Wednesday, 19 February 2020 00:00

የኢንተርኔት ወንጀለኞች በ2019 ብቻ 3.5 ቢ. ዶላር ዘርፈዋል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

    የአሜሪካ የፌደራል ምርመራ ቢሮ ኤፍቢአይ ባለፈው አመት ሪፖርት ከተደረጉለት የኢንተርኔት ጥቃቶች ብቻ ወንጀለኞች 3.5 ቢሊዮን ዶላር መዝረፋቸውን እንዳስታወቀ ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡
ባለፈው የፈረንጆች አመት 2019 ብቻ፣ በ48 የተለያዩ የአለማችን አገራት ውስጥ ከሚገኙ 467 ሺህ 361 ግለሰቦችና የንግድ ተቋማት፣ የኢንተርኔት ጥቃት ደርሶብናል የሚል አቤቱታ እንደቀረበለት የገለጸው ኤፍቢአይ፤ በአመቱ የኢንተርኔት ወንጀለኞች በድምሩ 3.5 ቢሊዮን ዶላር ያህል መዝረፋቸውንም አስታውቋል፡፡
የኢንተርኔት ወንጀለኞች ግለሰቦችንና የንግድ ተቋማትን የሚያጠቁባቸው መንገዶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየረቀቁና እየተወሳሰቡ መጥተዋል ያለው ቢሮው፤ ተጠቃሚዎችም ወንጀለኞችን ከጤነኞች ለመለየት የሚቸገሩበት ሁኔታ ተፈጥሯል ብሏል፡፡
ትክክለኛ በሚመስሉ ድረገጾችና የኤሌክትሮኒክ መልዕክት አድራሻዎች ተጠቅመው ከግለሰቦችና ተቋማት ጋር ግንኙነት የሚፈጥሩና ግላዊ መረጃዎችን የሚመነትፉ እንዲሁም ኮምፒውተሮችን ከአገልግሎት ውጭ የሚያደርጉ ወንጀለኞች እየበዙ መምጣታቸውንም ቢሮው ባወጣው ሪፖርት አመልክቷል፡፡
የግለሰቦችንና የንግድ ተቋማትን ኮምፒውተሮች በመዝጋትና ከጥቅም ውጭ በማድረግ፣ የተዘጋውን ለመክፈት ይህን ያህል ገንዘብ ክፈሉን እያሉ የሚደራደሩ የኢንተርኔት ጥቃት አድራሾች፣ ባለፈው የፈረንጆች አመት 2019 ብቻ፣ 8.9 ሚሊዮን ዶላር ያህል ገቢ ማግኘታቸውንም አክሎ ገልጧል፡፡

Read 3096 times