁፌም እነዚህን ትናንሽ በጎ ተግባራት ላጋራችሁ ወደድኩ፡፡ እነሆ፡-
***
ባለፈው ጽሁፌ፤ እኔ ባለሁበት አካባቢ ስለሚኖሩ አራት ኤርትራውያን ስደተኛ ህጻናት ጉዳይ አውግቼአችሁ ነበር፡፡ ከ6-14 ዓመት ዕድሜ ላይ የሚገኙ ናቸው ህጻናቱ:: እንደምታስታውሱት፤ ለእነዚህ ህጻናት በሳምንት አንድ ቀን ከካፌ ምግብ እገዛላቸው ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ግን አራቱን የሂሳብ ስሌቶች አስተምራቸው ጀመር፡፡ ማስታወሻ ደብተርና እስክርቢቶም ገዛሁላቸው፡፡   
ልጆቹን የሂሳብ ስሌት ማስተማር የጀመርኩ ዕለት በፊታቸው ላይ ያነበብኩትን የፈገግታ ጸዳል መቼም አልረሳውም:: ከኤርትራ ከወጡ አንድ ዓመት ገደማ ያለፋቸው እነዚህ ህጻናት፤ትምህርት በእጅጉ እንደተጠሙ ያስታውቃሉ፡፡   
ልጆቹ ከእኔ ጋር የማያሳልፉት የትምህርት (ጥናት) ጊዜ በእጅጉ ያስደስታቸው ነበር:: እኔ ማስጠናት ከጀመርኩ በኋላ ሌሎች ሰዎችም እኔ ለህጻናቱ የምሰጣቸውን የቤት ሥራ እየተመለከቱ፣ ተጨማሪ መልመጃዎችን መስጠት መጀመራቸው ብርታት ሆኖኛል፡፡    
እነዚህ ህፃናት ወደ ባህር ማዶ ለመሻገር ቪዛ እየተጠባበቁ ነበር፡፡ እናታቸውን በኤርትራ ሳሉ አጥተዋል። በዚህም የተነሳ አባታቸው እሱ ወደሚኖሩበት አገር ሊወስዳቸው ይፈልግ ነበር፡፡ ከኤርትራ ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ ለጥቂት ወራት በስደተኞች ካምፕ ውስጥ ተቀምጠዋል፡፡ በእነዚህ ጊዜያትም አንድ ዘመዳቸውን በሞት ተነጥቀዋል፡፡ ለዚህ ነው እኔ ሳገኛቸው እንደ ህጻን ፊታቸው በፈገግታ የፈካ ያልነበረው፡፡  
የልጆቹ ዘመድ ፓስፖርት ማውጣትን የመሳሰሉ የጉዞ ሂደቶችን ለማስፈጸም ብዙ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡  እኔ በዚህ ረገድ ብዙም ላግዛቸው ባልችልም፤ ቢያንስ ከአባታቸው ጋር በኢሞ በመገናኘት፣ የህፃናቱን ፎቶዎች ልኬላቸዋለሁ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ፣ ወደ ኤምባሲና ኢምግሬሽን አብሬአቸው እሄድ ነበር፡፡
በአጠቃላይ የጉዞ ሂደቱ፣ በውጣ ውረድ የተሞላና እልህ አስጨራሽ ነበር:: በአባታቸውና በዘመዳቸው ያላሰለሰ ጥረት ግን እነዚህ ህጻናት የማታ ማታ፣ ለጉዞ የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ አሟልተው፣ ቪዛቸውን አገኙ፡፡ ቦሌ አየር ማረፊያ ልሸኛቸው በሄድኩበት ዕለት፣ አራቱም ህፃናት ስቅስቅስ ብለው አለቀሱ፡፡ ስደተኛ ህጻናቱ በአዲስ አበባ አስቸጋሪ ህይወት መጋፈጣቸው የማይታበል ሃቅ ቢሆንም፣ በቆይታቸው ጥሩ ጓደኞችና ጐረቤቶች አግኝተዋል ብዬ አምናለሁ፡፡ አባታቸው ዘንድ በመሄዳቸውም ደስተኛ ነኝ፤የተሻለ የትምህርት ዕድልና ህይወት ያገኛሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ትንሽም ብትሆን ለእነዚህ ልጆች ባደረኩላቸው በጎ ነገር ሁሌም መልካም ስሜት ይሰማኛል፡፡    
***
በትርፍ ጊዜዬ ቀላል የሂሳብ ስሌት ያስተማርኩት ለኤርትራውያኑ ህፃናት ብቻ አይደለም፤ ሌሎች ሰዎችንም  አስተምሬአለሁ፡፡ ከገጠር የመጣች ምንም ያልተማረች አንዲት የማውቃት ሴት ነበረች፡፡ ከ1-10  ቁጥሮችን በደንብ ካስጠናኋት በኋላ የአውቶብስ ቁጥሮችን ማንበብ በመቻሏ አመስግናለች፡፡ በኢትዮጵያ እንዲህ ዓይነቱ ቀላል የሂሳብ ስሌት ትምህርት በማንኛውም ሰው ሊሰጥ እንደሚችል አምናለሁ፡፡ በቀን ጥቂት ደቂቃዎችን ብቻ መመደብ ነው የሚያስፈልገው፡፡
በአሁኑ ወቅት የቤት ሠራተኛዬን፣ የሂሳብ ሥሌት እያስተማርኳት ነው፡፡ ባህር ማዶ ለሥራ ሄዳ ከአምስት ዓመት በላይ የኖረች ሲሆን ግሩም የሞባይል ስልክም አላት፡፡ ነገር ግን በሞባይል ስልኳ ውስጥ ያለውን የስሌት መተግበሪያ (ካልኩሌተር) መጠቀም አትችልም ነበር፡፡ እናም ማታ ማታ ከመተኛታችን በፊት የሂሳብ ስሌቶችን አስተምራት ጀመር፡፡ በአሁኑ ወቅት፣ ባለ 3 አሃዝ ቁጥሮችን (345+670) መደመር ሁሉ ችላለች፡፡ እሷም እንደነዚያ የኤርትራ ህፃናት፣ ቁጥር ሳስተምራት ፊቷ በፈገግታ  ይፈካል፡፡
***
ጐረቤቴ አንድ ምሽት ላይ አንዲት ታዳጊ ልጃገረድ፣ መንገድ ላይ ስታለቅስ አገኘቻት:: በቤት ሰራተኛነት የቀጠሯት ሰዎች ከቤት አባረዋት ነበር፡፡ እናም ለአንድ ሌሊት ጎረቤቴ ቤት አደረች፡፡ አዲስ አበባ ዘመድ የላትም፡፡ በነጋታው ጐረቤቴንና ልጅቷን አነጋገርኳቸው፡፡ የሚያደርጉት ጠፍቷቸው ግራ ተጋብተው ነበር፡፡ እኔም በጉዳዩ ውስጥ ገባሁበትና መፍትሄ ማፈላለግ ጀመርን፡፡
ታሪኩን ለማሳጠር ያህል፣ ልጅቷን ወዲያው ወደ ክሊኒክ ወስደን አስመረመርናት፤ ነፍሰ-ጡር መሆኗንም አረጋገጥን፡፡ በገጠር ሳለች የመጠጥ ሱሰኛ ከሆኑ አያቷ ጋር ነበር የምትኖረው፤ነገር ግን ገና በልጅነቷ ከቤት አባረሯት፡፡ በአንድ ቤተሰብ ውስጥ በሞግዚትነት ተቀጥራ ትሰራ ነበር፡፡ ከዚያም በደላላ አማካኝነት ወደ አዲስ አበባ መጣች፡፡ በግለሰብ ቤትም ተቀጠረች:: በወር መቶ ብር ብቻ ነበር የሚከፈላት፡፡ እዚያም ስትሰራ ተገድዳ ተደፈረች፡፡
በአንድ ጓደኛዬ እርዳታ የዚህች ልጅ ታሪክ እውነት መሆኑን አረጋገጥኩኝ፡፡ ሌላው ጓደኛዬ ደግሞ እንዲህ ያሉ ሴቶችን የሚደግፉ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን በማፈላለግ አገዘኝ፡፡ አንደኛው መያድ፤ የሚደግፋቸው 450 ሴቶችና ከ150 በላይ ወላጅ የሌላቸው ህፃናት እንዳሉት በመግለጽ፤ ለሷ ቦታ እንደሌለው አስታወቀን፡፡ ሌላኛው መያድ ደግሞ ከወረዳ ፖሊስ ወይም ከሴቶች ጉዳይ የድጋፍ ደብዳቤ ማምጣት እንዳለብን ነገረን፡፡
በዚሁ መሰረት፤ ልጅቷና ሌላኛው ኢትዮጵያዊ ጓደኛዬ ሆነን፣ ወደ ፖሊስ ጣቢያ አመራን፡፡ ታሪኩን ከሰሙ በኋላ ሳቁብን፡፡ ተገረምኩ፡፡ የአስገድዶ መደፈር ሰለባዎችን መርዳት የሚችሉት ድርጊቱ በተፈፀመ በ24 ሰዓት ውስጥ ብቻ መሆኑን ገለጹልን፡፡ በተለይ ሴት ፖሊሷ፣ ልጅቱን ያስተናገደችበትና ያሳየቻት ፊት ጥሩ አልነበረም፡፡ በሁኔታው አዘንኩ፡፡
በመቀጠል የሄድነው ወደ ሴቶች ጉዳይ ሲሆን እዚያም ጥያቄያችን ምላሽ አላገኘም:: ቋሚ አድራሻ ስለሌላት ደብዳቤ መፃፍ እንደማይችሉ ነገሩን፡፡ ሁሉም የቢሮው ሰራተኞች በሥራ የተጠመዱ አልነበሩም፤ ነገር ግን አንዲት ገጽ ደብዳቤ ለመጻፍ የተለያዩ ሰበቦችን መደርደራቸው በጣም አስገረመኝ፡፡  
በሁኔታው የተሰላቸሁ ቢሆንም ተስፋ ቆርጬ ከቢሮአቸው አልወጣሁም፡፡ ዝም ብዬ ተቀምጬ ነበር፡፡ ምሳ ሰዓት ሲቃረብና ሌሎች ሠራተኞች ሲወጡ፣ አንድ የቢሮው ወጣት ሰራተኛ፣ ደብዳቤውን እንደሚጽፍልን ቃል ገባልን፡፡ ቢሮአቸው የሷ ዓይነት በርካታ ጉዳዮችን እየተቀበለ እንደሚያስተናግድም ወጣቱ ገለፀልን፡፡
ሌሎቹ ሰራተኞች ሊረዱን ያልፈለጉት ክፉ ሰዎች ሆነው አይመስለኝም፡፡ ለቤተሰቦቻቸውና ለጓደኞቻቸው ደግ ልብ እንደሚኖራቸው አምናለሁ፤ ለሥራ ቦታ ሲሆን ያደነድኑታል እንጂ፡፡ ይሄኛው ወጣት ግን አያቱ ሁልጊዜ ሰዎችን እንዲረዳ ይመክሩት ነበር፤ ስለዚህም ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ሌሎችን ከመርዳት እንደማይቦዝን አወጋን፡፡  
በመጨረሻም ደብዳቤውን ጽፎ ሰጠን:: ወጣቱ ትክክለኛውን ሥራ በመሥራቱ አመሰግነነው ወጣን፡፡ ወዲያውኑ ደብዳቤውን ይዘን ቃል ወደገባልን መያድ አመራን፡፡ ልጅቱን ሳያቅማሙ ተቀበሉን:: በአሁን ወቅትም እንደሷ ካሉ ሌሎች 80 ገደማ እንስቶች ጋር አብራ ትኖራለች:: ድርጅቱ በወሊድ ወቅትም ድጋፍ ያደርግላታል፡፡ ወደፊት ሥራ እንድታገኝም የተለያዩ ሥልጠናዎችን ይሰጣታል፡፡
በኢትዮጵያ በጐ ተግባራትን ማከናወን አስፈላጊ መሆኑን አበክሬ አምናለሁ፡፡ የግድ ሃብታም መሆን የለባችሁም፡፡ ትናንሽ በጐ ተግባራትን መፈፀም ትችላላችሁ፡፡
በእኔ በኩል፤ እንደ መያዱ መሥራች፣ ትላልቅ በጐ ተግባራትን ማከናወን አልችልም፤ ነገር ግን ትናንሽ በጐ ተግባራትን መፈጸሜን በጽናት እቀጥልበታለሁ፡፡ ምክንያቱም ትናንሽ በጎ ተግባራት፣ ህይወት እንደሚለውጡ አይቻለሁ፡፡  እናንተስ?? የነገ ሰው ይበለን!!



Read 1661 times