Saturday, 30 June 2012 12:21

የ”ምስጢር” ምስጢሮች

Written by  ብርሃኑ አበጋዝ (natanem2003@yahoo.com)
Rate this item
(0 votes)

ከኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ማዕከል አ.አ.ዩ

በደራሲ ፀሐይ ይስማው የተደረሰው “ምስጢር” የተሰኘው መፅሐፍ፤ በኢትዮጵያ ሴት ደራሲያን ማህበር የተመረቀው ባሳለፍነው ሳምንት ነበር፡፡ መፅሐፍ 208 ገፅ ሲኖረው በአንዲት ሴት የፍቅር ውጣ ውረዶችና መሰናክሎች ላይ ያተኮረ ነው፡፡ መፅሐፉን በዚህ መልኩ ልዳስሰው ወደድሁ፡፡“ምስጢር” ከገፅ 6 አንስቶ እስከ ገፅ 153 መቼቱን ያደረገው ከአርባ ምንጭ ወደ አዲስ አበባ በሚጓዝ አውቶብስ ውስጥ ነው፡፡ የሚገርመው ግን ይህን ሁሉ ገፅ ሳይሰለቹ ያነቡ ዘንድ ሃሳብዎን ሰቅዞ መያዝ መቻሉ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ የአንባቢን ቀልብ መሰብሰብ የምንችለው በመቼት መለዋወጥ ይመስለን ይሆናል፡፡ ይህ ግን እንዳይደለ “ምስጢር”ን ሲያነቡ ይገባዎታል፡፡

በተለምዶ አውቶብስ ውስጥ የተለያዩ ሰዎች ማለትም በፆታ፣ በእድሜ፣ በሃይማኖት፣ በብሔር የተሰበጣጠሩ በአንድ የሚሰባሰቡበት ቦታ ነው፡፡ በዚህም አውቶብስ ውስጥ የታሪኩ ዋና ዘውግ ከሆነችው የኔነሽና ይልቃል ውጪ ከእነርሱ በስተግራ ተቀምጠው ሙዚቃ ይከፈትልን እያሉ የሚጮሁት ሦስቱ ወጣቶች፣ ከፊት ለፊት ተቀምጠው የአሁኑን ትውልድ ከእርሳቸው ዘመን ጋር እያመዛዘኑ የሚታዘቡት አዛውንት ታሪኩን ሕይወት በማላበስ ጉልህ ድርሻ ነበራቸው፡፡

በተለይ በአዛውንቱና በአንድ ወጣት መሃከል የሚደረገው ሙግት አንባቢውም የአሁኑን ዘመን ካለፈው ዘመን ጋር እንዲያነፃፅር ይጋብዛል፡፡ በዚህም የአንዱን ማህበረሰብ አኗኗር፣ ባህል፣ ስነቃል፣ ታሪክ እንድንፈትሽበት ዓይነተኛ ሚና ይጫወታልና ቀንጨብ አድርጌ ላስነብባችሁ፡፡

እነ ይልቃል ከተቀመጡበት በስተግራ ሦስት ተሳፋሪ ወጣቶች እርስ በርሳቸው ጭውውታቸውን ተያይዘውታል፡፡ ከሁኔታቸው ለመረዳት እንደሚቻለው ቀደም ሲል የሚተዋወቁ ይመስላሉ፡፡ ከመሃል አንዱ “ለምን ሙዚቃ አይከፈትልንም?” ሲል በአንድ ድምፅ “ሙዚቃ!... ሙዚቃ!!” በማለት አጉረመረሙ፡፡ ሌሎችም ከየአቅጣጫው “ይከፈት! ይከፈትልን!” የሚል ድምፅ አስተጋቡ፡፡ ሹፌሩም ምላሹን ሰጠ፡፡ ምርጫውን ከፈተ፡ ሙዚቃው የታዋቂው እና የዝነኛው ድምፃዊ፣ የጥላሁን ገሠሠ “እይዋት ስትናፍቀኝ” የተሰኘው ሙዚቃ ነበር፡፡

ሁሉም በያለበት ከሙዚቃው ጋር መብከንከን ጀመረ፡ ተሳፋሪዎቹ ከግማሽ በላይ ወጣቶች ነበሩ፡፡

ከእነ ይልቃል ፊት ለፊት ባለው መቀመጫ ላይ የተቀመጡት አዛውንት ኋላውን፣ ፊት ለፊቱን፣ ግራ ቀኙን ካስተዋሉ በኋላ በመገረም “አይ ጊዜ!” አሉ፤ በሃይል በመተንፈስ፡፡ ከሙዚቃ ጋር አብረው የሚያዜሙትን ወጣቶች እያስተዋሉ፡፡

አጠገባቸው ያለው በእድሜ መካከለኛ የሆነው ጐልማሳ “ምነው አባቴ?” አላቸው ጨዋታውን ለመስማት በመጓጓት፡፡ “አሁን ይሄ ዘፈን ተሁኖ ተሙቶ ሁሉም ማንጐራጐሩ ደንቆኝ ነዋ”

“እንዴት አባቴ?”

“ቀረ ምን ያረጋል! ቀረ የኛ ጊዜ፡፡ የማሲንቆው፣ የክራሩ ቅኝት፣ የበገናው ድርደራ፣ የዘፋኙ ድምፅ አወራረድ፣ ኧረ ምን ብዬ ልንገርህ አያ…” ብለው በረጅሙ በመተንፈስ “አዬ… እ” ያለፈውን ጊዜያቸውን በንፅፅር እያስታወሱ፡ “ቀረርቶው፣ ሽለላው ወኔ የሚነካ” በማለት በእርጅና የተሸበሸበ ቆዳቸውንና ወደ መከደን የተጠጋውን የዓይናቸውን ቆብ እያፈጠጡ፣ አሁን አሁን ያላቸው ይመስል ሰውነታቸው ተቆጣ፡፡ መለስ አደረጉና “ዳሩ ምን ያረጋል ትላንት ዛሬ አትሆን” አሉ ጭንቅላታቸውን በመነቅነቅ፤ ተስፋ በቆረጠ አነጋገር፡፡

ጐልማሳውም ሁኔታቸው አስገርሞት ጨዋታቸውን እንዳያቋርጡበት “ይሔ መጥፎ ዘፈን ነው?” በማለት ጠየቃቸው፡፡

በንቀት አይን እያዩት “ተዘፍኖ ተሞቷል ኤልኝ ኤዳ፣ ጩኸት አይሉት ሙሾ ድምፅን አሰልሎ ማንቧረቅ… እንዲህ አይነቱ አይገባኝም ልጄ፡፡”

ጐልማሳው “ታዲያ አባቴ የእናንተ ጊዜ ምን እንደሚመስል ቢያጫውቱኝ” አላቸው ትህትና በተላበሰ አነጋገር፡፡

“አዬ ልጄ! ተወኝ እስቲ አታታክተኝ፣ ምን ያረጋል” በማለት ለአፍታ ዝም ካሉ በኋላ ጋቢያቸውን ከፍ ከፍ፣ አረጉና “እ… እ…. አውጋኝ ካልከኝማ ላውጋህ” አሉ ረጅሙን ጨዋታቸውን ለመጀመር እየተዘጋጁ፡፡

“እ… እድሜዬ እንዳንተ ጐበዝ ሳለሁ፣ ከአባቴ ጋር አደን ወጥተን ስንመለስ፣ ድግስ ተደግሶ ዳስ ተጥሎ የአካባቢው ወዳጅ ዘመድ፣ አዝማድ ተሰበስቦ፣ እየተበላ፣ እየተጠጣ መንደርተኛው ለሙገሳ አታሞውን ይዞ ተነሳ…”

“ጉሮ ወሸባዬ ጉሮ ወሸባ

ጉሮ ወሸባዬ ጉሮዬ እንዲያ እንዲያ ሲል ነው ግዳዬ” ሲሉ እናቴ እመሃል ገብታ

“ጉሮ ወሸባዬ ጉሮ ወሸባ

መሄዱ መች ቀረ፣ አቧራ መልበስ፣

ባይሰጠው ነው እንጂ በለስ በለስ” አለች፡፡ ለምን መሰለህ አባቴ እንጂ እኔ አልገደልኩምና እንዳላዝን፣ እንዳልሰደብ ብላ ነበር፡፡ በሜዳ ማቧረቅ፣ መጮህ፣ መዝፈን ይሉታል፣ ኤዳልኝ አያ እኔስ ከጆሮዬም አይገባልኝ፡፡ ደግሞም ለሠርግም ቢሆን ለሙገሳም አለው አባባል፡፡

አንዴ እቤታችን ለአውዳመት ድግስ ተደግሶ፣ ፍሪዳው ተጥሎ መቼም ያገሬ ሰው ተሰብስቦ መብላት፣ መጠጣት ይወዳል፣ ታዲያ እዚያ መሃል አዝማሪ አይጠፋም፡፡ ድግሱ ያማረ በመሆኑ አባቴ ደስታቸውን ሲገልፁ፡-

“ የባህር አረም ናት የበቅሎ ሥራት፣

ያቺ ጣይቱ ውቤ የፋንቴ እናት” በማለት ሲያሞግሷት፣

እሷም በተራዋ ወንድነታቸውን ጐበዝነታቸውን ለማወደስ ብላ

“ጐበዝ ነው ይሉታል፣ እኬሌም ጐበዝ ነው፣

ገዳይ ነው ይሉታል፣ እኬሌም ገዳይ ነው፣

የጐሼን ወንድነት የሚያገኘው ማነው! አለች፡፡” ብለው ፊታቸው በፈገግታ ተሞላ፡፡

“…የሚገርም ነው” አለ የአዛውንቱ ወኔ እና ለባህላቸው ያለውን ፍቅር ከአሁኑ ዘመን ጋር እያነፃፀረ - በምናቡ፡፡

“አሁን ወዴት ነው የሚሄዱት?” አላቸው፤ ጐልማሳው፡

“ወደ አዲስ አባ ነዋ”

“የት ነው የሚኖሩት?”

“አሁንማ ከየው ከአዲስ አባ ነው፡፡ ትውልድ አገሬ ግን ጐንደር ቤገምድር አውራጃ ደራ ሐሙሲት፣ ከሚባለው ነው፡፡”

“ታዲያ እዚህ ለምን መጥተው ነው?”

“እዚህማ ቅድም ከመኪናው ስንሰቀል አብሮኝ የነበረውን ጐበዝ አላየኸውም?”

“አዎ አይቼዋለሁ”

“ታውቀው ኖሯል?”

“አዎ በዓይን አውቀዋለሁ፡፡ ኢንጂነር የኔሰው አይደለም እንዴ?”

“እንግዲያማ” አሉ የልጃቸው ኢንጂነር መባል አስደስቷቸው፡፡ ምንም እንኳን የደጃዝማች፣ የግራዝማች፣ የቀኛዝማች መባልን ያህል ባያስደስታቸውም ከስሙ ጋር የተሰጠው ቅጥያ ማዕረግ እንደሆነ ይገባቸዋል፡፡

“ልጅዎት ነው?”

“እንዴታ… እንዴታ ይኸ ሦስተኛ ልጄ ነው፡፡ ሌሎች ትላልቆች አሉኝ” አሉ ተኩራርተው፡፡

“ብዙ ልጆች አሉዎት?”

“እግዚአብሔር ይመስገን የሚበቃኝን ያህል አንሻሽዌለሁ፣ ያውም ባዝራ ከድንጉላ” አሉ ወንድም ሴትም መውለዳቸው ደስ አሰኝቷቸው፡፡

ጐልማሳውም ከእውቀት ማነስ የተነሳ “ስንት ወልደዋል?” ሲል ጠየቃቸው፡፡

“ኧረ በወላዲት አምላክ፣ ምን የነካህ ነህ አያ፣ ለምን እቆጥራቸዋለሁ፣ ጥሩም እኮ አይደል” አሉ የስስት ስሜት እየታየባቸው፡፡

እንደገና ወደ ወጣቱ ፊታቸውን መለስ አድርገው ዝግ ባለ አነጋገር “ሞት አይቁጠርብኝና ከዋናዋ ሚሽቴ አራት ሴት፣ አምስት ወንድ፤ አንድ እቁባት ነበረችኝ፤ ሦስት ወንድና አንድ ሴት ወልጄአለሁ” አሉ ፈገግ ብለው፡፡

“አንተ አግብተሃል?” ብለው ጐልማሳውን በድንገት ጠየቁት

“አላገባሁም” አለ፡፡

በንቀት አይን እያዩት “ኤዲያ የማትረባ ነህ፡፡ ምን ስታረጅ ነው የምታገባ? ኧረ በወላዲት አምላክ፣ ወንድ ልጅ ከባለቀ ወዲያ፣ ምን ያስፈልጋል፡፡ በትኩሳቱ እንጂ ጋብቻ፣ ከበረደ ወዲያ ልትጦረው ነው? ሊጦርህ?... ኧረዲያ ሁሉ ነገራችሁ ከሰው አይገጥም” በማለት ምርር ብለው አዘኑ፡፡ ፊታቸውን ወዲያውኑ አዙረው ጋቢያቸውን ከፍ ከፍ ቆርጠጥ ቆርጠጥ አሉ፡፡

ጐልማሳው “አይደለም እኮ አባቴ አሁን የምሄደው ለማግባት ጭምር ነው” አለ ቁጣቸውን ለማብረድ ተቻኩሎ፣ በሁኔታውም ተደናግጦ፡፡

“ይበጅህ! ያውም አልፎብሃል እኔ አንተን ሳክል አንድ ስድስቱን አስጥያለሁ፣ እንዲህ ስታየኝ የዋዛ አልምሰልህ፣ የሰፈሩ ኮርማ ነበርኩ እኔ አባትህ፡፡ ምን ያደርጋል ታዲያ ትላንት ዛሬ አትሆን” አሉ፤ ያሳለፉትን ጊዜ በማስታወስ፡፡

ጐልማሳውም “አሁንም እኮ ገና ነዎት” አላቸው የሚሉትን ለመስማት፡፡

ከትከት ብለው ሳቁ፡፡ “እውን ከልብህ ነው?” አሉ የራሳቸውን ሁኔታ ከጐልማሳው ለመረዳት በማሰብ፡፡

“አዎ አባቴ”

“እንግዲያማ አንተ ትድረኛለህ” አሉ ለመቀለድ እየቃጣቸው፡

መለስ አደረጉና “…ልጅ በልጅነት፣ አበባ በጥቅምት፣ ይላሉ አባቶቻተን፣ ፌዝ አይምሰልህ፡፡ እኔ አባትህ ዛሬ እንዲህ የምንደላቀቀው አርሼ፣ ቆፍሬ፣ ሰርቼ መሰለህ፣ በልጆቼ፣ በፍሬዎቼ በጊዜያቱ በመድረሳቸው ነው፡፡”

“ጋብቻን የምትጠላው አንተ ብቻ አይደለህም፡፡ ይኼው የኔዎቹም አሻፈረን ብለዋል ወትሮ ትምህርታችንን ሳንጨርስ ሲሉ፣ ሙሎች ትምርታቸውን ጨረሱ፡፡ አሁን ደግሞ አንዱን ስትጠይቀው ቆየ ገና ነኝ፣ አልተዘጋጀሁም፣ ወደ ውጭ ለመሄድ “ፎሮግራም” አለኝ፡፡ እጮኛዬ ትምህርቷን አልጨረሰችም፡፡ የሚሉትን ፈሊጥ ይዘው አስቸግረውኛል፡፡ ለመሆኑ ግን የእናንተ ጊዜ ትምህርት እድሜ ሙሉ ነው?”

ከኋላ ተቀምጦ አንዳንዴ ሃሳቡን ሰረቅ በማድረግ ያዳምጣቸው የነበረው ይልቃል፤ በጨዋታቸው ተስቦ በጥሞና ይከታተላቸው ነበር፡፡ ጣልቃ ላለመግባት ፈልጐ እንጂ ቢያጫውታቸው በወደደ ነበር፡፡“ታዲያ ልጄ” አሉ ድምፃቸውን እየሳሉ “የዛሬ ልጆች ጨዋታችሁ፣ ሥራችሁ፣ ሙላው ነገራችሁ ከኛ ከአባቶቻችሁ ይራራቃል፡፡ ምክር አትቀበሉም፤ የሚነግሯችሁን በጀ አትሉም፡፡ መማራችሁ ባልከፋን፣ እኔን የሚገርመኝ ጠባያችሁ ብቻ አይደለም፣ ትምህርታችሁም ከእኛ ልዩ ነው፡፡ እኛ ወትሮ የምንሾም የምንሸለመው ደጃማች፣ ቀኛማች፣ አጤ፣ ጐበዝ አርበኛ ከሆነም በፈረሱ ስም ይጠራ ነበር፡፡

ግና ዛሬ ታዲያ ስልጣናችሁ፣ ሹመታችሁ በጫራችሁት ወረቀት ሆኖ ዶፍተር፣ ፕሮፌሰር፣ እንጅነር፣ ስስተር ኧረ ምኑ ቅጡ አያ፣ የማትባሉት የለም፡፡ ግዳይ የዋላችሁበት ሳይነገር ስም ብቻ” ብለው የአግራሞት ሳቅ ሳቁ፡፡

ስለ መፅሃፉ ይህን ካልኩ ወደተነሳሁበት ዋና ቁምነገር ስመልሳችሁ “ምስጢር” ታሪኩ በሙሉ የሚያጠነጥነው የፍቅር ሳንካ በባህር ላይ እንዳለች መርከብ እያንገላታና እያላጋ በራሷ ማንነት እና መንገድ ሳይሆን በሰዎች መንገድ ለመጓዝና ለመንገላታት የበቃችውን የኔነሽ (ምስጢር) በመተረክ ነው፡፡

የኔነሽ እናቷ ያወጡላት ስም ሲሆን ምስጢር ደግሞ አባቷ ያወጡላት ስያሜ በመሆኑ በሁለቱም ትጠራበታለች፡፡ የየኔነሽ የፍቅር ምስጢር የሚጀመረው ገና ሃይስኩል አብራው ትማር ከነበረው የዘውድዓለም ጋር በአጋጣሚ በተፈጠረ መግባባትና መፋቀር ነው፡፡ ሁለቱም ተግባብተው ለመፋቀር ቢታደሉም እንኳን መዝለቅ ግን አልቻሉም፡፡ የውድአለም ወንድም ታናሹን ለማስተማር ከ11ኛ ክፍል ወደ አዲስ አበባ ይወስደዋል፡፡ በመለያየት ሳንካ አፍላዋን ፍቅር ያጣች የመሰላት የኔነሽ የሕይወት ተግዳሮት እዚህ ጋር ይጀምራታል፡፡ ሆኖም ግን በሚመጡላት ደብዳቤ በመፅናናት ትምህርቱን በደንብ አጥንታ አዲስ አበባ ብትገባ ልታገኘው እንደምትችል በማሰብ፣ የቻለችውን ያህል ብትታትርም፣ ናፍቆት አዘናግቷት ኖሮ ውጤቷ ለዲፕሎማ ብቻ ያበቃታል፡፡ የዘውድአለም ግን ለዲግሪ ያልፋል፡፡ የኔነሽ በዚህም ሳታልፍ አዲስ አበባ ንግድ ሥራ ኮሌጅ በማመልከቷ ስላለፈች ደስ ብሏት ወደ አዲስ አበባ ናፍቆቷን በልቧ ይዛ ትጓዛለች፡፡ አዲስ አበባ ገብታም የዘውድአለምን ለማግኘት ስልክ ብትደውልም አልሆነላትም፤ በመጨረሻም እርሱን ባታገኝ እንኳ አስመራ ዩኒቨርስቲ እንዳለፈና የመመዝገቢያ ጊዜ በመድረሱ በቶሎ ወንድሙ ይዞት እንደሄደ ተረዳች፡፡ ከባህር ዳር አዲስ አበባ ድረስ የተጓዘችለት ፍቅር ላይጨበጥ ዳግም ይርቃታል፡፡ በአዲስ አበባ ንግድ ሥራ ኮሌጅ ገብታ ለመማር ብትጀምርም ተረጋግታ መማር ግን አልቻለችም ነበር፡፡

የኔነሽን ለጊዜው ያረጋጋት ነገር የአስመራ ዩኒቨርስቲን አድራሻ አግኝታ ለአለምዘውድ ፅፋ ደብዳቤዋ ምላሽ ያገኘ ጊዜ ነው፡፡ ይህም ቢሆን ብዙ አልዘለቀም፡፡ በአንድ ወቅት የአለምዘውድ ጭራሽ ድምፁን አጠፋ፤ የደብዳቤዋን ምላሽ ነፈጋት፤ ይባስ ብሎ እንደማይፈልጋት አዲስ አበባ ካፈቀራት ሴት ጋር አስመራ ዩኒቨርስቲ አብረው አንደሆኑ፣ እርሱን እንድትረሳው መርዶ ያዘለውን ደብዳቤ ላከላት፡፡ ልቧንም ሰበረው፤ በዚህም ራሷን ስታ ሆስፒታል እስከመግባት ደረሰች፡፡

የየኔነሽ የፍቅር ምስጢር እዚህ ጋር አበቃ ስንል ደግሞ ይቀጥላል፡፡ ሆስፒታል ታማ ከላይ ታች ሲል የነበረ እርሷን በማስታመም ብዙ የደከመው ዮሴፍ፤ ለካ በፍቅሯ ወድቆ ኖሮ እርሷን በመንከባከብ ብዙ ይታትራል፡፡ ከሀዘኗም እንድታገግም ይረዳታል፡፡

ቀስ በቀስ መልካምነቱ እየሳባት በፍቅሩ ለመሸነፍ በቃች፤ ብዙ ጊዜም አብረው አሳለፉ፡፡ ትምህርቷን ጨርሳ ሥራ የያዘችበት ወቅት ነውና በዮሴፍ ቤት ተጠቃላ ባትገባም ውሎዋና አዳሯ እዛው ሆነ፡፡ አንድ ቀን ስልክ ሲደወል ታነሳለች፡፡ ደዋይዋ ሴት ነበሩ፡፡ “ዮሴፍ የለም” አሉ፡፡ “ተሳስተዋል ዮሱፍ የሚባል የለም” አለች የኔነሽ፡፡ ሴትየዋም ቆጣ ብለው “ደግሞ አንቺ ማን ነሽ ዮሱፍን አቅርቢልኝ” አሉ፡፡ ግራ ቢገባት ለሠራተኛዋ ሰጠቻት፤ ከሠራተኛዋ ጋር አውርተው ስልኩን ዘጉ፡፡ ደግሞ ዮሱፍ ማነው ብላ ጠየቀች፡፡ የዮሴፍ ሌላኛው ስሙ እንደሆነ፣ የደወለችውም እናቱ እንደሆኑ ተረዳች፡፡ በስሙም የሃይማኖት ልዩነት እንዳለ ሲገባት ተሸበረች፡፡

ዮሴፍም ተረጋግቶ የሆነውን አስረዳት፡፡ ሙስሊም እንደሆነ አባቱ ግን ክርስቲያን እንደሆኑ፤ አባቱ ዮሴፍ እንደሚሉት፤ ያም ሆኖ ግን እርሷን ለማግባት ሃይማኖቱንም ቢሆን ሊለውጥ ዝግጁ መሆኑን ነገራት፡፡ የኔነሽ ግን የእናቷን ወግ አጥባቂነት ጠንቅቃ ስለምታውቅ አዘነች፡፡ ከአክስቷ ተማክራ እናቷ ጋ በመሄድ ማግባት እንዳሰበች፤ ዮሴፍም በሃይማኖት ቢለያዩም ክርስቲያን ሊሆን እንደወሰነ ብታስረዳቸውም ወይ ፍንክች አሉ፡፡ ሞቼ እገኛለሁ ልጄ አይደለሽም ብለው ተለያዩ፡፡ የኔነሽ እናቷ ያለአባት አሳድገዋታልና በምንም መንገድ እርሳቸውን ማሳዘን ባለመፈለጓ እንደተመለሰች ከዮሴፍ ጋር ተለያዩ፡፡ እርሱን ለመርሳትም ስትል በመስሪያ ቤት በኩል ልዋጭ ፈልጋ ደብረዘይት ገባች፡፡ ያልተቋጨ የፍቅር ውጣ ውረድ፡፡

ደብረዘይት ለጊዜውም ቢሆን ሃሳብዋን ለመርሳት ችላበታለች፡፡ ደብሪቱ ጓደኛዋ በመሆኗ ብቸኝነቷን ካስረሳቻት መካከል አንዷ ነች፡፡ ሆኖም ግን ሌላ የፍቅር ተግዳሮት ገጠማት፡፡ አለቃዋ (ሥራ አስኪያጁ) ብሩክ የኔነሽን ካላገኘሁ መሞቴ ነው፤ ማበዴ ነው ብሎ ተፈጠመ፡፡ በደብሪቱ አማላጅነት ቀስ በቀስ እየተግባቡ ወደ ፍቅር ነጐዱ፡፡ ብሩክ አላማው ማግባት ብቻ ነው፡፡ የኔነሽም ከብሩክ ፀነሰች፡፡ ሊጋቡም ወስነው ሁለቱም ለቤተሰብ ያሳውቃሉ፡፡ በሁለቱም ቤተሰብ በኩል ሽር ጉዱን ይያያዙታል፡፡

በመሃሉ አዲስ አበባ ከደብሪቱ ጋር በሄዱ ጊዜ ዮሴፍ መንገድ ላይ አይቷቸው ይገናኛሉ፡፡ ጊዜ ካላቸው ሻይ ቡና እንዲሉ ይማፀናቸዋል፡፡ በማግስቱም ተገናኝተው ዮሴፍ ለየኔነሽ መልካም እድል ተመኝቶላት ለማስታወሻ ፎቶ ተነስተው ይለያያሉ፡፡ ይህን ፎቶ ደብሪቱ ቦርሳ ውስጥ ያገኘው ሳሙኤል፤ የኔነሽን ከአዲስ አበባ ጀምሮ ገልጦ ባይናገርም ያፈቅራት ኖሯል፡፡ ደብረዘይት ስትመደብም ያገኛት መስሎ ደስ ተሰኘ፡፡ ሆኖም ግን የልቡን አውጥቶ ሳይናገር በአለቃው ተቀደመ፡፡ እንዳይታገለው አለቃው በመሆኑ ደብሪቱን ባገኘ ቁጥር “ሸጥሻት” በማለት ይዘልፋታል፡፡ አሁን ይህን አጋጣሚ ተጠቅሞ በፎቶው ጀርባ ላይ ዮሴፍ የፃፈው በማስመሰል ልጁ የዮሴፍ እንደሆነ አድርጐ በማቀነባበር ፎቶውን ለብሩክ ይሰጠዋል፡፡

ብሩክ፤ የኔነሽ ከዚህ በፊት ከዘውድአለም ጋር ስለነበራት የፍቅር ግንኙነት እንጂ ስለዮሴፍ ስላልነገረችው፣ በፎቶው ማስረጃነት እንደ ከሃዲ ቆጥሮ ድብልቅልቅ ያለ ፀብ ይፈጠራል፡፡ ቤቱን ለቃ እንድትወጣ ይነግራታል፡፡ ያፈቀራትን ያህል ሳይሆን ከዛ በላይ ንቆ አዋርዶና ሰድቦ “ለዛሬ ስለመሸ ሴት ስለሆንሽ ውጪ አድራለሁ፡፡ ነገ ግን ቤቴ እንዳላይሽ” ብሎ ሊወጣ ሲል የኔነሽ “በፍፁም ቤቱ ያንተ ነው አንተ አትወጣም፤ እኔው እወጣለሁ” ብላ ታግላ ስትወጣ በመውደቋ ለህመም ትዳረጋለች፡፡ በዚህም ምክንያት ሆስፒታል ገብታ ልጇ (ፅንሷ) ስለተጐዳ ውርጃ ይፈፀማል፡፡ ደብሪቱ በጣም ትፀፀታለች፡፡ ሳሙኤልም ይህን ያህል የከፋ ጉዳት ይደርሳል ብሎ ባለማሰቡ ያዝናል፡፡ ብሩክ እውነታውን ሳይረዳ ቅያሬ ጠይቆ ወደ አዲስ አበባ በመግባቱ ፍቅራቸው እና የሠርጉ ሽርጉድ በዚሁ ይቋጫል፡፡ይህን ሁሉ ምስጢር በምልሰት የምትናገረው ለይልቃል ነው፡፡ ከእርሷ ጋር በአውቶብስ ውስጥ አብሯት እየተጓዘ ያለ አብሯት የተቀመጠ መንገደኛ ነው፡፡

ስለተግባቡና ስለጠየቃት ነበር ታሪኳን ያጫወተችው፡፡ ይህ ታሪክ ግን ይልቃልን በየመሃሉ የራሱን ሕይወት እንዲያይበት ይጋብዘዋል፡፡ ታሪኳ መስጦታል፡፡ በየኔነሽ የፍቅር ውጣ ውረድ ልቡ አዝኗል፡፡ ለፍቅር ምን ያህል ታማኝ ሴት እንደሆነች ሲገባው፣ የእርሱ ልብ በፍቅሯ ሳይሳብ አልቀረም፡፡ አዲስ አበባ ከደረሱ በኋላ ጉዟቸው ሁለቱም ወደ ባህር ዳር ስለሆነ፣ የአንድ አካባቢም ልጆች በመሆናቸው፣ አብረው ለመሄድ ይስማማሉ፡፡ ነገ ሊጓዙ ዛሬ ሆቴል ማደር ነበረባቸው፡፡ ለሁለቱም የተለያየ ክፍል ተከራይቶ እንዳከበራት ያድራሉ፡፡ በዚህም አድራጐቱ የኔነሽ ታከብረዋለች፡፡

ባህር ዳር ከደረሱ በኋላ ስልክ ተለዋውጠው ወደየቤተሰቦቻቸው ይጓዛሉ፡፡ ይልቃል በልቡ የኔነሽን የራሱ የማድረግ እቅድ ስለነበረው፣ በቤተሰብ መካከል የትዳር ጨዋታ ሲነሳ “በቅርቡ አሳያችኋለሁ” ብሎ ፎክሯል፡፡ እነይልቃል ቤት ድል ያለ ድግስ ተደግሶ ዘመድ ተጠርቶ ግብዣ ይደረጋል፡፡

የዝግጅቱ ምስጢር ምን እንደሆነ ሁሉም አልገባቸውም፡፡

ይልቃል ሃሳቡ ያለው የኔነሽ ጋር ነበር፡፡ በድግሱ እለት ግን ከተጋበዙት እንግዶች አንዷ ራሷ የኔነሽ ሆና ብቅ ትላለች፡፡

ይልቃል ግራ በመጋባት በድንጋጤ ክው ብሎ ይቀራል፡ ሁሉ ነገር ይምታታበታል፡፡ የዝግጅቱን ምስጢር የይልቃል አባት የነፍስ አባት የሆኑት ቄስ ያስረዳሉ፡፡ ለካ የኔነሽ የይልቃል አባት በድብቅ የወለዷት፣ እስከዛሬም አባትነታቸውን ክደው የኖሩ፤ አሁን ግን እድሜያቸው ስለገፋ ለንሰሀ እንዲበጃቸው ብለው እውነቱን በማመን የኔነሽን ከቤተሰቡ ለማስተዋወቅ ያዘጋጁት ዝግጅት ነበር፡፡ ምስጢርም ያሏት ሀቁን ለመደበቅ ነበር፡፡

ይልቃል የፍቅር ንግስት አድርጐ በልቡ ያነገሳት፣ ስለፍቅር ታማኝ ሆና የሕይወትን ውጣ ውረድ ያየችው ሴት፤ የገዛ ራሱ እህት መሆኗ ሲነገረው ማመን አቃተው… ሌላ ምስጢር ሆነችበት

፡፡ በተረፈ “ምስጢር”ን ገዝተው ሲያነቧት በእርስዎ እይታ ደግሞ ሌሎች ብዙ ምስጢሮች ያገኙባታል፡፡ መልካም ንባብ፡፡

 

 

Read 1831 times Last modified on Saturday, 30 June 2012 12:25