Saturday, 15 February 2020 12:29

ሲቪል ሰርቪሱና የለውጡ ሂደት

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

   የተሳካ ሀገር የሚኖረን የተሳካ ሲቪል ሠርቪስ ሲኖረን ነው

          በኢትዮጵያ የመንግሥት አገልግሎት (ሲቪል ሰርቪስ) ውስጥ የሚታዩ ችግሮች ምንድን ናቸው? ችግሮቹ እንዴት መቃኘት ይችላሉ? በሚሉና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕዝብ አስተዳደርና የልማት አመራር ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑትና፣ በድህረ ደርግ በተካሄደው የኢትዮጵያ የመንግሥት ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ለውጥ ሂደት ላይ በአማካሪነት የሰሩት እንዲሁም ሲቪል ሰርቪሱን በተመለከተ በርካታ ጥናቶችን ያደረጉት ዶ/ር ፈንታ ማንደፍሮ፣ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርገዋል፡፡


              ሲቪል ሰርቪስ ምንድን ነው?
አንድ መንግሥት ሶስት መሠረታዊ ክፍሎች አሉት፡፡ ሕግ አውጭ፣ ሕግ ተርጓሚና ህግ አስፈፃሚ፡፡ ሲቪል ሰርቪስ የምንለው በሕግ አስፈጻሚው ስር የምናገኘው መዋቅር ነው:: ሕግ አስፈጻሚ ስንል ፕሬዚዳንታዊ ሥርዓት ባላቸው፣ በፕሬዚዳንቱ የሚመራው ሲሆን እንደኛ ፓርላሜንታዊ ሥርዓት ያላቸው ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትር የሚመራና ከዚያ በታች በየደረጃው ባሉት የሚመራ ነው፡፡ ከወታደራዊ ክፍል ውጪ ያለውን ጠቅልለን ሲቪል ሰርቪስ ብለን እንገልፀዋለን፡፡ ሲቪል ሰርቪስ ለአንድ አገር ትልቅ ዋልታ ነው። በዋናነት ደግሞ በሙያተኞች የሚያዝ ቦታ ነው፡፡ የወጣን ሕግ ያስፈጽማል ይፈጽማል፡። የሕግ ምንጭም ይሆናል፡፡ ሲቪል ሰርቪስ ወሳኝ የመንግሥት ክንፍ ነው የሚባልበት ዋናው ጉዳይ በሲቪል ሰርቪሱ በአዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ ውስጥ የማይወድቅ የለም፡፡ ይሄ ማለት የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ አስተዳደር፤ በመንግሥት ሲቪል ሰርቪስ ቀልጣፋ አገልግሎት አሰጣጥ ሊሳለጥ ይችላል ወይም ደግሞ በመንግሥት ሲቪል ሰርቪስ አገልግሎት አሰጣጥ መንቀራፈፍ ምክንያት የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ራሱ ሊጎተት ሊሰነካከል ይችላል፡፡ ለዚህ ነው የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ የሲቪል ሰርቪሱ የመስታወት ገጽ ነው የሚባለው፡፡ ደካማ ሲቪል ሰርቪስ ካለ፣ ደካማ የግል ክፍለ ኢኮኖሚ ነው የሚፈጠረው። ይሄ ብቻ አይደለም፡፡ የበጎ አድራጎት ተቋማት ራሳቸው የሚጠበቅባቸውን ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲሰጡ፣ የሲቪል ሰርቫንቱን ሚና ጉልህ ነው:: በምሳሌ ባስረዳ፣ ንግድን እንውሰድ፡፡ ንግድ ከንግድ ፍቃድ አወጣጥ አንስቶ እስከ ግብርን መክፈል ያለው ሥርዓት  ቀልጣፋ ካልሆነ፣ የግሉ ሴክተር ብዙ ጊዜውን የሚያጠፋው የመንግሥትን አገልግሎት ፍለጋ ላይ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ብዙ ሀብቱን የሚያባክነው አገልግሎት ፍለጋ ላይ ይሆናል ማለት ነው:: ስለዚህ የሲቪል ሰርቪሱ ድርሻ እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ ሲቪል ሰርቪሱ በአንድ አገር ልማት ውስጥ ተፅዕኖ የማያሳድርበት ክፍል የለም፡፡
ሲቪል ሰርቪሱ ይሄን ሚናውን በአግባቡ እንዲወጣ በምን መልኩ ነው መደራጀት ያለበት?
በመጀመሪያ ደረጃ ሲቪል ሰርቫንቱ በችሎታው ብቻ ነው መመልመል ያለበት:: የሚጠበቅበትን ሚና ይጫወትም ዘንድ የተደራጀ አቅም ሊኖረው ይገባል፡፡ አቅም ሲባል ደግሞ ቴክኒካል አቅምና የስራ ልምድ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ቁርጠኝነት፣ ታታሪነት  ይከተላሉ፡፡ ነገር ግን ሲቀጠር፣ በመጀመሪያ ሳይንሳዊ አለማቀፍ መስፈርቶች ነው መጠቀም የሚገባው፡። እዚህ ተወዳድረው የገቡ ባለሙያዎች ደግሞ ወደ ላይ ሲያድጉ፤ የሥራ እድገት ሊያገኙ የሚገባው ባላቸው የፖለቲካ ውግንና ሳይሆን ባሳዩት ትጋት፣ ባሳዩት ቁርጠኝነት፣ ባላቸው ለሕዝብ ጥቅም ተቆርቋሪነት ተመዝነው ነው፡፡ እነዚህ መለኪያዎች ተቆጥረው ነው ግልጽ በሆነ መንገድ ሥራ ላይ መዋል ያለበት፡፡
በተለይ በእኛ አገር ሁኔታ የሲቪል ሰርቫንቱና የፖለቲካ ተሿሚዎች ድንበር እንዴት ነው የሚለየው?  
ድንበራቸው ግልጽ ነው፡፡ ሲቪል ሰርቫንት የሚመራው በፕሬዚዳንቱ ወይም በጠቅላይ ሚኒስትሩ በተዋቀረ ካቢኔ ነው። እዚህ ላይ ብዥታ ያለው፣ ሲቪል ሰርቪስ ሲባል፣ ምንም ፖለቲካ የማይነካው አድርጎ ማየት ነው፡፡ ይሄ ስህተት ነው፡፡ ሲቪል ሰርቫንቱ የሚመለመለው በብቃቱና በችሎታው ነው፤ በፖለቲካ ዝንባሌው ወይም አባልነት መሆን የለበትም፡፡ ደጋፊም ነቃፊም መሆን የለበትም፡፡ ነገር ግን የአሸናፊውን የፖለቲካ ሀይል ፖሊሲና ፕሮግራም ደግሞ አስፈጻሚ ነው፡፡ ለምሳሌ የአሜሪካ የሲቪል ሰርቫንት ታሪክ ከ250 አመት በላይ ነው፡፡ ነገር ግን ሪፐብሊካንና ዴሞክራቶች ስልጣን በተቀያየሩ ቁጥር ግን አይቀያየርም፤  ያው ነው፡፡ የመጣውን ሳይደግፍ ሳይነቅፍ፣ ፖሊሲና ፕሮግራሙን ያስፈጽማል። የሲቪል ሰርቪስ ተቋም በየጊዜው እየተገነባ የሚሄድ ነው፡፡ ሲቪል ሰርቪሱ አሸናፊው የፖለቲካ ሀይል ያመጣውን የፖለቲካ ፕሮግራም ለምን አስፈጽማለሁ ብሎ መለገም አይችልም፡፡ አይገባምም፡፡ አሁን በኢትዮጵያ የሚታዩት ብዥታዎች እነዚህ ናቸው። የፖለቲካ አባልነትን ከሲቪል ሰርቪሱ ማስፈጸም ጋር አቀላቅሎ ማየት አይገባም፡፡ አንድ የሲቪል ሰርቪስ ሰራተኛ የሆነ የፓርቲ አባል ግን የፓርቲ ፕሮግራሙን በተቀጠረበት አገልግሎት ሰጪ መሥሪያ ቤት ውስጥ የመንግሥትን ሃብትና ጊዜ ተጠቅሞ መፈጸም ግን ስህተት ነው፡፡
በአገራችን የሲቪል ሰርቪስ ሥርዓት ውስጥ የሚስተዋሉ ዋና ዋና ችግሮች ምንድን ናቸው?
በነገራችን ላይ በኢትዮጵያ የሲቪል ሰርቪስ ሥርዓት ውስጥ የሚታዩ ችግሮች የቅርብ ቀን አይደሉም፡፡ አንዱ መሠረታዊ ችግር፣ የሲቪል ሰርቪሱ ፖለቲከኛ እንዲሆን የማድረግ አባዜ ነው:: ሲቪል ሰርቫንቱ የፖለቲካ አራማጅና የፖለቲካ ድርጅት አባል ሆኖ፣ ዩኒፎርም ለብሶ፣ የአንድ ፓርቲ አባል እንዲሆን የተጀመረው በደርግ ሥርዓት ነው፡፡ የደርግ ሥርዓት ምንም አይነት የነፃ የሲቪል ሰርቪስ ሥርዓት ክፍተት እንኳ ሳይተው ነው በግልጽ በፊት ለፊት ዩኒፎርም አስለብሶ ከፖለቲካ ጋር ቀላቅሎት የነበረው:: የአገሪቱን የሲቪል ሰርቪስ ሥርዓት በሰፊው ያበላሸውና ባህሉን የለወጠው የደርግ ሥርዓት ነው፡፡ ያ ባህል ከፍተኛ ጉዳት አድርሶብናል:: ሲቪል ሰርቫንቱ ከዚያ በኋላ በችሎታዬ አድጋለሁ የሚለውን መተማመን ከውስጡ አውጥቶ በፖለቲካ አባልነት ነው ማድገው ብሎ እንዲያምን አድርጎታል፡፡ በዚያው ልክ የሲቪል ሰርቪሱ ሥርዓትም ይሄን ባህል ይዞ ቀጥሏል:: ኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላም የቀጠለው ችግር ይሄ ነው፡፡ በተለይ በለውጡ ወቅት አካባቢ የኢትዮጵያ የሲቪል ሰርቪስ ሥርዓት ስንክልክል ያለበትና ግራ የተገባበት ነበር፡፡ ኢሕአዴግ በወቅቱ ከደርግ ሥርዓት ጋር ወግነህ ነበር ያለውን ጠራርጎ ከሲቪል ሰርቪሱ ሲያስወጣው ነበር፡፡ ስለዚህ ሲቪል ሰርቫንቱ በወቅቱ ተጠቂ ነበር ማለት ነው፡፡ ይሄ እንግዲህ የሲቪል ሰርቪስ ተቋምን የማስቀጠል ባህል አለመኖሩን አመላካች ነው፡፡ አሜሪካውያን መንግሥታት ሲለዋወጡ ሲቪል ሰርቫታቸውን አልቆረጡትም፡፡ በሌላ በኩል፤ ኢሕአዴግ ሲቪል ሰርቪሱን ከፖለቲካ ጋር አቆራኘው። እድገትን በፖለቲካ ታማኝነት አድርጎ ሲቪል ሰርቪሱ ወይም የሕዝብ አገልግሎት በመሀል ተዘነጋ። ይሄ ነው እንግዲህ ዋነኛ ችግር ሆኖ የዘለቀው፡፡
አሁን በመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ ወይም በሲቪል ሰርቪሱ ላይ የሚስተዋለው ችግርስ ከምን የመነጨ ነው?
ይሄ አሁን እየተደረገ ያለው ለውጥ ከዘውድ ሥርዓት ወደ ደርግ፣ ከደርግ ወደ ኢሕአዴግ ካደረግናቸው ሽግግሮች በባህሪው የተለየ ነው:: የፖለቲካ ሽግግር ባህሪውም ይለያል፤ የሲቪል ሰርቪሱ ሽግግር ላይም ይለያል፡፡ ቀደም ብሎ የነበሩት ሁለቱ ሽግግሮች ማለትም የደርግም ሆነ የኢሕአዴግ አፍርሶ በመስራት ላይ የተመሰረቱ ናቸው፡፡ ይሄኛው ግን ከውስጥ የመነጨ ለውጥ ነው፡፡ የሕዝብ ከፍተኛ ትግል የተካተተበት ነው፡፡ በነገራችን ላይ ሁሉም ለውጦች በሕዝብ ተሳትፎ ነው የመጡት፡፡ እኔ እንደ አንድ የሕዝብ አስተዳደር ባለሙያ ሁኔታውን ስረዳው፣ ለውጦቹ በሙሉ በሕዝብ ተሳትፎ የታጀቡ ብቻ ሳይሆኑ ሕዝብ ከፍተኛ ዋጋ የከፈለባቸው ናቸው፡፡ አሁንም ባለው ለውጥ የሕዝብ ተጋድሎ ዋናውን ድርሻ ይይዛል፡፡ ይሄ ለውጥ ባህሪው የተለየ ነው በምንልበት ጊዜ፣ ሥርዓቱን አፍርሶ በመስራት ሳይሆን፣ የነበረውን ሥርዓት ችግሮች በማረም፣ የነበረውን በጎ በማስቀጠል ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ይሄ ለውጥ በዚህ መልኩ ቢመራም፣ በኢሕአዴግ ሥርዓት 27 ዓመት የፖለቲካ አባል ሆኖ የነበረ ሲቪል ሰርቫንት ብዙ ነው። ስለዚህ   በሲቪል ሰርቪሱ ውስጥ የዚህ አይነት የፖለቲካ ዝምድና የነበረው ሲቪል ሰርቫንት ለውጡን በሙሉ ልቡ እኩል ተቀብሏል ወይ? የሲቪል ሰርቪሱ አንዱ ፈተናው ይሄ ነው፡፡
በከፍተኛ የፖለቲካ ወገንተኝነት ውስጥ የኖረ በፖለቲካ ወገንተኝነቱ እድገት ሲያገኝ የነበረ፣ ጥቅም ሲፈልግ የነበረ አሁን ለውጥ መጥቶ ሌላ ድባብ ሲያመጣ ብዙ መመሠቃቀል የሚጠበቅ ነው፡፡
አሁን ሲቪል ሰርቪሱ ውስጥ ያለው ውስጣዊ ተቃውሞ በፖለቲካ ወገንተኝነት ውስጥ ሆኖ ሲያድግ የነበረ ሃይል አሁን የለውጡን ባቡር ካልተሳፈረ ለለውጡ እንቅፋት ነው የሚሆነው ማለት ነው፡፡ ለውጡ የገጠመው የሲቪል ሠርቪስ አንዱ ፈተና ይሄ ነው፡፡
ለውጡን እስከታች ለማውረድ አስቸጋሪ ያደረገውም ይሄ ሁኔታ ነው፡፡
ሲቪል ሰርቫንቱ ጋ ያለው ጉራማይሌነት ለውጡ እንደፈለገው እንዳይሄድ አድርጐታል፡፡
ይሄ ችግር እንዴት ነው መስተካከል የሚችለው? የኢትዮጵያ የሲቪል ሰርቪስ ስርአትን እንዴት ነው ሊመራ የሚገባው?
በመጀመሪያ ደረጃ የኢትዮጵያ የሚባል የተለየ ሲቪል ሰርቪስ የለም፡፡ አለም የሄደበትና ጠንካራ ሲቪል ሰርቪስ የገነባበት መንገድ አለማቀፋዊ እሣቤን ይዞ ነው፡፡ ጠንካራ ሲቪል ሰርቪስ የሚገነባው አቅምን ችሎታንና ቁርጠኝነት፣ ለህዝብ ተቆርቋሪነትን መሠረት አድርጐ ሲዋቀር ነው፡፡
ይሄን አይነት ተቋም መገንባት ነው የሚያስፈልገው፡፡ አሁን ያለውን ሁኔታ ለማስተካከል አንደኛ ፖለቲከኛ ሆኖ መቀጠል የሚፈልገውን ወደ ፖለቲካው አለም ለይቶ ማቀላቀል በአንፃሩ በሲቪል ሰርቫንትነቱ የሚቀጥለውን ደግሞ በአቅሙ እና በችሎታው እንዲወዳደርና እንዲመደብ ማድረግ ነው፡፡ ሰው በማይችለው በማይመጥነው ቦታ ላይ ተመድቦ ካለ እንደገና በሚችለውና በሚመጥነው መመደብ ያስፈልጋል፡፡ ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ መሆኑን በዚህ ሂደት ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስን እንደገና አፍርሰን መስራት ስለማይጠበቅብን አሁን ያለውን ሃይል በአቅምና በችሎታ፣ በህዝብ ተቆርቋሪነት እንዲመደብ ማድረግ ነው አንዱ ማስተካከያ መንገድ፡፡ መንግስትም አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን በባለሙያዎች የመሙላት ሂደት አጠናክሮ መጠቀል አለበት፡፡ አንድ ባለሙያ የሚደግፈው የሚነቅፈው የፖለቲካ ፕሮግራም ሊኖር ይችላል፡፡ ነገር ግን አሁን በተመደበበት ቦታ ሆኖ የሚነቅፈውን የፖለቲካ ፕሮግራም እያስፈፀመ ከሆነና ፖለቲካውን ለመጉዳት ስራውን የሚበድል ከሆነ ህዝብን እየጐዳ ነው ማለት ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ህዝብን ማማረር ነው፡፡ እንዲህ አይነቱ ለግል የፖለቲካ ፍላጐት ሲባል ህዝብን በአገልግሎት በድሉ አማሮ ወደ ነውጥ እንዲሄድ የማድረግ ስነልቦና መስተካከል አለበት፡፡ መታከም አለበት፡፡ ህዝብን በአገልግሎት አማሮ ወደ አመጽ መግፋት ነውር ነው፡፡ የአገልግሎት ቃል ኪዳንን መብላት ነው፡፡
የአገልግሎት አሠጣጥ ደካማነት በኛ ሀገር ተጨባጭ ሁኔታ ህዝብን ለአመጽ የመግፋት አቅም ይኖረው ይሆን?
አዎ ሊኖረው ይችላል፡፡ ምክንያቱም ዜጐች የሚያውቁት መንግስትን ነው እንጂ እያንዳንዱን ግለሰብ አገልግሎት ሰጪ አይደለም፡፡ ስለዚህ የሚያማርሩት መንግስትን ነው፡፡ ህዝባዊ ሮሮዎች በተለያየ መንገድ እየተጠራቀሙ ሲሄድ ከሌሎች ነገሮች ጋር ተደማምረው አመጽ ነው የሚፈጥሩት፡፡ ባለፈው ለለውጥ ምክንያት የሆነው አመጽ እኮ የፖለቲካ ጥያቄ ብቻ አልነበረም ዜጐች የሚፈልጉትን ጥራት ያለው አገልግሎት የማግኘት ችግርም ጭምር ነው:: ሲቪል ሰርቪሱ የአመጽ ምንጭ እንዳይሆን መንግስት ደጋግሞ ማሠብና ጠንካራ ስራ መስራት አለበት፡፡
ይህቺ ሃገር ተሻግራ ተስፋ የምናደርግባት፣ ልጆቻችን ስደት የማይናፍቁባት ሀገር ለመገንባት እንችል ዘንድ እኛ ዛሬ በምንሰጠው አገልግሎት ላይ፤ እኛ ዛሬ በምናስቀምጠው የመሠረት ድንጋይ ላይ ይሆናል እንጂ በአንድ ቀን ተክቦ ያደገ ሀገር የለም፡፡
የእያንዳንዱ ዜጋ ጥረት ፍሬ የሚያፈራው ሲቪል ሠርቪሱ ሲስተካከል ነው፡፡ መልካም ሲቪል ሠርቪስ መፍጠር ካልቻልን እንደ ሀገር ማደግ አንችልም፡፡ ተሠነካክለን ነው የምንቀረው፡፡
በምርጫ ወቅት እሱን ተንተርሶ በሚፈጠሩ ችግሮች ሲቪል ሰርቪሱ ምን አይነት ኃላፊነት ነው የሚጠበቅበት? እንዴትስ ነው መተዳደር ያለበት?
የሲቪል ሰርቪስን ነፃ ማድረግ ጥቅሙ በእንዲህ ያለ ወቅት ነው፡፡ ሲቪል ሠርቪሱ ነፃ ሆኖ የአሸናፊውን ፓርቲ ፕሮግራም ሲያስፈጽም የቆየ ፓርቲ ነው፡፡ ይሄን ሲያደርግ በመርህ የፖለቲካ ውግንናን ይዞ አይደለም፡፡ በምርጫ ወቅትም ተመሳሳይ ነው መሆን ያለበት፡፡ ለምሣሌ የአሜሪካ ሲቪል ሰርቪስ ዲሞክራቶች እና ሪፖፕሊካኖች ጐራ ለይተው ሲነታረኩ አርፎ ስራውን ነበር የሚሠራው በምርጫ ስልጣን ሲቀያየሩም ሲቪል ሰርቪሱ አይናወጥም አርፎ ስራውን ነው የሚሠራው፡፡ የኛም ሀገር ሲቪል ሰርቪስ የምርጫ ጊዜና የምርጫ ውጤትን ተከትሎ የሚመጡ የፖለቲካ አለመግባባቶች የሚናድ መሆን የለበትም፡፡
አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በሙሉ እንደወትሮው ነው አገልግሎታቸውን መቀጠል ያለባቸው፡፡ ሲቪል ሠርቪስ የተቋቋመው ለዜጐች አገልግሎት ነው፡፡ የምርጫ ወጀብን ተከትሎ መወዛወዝ የለበትም፡፡
በኛ ሀገር ነባራዊ ሁኔታም ሲቪል ሰርቪሱ በቀጣይ ምርጫ ውስጥ ድርሻ እንደሌለው የሚገነዘብበትን መንገድ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ለማንም የፖለቲካ ሃይል ውግንና እንዳይኖረው፣ ምንም ይፈጠር ምንም ስራውን ተግባሩን ከማከናወን ውልፍት እንዳይል ከወዲሁ ስራ መስራት ያስፈልጋል፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ ምን አይነት የሲቪል ሠርቪስ ስርዓት ነው መፈጠር ያለበት?
ኢትዮጵያ የሁላችንም ሀገር ናት፡፡ እንዲህ ሲባል የእያንዳንዳችን የግለሰቦች ነች ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ በእኩልነት በፍትሃዊነት ያለ አድልኦ ሠርተን የምናድርባት፤ ልጆቻችን ተምረውም ማዕረግ የሚያዩባት፣ ወገኖቻችን የበላኝ አሞራ ይብላኝ ብለው የማይሰደዱባት ሀገር ለማድረግ የሁላችንም ኃላፊነት ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
የሁላችንም ኃላፊነት ነው ስል የእያንዳንዱ ሲቪል ሠርቫንት ኃላፊነት ማለቴ ነው:: ሁላችንም በዚህ ሂደት ላይ የምናደርገው አሉታዊ አስተዋጽኦ ችግር ውስጥ የሚከተን ይሆናል፡፡ በጐ አስተዋጽኦዎችን ደግሞ አሁን ካለንበት ተስፋ ወደምናደርግበት ከፍታ ለመሄድ እያንዳንዳችን ጠጠር ብናበረክት ትልቅ ተራራ ማቆም ይቻላል፡፡
ስለዚህ አገልግሎት የሁላችንም መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡ ሁለተኛ ደግሞ ሲቪል ሰርቪስ ውስጥ ያለ ሰው ብዙ ጊዜ ራሱም ከሲቪል ሰርቪሱ ተጠቃሚ እና ተጐጂ አድርጐ አያይም፡፡ እኔ አስተማሪ ነኝ፡፡ ስለ መሬት ጉዳዩ መሬት አስተዳደር እሄዳለሁ፡ ለጤና ጉዳይ ሆስፒታል እሄዳለሁ ስለትምህርት ጉዳይ የልጆች ት/ቤት እሄዳለሁ፡፡ ይሄን የአስተማሪነት አገልግሎት ፈልገው ለሚመጡ ደግሞ አገለግላለሁ፡፡ እያንዳንዱ በዚህ ግልባጭ ማየት ቢቻል መልካም ነው፡፡ እኔ አስተማሪነቴን በአግባቡ ባልወጣ የኔን ሙያ ፈልገው በመጡት ላይ ችግር እፈጥራለሁ፡፡ በዚያው መጠን እኔ ደግሞ ብዙ አገልግሎት ከብዙ ተቋማት ፈልጌ ሄጄ ባጣ በብዙ እጎዳለሁ፡፡
የመንግሥት አገልግሎት ጉዳይ የመንግሥት አቋምን ማገልገል ጉዳይ አድርጎ መመልከት መቅረት አለበት፡፡ የሕዝብና የአገር አገልግሎት ነው ብለን አምነን መቀበል አለብን፡፡ የተሳካ አገር የሚኖረን የተሳካ ሲቪል ሰርቪስ ሲኖረን ነው፡፡ የተሳካ ልማት የሚኖረን የተሳካ ሲቪል ሰርቪስ ሥርዓት ሲኖረን ነው፡፡ ፖለቲከኞችም ሲቪል ሰርቫንቱም ይሄን መረዳት አለባቸው፡፡
ባለፉት ዘመናት የግል ዘርፍ ለሲቪል ሰርቫንቱ መበላሸት አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ የሚገባውን አገልግሎት በተገባው መንገድ ማግኘት ሲችል ገንዘብ ስላለው ብቻ በገንዘቡ አገልግሎትን ሲገዛ ነበር፡፡ ስለዚህ ገንዘብ የሌለውና መክፈል ያልቻለው አንደኛ ወረፋ ሲጠብቅ ይከርማል ሁለተኛ ገንዘብ ስለሌለው የተቀላጠፋ አገልግሎት ማግኘት አቅቶት ተሰነካክሎ ይቀራል፡፡ ስለዚህ ገንዘብና አገልግሎት መራራቅ አለባቸው፡፡ አሁን ላይ መንግሥት የጀመረውን ሲቪል ሰርቪሱን በሙያተኛ የማደራጀት ተግባርን በርትቶ መቀጠል አለበት:: ይሄን በርትቶ መስራትና ማስቀጠሉ ተስፋ ለምናደርገው ለውጥና የመሻገር ሂደት እውን ለማድረግ ቁልፍ መሆኑን ተረድቶ ማስቀጠል አለበት፡፡ ጅምሮቹ ተጠናክረው ከቀጠሉ ጥሩ የሲቪል ሰርቪስ መገንባት እንችላለን የሚል ተስፋ አለኝ፡፡     


Read 2923 times