Saturday, 29 February 2020 11:02

ፖለቲካ ገነነ፤ ሕይወትን የምንገብርለት ጣዖት ሆነ

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(3 votes)

   - በዓመት፣ 135ሺ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች በስደት ወደ የመን ገብተዋል (በጦርነት ወደታመሰችው የመን)፡፡
         - በየዓመቱ፣ 110ሺ ኢትዮጵያውያን ከሳውዲ አረቢያ እየተባረሩ ነው፡፡ (የዋሺንግተን ፖስት ዘገባ)፡፡
            
            በአዲስ አበባ፣ በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ተማሪዎች፣ ያለ ምግብ እርዳታ፣ መማር አይችሉም? ብዙ የከተማዋ ነዋሪዎች፣ በከባድ ድህነት ምንኛ እንደተጐሳቆሉ አስቡት፡፡ የፋብሪካ ኢንቨስትመንት ሳይኖር፣ ከወዴት የሚያኖር ስራ ይምጣ? የሚያወላዳ የመተዳደሪያ ገቢስ ከየት ይምጣ? ለዚህ ደንታ የሌላቸው ምሁራንና ፖለቲከኞች ብዙ መሆናቸው ነው ክፋቱ፡፡ ጭስ አልባ፣ ማለትም ፋብሪካ አልባና ስራ የለሽ ከተማ ለመፍጠር እቅድ የሚያወጡ  ምሁራን፣ የፖለቲካና የኤንጂኦ ወገኖች በዝተው ምን ይደረግ?
በየዓመቱ ሩብ ሚሊዮን ወጣቶች፣ ከዩኒቨርስቲና ከኮሌጅ፣ እንዲሁም ከቴክኒክና ሙያ ተቋማት እየተመረቁ እንደሚወጡ አስታወሱ፡፡ ነገር ግን፣ ከመቶ ተመራቂ ውስጥ፣ ለአስሩ እንኳ የስራ እድል መፍጠር የሚችሉ ፋብሪካዎች እየተቋቋሙ አይደሉም፡፡
ያለስራ የሚቀመጡ፣ ቆመው የሚቀሩ፣ ቀኑን ሲባክኑ የሚውሉ፣ በየከተማውና በየመንደሩ፣ በየጐዳናውና በየጥጋጥጉ የሚባዝኑ ወጣቶች ሲበዙ፣ ለወላጆች አያስጨንቅም? ለአገርስ አያሰጋም? በአዲስ አበባ፣ በየጐዳናው የሚያድሩና የሚውሉ ልጆችን ማየት ትችላላችሁ፡፡ ያስፈራል፡፡ ለብዙ ፖለቲከኛና ለብዙ ቆስቋሽ (activist) ነውጠኞች ግን፣ የሚያስፈራ ሳይሆን የሚያስጐመጅ ሆኖ ይታያቸዋል፡፡
ተመርቆ ያለስራ የተማረረ፣ ያለተስፋ የባዘነ ወጣት ሲበራከት፣ ለአጥፊ ፖለቲከኞችና ለክፉ ቆስቋሾች ይመቻቸዋል - በዘርና በሃይማኖት የሚቧደን ጭፍራ፣ በትንሽ ሽውታ የሚቀጣጠል ማገዶ ተትረፍርፎ ይታያቸዋል፡፡
በጥቅሉ ሲታይ፣ የድህነት ኢኮኖሚና የኑሮ ችግር፣ ስራ አጥነትና ተስፋ አጥነት፤ የአብዛኛው ነዋሪ ዋነኛ ጭንቀት ቢሆኑም፤ ብዙ ምሁራንና ፖለቲከኞች ግን ነገሩ የገባቸው አይመስሉም፡፡ ወይም ደንታቸው አይደለም፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ፣ ይጎመጁበታል - ከክፋት የተነሳ፡፡
እዚህ አገር ከ100 በላይ ፓርቲዎች፣ እልፍ አእላፍ ቋሚና ጊዜያዊ ፖለቲከኞች አሉ፡፡ ስንቶቹ ስለኢኮኖሚና ስለኑሮ ተናግረዋል? ሰዎችን በብሔር ብሔተሰብ፣ በቋንቋ ወይም በሃይማኖት ለማቧደንና ጥላቻ ለመዝራት፣… የጭፍራ አለቃና አዝማች ለመሆን የሚራኮት ነው የሚበዛው፡፡
“ደህና ናቸው” የምንላቸው ጥቂት ፓርቲዎች፣ ፖለቲከኞችና ምሁራን እንኳ፣ ይህ ነው የሚባል መፍትሔ በቅጡ ሲያቀርቡ አንሰማም፡፡
የሰዎች ዋነኛ አላማ፣ ‹‹በእውቀትና በጥረት ኑሯቸውን ማሻሻል፣ በስነምግባርና በግል ኃላፊነት ሕይወታቸውን ማለምለም›› መሆን እንዳለበት፣ የአገራችን ፖለቲከኞችና ምሁራን አላወቁም፡፡ ወይም ከልብ ከምር አልተገነዘቡትም፡፡
በተቃራኒው፤ የሰው ልጅ ትልቁ ተልዕኮ፣ አልፋና ኦሜጋ የሰው አላማ፣… የፓርቲ ፉክክርን ማጀብ፣ የፖለቲከኞችን ክርክር ማድመቅ፣ ቲፎዞነቱንም በምርጫ ማሳየት ብቻ ይመስላቸዋል - ቀሽሞቹ ምሁራንና ፖለቲከኞች፡፡…
በአጭሩ ሰው ሁሉ፣ ውሎና አዳሩ፣ ሀሳቡና ተግባሩ፣ ምኞትና ሕልሙ በሙሉ፣ ‹‹ዴሞክራሲ›› ለተሰኘ የፖለቲካ ሕይወት አሳልፎ እንዲሰጥ፤… ይህም ትክክለኛ ብቻ ሳይሆን ብቸኛው የሰው አላማ እንዲሆን ይጠብቃሉ፡፡
በሕይወትና በኑሮ ምትክ፣ ‹‹ፖለቲካ›› ዋና ነገራችን እንዲሆን ይመኛሉ፡፡ በእውቀትና በሙያ፣ በስራና በጥረት ምትክ፣ የፓርቲ ቲፎዞነትና የፖለቲካ ብሽሽቅ፣ የዘወትር ‹‹መዋያ››ችን ምሳና እራታችን ናቸው ብለን ብናምን ይወዳሉ፡፡ ደግሞም እየተሳካላቸው ነው፡፡ ፖለቲካ፣… የህይወትና የኑሮ አገልጋይ መሆኑ ቀረና፣ በላያቸው ላይ ገንኖ ነግሷል፡፡
በአምስት አመት አንዴ፣ የጥበቃ ሰራተኞችን የሚከታተሉና የሚቆጣጠሩ ጥቂት ሰዎችን የመምረጥና የመቅጠር ቀላል ሥራ መሆን ነበረበት - የፖለቲካ ምርጫ፡፡
ሰዎች፣ ያለ ስጋት በሰላም፣ አእምሯቸውን ተጠቅመው፣ እውቀታቸውን አገናዝበው፣ አስልተውና አቅደው፣ ለነገም ሙያቸውን እያሳደጉ፣ ለዛሬም ኑሮን የሚያሻሽል እህል ለማምረትና ቁሳቁስ ለመፈብረክ በትጋት እንዲሰሩ፣… በነፃነት ሰርተውም በገዛ ምርታቸው እንዲጠቀሙ፣ የባለቤትነት መብታቸው ተከብሮም በነፃነት እንዲገበያዩ፣… ይህንን የነፃነትና የመብት ቀይ መስመር የሚጥስ ወንጀለኛን በሕግ ለመከላከልና በሕግ ለመዳኘት፣ የጥበቃ ስራ ማከናወን ብቻ ነው - ትክክለኛው የመንግሥት ስራ፡፡
ይህንን መርህ የያዘና በቀጭኗ ቀይ መስመር ላይ ብቻ የተገደበም ነው ትክክለኛው የፖለቲካ ቦታ፡፡
ሰዎች፣ የገዛ ህልውናቸውን በሃላፊነት እንዲመሩ፣ የገዛ ኑሯቸውን በስራ እንዲያቃኑ፣ የገዛ ንብረታቸው ባለቤት እንዲሆኑ፣ መንግሥት… ወደ ሰፊው የሰዎች የኑሮ ሜዳ ውስጥ ሳይገባ፣ ከዳር ሆኖ፣ የአጥር ጥግ ላይ፣ ቀጭኗን ቀይ መስመር በንቃት የሚያስከብር የጥበቃ ሰራተኛ መሆን ይገባዋል፡፡
እንደ አገር እና እንደ ድንበር ናቸው፤ ኑሮ እና ፖለቲካ ሲነፃፀሩ፡፡
አገር በጣም ሰፊ ነው፡፡ ድንበር ግን፤ ቀጭን ቀይ መስመር ናት - በሰፊው አገር ዳርቻ ዙሪያ፡፡ ሰፊውን አገር ዘንግተን፣ ቀጭኗን መስመር እንደ አገር ከቆጠርናት፣ አገርን ለስርዓት አልበኞችና ለነውጠኞች አስረክበን አገር አልባ እንሆናለን፡፡
በሰዎች ኑሮና በፖለቲካ መካከል ያለው ልዩነት፣ ከዚህ ጋር ይመሳሰላል፡፡ የሰዎች ኑሮ እጅግ ሰፊ ሜዳ ነው፡፡ ፖለቲካ ደግሞ፣ በሰዎች ሰፊ የኑሮ ሜዳ ዙሪያ የተዘረጋ ቀጭን ቀይ መስመር ነው፡፡ ዋናው ቁምነገር፣ የሰዎች ህይወትና ኑሮ እንጂ፣ ፖለቲካ አይደለም:: ፖለቲካ፣ ሕይወትንና ኑሮን ለማገለገል፣ ራቅ ብሎ ከጥቃት ለመከላከል፣ በሰፊው የኑሮ ሜዳ ዙሪያ የተሰመረ ቀጭን ቀይ አጥር እንደሆነ ካልተገነዘብን፣ ህይወታችን ‹‹የፖለቲካ አገልጋይ›› ይሆናል፡፡
ሰፊውን የህልውናና የኑሮ ሜዳ ትተን፣ ቀጭኗን መስመር (ፖለቲካን) እንደ ሕይወት እና እንደ ኑሮ የምንቆጥራት ከሆነ፣ ህይወትና ኑሯችን ላይ ለሚቆምሩ ፖለቲከኞችና ቆስቋሾች ተመቸንላቸው፡፡ ቀጭኗን መስመር መጠበቅ የነበረባቸው ፓርቲዎች፣ ፖለቲከኞችና ባለስልጣናት፣ ሰፊውን ሜዳ ወርሰው እንዳሻቸው ይፈነጩበታል:: እንዳሰኛቸው፤ በዜጐች ኑሮና ሕይወት ላይ ይቀልዳሉ፤ በዜጐች ስራና ንብረት ላይ ይጫወታሉ ማለት ነው፡፡
አንዴ በብሔር ብሔረሰብ፣ ሌላ ጊዜ በቋንቋና በሐይማኖት ተከታይነት፣ ሲመቻቸውም ሃብታምና ድሃ እያሉ፣ የሰውን ህይወትና ንብረት ይማግዳሉ፡፡
ፖለቲካን ከህይወት በላይ እያገነኑ፣ ለዚያውም ለስነምግባርና ለህግ ተገዢ ያልሆነ፣ ቁንፅል “ዲሞክራሲ”ን፤ እና ቁንፅል “የፖለቲካ ምርጫ”ን እየሰበኩ፤ በብብሽሽቅና በንትርክ፣ ከዚያም በግርግርና በረብሻ፣ ወይም በፕሮፖጋንዳና በአፈና፣ በአመጽና በትርምስ፣ አልያም በእስርና በአምባገነንነት፣ በዝርፊያና በቃጠሎ፣ በማፈናቀልና በግድያ ዘመቻ፣ ዘላለም ለመቀጠል ይመኛሉ -  ነውጠኛ የፖለቲከኞችና ቆስቋሾች፡፡
ወገኖቹ ምሁራንና ፖለቲከኞችስ?  
ለሰዎች የስራ ነፃነትና ለንብረት ባለቤትነት፣ ለሰላምና ለህግ የበላይነት፣ በዚህም ለግል ኢንቨስትመንት በተለይም ለፋብሪካ ኢንቨስትመንትና ለስራ ፈጠራ፣ ለወጣቶች የስራ እድል፣ ኑሮን ለሚያሻሽል የዜጐች ጥረት… ቅንጣት ክብር የላቸውም -  አብዛኞቹ ወገኛ ምሁራንና ፖለቲከኞች::  ለዚህም ነው፤ ስለ ኢኮኖሚና ስለ ኑሮ፣ ስለ ኢንቨስትመንትና ስለ ስራ፣ ስለ ንብረት ባለቤት መብትና ስለ ገበያ ነፃነት ብዙም የማያወሩት፡፡
ግን አስቡት፡፡ በዓመት 135ሺ ወጣቶች፣ ጦርነት ባተራመሳት አገር፣ በየመን በኩል ለመሰደድ ጥሪታቸውን አሟጥጠው ሲከፍሉ፣ በአደጋ ብቻ ሳይሆን በጥቃት ሕይወታቸውን ሲያጡ፣ ምን ማለት ነው?
ዲሞክራሲና ምርጫ ናፍቋቸው ነው?
በሃይማኖት መቧደንና መበሻሸቅ አምሯቸው ነው? በብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካ ተማርከው፣ በዘር ለመቧደን፣ ሰዎችን ከኑሮ ነቅሎ ለማባረር፣ ንብረት ለመዝረፍና ለማቃጠል፣ መንገድ ለመዝጋትና ፋብሪካዎችን ለማውደም ጓጉተው ነው? ‹‹ይሄኛው ቦታ የእገሌ ብሔር፣ ያኛው የእገሊት ብሔረሰብ መሬት›› እያሉ መፈክር ለማሰማት፣ ወረዳ እና ክልል ለመፍጠር፣ በዘር እና በቋንቋ ባለስልጣናትን ለመሾም ነው እልፍና እልፍ ወጣቶች የሚሰደዱት?


Read 1092 times