Monday, 17 February 2020 00:00

ዲሞክራሲ ስንት ዓመት ይፈጃል?

Written by  አልአዛር ኬ.
Rate this item
(4 votes)

    (የሁለት አገሮች ወግ)
ስለ ህዝቦች እኩልነት፣ መብትና ፍትሀዊ ተጠቃሚነት መረጋገጥ፣ ላለፉት ሀያ ስድስት አመታት በኩራት ተጀንነን “ላሎ መገን” እያልን ስንጨፍር ኖረን፣ ዛሬ እንደ አዲስ ተመልሰን፣ ስለ ዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ ሀሁ መቁጠር መጀመራችን በእውነቱ ያሳዝናልም ይገርማልም፡፡
 መልስ የማይጣው ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ወይም ልማታዊ መንግስታችን፤ “ምነው ዲሞክራሲ የህልም እንጀራ ሆነሳ?” ተብሎ በተጠየቀ ቁጥር፤ ‹‹የዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ በ24 ሰአት የሚጠናቀቅ ጉዳይ አይደለም፤ እንዲህ ቢሆን ኖሮ፣ ከ1984 ማግስት ጀምሮ ተግባራዊ ባደረግነው ነበር፡፡ እንኳን እኛ ምንም አይነት ልምድ የሌለን ይቅርና፣ አሜሪካም አሁን ያለውን የዲሞክራሲ ስርአቷን ለመገንባት የፈጀባት ጊዜ 100 ዓመት ነው›› የሚለውን የተለመደ አሰልቺ መልስ፣ ዛሬም  ከ25 ዓመት በኋላ መስጠቱ አለመታደል ነው፡፡   
ኢህአዴግ ራሱን ከህዝብ ወቀሳና ተጠያቂነት ያዳነ መስሎት፣ በሀገራችን የዲሞክራሲ ስርአት ለመገንባት ልክ እንደ አሜሪካ 100 አመት ሊፈጅብን እንደሚችል የሚነግረንን የተለመደ ተረክ አምነን እንድንቀበለው ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል በእጅጉ ጥሯል:: ዛሬም ቢሆን ከዚህ ጥረቱ አልተገታም፡፡
 እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ይህ ትልቅ የዋህነት ነው፡፡ ለምን ቢባል? ከ20 ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ትልቅ ስኬት ያስመዘገበችው አፍሪካዊት ሀገር ጋና እያለች፣ ባለ 100 አመቷን አሜሪካንን በምሳሌነት መጥቀስ ምን አመጣው?
ከአሜሪካ ይልቅ በማለፊያ ምሳሌነት ለኢትዮጵያ መቅረብ ያለባት ሀገር ጋና ናት የምለው፣ “ደም ከውሀ ይወፍራል” እንደሚባለው፣ በአፍሪካዊነት ልቤ አድልቶላት አይደለም፡፡ ይልቁንም ጋናውያን ነፃነታቸውንና መብታቸውን ለመጎናፀፍ የተጓዙበት መንገድ፣ ኢትዮጵያውያን ከተጓዙበት መንገድ ጋር በእጅጉ ስለሚመሳሰል ነው፡፡
ኢትዮጵያውያን፤ በደርግ ወታደራዊ አገዛዝ ስር ለአስራ ሰባት አመታት አሳር መከራቸውን በልተዋል። ጋናውያንም፤ ከአስራ ሰባት አመታት በላይ በየተራ በተፈራረቁባቸው ወታደራዊ አምባገነን መሪዎች ፍዳቸውን ቆጥረዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን፤ ከደርግ የጭቆና አገዛዝ ለመላቀቅ፣ ግዙፍ የህይወትና የአካል መስዋዕትነት የጠየቀ፣ እጅግ መራራ የትጥቅ ትግል አካሂደዋል፡፡ ጋናውያንም በበኩላቸው፤ እንደ ኢትዮጵያውያን ጫካ ወርደው የትጥቅ ትግል ባያካሂዱም፣ ተገቢ ነው ባሉት ስልት ወታደራዊውን አገዛዝ ተፋልመው፣ ቀላል የማይባል የህይወትና የአካል መስዋዕትነት ከፍለዋል፡፡
ኢትዮጵያና ጋና ከወታደራዊ አገዛዝ ወደ መድብለ ፓርቲ ስርአት መሸጋገር የጀመሩት የዛሬ 25 ዓመት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ለዜጎች ነፃነት፣ እኩልነት፣ ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች እውቅናና ጥበቃ የሚያደርግ ህገ መንግስት ያፀደቀችው የዛሬ 23 አመት ሲሆን ጋና ይህንን ያደረገችው ከኢትዮጵያ አንድ አመት ቀደም ብላ ነው፡፡
ያለ ህግ የበላይነት የዜጎች ነፃነት፣ እኩልነትና መብት ፈጽሞ እንደማይረጋገጥ፤ ያለ ነፃ፣ ገለልተኛና ጠንካራ የዲሞክራሲ ተቋማት፣ እውነተኛና ሁነኛ የዲሞክራሲ ስርዓት መገንባት እንደማይቻል የኛው ኢህአዴግም ሆነ የጋና መሪዎች ተገቢው ግንዛቤ ነበራቸው:: ይህንን እውን ለማድረግ የነበራቸው ፍላጎትና ቁርጠኝነት ግን በጣም ይለያያል፡፡ ከመንግሥት ተጽዕኖ ነፃ የሆነ ገለልተኛና ጠንካራ የፍትህ አካልና የዲሞክራሲ ተቋማትን ለመገንባት ኢትዮጵያን የሚመራው ኢህአዴግ፤ ትናንትም ሆነ ዛሬ ያለው ፍላጎትና ቁርጠኝነት አፍአዊና የይስሙላ ሲሆን የጋና መሪዎች ፍላጎትና ቁርጠኝነት ግን ከፍተኛና የማያወላውል ነው፡፡
በዚህ የተነሳም ሀገራችን ኢትዮጵያ ከ26 ዓመት በኋላ ዛሬም ስለ ዲሞክራሲ ሥርአት ግንባታ ሂደት የውይይት መድረክ እያዘጋጀች፣ ሀሁ በመቁጠር ላይ ስትገኝ፤ ጋና ግን ለአካባቢ ሀገራት ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካ በድንቅ ምሳሌነት የሚቀርብ ጠንካራና የበለፀገ የዲሞክራሲ ስርአት ባለቤት ለመሆን በቅታለች፡፡ ለምሳሌ፡- የጋና ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ ነፃና ገለልተኛ መሆኑን ያስመሰከረው፣ በ1984 ዓ.ም ለመንግስት ወግኖ፣ ለተቃዋሚው ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳ የአየር ሰአት አልሰጥም ብሎ ባስቸገረው የጋና ብሮድካስቲንግ ኤጀንሲ ላይ ተገቢውን ቅጣት በመበየን ነበር፡፡ ይሄም ብቻ አይደለም፡፡
የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎችን፣ ከህገ-መንግስቱ በተቃራኒ፣ “መንግስትን ሳታስፈቅዱ ሰላማዊ ሰልፍና ህዝባዊ ስብሰባ አታካሂዱም” በማለት መከልከል ሳያንሳቸው፣ በመቶዎች የሚቆጠሩትን አለአግባብ እስር ቤት አጉረው፣ ድብደባ በፈጸሙት የጋና ፖሊስና ደህንነት ተቋምና አባላት ላይም ፍርድ ቤቱን ነጻነቱንና ገለልተኝነቱን የሚያስመሰክር ተገቢ የቅጣት ውሳኔ አሳልፎባቸዋል፡፡  ይህ ፈር ቀዳጅ ነው የተባለለት የፍርድ ቤት ውሳኔ በእነዚህ ቁልፍ የዲሞክራሲ ተቋማት ላይ ከተላለፈባቸው ጊዜ ጀምሮ ቀልዳቸውን ማቆምና አደብ መግዛት ችለዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ጀሪ ሮውሊንግስን ተከትለው በህዝባዊ ምርጫ ፕሬዚደንታዊ ስልጣን የጨበጡት ጆን ኩፎር፣ ጆን አታ ሚልስና፣ ጆን ማሀማም በአገራቸው ጠንካራ የዲሞክራሲ ስርአት  እንዲገነባ ለማድረግ የነበራቸው ፍላጎትና ቁርጠኝነት ከፍተኛ ስለነበር፣ የጋና የፍትህ ስርአትና የዲሞክራሲ ተቋማት ነፃነታቸውና ገለልተኝነታቸው ተጠብቆ ይበልጥ እንዲጠናከሩ በስልጣን ዘመናቸው የየበኩላቸውን ሚና በብቃት ተወጥተዋል:: በዚህ የተነሳም የጋና ብሮድካስቲንግ ኤጀንሲ፤ ባለፈው አመት እስከተካሄደው ብሄራዊ ምርጫ ድረስ ህግ በሚፈቅደው መሰረት፣ለተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ከገዥው ፓርቲ እኩል የአየር ሰዓት በመመደብ፣ ያለ አንዳች አድልኦ አገልግሎቱን ሰጥቷል፡፡
የጋና የፖሊስና የደህንነት ተቋምም ያኔ ከተፈረደበት ወዲህ ለመንግስት ወይም ለገዥው ፓርቲ ወግኖ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎችን “የፍቃድ ደብዳቤ አምጡ” በሚል ሰላማዊ ሰልፍም ሆነ ህዝባዊ ስብሰባ እንዳያካሂዱ ከልክሎ ወይም አግዶ አያውቅም፡፡ በህገወጥ ተግባር ላይ ካልተሰማሩ በቀር ሰላማዊ ሰልፍና ስብሰባ አደረጋችሁ በሚል እንኳን ማሰርና መደብደብ፣ ዝንባቸውንም እሽ ብሎ አያውቅም፡፡  የጋና የዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ ታሪክ በዚህ ብቻ አያበቃም፡፡ የፕሬስ ነፃነትን ለማረጋገጥ በሙሉ ፍላጎት፣በማያወላውል ቁርጠኝነት የሰሩት ስራ እጅግ የሚያመረቃ ውጤት አስገኝቶላቸዋል፡፡
የህገ መንግስታቸውን ድንጋጌዎች በአፋቸው በማነብነብ ሳይሆን በትክክል በተግባር መተርጎም በመቻላቸው፣ ዛሬ የዳበረና በዓለም አቀፍ መድረክ የተመሰከረለት የ”ነፃ” ሚዲያ ባለቤት ለመሆን በቅተዋል:: ድንበር የለሽ ሪፖርተሮችና ፍሪደም ሀውስ የተባሉት አለም አቀፍ ተቋማት፣ የጋናን ሚዲያ ነፃ ከሚባሉት የሀገራት ሚዲያ ጎራ በመመደብ እማኝነታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ነፃ፣ ገለልተኛና ጠንካራ የምርጫ አስፈፃሚ ተቋም ለመገንባት ጋናውያን መሪዎች ያደረጉት ያላሰለሰ ጥረት ያስገኘላቸው ውጤትም ተመሳሳይ ነው፡፡ የጋና ብሄራዊ የምርጫ ኮሚሽን፣ የዛሬ 25 ዓመት ከተቋቋመ ጊዜ አንስቶ፣ እስካሁን ድረስ ሰባት ብሄራዊ ምርጫዎችን አካሂዷል፡፡ ነፃና ገለልተኝነቱን በተመለከተ ግን በአንዱም ምርጫ ላይ እንኳ በገዥውም ሆነ በተቃዋሚው ፓርቲ ጥያቄም ሆነ ቅሬታ ቀርቦበት አያውቅም፡፡ በምርጫ የተነሳም የአንድ ጋናዊ የህይወት መጥፋትም ሆነ የአካል መጉደል አልተመዘገበም፡፡
የጋና መሪዎች ጠንካራ መሰረት ያለውና ስር የሰደደ የዲሞክራሲ ስርአት በሀገራቸው ለመገንባት ላለፉት 25 አመታት በሙሉ ፍላጎትና በከፍተኛ ቁርጠኝነት ያደረጉት ይህ ጥረት፤ ለሀገራቸው ለጋና በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅናና ታላቅ ከበሬታ የተቸረው መልካም ስም አትርፎላታል፡፡ ለመላው ጋናውያንም፣ ለድፍን አፍሪካ ምሳሌ የሆነች ብቻ ሳይሆን የዛሬውም ሆነ መጭው ትውልድ በፖለቲካ ምክንያት እንደ ሌሎቹ የአፍሪካ ሀገራት ህይወቱንም ሆነ አካሉን የማያጣባት ሀገር ባለቤት እንዲሆኑ አስችሏቸዋል፡፡  እንግዲህ ጋና ከ25 አመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ አሳምራ የገነባችው የዲሞክራሲ ስርአት ገድል፣ እጅግ በጥቂቱ ይህን ይመስላል፡፡ የኢህአዴግና የሚመራው መንግስት የሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብት አያያዝ፣ የፈጠረው የፖለቲካ ምህዳር፣ የዲሞክራሲ ተቋማቱ ነገረ ስራ በተለይም የህግ የበላይነት ምን እንደሚመስል ፀሀይ የሞቀው፣ አለም ያወቀው ጉዳይ በመሆኑ በዝርዝር መተረክ፣ የአንባቢዎችን ንቃተ ህሊና እጅግ አሳንሶ እንደመገመት ይቆጠራል፡፡
ታዲያ የዛሬ 25 ዓመት የዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ ሂደቱን እኩል በጀመርነው  በእኛና በጋና መካከል፣ ዛሬ የሰማይና የምድር ያህል ርቀት የተፈጠረው፣ እኛ የአርባ ቀን እድላችን ጎደሎ ስለሆነ ነው ወይስ ታሪካዊ ጠላቶቻችን ክፉ መተት አዙረውብን? ወይስ ደግሞ የእኛ ንቃተ ህሊና ከጋናውያን ያነሰ ሆኖ ነው?
ይህ ከቶውንም አይደለም፡፡ ይልቁንስ በእኛና በጋና መካከል ይህን የመሰለውን እጅግ ግዙፍ ልዩነት የፈጠረው፣ ከጋናውያን በተቃራኒ እኛ ጠንካራ የዲሞክራሲ ስርአት ለመገንባት ፍላጎቱና ቁርጠኝነቱ የይስሙላ የሆነ፣ ከህዝብና ከሀገር ጥቅም ይልቅ የቡድንና የፓርቲን ጥቅም የሚያስቀድምና የሀገርና የዜጎች መፃኢ እጣ ፈንታ ብሩህ እንዲሆን ነገን አሻግሮ ከማየት ይልቅ ሀገርና ህዝብን በትናንት የታሪክ ጉድፍ ተብትቦ የሚጎትት ክፉ አመራር ባለቤቶች በመሆናችን  ብቻ ነው፡፡


Read 9087 times