Saturday, 30 June 2012 12:28

ቤኒናዊው ከአፍሪካ ምርጥ ተዋናዮች አንዱ ተባለ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

ትውልዱ ከቤኒን የሆነው የ48 ዓመቱ ዲጃይዋን ሃውንሶ አፍሪካ ለሆሊውድ ካበረከተችው ምርጥ ተዋናዮች አንዱ መሆኑን ሲኤን ኤን አስታወቀ፡፡ በሆሊውድ በተሰራ ፊልም ለመጨረሻ ጊዜ ከሁለት ዓመት በፊት የተወነው ዲጃይዋን፤ ሰሞኑን ኪሞራ ሊ ከተባለች ታዋቂ ሞዴል ጋር ለአምስት ዓመታት የቆየበትን ትዳር በፍቺ ደምድሟል፡፡ ከታዋቂዎቹ የሆሊውድ ባለሙያዎች ስቲቨን ስፒልበርግ፣ ሊዮናርዶ ዲካርፒዮ፣ አንቶኒ ሆፕኪንስና ሞርጋን ፍሪማን ጋር ስኬታማ በሆኑ ምርጥ ፊልሞች ላይ የተወነው ዲጃይዋን፤ በፈረሰበት ትዳር ከትወናው እንዳማይርቅ ሎስአንጀለስ ግምቱን አስቀምጧል፡፡ ቤኒናዊው ተዋናይ ከጐዳና ተዳዳሪነት ተነስቶ ዓለም አቀፍ ሞዴልና አንደኛ ደረጃ የሚሰጠው ተዋናይ ለመሆን መብቃቱን ያስታወሰው ሲኤንኤን፤ ተዋናዩ በአካባቢ ጥበቃ ዘመቻዎችና በሌሎች የበጎ አድራጎት እንቅስቃሴዎች የተከበሩ ስራዎችን እንዳከናወነ በመግለፅ አወድሶታል፡፡

ዲጃይዋን ሃውንሶ ከተወነባቸው ምርጥ ፊልሞች መካከል “አሚስታድ”፣ “ብለድ ዳይመንድ” እና “ኢን አሜሪካ” ይገኙበታል፡፡ በ13 ዓመቱ ቤተሰቡንና የትውልድ አገሩን ለቅቆ ወደ ፈረንሳይ የተሰደደው ተዋናዩ፤ በፓሪስ የሞዴል ስራውን የጀመረ ሲሆን እ.ኤ.አ በ1994 በሮናልድ ኤምሪክ በተሰራው “ስታር ጌት” ፊልም ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ከተወነ በኋላ በሆሊውድ ፊልም ሰሪዎች ትኩረት እንዳገኘ ይታወቃል፡፡

“ኢን አሜሪካ” በተባለው ፊልም ላይ ባሳየው ድንቅ ትወና ለኦስካር በመታጨት የመጀመርያው አፍሪካዊ አሜሪካዊ የሆነው ዲጃይዋን፤ በትወና በቆየባቸው ያለፉት 25 ዓመታት ከ15 በላይ ፊልሞች ሠርቶ ከ1.84 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ያስገባ ሲሆን በአንድ ፊልም በአማካይ 49 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እንደሚያስገኝ የቦክስ ኦፊስ ባይነምበርስ መረጃ አመልክቷል፡፡

 

 

Read 878 times Last modified on Saturday, 30 June 2012 12:35