Saturday, 22 February 2020 10:23

የትግሬ ወርጂ ብሔረሰብ፤ የህልውና ማጣት ተጋርጦበታል ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

   የትግሪ ወርጂ ብሔረሰብን ማንነት የማጥፋት ስውር እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን የትግሬ ወርጂ ብሔረሰብ ዲሞክራሲዊ ድርጅት ያስታወቀ ሲሆን፤ የብሔረሰቡ ማንነት ከመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ዝርዝር እንዲሠረዝ ተደርጓል ብሏል፡፡
ድርጅቱ ለአዲስ አድማስ ባደረሰው ጋዜጣዊ መግለጫው፤ የትግሬ ወርጂ ብሔረሰብ ከ1983 ዓ.ም ወዲህ ባሉ ሁለት የቤትና ህዝብ ቆጠራ መርሃ ግብሮች መቆጠር ቢችልም፣ በቀጣይ ሊደረግ ከታሰበው የቤትና ህዝብ ቆጠራ ሰነድ ውስጥ አለመካተቱን አስታውቋል፡፡
በተጨማሪም በመንግስት አገልግሎት ሰጪነት የተቋቋመ የወጣት ኩነቶች ባለስልጣን፣ በትግሬ ወርጂ ብሔረሰብ ስም መታወቂያ ካርድ፣ የልደትና የጋብቻ የምስክር ወረቀት ለመስጠት ፍቃደኛ አለመሆኑ፣ የብሔረሰቡ ተወላጆች ለጉዳያቸው ማስፈፀሚያ ሲሉ ያለ ፈቃዳቸው በሌሎች ብሔረሰብ ማንነት ስም ለመስተናገድ መገደዳቸውን ድርጅቱ አስታውቋል፡፡
በብሔረሰቡ ላይ የተጋረጠውን ይህን የህልውና ስጋት ለመፍታት ድርጅቱ ለፌዴሬሽን ም/ቤትና ለተለያዩ የመንግስት አካላት ቢያሳውቅም ምላሽ ማጣቱንም አስገንዝቧል - በመግለጫው፡፡
የብሔረሰቡን ማንነት ለማስመለስና ለማስጠበቅ የፖለቲካ ድርጅቱ ሌሎች የህልውና ስጋት ከተጋረጠባቸውና በተለያዩ ክልሎች ከሚገኙ ብሔረሰቦች ጋር ትግሉን ለማቀናጀት ማቀዱንም አስታውቋል፡፡
የወርጂ ብሔረሰብ በተለይ በሸዋ እስላማዊ ስልጣኔት ውስጥ የራሱን ጉልህ ድርሻ ሲጫወት የቆየ መሆኑን፣ በ1285 ዓ.ም ከሸዋ ስልጣኔት መፍረስ በኋላ ብሔረሰቡ መኖሪያውን በዛሬዋ አዲስ አበባ ከተማና በሰሜን ሸዋ አድርጐ መቆየቱንም መግለጫው ያትታል፡፡ የወርጂ ብሔረሰብ በአዲስ አበባ ለመኖሩም በእንጦጦ ተራራ ላይ፣ በመሃል አዲስ አበባ አዋሬ አካባቢ እንዲሁም በአዲስ አበባ ዙሪያ በአቃቂ፣ ዳሊቲ፣ ሰንዳፋ፣ ሮጌ፣ ጫጫና በሌሎች የሰሜን ሸዋ ወረዳዎች የሚገኙ ጥንታዊ የሙስሊም መካነ መቃብር ጉልህ ማሳያዎች ናቸው ብሏል - ድርጅቱ በመግለጫው፡፡
በዚህ ምክንያትም በተለይ ባለፉት ሁለት አመታት፣ ከአዲስ አበባ የባለቤትነት መብት ጋር ተያይዞ የተፈጠሩ ጡዘቶችን ተከትሎ፣ ብሔረሰቡ በማንነቱ ላይ የሚታዩ ጫናዎች በርክተዋል ብሏል - ድርጅቱ፡፡     


Read 2883 times