Saturday, 15 February 2020 12:28

‹‹ወደ ፓርቲ ፖለቲካ የገፋኝ ጠ/ሚኒስትሩ ነው››

Written by  ሰላም ገረመው
Rate this item
(7 votes)

    - ኢህአዴግን መቀመቅ ከከተቱት ሰዎች አንዱ ነኝ
         - ተቃውሞ የማደርገው ሽግግሩን ለማሳካት ነው
         - በምርጫው ማንም ያሸንፍ ከሁሉም ጋ አብሮ ለመስራት ዝግጁ ነን
        - ህወኃት ቢሄድም የኢህአዴግ ስርዓት ቀጥሏል


              ለበርካታ አመታት በአገሪቱ የነበረውን ስርዓት በመቃወም ከፍተኛ ትችቶችን በማህበራዊ ሚዲያ ሲሰነዝር ቆይቷል፡፡ በዚህም ምክንያት በሽብርተኝነት እስከ መፈረጅ ደርሷል፡፡ ለውጡን ተከትሎ ወደ አገሩ የተመለሰው አክቲቪስት ጀዋር መሃመድ፤ ከጥቂት ወራት በፊት የኦሮሞ ፌደራሊስት
ኮንግረንስ (ኦፌኮ) አባል ሆኗል፡፡ በቀጣይ ምርጫም እንደሚወዳደር ተናግሯል፡፡ ከምርጫ ቦርድ ጋር በዜግነት ጉዳይ እየተወዛገበም ይገኛል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ሰላም ገረመው አክቲቪስትና ፖለቲከኛ ጀዋር መሃመድን በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ አነጋግራዋለች፡፡


             ወደ ፓርቲ የመጣኸው በእልህ ነው፤ በተለይ ከጠባቂዎችህ ጋር በተያያዘ የተፈጠረውን ችግር ተከትሎ… እውነት ነው?
እኔን ወደ ፓርቲ ፖለቲካ የገፋኝ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የወሰደው አቅጣጫ ነው፡፡ ቀኝ ዘመም እየሆነ በሄደ ቁጥር… ሌላው ደግሞ በውስጥ የሚቃወሙትን ማስፈራራት ሲጀምር፣ ጠንከር ያለ ተቃዋሚ ያስፈልገዋል ወደሚለው ገባን፡፡ የጥበቃዎቼን የማንሳት ስራም የነበረው እኮ… ከዚህ ጋር ተያይዞ ነው፡፡ ቢሾፍቱ ላይ ሄጄ ስለተቃወምኳቸው ነው፡፡  
ሰሞኑን በጅማ ያቀዳችሁት የህዝብ ውይይት ምን ገጠመው?
የከተማው ከንቲባ ፍቃድ መስጠት ስላልቻለና ደብዳቤ ስለፃፈልን ነው፡፡ ለደብዳቤውም ምላሽ ሰጥተናል፡፡ የእነሱን መልስ እየጠበቅን ነው፡፡ እንጂ ስብሰባውን ማካሄዳችን አይቀርም፡፡
ብዙዎች ከህወሃት ጋር ግንኙነት እንዳለህ ያስባሉ…
በርግጠኝነት አንድ ናቸው ብለው አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም ኢህአዴግን መቀመቅ ከከተቱት ሰዎች አንዱ እኔ ነኝ፡፡ እኔ የኦነግ ልጅ ነኝ፤ ይሄ ማለት በኦነግ ውስጥ ተወልጄ ነው ያደኩት፤ ቤተሰቦቼ ኦነግ ነበሩ፡፡ ኦህዴድ (ኦዴፓ) በሚያስተዳድረው ኦሮሚያ ውስጥ በማደጌ የተነሳ ኢህአዴግና ኦዴፓን በደንብ ነው የማውቃቸው፡፡ ጭቆናቸውን፣ ድክመታቸውንና ጥንካሬያቸውን በደንብ ስለማውቅ ነው ለመገርሰስ የቻልነው፡፡ ከኢህአዴግ ጋር ዝምድና የለንም፡፡ ከህወሃት ጋር የጠላትነት ግንኙነት ነው የነበረን ህዝባችንን ሲጨፈጭፍ ነበር፡፡
እኔም አብዛኛውን የፖለቲካ ተቃውሞዬን… እነሱን በመታገል ነው ያሳለፍኩት፡፡ በዚህ ምክንያት አሁን ከህወሃት ጋር ጠላትም ወዳጅም አይደለንም፡፡ ባላንጣም አጋርም አይደለንም:: ህወሃት ተሸንፏል፤ ያሸነፍነውን ድርጅት በወደቀበት መቀጥቀጥ አልፈልግም፤ ከዛ ባለፈ አጋር ሊሆኑን አይችሉም፡፡ በዓላማም አንድ ልንሆን አንችልም፤ በዐቢይና በእነርሱ መካከል ያለው የአንድ ድርጅት የውስጥ ሽክቻ እንጂ የመርህ ጉዳይ ነው ብለን አናስብም፡፡ እኛ ያስቀመጥነውን የሽግግር እቅድ ቢከተሉ፣ ህወሃትና ዶ/ር ዐቢይ አይጣሉም ነበር:: ስለዚህ ህወሃት ለእኛ  አጋርም ባላንጣም አይደሉም፡፡ በእነርሱ እና በአብይ መካከል ያለው ሁኔታ በአገር ላይ የሚፈጥረው እንደምታ ስለሚያሳስበን አልፎ አልፎ ሀሳብ እንሰጣለን እንጂ ከህወሃት ጋር የመስራትም ሆነ የመዋጋት ፍላጎቱ የለንም፡፡ አሰራራችንም አይፈቅድም፡፡
ብዙ ጊዜ ለውጥ የለም ትላለህ፤ ለውጥ የለም ስትል ምን ማለትህ ነው?
በጠቅላይ ሚኒስትሩና በህወሃት መካከል የስልጣን ሽክቻ ነው ያለው፡፡ ከዛ ያለፈ የአመለካከት ወይም የመርህ ልዩነት ያለ አይመስለኝም፡፡ ህወሃት ሄደ እንጂ የኢህአዴግ ስርዓት እንደቀጠለ ነው፡፡ ሙስናው፣ አፈናው የቀጠለበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ስለዚህ በህወሃትና በዐቢይ መካከል ብዙ ልዩነት አላይም፤ በመሃከላቸው ያለው ነገርም ያሳስበኛል፡፡
በህወሃትና በብልፅግና ውስጥ የተፈጠረው አለመግባባት እንደ ትልቅ ነገር የሚታይ አይደለም፡፡ ህወሃቶችም የኢህአዴግን መፍረስ ለጦርነት ከበሮ የሚያዘጋጁበት ምክንያት አይታየኝም፤ ህወሃት እንደ አንድ ክልላዊ ፓርቲ ነው፡፡ በትግራይ ክልል ላይ ገዢ ፓርቲ ነው፡፡ እስከ ምርጫው ድረስ ማስተዳደሩ ይቀጥላል:: ምርጫውን ካሸነፈ በአዲስ መልክ እንደ ማንኛውም ፓርቲ ክልሉን እያስተዳደረ፣ በፌደራልም ደግሞ የክልሉን ድርሻ መቋደስ ነው፡፡
ወደፊት ኢትዮጵያ ውስጥ በክልሎች የተለያዩ ፓርቲዎች የሚያሸንፉበት፣ በፌደራል ደረጃ የተለየ ፓርቲ የሚያሸንፍበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ይህ ማለት አገር ይፈርሳል ጦርነት ይነሳል፤ ማለት አይደለም፡፡ ሽክቻዎች ፉክክሮች ይኖራሉ፤ ነገር ግን አገር ይቀጥላል፡፡ ስለዚህ እነ ዶ/ር ዐብይ በህወሃት ላይ የሚያደርጉት ዘመቻ ስሜት አይሰጥም፡፡ ህወሃትም ሰሞኑን በተለይ አስፋልት ላይ ላውንቸር ይዘው የሚዞሩት ነገር አይገባኝም፡፡ የጦርነት ፖለቲካ ለእኔ አስፈላጊነቱ አይታየኝም፡፡
የተጠቀምበትን ላፕቶፕ በማስረከብ የለውጡ ደጋፊ መሆንህን ገልጸህ ነበር… እንዴት በአንድ ጊዜ የለውጡ ተቀናቃኝ ሆንክ?
በወቅቱ ያንን ኮምፒዩተር ስሰጥ ለተምሣሌትነት ነበር፡፡ የእኛ አገር ፖለቲካ የትግል ነበር፤ ስለዚህ ከትግል ፖለቲካ ወደ እኩልነት መሄድ አለብን፤ ይሄ የሽግግር ወቅት ነው ማለት ፈልጌ ነው፡፡ ምክንያቶቼ ሶስት ነበሩ፤ አንደኛው ወጣቱ በዛን ጊዜ በጣም ድል አድርጎ የገነፈለበት ወቅት ስለነበር፣ ወጣቱን ለማረጋጋት እንፈልግ ነበር፡፡ ያኔ ኢትዮጵያ ውስጥ የመንግስት አቅም በጣም የተዳከመበትና ወጣቱ በጣም ስሜት ውስጥ የነበረበት ጊዜ ነው፡፡ ያንን ለማረጋጋት ነበር፡፡ እኛና መንግስት በተለያየ ጎራ ውስጥ የነበርን ብንሆንም፣ አሁን አገርን የማሻገር ስራ አብረን እንሰራለን የሚል ተስፋ መስጠት ፈልጌ ነበር፡፡ ሁለተኛው፤ ካለኝ ከፍተኛ ተፅእኖና በትግሉ ውስጥ ካለኝ ሚና አንፃር፣ ስልጣን ላይ ያሉ ወንድሞቻችን የነበራቸውን ስጋት ቀለል ለማድረግ ስለፈለኩም ነው፤ ከእንግዲህ በኋላ ‹‹እኛና እናንተ ባላንጣ አይደለንም፣ ልንረዳችሁ ነው የመጣነው እንጂ ልንወጋችሁ አይደለም፡፡ ስልጣናችሁን ልንደግፍ እንጂ ስልጣናችሁን ልንፈታተን አይደለም የመጣነው›› ብዬ ነው ኮምፒዩተሩን የሰጠሁት፡፡
በሶስተኛ ደረጃ ለአቶ ለማ ከፍተኛ ክብርና አድናቆት አለኝ፡፡ ለዚህ ለውጥ ከፍተኛ ዋጋ የከፈለ ሰው ነው፡፡ በወቅቱም በዝግጅቱ ላይ እንዲገኝ የጋበዝኩት እኔ ነኝ፤ ምስጋናዬን ክብሬን ለእሱ ማሳየት ስለፈለኩ ነው፡፡ ከዛ ወዲህ ለውጡ (ሽግግሩ) በታለመለት መልኩ አልሄደም፡፡ አቶ ለማም አቶ ገዱም ተገፍተው ወጡ ይሄንን ያሻግራሉ ያልናቸው እንደነ ዶ/ር ወርቅነህ ያሉ ሰዎች ተገፉ፡፡ እነሱ በተገፉ ቁጥር እነ ዶ/ር ዐቢይም አገርን ከማሻገር ይልቅ የራሳቸው የግል አዲስ የአመራር ስርዓት ወደ መገንባት ማዘንበላቸውን ሳይ፣ ‹‹እኛ ለዚህ አይደለም ወደ ሀገር ቤት የገባነው፤ እነርሱንም የደገፍነው፣ ሃገር ያሻግራሉ ብለን እንጂ አዲስ ስርዓት፣ የአንድ ፓርቲን የበላይነትን አፍርሶ የአንድ ግለሰብ መንግስት መመስረቱን ስለማንፈልግ፣ ይሄንን መጋፈጥ አለብን›› ወደሚለው ሔድን፡፡ በተለይ የተቃዋሚውን ሃይል አቅም ማጎልበት ለዚህ ወሳኝ ነው፤ ሽግግሩን ለማሳካት፡፡ በፊትም እነሱን ስደግፍ የነበረው ሽግግሩን ለማሳካት ነው፡፡ አሁንም ቢሆን ተቃውሞ የማደርገው ሽግግሩን ለማሳካት ነው፡፡ ይሄ ትግላችን ለኢትዮጵያ ህዝብም ሆነ ለኦሮምያ ማህበረሰብ በጣም ይጠቅማል ብዬ ስለማስብ ነው፡፡
ብልፅግናን የማትደግፍበት ምክንያቱ ይሄ ነው?
ብልፅግና ፓርቲ አህዳዊ ነው፡፡ የብሄር ፖለቲካ አያስፈልግም፤ ብሄሮች ራሳቸውን ማስተዳደራቸው ትክክል አይደለም፤ አህዳዊ የሆነ አደረጃጀት ነው የሚያስፈልገው፤ የተጠናከረ ማዕከላዊ መንግስት እንጂ የተጠናከረ ክልላዊ መንግስት አያስፈልግም፤ የክልሎች አቅም መዳከም አለበት፤ መመስረት ያለበት አንድ ወጥ ፓርቲ ነው፡፡ በክልል ያሉ ፓርቲዎች መዳከም አለባቸው… ነው የሚሉት:: ይሄ ደግሞ ለታገልኩለት ለኦሮሞ ህዝብም፣ ለታገልኩለት ለብሄር እኩልነትም አደጋ አለው:: እኔ እማምነው… ብዙ ታጋዮችም የሚያምኑት… ህዝቦች በቀዬአቸው ላይ ሙሉ የሆነ እራስን በራስ የማስተዳደር መብት ኖሯቸው፣ አገርን በጋራ ስልጣንና ሃብት ተከፋፍለው ማስተዳደር አለባቸው በሚል ነው፡፡ የብልፅግና ፓርቲ ግን ልክ እንደ ኢዜማ አይነት አመለካከት ነው ያላቸው፡፡ የተማከለ መንግስት አህዳዊ ስርዓት ነው የሚፈልጉት፡፡ ይሄንን ስርዓት እቃወመዋለሁ አንዱ እሱ ነው፡፡
ሁለተኛው ሽግግሩን ያደናቀፈ ነው፡፡ ወደ ምርጫ ስንሄድ፣ ይሄንን ሽግግር ያሻግሩናል ያልናቸው ‹‹ቲም ለማ›› የምንለው ቡድን ነው፤ ይሄ ቡድን እስከ ምርጫ ድረስ መርቶ፣ ሰላማዊ ምርጫ አካሂዶ ስልጣኑን ያስረክባል ብለን ነበር:: ግን በውስጡ ምስቅልቅልነት ነበረው በተለይ ብልፅግና የተባለውን ፓርቲ ለመመስረት ፓርቲው ውስጥ ከፍተኛ ምስቅልቅልነት በማምጣት፣ አገርንም ሽግግሩንም ለአደጋ ያጋልጣል ብለን ገና ሃሳቡ ህዝቡ ጋ ሳይደርስ… ለዶ/ር ዐቢይ ስንነግረው ነበር፡፡ አሁንም ቢሆን ያ የፈራነው ነገር ነው የመጣው፤ ከዚህ ጋር ተያይዞ ነው እንግዲህ ተቃውሞዬ የመጣው፡፡
ብዙ ጊዜ ‹‹ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ›› የሚሉትን ‹‹የኦሮሞ ጠላቶች ናቸው›› እያልክ ትቃወማለህ ይባላል…     
እኔ በርግጠኝነት፤ በእንደዛ አይነት መልኩ ተናግሬ የማውቅ አይመስለኝም፤ ነገር ግን ኦህዴድ (ኦዲፒ) በዳቦ ስሙ ብልፅግና የተባለው… እንደምናውቀው ለኦሮሞ ህዝብ የቆመ ድርጅት እንዳልሆነ፣ ትላንትና ከህወሃት ጋር በመወገን የኦሮሞ ታጋዮችን ጠባብ ብሄርተኛ በማለት በየእስር ቤቱ ሲያሰቃይ ሲያስገድል የነበረ፤ ኦሮሚያን ዘርፎ እያዘረፈ ለራሱም በልቶ ህወሃትን ሲቀልብ የነበረ ድርጅት ነው፡፡ ይሄ የሚደበቅ አይደለም፤ አሁንም ቢሆን ህዝቡ አደራ ሰጥቷቸዋል፤ ከህወሃት ጭቆና ስር እነሱን ነፃ አውጥቶ፣ አገር አሻግሮ አደራ ሰጥቷቸዋል፡፡  ያንን አደራ ነው የበሉት፤ የኦሮሞ ህዝብ የታገለለት ጠንካራ የፌደራል ስርዓት፣ እራስን በራስ የማስተዳደር ስርዓት እንዲደናቀፍ እየሰሩ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ነው ኦሮሞ አይደሉም እያልን የምንናገረው:: የኦሮሞን መብትና ጥቅም ትላንትናም አላስከበሩም፤ ዛሬም ለአደጋ እያጋልጡ ነው:: ኦሮሞ ስንል የኦሮሞ ህዝብ ብቻ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ጭቁን ህዝቦችም… በነገራችን ላይ ኦህዴድ ብቻ ሳይሆን የኦህዴድ ተመሳሳይ ብዙ ጨቋኝ ድርጅቶች አሉ፡፡ እነዛ ድርጅቶች ውስጥ የነበሩ ግለሰቦች የብሄራቸውንና የህዝባቸውን ጥቅም ከማስከበር ይልቅ የገዢያቸውን ጥቅም ሲያስጠብቁ የኖሩ ናቸው፡፡ አሁንም ቢሆን በህዝብ ነፃ ከወጡ በኋላ ከተላላኪነት ያላለፉ፣ ታማኝነታቸውን ለህዝባቸው ሳይሆን ለራሳቸውና ለባልንጀሮቻቸው ብቻ ያደረጉ ናቸው፡፡ በሌላ ወገን ታጋዮች፣ ሲታገሉ የነበሩ ድርጅቶች፣ ምሁራን፣ ወጣቶች ትላንትናም ለጥቅም ብለው ሳይሆን ለአንባገነን ሳይንበረከኩ፣ ስቃይ ሲደርስባቸው ቶርቸር ሲደረጉ ነበር፡፡ ዛሬም ሳይታለሉ በአንድነት ጠንክረው፣ የኦሮሞና ሌላውን ህዝብ ጥቅምና መብት ባማከለ መልኩ እንዲቀጥል በሚል የሚከራከሩ ናቸው፡፡
የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ ምንድነው?
የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ በርካታ ቢሆንም… በዋናነት ሶስት ናቸው፡፡ የማንነት ጥያቄ፣ የኢኮኖሚ ጥያቄና እራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ነው፡፡
የማንነት ጥያቄ ስንል ራሱ ሶስት ንኡሶች አሉት፤ አንደኛ የቋንቋ ጥያቄ ሲሆን የኦሮሞ ቋንቋ የተጨቆነ ነበር፤ በስንት ትግል ነው ትንሽ የተሻሻለው፡፡ ዛሬም ቢሆን የመንግስት ትኩረት የሌለው ስለሆነ ትኩረት ያሻዋል:: ቋንቋው በትምህርትና በተለያዩ መንገዶች እንዲያድግ እንፈልጋለን፡፡ ሁለተኛው የባህል ጥያቄ አለ፤ ለረጅም ጊዜ ታጥፎ (ተደብቆ) ነበር የቆየው:: ዛሬም ድረስ በየክልላችን የኦሮሞን ባህል ትውፊቶች የሚያሳዩ በጣም ጥቂት ነገሮች ናቸው የሚታዩት፡፡ ስለዚህ ከጭቆና ወጥቶ እንዲዳብር እንፈልጋለን፡፡ ሶስተኛው የታሪክ ጥያቄ ነው፤ የኦሮሞ ታሪክ የተዛባ፣ የተጣመመ አልፎም ተርፎ የተሰረዘ ሆኖ የቀረበ ነው፡፡ በአገራችን ታሪክ ውስጥ የኦሮሞ ታሪክም ጉልህ ሚና እንዲኖረውና የተንሸዋረረውና የተወላገደው እንዲስተካከል እንፈልጋለን፡፡ ስለዚህ በማንነት ጥያቄ ውስጥ የምናነሳው የቋንቋ፣ የባህል፣ የታሪክ ጥያቄዎች ናቸው፡፡
ሁለተኛው የኢኮኖሚ ጥያቄ ነው፡፡ ኦሮሚያ ብዙ ሃብት ያላት ናት፡፡ ከኢትዮጵያ አጠቃላይ አገራዊ ምርት ውስጥ ትልቅ ፐርሰንት ከኦሮሚያ ነው የሚወጣው፣ ወደ ውጪ የምንልከው አብዛኛው ምርት ከኦሮሚያ ነው የሚመጣው፣ ሰፊው ለም መሬት ኦሮሚያ ውስጥ ነው ያለው፡፡ ሆኖም ግን በንጉሱ ጊዜ በባላባቶች ተይዞ ህዝባችን ጭሰኛ ሆኖ ሲሰቃይ ነበር፡፡ በህወሃትም ጊዜ በኢንቨስትመንት ስም ህዝባችን ሲፈናቀል ነበር፤ ወጣቱ በከፍተኛ ደረጃ ተቸግሮ ስራ አጥነት ከመስፋፋቱ የተነሳ ከኢትዮጵያ ህዝብ ትልቁ እጅ ተሰዳጅ ከኦሮሚያ ነበር፤ ስለዚህ አሮሚያ ባላት ሃብት ላይ የኦሮሚያ ህዝብ የባለቤትነት ድርሻ እንዲኖረው እንፈልጋለን፡፡ የማዕድን ይሁን የማንኛውም መሬት ሃብት ለክልሉና ለህዝቡ ጥቅም መዋል አለበት፤ የሚል የኢኮኖሚ ጥያቄ አለ፡፡ ይሄንን ለማድረግ ደግሞ ህዝብን ያማከለ ፖሊሲና ስትራቴጂ መሆን መቻል አለበት፡፡ የሚወጡት ህግጋቶች ህዝብን የሚቦጠቡጡ ሳይሆን ህዝብን የሚያሳድጉ መሆን አለባቸው፤ በጤናም ሆነ በኢኮኖሚ በማንኛውም ደረጃ ክልሉ ወደ ኋላ የቀረ ስለሆነ ያለውን ኢኮኖሚ ለህዝቡ መሰረተ ልማት ማዋል መቻል አለበት፡፡  ሃገር ማለት ለእኛ ህዝብ ነው፡፡ ስለዚህ ሃገር ሲያድግ አብሮ ህዝብ ነው የሚያድገው፡፡ ባለፈው 27 ዓመት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አድጓል፤ ህዝቡ ግን እየደኸየ ነው የሄደው፡፡ ከዚያ ድህነት ውስጥ መውጣት አለበት የሚል ነው፡፡
ሶስተኛና የመጨረሻው፣ የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ፣ እራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ነው:: ይሄ ሁለት ነጥቦች አሉት፡፡ የመጀመሪያው ጥያቄ፣ በህገመንግስቱ መሰረት፣ የራስ አገዛዝ ነፃነት (autonomy) ማስተዳደር ነው፡፡ ይሄንን ስንል በተሾሙለት፣ በተላከለት አመራር ሳይሆን ህዝቡ ራሱ በመረጣቸው፣ በሾማቸው ግለሰቦች መተዳደር መቻል አለበት፡፡ ሁለተኛ፣ በፌደራል ስርዓት ውስጥ የቆዳ ስፋቱ ከፍተኛ እንደመሆኑ መጠን፣ በፌደራል ስርዓት ውስጥ የሚገባውን የስልጣንና የሃብት ክፍፍል ማግኘት አለበት ባይ ነን፡፡
ያለፉ የጭቆና ስርዓቶችን እያነሱ ማስታወስ ሕዝብን በሕዝብ ላይ እንዲነሳሳ ማድረግ አይሆንም ወይ?
ኦሮሞን የቦጠቦጠ የዘረፈ ብሄር የለም:: ኦሮሞን የቦጠቦጡት ከገዢው ስርዓት ጋር የተባበሩ፣ የውጪና የሃገር ውስጥ ባለሃብቶች ናቸው፡፡
እነዚህ ባለሃብቶች እነ ማናቸው?
ኦሮሞዎች አሉበት፣ ቻይናዎች አሉበት፣ አማራዎች፣ ትግሬዎች… ሁሉም አሉበት፡፡ ለምሳሌ ባሌ… አርሲ… ወለጋ… ላይ አብዛኞቹ መሬቶች ለህዝቡ ተመልሷል፡፡ ስለዚህ ትላንትና ህዝቡን ሳይወያይ ለህዝቡ አስፈላጊው ካሳ  ሳይሰጠው ነበር የተደረገው፡፡ ህዝቡ በራሱ ጊዜ ባደረገው ለውጥ እነዚህ ከስርዓቱ ጋር ሆነው አገር የዘረፉ ባለ ሃብቶች ለቀው የሄዱበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡
ሁሌም የኦሮሞን ጭቆና ብቻ ነው የምታጎላው፡፡ ሌሎች ብሄሮች አልተጨቆኑም ብለህ ታምናለህ ወይስ የምታገለው ለአንድ ብሄር ነው?
ኦሮሞነትን ልክ እንደ አማራነት፣ እንደ ሲዳማነት፣ እንደ ሌላው ብሄር ነው የማየው:: ኦሮሞ እዚህ አገር ያለ ብሄር ነው፤ ወጪ ወራጁ መንግስት ሲጨቁነው ሲበድለው የነበረ ህዝብ ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ህዝብ ማንነቱ መከበር አለበት፤ የራሱ ሃብት ባለቤት መሆን አለበት፣ እራሱ በመረጠው መንግስት መተዳደር አለበት፡፡ ለእኔ ኦሮሞነት ማለት የራሱን መብት የሚያስከብር፣ የሌላውን ማህበረሰብ መብት የሚያከብር ነው፡፡ የዛሬ አምስት አመት፣ አንቺ ያልሽው ትችት ሊሰራ ይችላል፤ ዛሬ ግን አይሰራም፡፡ የወያኔ ስርዓት በመውደቁ የኦሮሞ ህዝብ ብቻ አይደለም የተጠቀመው፡፡ ምናልባት እኛ ከተጠቀምነው በላይ የተጠቀመው ሌላ ማህበረሰብ ሊኖር ይችላል፡፡ ለምሳሌ እኛ ባደረግነው ትግል የፕሬስ ነፃነት በተሻለ መልኩ መጥቷል፡፡ እየተጠቀመበት ያለው በአብዛኛው የአማርኛ ተናጋሪ ሚዲያ ነው፡፡ ከነባሮ ቱምሳ ጀምሮ እነ ተሰማ ነዲ፤ ዘገየ አስፋው ናቸው መሬት ላራሹን በከፍተኛ ደረጃ ሲገፉ የነበሩት:: የጭሸኛ ስርዓት መፍረሱ ለደቡብ ህዝባችን ከፍተኛ ለውጥ ነው ያመጣው፡፡ የቋንቋን ጥያቄ በከፍተኛ ሁኔታ ሲጠይቅ የነበረው የኦሮሞ ታጋይ ነው፡፡ ህዝብ በራሱ ቋንቋ እንዲማር፣ መደረጉ ለኦሮሞው ብቻ አይደለም፣ ለሲዳማው፣ ለአፋሩ፣ ለትግራዩ… አትርፏል:: ስለዚህ ለኦሮሞነት መታገል የሌላውን መብት መግፋት አይደለም፡፡ ይሄ አሁን የሚነሳው ‹‹የኦሮሞ ባለሃብት ተጎዳ›› ሲባል የሌላውም ባለሃብት ይጎዳ ማለት አይደለም:: አንድ ባለሃብት ማንም ይሁን ማንም መዘረፍ የለበትም፤ መበዝበዝ የለበትም:: ስለዚህ ‹‹እኛ ታግለን አምጥተን›› ስል አዎ የህወሃትን ስርዓት በህዝብ ትግል ተገርስሷል:: ዛሬ ግን ያ ባለሃብት ያ ነጋዴ፤ ያ ጋዜጠኛ መጎዳት የለበትም፤ የመንግስት ኃላፊነት መሆን አለበት:: የሁሉንም መብት ማክበር እንጂ መብት መሸርሸር የለበትም:: ከሚሉት ጋር ነኝ፡፡ ከዛ ባለፈ የኦሮሞ ነጋዴ ይጠቀም፤ የትግራይ ነጋዴ ይጎዳ የሚለውን ፈፅሞ አላስበውም፡፡ ሊሆንም የሚችል አይደለም፡፡የሌላው መብት ሳይከበር የምትኖር ሃገር ለኦሮሞም አትጠቅምም፡፡
አዲስ አበባ ላይ ምርጫ ትወዳደራላችሁ አይደል? ከነዋሪው ጋር ውይይት አድርጋችኋል?
ሁሉም ቦታ እንወዳደራለን፡፡ አሁን እየሰራን ያለነው ራቅ ያሉ ክልሎች ላይ ነው፡፡ አዲስ አበባ ቅርብ ስለሆነች እንደርሳለን በማለት ነው እንጂ ውይይት ማድረጋችን አይቀርም፤ ቅርጫፍ ቢሮ አለን፡፡
አዲስ አበባ ላይ አተኩሮ የሚወዳደረው ‹‹ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ›› ፓርቲ እንደ ተፎካካሪ አያሰጋችሁም?
አያሰጋንም፤ የሚያሰጋን ነገር የለም:: በከፍተኛ ደረጃ ከህዝቡ ጋር እንወያያለን:: እኛ ሁሉም ጋ እንወዳደራለን፤ እናሸንፋለን ብለን እናስባለን፤ የማናሸንፍባቸው ቦታዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ምክንያቱም አንዳንዶች የድሮ ስርዓት ሁሉም ቦታ አሸነፍኩ ስለሚል እንደዛ ያለ ይመስላቸዋል፡፡ ነገር ግን አሁን እንደዛ የለም፤ ሁሉም ጋ የተለያየ ፓርቲ ሊሆን ይችላል የሚያሸንፈው፡፡ እኛ ማንም የትም ያሸንፍ፣ ከሁሉም ጋር አብረን ለመስራት ዝግጁ ነን፡፡ እንዴት እንስራ የሚለውን፣ እኛም እየሰራን ነው:: ሌላውም እየሰራ እንደሚሆን አምናለሁ፡፡


Read 17084 times