Print this page
Saturday, 29 February 2020 11:00

ለሁለት ወጣቶች ህልፈት ምክንያት የሆነው የቦታ ውዝግብ እንዲጣራ ተወሰነ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

    የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና የቤተ ክርስቲያኒቱ ቅዱስ ሲኖዶስ በተለምዶ 24 ቀበሌ ተብሎ በሚጠራው ቦታ ከቤተ ክርስቲያን የቦታ ጥያቄ ጋር በተያያዘ የተፈጠረው ችግር ከስረ መሠረቱ ከሶስት አካላት በተውጣጣ ኮሚቴ እንዲጣራ ተስማሙ፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ም/ከንቲባ ኢ/ር ታከለ ኡማ የካቲት 12 ቀን 2012 ዓ.ም ከቅዱስ ሲኖዶስ ጋር በጉዳዩ ላይ ባደረጉት ውይይት ለሁለት ወጣቶች ሞት ምክንያት የሆነው የቦታ ውዝግብ ከአካባቢው ሽማግሌዎች፣ ከቤተ ክርስቲያኒቱና ከመንግሥት አካል በተውጣጣ የጋራ ኮሚቴ እንዲመረመር ተስማምተዋል፡፡
የተቋቋመው የጋራ አጣሪ ኮሚቴውም በቀጣይ 10 ቀናት ውስጥ ችግሩ እንዴት እንደተፈጠረ? ችግሩን መጀመሪያ የነበረውን የቤተ ክርስቲያኒቱን ንዋየ ቅዱሳት ሁኔታ እንዲሁም ስለቦታው በዝርዝር አጥንቶ ሪፖርት እንዲያቀርብ ይጠበቃል ሲሉ ምንጮች ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡
ከዚህ የቦታ ውዝግብ ጋር በተያያዘ ታስረው የነበሩ የአካባቢው ወጣቶችና የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮች ከእስር እንዲለቀቁም ስምምነት ተደርሷል፡፡
የቤተ ክርስቲያኒቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ቀደም ባለው ሳምንት ባካሄደው ልዩ ጉባኤው ቦታው የሁለት ክርስቲያን ወጣቶች ደም የፈሰሰበት እንደመሆኑና ቤተ ክርስቲያኒቱ በቦታው ላይ ቀደም ብላ ጥያቄ አቅርባ የነበረ በመሆኑ ቦታው ለቤተ ክርስቲያኒቱ ሊሰጥ ይገባል ማለቱ ይታወሳል፡፡   

Read 11527 times