Print this page
Saturday, 22 February 2020 09:53

ግዙፉ አልፎዝ ፕላዛ ዛሬ ይመረቃል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

     በሆቴል ሪል እስቴትና በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ምርት ላይ ሊሰማራ ነው
             
           ላለፉት 22 ዓመታት በተለያዩ የንግድ ሥራዎች ላይ ተሰማርቶ ስኬት የተቀዳጀው አልፎዝ የጠቅላላ ንግድ ድርጅት፤ ኢምፔሪያል ሆቴል አካባቢ ያስገነባውን ‹‹አልፎዝ ፕላዛ››፤ የተሰኘ ግዙፍ የንግድ ማዕከል በዛሬው ዕለት ፕሬዚዳንት ክብርት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ በተገኙበት እንደሚያስመርቅ አስታወቀ፡፡
ድርጅቱ ማክሰኞ ረፋድ ላይ በአልፎዝ ፕላዝ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ በ3 ሺህ ካ.ሜ ላይ ያረፈውና ስምንት ወለል ያለው ይህ የንግድ ማዕከል፤ ከፍተኛ ወጪ የወጣበትና ሁሉንም አገልግሎት በአንድ ላይ የያዘ መሆኑን የአልፎዝ ፒኤልሲ ባለቤትና ዋና ዳይሬክተር አቶ አሊ መሐመድ ሁሴን ተናግረዋል፡፡ ግንባታው 6 ዓመት የፈጀው ግዙፉ የንግድ ማዕከል፤ 700  ክፍሎች ሲኖሩት፣ 400 ያህሉ ለተለያዩ ሱቆች፣ 300ዎቹ ደግሞ ለቢሮ አገልግሎት እንደሚውሉ ተገልጿል፡፡ የንግድ ማዕከሉ በአንድ ጊዜ ብዙ ተሽከርካሪዎችን የማስተናገድ አቅም ያለው ሲሆን ለ300 ያህል ሠራተኞች የስራ እድል እንደሚፈጥር ታውቋል። በምርቃቱ ላይ በርካታ ባለሀብቶች፣ የመንግሥት ኃላፊዎች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና ታዋቂ ሰዎች ይገኛሉ ተብሏል፡፡
አልፎዝ የጠቅላላ ንግድ ድርጅት ከተሰማራባቸው የንግድ ዘርፎች መካከልም በቦንጋና ጅማ የቡና እርሻ ልማት፣ በአዳማ ቱሉ የእንስሳት ሀብት ልማትና የስጋ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ፣ በድሬዳዋና በአዲስ አበባ እያንዳንዳቸው 30 ሺህ ቶን ቡና ማከማቸትና ማደራጀት የሚችሉ ተቋማት፣ በአዲስ አበባ፣ በድሬዳዋና በቃሊቲ ቡናን ቆልቶና ፈጭቶ ለውጭ ገበያ ማቅረብ ይገኙበታል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የግንባታ ማሽኖችንና የብረት ጥሬ ዕቃዎችን ወደ አገር ውስጥ በማስገባት እስካሁን ከ1.ቢ. ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ያስገኘ ሲሆን ከ2ሺህ በላይ ለሆኑ ዜጎችም የሥራ ዕድል መፍጠሩ ተገልጿል፡፡
ኩባንያው ከንግዱ ጎን ለጎን መንግሥት ለሚያከናውናቸው ልማቶች ድጋፍ በመስጠትም ይታወቃል፡፡ ኩባንያው ለአባይ ግድብ 10 ሚ. ብር፣ ለሸገር ማስዋቢያ ፕሮጀክት 5.ሚ ብር የለገሰ ሲሆን በይርጋ ጨፌ አካባቢ ድልድይ በመገንባት፣ በጅማ፣ በይዳና ከፋ መንገድ በመስራት፣ ዝዋይና አዳሚ ቱሉ አራት የውሃ ጉድጓዶችን በመቆፈርና ንፁህ የመጠጥ ውሃ በማቅረብ፣ ቦንጋ የመብራት ትራንስፎርመር ገዝቶ በማቅረብ፣ ህብረተሰቡን የመብራት አገልግሎት ተጠቃሚ አድርጓል፡፡
የንግድ ድርጅቱ በቀጣይም በሆቴል፣ በሪል እስቴት፣ በሞል ግንባታና የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች መገጣጠሚያ ፋብሪካ ለመሰማራት ዝግጅቱን እንዳጠናቀቀ ባለቤቱ ተናግረዋል፡፡

Read 2882 times