Saturday, 30 June 2012 12:25

“የአባቴ ሕልም ወደ ቤተ-መንግሥት፣ የእናቴ ሕልም ወደ ቤተ-ክህነት፣ የእኔ ሕልም ወደ-ኪነት ያመራሉ”

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(0 votes)

ባለፈው እሁድ ሰኔ 17 ቀን 2004 ዓ.ም በሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን ሥራዎችና ግለ-ሀሳብ ላይ የውይይት መድረክ ያሰናዳው ሚዩዚክ ሜይዴይ፤ ለውይይቱ መነሻ የሚሆን ዳሰሳ እንዲያቀርቡ የጋበዛቸው አርክቴክት ሚካኤል ሽፈራው “አርክቴክት ሆነህ ወደ ኪነ ጥበቡ ሠፈር ምን አመጣህ?” ብለው ለሚጠይቁ መልስ ይሆናል ያሉትን በመግለጽ ነበር ንግግር የጀመሩት፡፡ “ምሥጢረኛው ባለቅኔ” በሚል ርዕስ የሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን ሥራዎች ላይ ትኩረት ያደረገ መጽሐፍ ያሳተሙት አርክቴክት ሚካኤል ሽፈራው፤ ሰው በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረ በመሆኑ ባለ ሙሉ ነፃነትና በሁሉም ቦታ የመገኘት መብት ያለው መሆኑን አመልክተው፤ የኑሮ ጉዳይ ሆኖ ግን የምህንድስና፣ የኪነጥበብ፣ የፖለቲካ፣ የስፖርት፣ የንግድና የመሳሰሉት ሠፈሮችን ፈጥረን ለልዩነት በር ከፍተናል ብለዋል፡፡

ወጥ የሚሰራው ለወጥ ቤት ሰዎች ብቻ እንዲቀርብ ታስቦ እንዳልሆነው ሁሉ፣ በምህንድስና ሠፈር ሆኜ የተረዳሁትን የፀጋዬ ገ/መድህን ሥራዎች ላይ ለውይይት የሚሆኑ ሀሳቦችን አቀርባለሁ ያሉት አርክቴክት ሚካኤል፤ ከወጣትነታቸው ጀምሮ በሎሬት ፀጋዬ ሥራዎች ይመሰጡ እንደነበር ጠቁመዋል፡፡ ሆኖም በኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ታሪክ ውስጥ የሎሬት ፀጋዬ ጉዳይ አወዛጋቢ ነው፡ ውስብስቡና አወዛጋቢው ነገር የእኛም ጉዳይ ስለሆነ እንወያይበታለን ብለዋል፡፡

እኔን ጨምሮ በደርግ ዘመን ብዙ ወጣቶች ለሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን ጥላቻ ነበረን፡፡ የጥላቻችን መነሻና ምክንያቱ የፀጋዬ ሥራዎች ምስጢር አዘል፣ ከባድና ጠንካራ ናቸው፡፡ ይህን ዕውቀትና ችሎታውን የዘመኑን ችግር ለመግለጽ ለምን አልተጠቀመበትም የሚል ነበር፡፡ እኛን ተጭኖን የነበረው ሥርዓት እሱንም ተጭኖት ይሆናል፡፡ ወደ በኋላ ላይ የፀጋዬን ሥራዎች መመርመር ስጀምር ግን ጩኸታችንን ሊጮህ ሞክሮ እንደነበር መረጃ አገኘሁ፡፡

“ሀሁ ወይም ፐፑ” በሚል ርዕስ ጽፎ በ1984 ዓ.ም ለዕይታ ያበቃው ቴአትር ትዕይንት አንድ የሚጀምርው “…ጀግና አባቴ፤ ገባ ጉባኤ እሚሉት መሀል ክንፍና ጥፍሩን እንደንሥር አናፍሮ፡፡… ተንደረደረ፡፡ ከመድረክ ማዶ ዘሎ ጉባኤ እሚሉት መሀል ዋኘ፡፡ ተዋነየ፡፡ ግን፣ ግን ወዲያውኑ “እግዚኦ የሌባው ብዛት!” አለና ሮጦ ተዋናይቱ ቀሚስ ሥር ተወሸቀ፡፡ ፈራ! በሌባው ብዛት ተንቀጠቀጠ፡፡ ተርበተበተ…” በሚል ቃለ ተውኔት ነው፡፡

በ1984 ዓ.ም በቀረበው “ሀሁ ወይም ፐፑ” ቴአትር ላይ የተጠቀሰው ይህ ታሪክ “ዚቀኛው ጆሮ” በሚል ርዕስ በሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን ተደርሶ፣ በ1977 ዓ.ም የኢሠፓ ምሥረታ ዕለት በኢሠፓ አዳራሽ (ጉባኤ አዳራሽ) ታግቷል፡ ይህን በማድረጉም ማስጠንቀቂያ ደርሶታል “በየት በኩል ዞርክና ደሞ ያን ሀሁ ፊደልህን፣ ዳግመኛ ደገምክብን?!” ተብሏል፡፡

በ1929 ዓ.ም በጊንጪ ተወልዶ በልጅነቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ጽፎ ያዘጋጀውን ቴአትር ለሕዝብ ሲያቀርብ ከተመልካቾቹ አንዱ አፄ ኃይለሥላሴ እንደነበሩ ጠቅሶ፤ ፀጋዬ ገ/መድህን በወቅቱ ከንጉሡ ሽልማት ማግኘቱን በመግለፅ፤ ስለ ሎሬት “ጥሬ መረጃዎች”ንም አቅርበዋል፡ በዊንጌት፣ በንግድ ሥራ ኮሌጅ፣ በቺካጎ፣ በለንደንና በፈረንሳይ የተልዕኮ ትምህርትን ጨምሮ የተለያየ ዕውቀት ገብይቷል፡፡ የብሔራዊ ቴአትር ቤት ሥ/አስኪያጅ ሆኗል፡ የባህል ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር ደረጃ ላይም ደርሶ ነበር፡፡

“የአባቴ ሕልም ወደ ቤተ-መንግሥት፣ የእናቴ ሕልም ወደ ቤተ-ክህነት፣ የእኔ ሕልም ወደ-ኪነት ያመራሉ” ይል የነበረው ፀጋዬ ገ/መድህን፤ ወደ ወላጆቹ ሕልም በከፊል ወደ ራሱ ሕልም በቅርበት ደርሷል ያሉት አርክቴክቱ፤ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን ቴአትርን በለንደን ሮያል ኮሌጅ የተማረ ቢሆንም ቴአትሮቹን ስናያቸው ከተለመዱት ቴአትሮች ጋር የማይናበቡ ናቸው፡፡ ለቴአትር አላባዊያን የሚጨነቅ አይመስልም፡፡ ግን ደግሞ አዳዲስ ነገሮችን ፈጥሮ ያሳየናል፡፡ ፀጋዬና ሥራዎቹ የሚያወዛግቡት አንድም በዚህ ነው፡፡ ሌሎች አወዛጋቢ ጉዳዮችም አሉት፡፡

ሁላችንም ስለ ኪነ ጥበብ ሰዎች ስናስብ ሌሎች የማይደፍሩትን ደፍረው ማየትን እንመኛለን፡፡ ምንም ዓይነት ነውር ልናይባቸው አንፈልግም ያሉት አርክቴክት ሚካኤል ሽፈራው፤ በሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን ዙሪያ የተከሰተው አወዛጋቢው ጉዳይ ከዚህም አንፃር መፈጠሩን ጠቁመዋል፡፡

ፀጋዬ የእውነትን መንገድ እስከ መጨረሻው ለመጓዝ ይጥራል፡፡ ሆኖም ይሸነፋል፡፡ ሰው ፃድቅ አይደለም፡ ለጽድቅ ቅርብ የሆነው የመጽሐፍ ቅዱሱ ንጉሥ ዳዊት እንኳን የወታደሩን ሚስት አፍቅሮ ያልተገባ ብዙ ጥፋት በመስራት፣ ከእውነት መንገድ ለመራቅ ምክንያት እንደሆነው በምሳሌነት ጠቅሰውታል፡፡

ንጉሥ ዳዊት በመጨረሻ ወደ ንስሐ እንደተመለሰው ሁሉ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህንም “ሕይወት ቢራቢሮ” እና መሰል ግለ ሒስ ግጥሞችን እየፃፈ “ከውድቀቱ ለመነሳትና እውነታን ለመጨበጭ በሕይወት ውስጥ የሚገጥመንን ውጣ ውረድ፣ መውደቅና መነሳት፣ ደስታና ሀዘን … አመልክቷል፡ እውነትም አንፃራዊ መሆኗን በ”እሳት ወይ አበባ” የግጥም መጽሐፉ መግቢያ መግለጹን አርክቴክት ሚካኤል ሽፈራው ገልፀዋል፡፡

ፀጋዬን በጥልቀት ለማወቅ በጣራችሁ ቁጥር ራሳችሁን በጥልቀት ታውቃላችሁ ያሉት አርክቴክቱ፤ ሎሬት ፀጋዬ በሕይወትም በሥራዎቹም እንደማንኛችንም የስጋዊና የመንፈሳዊ ጦርነቶች ውጤት ሆኖ ታገኙታላችሁ፡፡ “ሕይወት ቢራቢሮ” ግጥሙ የሰው ልጆች እንደ ዘመኑ ሁኔታ መለዋወጣቸውን ያመለከተበት ነው፡፡ በዚህ እውነታ ውስጥ ብዙ ሰዎች እንገኛለን፡፡ “አዋሽ” እና “ክልስ-አባ-ልበ-እግረኛ” የሚለው ግጥሙም በተመሳሳይ መልኩ ስለ ማንነት ነው የሚሞገትበት፡፡

ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን ቴአትሩን በማዘመን፣ ምሳሌያዊና ሕልማዊ አቀራረብን በመጠቀም በአገራችን የቴአትር ታሪክ ጀማሪ ሊባል ይችላል ያሉት አርክቴክቱ፤ ያለፉ ጀግኖችን ሥራና ታሪክ ለአዲሱ ትውልድ በማስተዋወቅ አያቶቻችሁ፣ አባቶቻችሁ፣ እናቶቻችሁ … ይህንን ይመስሉ ነበር ብሎ ለማሳየት ተግቷል ሲሉ አብራርተዋል፡፡

እንግሊዛዊያን ሳይቀሩ በቅጡ ያልተረዱትን ሼክስፒርን ወደ አማርኛ የተረጎመው ሎሬት ፀጋዬ፤ ብዙ ሰዎች የተረዱት አይመስለኝም ያሉት አርክቴክቱ፤ እኔም አንድትወዱት ሳይሆን እንድትረዱት በሚል ነው ይህን አጭር ገለፃ ያቀረብኩት በማለት ሲያጠቃልሉ የተለያዩ አስተያየትና ጥያቄዎች ቀረቡ፡-

ለእኔ ፀጋዬ ገ/መድህን የገባው ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ ስራዎቹ ኢትዮጵያ ላይ ትኩረት ያደረጉ ናቸው፡፡ ፀጋዬ ተኪ አላገኘም፡፡ የሚተካው መጥፋቱ ብቻ አይደለም የሚያሳዝነው፡፡ ያልታሰበ፣ ያልተዘራ እየበቀለ ነው፡፡ ፀጋዬ በአፄ ቴዎድሮስ እንድንኮራ ነው ያቀረበልን፡፡ አሁን ከፀጋዬ በተቃራኒ የሚያስብ ትውልድ እየተፈጠረ ነው፡፡

ፀጋዬ በንግግሮቹ እያናደደኝ የጽሑፍ ሥራዎቹን እያየሁ እገረም ነበር፡፡ የሚጽፈው እየደማና በድካም ነው፡፡ ለዚህም ነው ሥራዎቹ ጉልበት ያላቸው፡፡ ጽሑፍ አቅራቢውም ጥሩ ተመልክቶታል፡፡ በዚህ አገር ሐውልት ሊቆምላቸው ከሚገቡ ሰዎች አንዱ ፀጋዬ ነው፡፡

የኪነ ጥበብ ሥራ በቀላሉ እንዲቀርብ ነው የሚመከረው፡፡ የፀጋዬ ገ/መድህን ሥራዎች ግን ለመረዳት ከባድ የሚባሉ ናቸው፡፡ ሌላው ችግር ፀጋዬ ዓለም አቀፍ ተደራሽነትን ዓላማ አድርጎ የሚሰራ አይመስልም፡፡

ፀጋዬ ቴአትር አጥንቶ የተማረውን በተግባር ላይ ለማዋል ያልፈለገበት ምክንያት ምንድነው? ከተማረው ውጭ መስራትን ለምን ፈለገ? በትምህርቱ አያምንበትም ነበር?

ስለ ቀድሞ ዘመን የፀጋዬ ገ/መድህን ሥራዎች ሲነገር አሁን ካለው ጋርም ተመሳሳይ መሆኑን አስተውያለሁ፡፡ ሥራዎቹን አሁን ወደ መድረክ ማምጣት አይቻልም ወይ?

አፍሪካ የስልጣኔ ሁሉ ምንጭ ናት ብሎ ማመን ብቻ ሳይሆን የተናገረ፣ የፃፈ፣ ቴአትርን ያሳየ ነው፡፡ እኛ በአድዋ ድል ላይ ቆመን እናወራለን እንጂ የዓለም ዕድገትና የሥልጣኔ ምንጭ አገራችን መሆኗን ለማሳወቅ በብዙ የለፋው ፀጋዬ ነው፤ ስለሱ ስንነጋገር እነዚህንም ጉዳዮች ብናነሳ፣ ጥሩ ነው፡፡

ፀጋዬ አስመሳይ ሰው ነበር ወይ? “ሎሬት” የሚለውን ማዕረግ ለራሱ የሰጠው ራሱ ነው ወይም ጓደኞቹ ናቸው የሚባለው እውነት ነው ወይ?

ፀጋዩ ገ/መድህን የፈጠራ ሥራዎቹን በነፃነት ሰርቷል ብዬ አምናለሁ በማለት ምላሽ መስጠት የጀመሩት አርክቴክት ሚካኤል ሽፈራው፤ ትምህርት በነፃነት ማሰብንና መሥራትን መገደብ አለበት ብዬ አላምንም፡፡ የሥነ ጽሑፍ ሰዎች ሲናገሩና ሲጽፉ ለየቅል ናቸው፡፡ የፀጋዬ ሥራዎች በራሳቸው ስለራሳቸው የመናገር ብቃት አላቸው፡፡

ዓለም አቀፋዊነትን ዓላማው አድርጎ አልሰራም የተባለው እውነት ቢመስልም በእንግሊዝኛ ቋንቋ ባዘጋጃቸው መጻሕፍቱ ሳይቀር ኢትዮጵያን ማዕከል ቢያደርግም በጥልቀት ለሚመረምራቸው ግን ዓለምአቀፋዊ ርዕሰ ጉዳዮች በውስጣቸው የያዙ ናቸው፡፡ ኦቴሎ ከሰሜን አፍሪካ በምርኮ ተወስዶ በብሪቲሽ ጦር ውስጥ በጀግንነቱ የታወቀ ወታደር ነው፡፡ ፀጋዬ ኦቴሎን ሲተረጉም በዓለም አቀፉ ጉዳይ ውስጥ ስለ አፍሪካ (ኢትዮጵያ) ነው የሚናገረው፡፡ በቅርቡም ቢቢሲ (BBC) ባሰራጨው የቴሌቪዥን ፕሮግራም ሼክስፒርን በአማርኛ ቋንቋ ያስተዋወቀ ኢትዮጵያ ብለው ለፀጋዬ ዕውቅና ሰጥተውታል፡ የፀጋዬ ቋንቋ አጠቃቀም ከባድ ሊሆን የሚችለውም እውነታን በምሳሌያዊ አቀራረብ ለማሳየት ከመጣሩ ጋር በተያያዘ ነው፡፡ በሌሎች አገራት በቋንቋ አጠቃቀማቸው ከባድ ናቸው የሚባሉ ፀሐፍት፤ ከብደውናል ተብለው ብቻ አይተውም፡፡

ፀሐፍቱ ምን ሊያስተላልፉ እንደፈለጉ የተለያዩ ትርጉም እየተሰራላቸው ከሕዝቡ ጋር እንዲተዋወቁ ጥረት ይደረጋል፡፡ በአገራችንም እንዲህ ዓይነት ልማድ ቢኖርና የፀጋዬ ሥራዎች በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲታወቁ ጥረት ቢደረግ የአንድ አይደለም የአራት ኖቤል ተሸላሚ በሆነ ነበር፡፡

አውሮፓውያን ስለ እኛ ብዙ ነገር ለማወቅ የቻሉት ጊዜ ወስደው ስላጠኑን ነው፡፡ የጥናታቸው ድምዳሜ ግን ሁለት መልክ አለው፡፡

አንደኛው እውነት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ይህንን መረጃ ፀጋዬ ገ/መድህንም እንደ ምንጭ እየተጠቀመ አፍሪካ (ኢትዮጵያ) የዓለም ታሪክ መነሻ መሆኑን ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ በድፍረት ምስክርነት እንዲሰጥ አድርጎታል፡፡

በተቃራኒ የሚገኘው የአውሮፓውያኑ የጥናት ድምዳሜ፣ ጥቅማቸውን መሠረት ያደረገና ከቅኝ ግዛት ወረራ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ይህ ጥፋት እስካሁንም በተለያየ መልኩ ቀጥሏል፡፡ የአፍሪካ የኖቤል ተሸላሚ ፀሐፍት በእንግሊዝኛና በፈረንሳይኛ ቋንቋ የሚጽፉ ናቸው፡፡ ፀጋዬ በራሱና በታሪኩ ኮርቶ ኢትዮጵያንና አፍሪካዊያንን ለማስተዋወቅ ጥሯል፡፡ የተረዳው ግን ያገኘ አይመስልም፡፡

ሥራዎቹም ዳግመኛ ለዕይታ ቢቀርቡ ጥሩ ነው ብለዋል - አርክቴክቱ፡፡ ፀጋዬ “ሎሬት” የሚለውን ማዕረግ ለራሱ መስጠቱንም ሆነ ከጓደኞቹ ተበርክቶለት እንደሆነ ያጠናሁት ነገር የለም ያሉት አርክቴክት ሚካኤል ሽፈራው፤ ፀጋዬ ገ/መድህን “ሎሬት” ተባለም አልተባለም በዚህ ማዕረግ ተጠርተው የተለያዩ ተግባራት ካከናወኑ ሰዎች የሚያንስ ሥራ አለው ብዬ አላምንም በማለት ሃሳባቸውን አጠቃለዋል፡፡

 

 

Read 1642 times Last modified on Saturday, 30 June 2012 13:25