Monday, 24 February 2020 00:00

አንዳንድ ነጥቦች ስለ ሰብአዊ መብት…

Written by  (ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል)
Rate this item
(3 votes)

    “--በአጠቃላይ፤ መብት - ከ“ግዴታ ወሰን” ተሻግረን እንዳሻን የምንፈነጭበት ተፈጥሯዊ ወይም ደመነፍሳዊ ፀጋ አይደለም፡፡ የውዴታ ግዴታን በመወጣት የምንጎናጸፈው ትሩፋት ነው፡፡--”
    
             የዛሬ ሳምንት በዚሁ ርዕስ ስር በቀረበው ክፍል አንድ ጽሑፍ፣ ስለ መብት ምንነትና ስለ ሰብአዊ መብት ዘርፎች አጠር ያለ ማብራሪያ መቅረቡ ይታወሳል፡፡ በክፍል 2 ደግሞ ስለ ሰብአዊ መብት ታሪካዊ አጀማመር፣ ስለ መብትና ግዴታ፣ ስለ መብትና ትግል እንዲሁም መብት በዴሞክራሲ ስርዓት ውስጥ እንዲኖር ለምን እንዳስፈለገ፣ በአጭር በአጭሩ ለማቅረብ ጥረት ይደረጋል፡፡
የሰብአዊ መብት ታሪካዊ አጀማመር
የሰብአዊ መብትን ታሪካዊ አመጣጥ በተመለከተ ቀዳሚዎቹ የሰብአዊ መብት መርሆዎች ግልጽ የተደረጉት ከክርስቶስ ልደት በፊት በ6ኛው ክፍለ ዘመን መሆኑን በዘርፉ ጥናት ያደረጉ ባለሙያዎች ይናገራሉ:: የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተ.መ.ድ) የሰብአዊ መብት መርሆዎችን ታሪካዊ መነሻ አድርጎ የሚያስቀምጠው ጊዜ ከክርስቶስ ልደት በፊት እ.ኤ.አ 539 ዓመተ ዓለምን ነው፡፡ በዚያ ወቅት የፐርሺያ ኢምፓየር ትባል በነበረቺው ጥንታዊት ኢራን ንጉስ የነበረው ታላቁ ሳይረስ (Cyrus the Great - 576 or 590 BC - 530 BC)፤ ባቢሎንን በጦርነት አሸንፎ ካስገበረ በኋላ ባልተጠበቀ ሁኔታ ባወጣው አዋጅ፣ በባርነት የተያዙ ሰዎችን ነፃ አድርጎ አሰናብቷል፡፡ በግዛቱ የሚኖሩ ዜጎች ሁሉ የፈለጉትን ሃይማኖት የመምረጥና የመከተል መብት እንዳላቸው ደንግጓል፡፡ የዘር ልዩነት እንደማይደረግ ማወጁም ይነገራል፡፡ እነዚህ በቅርጻ ቅርጽ ላይ ተጽፈው የተገኙ የሰብአዊ መብት መሰረታዊ ሃሳቦች እ.ኤ.አ በ1948 በወጣው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ድንጋጌ ሰነድ ላይ የመጀመሪያዎቹ አራት አንቀፆች ሆነው እንዲሰፍሩ ተደርገዋል፡፡
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተ.መ.ድ) በኩል የሰብአዊ መብት መርሆዎችን የያዘ እንደሆነ የሚነገርለት ሁለተኛው ታሪካዊ ሰነድ አድርጎ የሚያቀርበው እ.ኤ.አ በ622 ነብዩ ሙሐመድ (ሰዐወ) ከመካ ወደ መዲና ሄደው የመንግስት አስተዳደር ባቋቋሙበት ወቅት የመካ ነዋሪ የሆኑ ሙስሊሞችን፣ ክርስቲያኖችን፣ አይሁዶችን፣ እምነት የለሾችንና ጣዖት አምላኪዎችን መብት የዘረዘሩበት “የመዲና ህገ መንግስት” (The constitution of Medina) የተሰኘ 12 አንቀፆች ያሉት ሰነድ ነው፡፡
ከላይ ከተጠቀሱት ሁለት ታሪካዊ ሰነዶች በኋላ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት በኩል “የሰብአዊ መብት መርሆዎችን የያዙ ሰነዶች” ተብለው ከተዘረዘሩት ውስጥ የሚከተሉት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ እነሱም፡- እ.ኤ.አ በ1215 በእንግሊዙ ንጉስ ኤድዋርድ የተዘጋጀው ማግና ካርታ፣ እ.ኤ.አ በ1222 በሀንጋሪ አስተዳደር የተዘጋጀው “the Golden Bull of Hungary”፣ እ.ኤ.አ በ1320 በስኮትላንድ የተዘጋጀው “Declaration of Arbroath”፤ እንዲሁም የዴንማርክ፣ የቤልጂየም፣ የኔዘርላንድና የኢንግላንድ “Bill of Rights”፣ እ.ኤ.አ በ1789 የወጣው የፈረንሳይ “Declaration of the Rights of Man and of the Citizen፣ እ.ኤ.አ በ1789 –1791 የተዘጋጀው የአሜሪካ “Bill of Rights” … እያለ ይመጣና እ.ኤ.አ በ1948 የወጣው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌ (Universal Declaration of Human Rights) ላይ እንደርሳለን፡፡ እነዚህ ሁሉ ስለ ሰዎች መብትና ነፃነት የተደነገገባቸው ሰነዶች ናቸው፡፡
መብትና ግዴታ - መብትና ትግል
የአንድ ሰው መብት በሌላ ግለሰብ ላይ ግዴታን ያስከትላል፡፡ መብት ድንበር ያልተደረገበት፣ ወሰን የሌለው (ቀይ መስመር የሌለው) ልቅ ነገር አይደለም፡፡ በህግ ገደብ ይበጅለታል፡፡ በማህበረሰብ ወሰን ይቀመጥለታል፡፡ ተያይዘው የሚመጡ ግዴታዎችም አሉት፡፡ መብት ከግዴታ ጋር የመቆራኘቱ ምክንያት የአንድ ግለሰብ የመብት ጣራ የሌላን ሰው መብት የማይነካ፣ የማህበረሰብን ሰላም የማያደፈርስ፣ ባህሉን የማይጋፋ መሆን ስለሚገባው ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት የመብት መደፈር እንዳይከሰት የሚገደብበት ተፈጥሯዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊና ህጋዊ ክልከላዎችና ግዴታዎች ይኖራሉ፡፡ በአጠቃላይ፤ መብት - ከ“ግዴታ ወሰን” ተሻግረን እንዳሻን የምንፈነጭበት ተፈጥሯዊ ወይም ደመነፍሳዊ ፀጋ አይደለም፡፡ የውዴታ ግዴታን በመወጣት የምንጎናጸፈው ትሩፋት ነው፡፡
በሌላ በኩል፤ መብትና ትግል ያላቸው ቁርኝት ችላ ተብሎ የሚታለፍ ጉዳይ አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ “መብት” የሚባለው ነገር የተደረገለትን ትግልና የተነገረለትን ያህል፤ እንዲሁም የትናንትናና የዛሬ የትግል መንፈስ ከወቅታዊ አስተሳሰብ ጋር ያላቸውን ግንኙነት አያመላክትም፡፡ “መብት” ግለሰቦች ከሌሎች ሰዎች፣ ከማህበረሰብና ከመንግስት የሚጠይቁት ነገር ነው:: በማህበረሰብ ተቀባይነት ያገኘ መብት ህግ ሆኖ ተጽፎ ተጨባጭ የማስፈጸሚያ ስልጣንና የማስፈጸሚያ አካል ያስፈልገዋል:: ካለበለዚያ ተፈጥሯዊ የሞራል ህግ ሆኖ ይቀራሉ፡፡ ህግ ሆኖ ከተጻፈ የተፈጻሚነት አቅም ይኖረዋል፡፡ ህግ ከሆነ ደግሞ በሥራ ላይ እንዲውል ጥያቄ ማቅረብ ይቻላል፡፡ ግለሰቦች ወይም መንግስት ህጉን ካላከበሩ የመብት ጥሰት እንደተፈጸመ ተቆጥሮ ትግል ማድረግ አስፈላጊ ይሆናል፡፡
ዜጎች ከቤተሰባቸውና ከአካባቢያቸው ጀምሮ የመብትን አስፈላጊነትና ጠቀሜታ እየቀሰሙ ያድጋሉ፡፡ በዚህም መሰረት በቅድሚያ ለቤተሰባቸው፤ ቀጥሎም ለአካባቢያቸው ህግ ሲገዙ የማህበረሰቡንም ህግ እንደዚያው እያከበሩና የመብታቸውንም ሁኔታ ከዚሁ አንጻር እያጤኑ ይዘልቃሉ:: ነገር ግን አንድ ግለሰብ በቤተሰቡና በአካባቢው ስለሚኖረው መብት ሊያውቅ ካልቻለ ወይም በቂ የሆነ ግንዛቤ ከሌለው ከፍተኛ ለሆኑት ሰብአዊና ዜግነታዊ መብቶች ቁብ አይኖረውም፡፡ በተጨማሪም ስለ መብት የሚኖረው ትርጓሜ የተንሸዋረረና የተወላገደ መሆኑ አይቀርም፡፡
በሌላ አገላለጽ፤ሰዎች ራሳቸው ሊጠብቋቸውና ያለ ፖሊስ ኃይልና ያለ ፍርድ ቤት ውጣ ውረድ ሊያስከብሯቸው የሚችሏቸውን መብቶች የማስከበር አቅማቸው እየላላ ከመጣ በከፍተኛ ደረጃ የሚገኙ መብቶችን ለማስጠበቅ የሚኖራቸው ተነሳሽነት ሙት ይሆናል ማለት ነው፡፡ በመሆኑም እያንዳንዱ ሰው የመብቱን መከበር አስፈላጊነት ችላ በማለቱ ወይም ለመብቱ መከበር የሚኖረውን ግለሰባዊ ድርሻ ትርጓሜ በማዛባቱ ምክንያት፤ ማንም ሊነጥቀው የማይገባውንና የማይቻለውን መብቱን አሳልፎ ለሌሎች ይሰጣል፡፡ መብትን ለማስከበር ቁርጠኛነት ሲጠፋና በአንጻሩ ቸልተኛነትና ግዴለሽነት እየጎለበተ ሲሄድ፤ በአምባገነኖች፣ በእናውቅልሃለን ባዮችና የሰውን ልጅ ድክመት እየፈለጉ በሚፈጽሙት አስነዋሪ ድርጊት የታላቅነት ስሜት በሚሰማቸው ጀብደኞች፣ የሰው ልጅ ሁለንተናዊ መብት ቀን በጠራራ ፀሐይ፣ ማታ በጠፍ ጨረቃ ብርሃን ይነጠቃል፡፡
መብት በዴሞክራሲ ስርዓት ውስጥ
መብት ቀጣይነት ላለው ዴሞክራሲ አስፈላጊ ነው፡፡ በዴሞክራሲያዊ ስርዓት እያንዳንዱ ዜጋ የመምረጥ መብትና መንግስትን የማቆም መብት አለው፡፡ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሄድ ደግሞ የመናገር ነፃነት፣ የፖለቲካ ፓርቲ የማቋቋምና በፖለቲካ የመሳተፍ መብት አስፈላጊ ነው:: መሰረታዊ ሰብአዊ መብቶች የፖለቲካ ዴሞክራሲን እውን ለማድረግ ወሳኝ ናቸው::
መብት የህግ ጥበቃ ይደረግለታል፡፡ መብት አናሳዎች በብዙሃን እንዳይጨቆኑ ይረዳል፡፡ መብቶች በሰዎች ላይ መጥፎ ተግባራት እንዳይፈጸሙ ዋስትና ይሰጣሉ:: መብቶች የግለሰቦችን እኩልነት፣ ክብር፣ የብዙሃንን ፍላጎትና የሀገርን አንድነት ለማስጠበቅ ይረዳል፡፡ መብት አምባገነን መንግስት እንዳይፈጠር ይከላከላል፡፡ መብት የግላሰቦች መብትና ነፃነት በመንግስታት እንዳይደፈቅ ይመክታል፡፡ ዴሞክራሲን ባሰፈኑ ሀገሮች፣ አንዳንድ መብቶች መንግስታት እንዳሻቸው እንዳይጥሷቸው ተደርገው፣ በህገ መንግስት መደንገጋቸው በዚህ ምክንያት ነው፡፡
ከአዘጋጅ፡-  ጸሐፊውን Email: This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 9182 times