Print this page
Sunday, 16 February 2020 00:00

ለኢንዱስትሪ ቢዝነስ ያልተመቸ አገር፣ ተስፋው ይጨልማል

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(0 votes)

  “የሰሜን ዋልታ በረዶ እንዳይሳሳ …ያሳስበናል” እያሉ፣ ኢንዱስትሪን እንደ ሃጥያትና እንደ ወረርሺኝ የማጥላላት፣ ፋብሪካን እንደጠባሳና እንደ ጥላሸት የማንቋሸሽ ክፉ ሱስ የተስፋፋበት፣ እጅግ የተሳከረ ዘመን ላይ ነን፡፡
የኤሌክትሪክ ሃይል፣ ለወትሮ የእድገትና የስኬት ውጤት፣ ከዚያም አልፎ ወደላቀ እድገት የሚያስወነጭፍ የስኬት ኃይል እንደሆነ ይታወቅ ነበር፡፡ ዛሬ ዛሬ ግን፣ መቀለጃና መዘባበቻ እየሆነ ነው::  በአነስተኛ ዋጋ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት፣ አያስመሰግንም፡፡ ንስሐ እንደሚያስፈልገው እንደ አሳፋሪ ድክመትና እንደሴሰኝነት ነው የሚቆጠረው፡፡ ኤሌክትሪክን እስከማውገዝ የደረሰ ብልሹ አመል የተንሰራፋበት የቅሌት ዘመን ውስጥ ነን የምንኖረው፡፡
“ከኤሌክትሪክ ነፃ የሆነ ቀን” ወይም “መብራት የማጥፋት ሰዓት” ብለው እየደሰኮሩ፣ “ከተሞችን የማጨለም” የክብረ በዓል ቀን ማወጅ፣ እንዴት የጤንነት ሊሆን ይችላል? እንዲህ አይነት የጨለመና የተሳከረ አስተሳሰብ የተስፋፋው በመላው ዓለም የመሆኑ ያህል፣ ከድሃ አገራት በተጨማሪ፣ በብልጽግና ጐዳና ሲጓዙ የነበሩ የአውሮፓ አገራትም ጭምር፣ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ እየተዘፈቁ ነው፡፡
አሳፋሪነቱ እና አጥፊነቱ ግን፣ በድሃ አገራት ይከፋል፡፡
አንደኛ ነገር፣ ፋብሪካዎች በኤሌክትሪክ እጥረት በሚከስሩበት አገር ውስጥ፣ በፋብሪካዎች እጦትም በርካታ ወጣቶች በሚሰደዱበት፣ የስራ አጥ ወጣቶች ቁጥር ሚሊዮን በሚሊዮን  እየጨመረ የአመጽና የትርምስ ሰበብ በሚሆንበት ጨለማና ድሃ አገር ውስጥ፣ “መብራት የማጥፋት” በዓልን ማክበር ያሳፍራል፡፡ “ሲሉ ሰምታ ታንቃ ሞተች” ተብሎ የተተረተባት በወሬ የሰከረች ወገኛ ዶሮ አትሻልም እንዴ?
እንደ ኢትዮጵያ የመሳሰሉ ድሃ አገራት፣ ድህነትን በሚያባብስ ወገኛ ስካር ተጠምደው፣ ነገር አለሙ ዞሮባቸዋል፡፡
ሁለተኛ ነገር፣ “ኧረ ይሄ ስካር አይበጀንም:: ወደ ህሊና እንመለስ” ብለው እንድንነቃ የሚወተውቱ፣ የጥፋትና የጨለማ ጐዳናን ለመቃወም የሚተጉ ምሁራንና ተቋማት የሉንም፡፡
በሌላ በኩል፣ “ጨለማን ማክበር የጤና አይደለም” ብለው የሚከራከሩ በርካታ ምሁራንና ተቋማት፣ እንደ አሜሪካ በመሳሰሉ አገራት አሉ፡፡ “ከተሞችን የማጨለም ቀን” ሳይሆን፣ ብሩህ “የስኬት ቀን” የተሰኘ ክብረ በዓል እንደሚያስፈልግ የሚያስረዱ ምሁራን፣ በአውሮፓና በአሜሪካ ገና አልጠፉም፡፡
የሳይንስ፣ የቴክኖሎጂና የፋብሪካ ውጤቶችን በአግባቡ በመጠቀም፣ የበዓል ቀን ሰይመን፣ 1ስልጣኔን እናክብር፣ ብልጽግናን እናወድስ” በማለት፣ የተሳከረ የጨለማ አስተሳሰብን ለመከላከል የሚተጉ ተቋማት አሉ - በነ አሜሪካ፡፡
በአገራችን በኢትዮጵያ ግን፣ በስህተትና በጥፋት ላይ፣ ስካርንና ጨለማን የሚጨምር ሰው ነው የበዛው፡፡ ያለ ከልካይ፡፡
የትራንስፖርት እጥረትን ለማቃለል አለመትጋት፣ ትልቅ ችግር ነው፡፡  ሆን ብሎ የትራንስፖርት ችግርን ለማባባስ እቅድ ማውጣት ደግሞ፣ ሌላ አይነት ጥፋት ነው:: ይሄ፣ ተራ ስህተትና ጥፋት አይደለም:: የባሰም አለ፡፡ የትራንስፖርት እጥረትን ለማባባስ ገንዘብ ማባከን! ይሄስ የጤና ነው?
እንግዲህ ልብ በሉ፡፡ “ከመኪና ነፃ የሆኑ መንገዶች” እያሉ በኩራት የሚናገሩ ፖለቲከኞችና ባለስልጣናት፣ አርቲስቶችና አክቲቪስቶችን አይታችኋል፡፡ አገር ሲሰክር እንዲህ ነው፡፡ ቅሌትና ኩራት ተምታትተዋል፡፡
“ለአውቶብስ ብቻ” ብሎ የአስፋልት መንገዶችን በመዝጋት የትራንስፖርት እጥረትን የሚያባብስ፣ ይህንንም እንደ ስኬት ቆጥሮ በኩራት የሚደሰኩር፣ ለተጨማሪ ጥፋት፣ ሆን ብሎ እቅድ የሚያወጣ፣ ለእንዲህ አይነት እቅድም ከአለም ባንክ እና ከፈረንሳይ መንግስት ብድር እየወሰደ፣ በአገር ላይ እዳ የሚያበዛ ምሁርና ፖለቲከኛ ሞልቷል፡፡ የዚህን ያህል “ፍሬን የበጠሰ” ሆኗል የዘመናችንና የአገራችን ስካር፡፡  
ኢንዱስትሪና ፋብሪካ እየተንቋሸሹ በእንጭጩ ከተቀጩ፣ የፋብሪካ ዋና መንቀሳቀሻ ጉልበት የሆነውን የኤሌክትሪክ ኃይል ለማሰናከል፣ ትራንስፖርትን ለማደናቀፍ እቅድ ከተዘጋጀ፣ ለዚህም በበጀትና በብድር ሃብት ከባከነ፣ አገሬው ምን ተስፋ ይኖረዋል? ይህም ብቻ አይደለም ችግሩ፡፡
“ሁሉንም ነገር እሠራለሁ፤ ፍላጐታችሁን ሁሉ አሟላለሁ” እያለ፣ አለቦታው መግባት፣ ከመስራት ይልቅ ማበላሸት፣ ከማሟላት ይልቅ ማጉደል፣… መደበኛ የመንግስት ተፈጥሮ በመሰለበት አገር ውስጥ ነው የምንኖረው፡፡
የቢዝነስ ስራ ደግሞ፣  እንደ ማምታታትና እንደማጭበርበር እየተቆጠረ ይወገዛል:: በስግብግብነት የማታለልና የመበዝበዝ ያህል፣ የፋብሪካ ቢዝነስ ይኮነናል፡፡ “በካይ” ብሎ ይወነጀላል፡፡ እንዲህ አይነት ድፍን የክፋት አስተሳሰብ ካልተስተካከለ፣ የአገሪቱ ተስፋ እንዴት ሊፈካ ይችላል?
የፋብሪካ ስራ፣ ዋናው የስራ እድልና የእድገት ምንጭ፣ ዋናው የህልውና አለኝታ እንደሆነ ዘንግተን፣ እንደ ደመኛ ጠላታችን ከጠመድነው፣ የአገራችን ተስፋ እንዴት አይጨልምም?
የፋብሪካ ስራ፣ የስልጡን ኢኮኖሚ “አስኳል”፣ አስተማማኝ የብልጽግና “ኃይል” ነው፡፡ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ፣ ከኢንዱስትሪ ጋር ያልተሳሰረ የብልጽግና ታሪክና መንገድ የለም፡፡ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ፣ ብዙ ሕዝብ ያላቸው አገራት፣ በተዘዋዋሪ ሳይሆን በቀጥታ ለኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንት በመመቸት እና የፋብሪካ ስራዎችን በማስፋፋት እንጂ፣ በሌላ ተዓምር ቅንጣት የመበልፀግ ተስፋ የላቸውም፡፡
እናም፣ የአገራችን የተስፋዋ ልክ፣ ከኢንዱስትሪ ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ የማደግና የመበልፀግ፣ የስልጣኔና የክብር ተስፋዋ ብቻ ሳይሆን፣ የሰላምና የህልውና ተስፋዋም፣ በፋብሪካዎች  ብዛትና ምርት ነው ልኩ:: ለኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንት ከተመቸች ተስፋዋ ይፈካል፡፡ ካልተመቸች ተስፋዋ ይደበዝዛል፡፡  
ለኢንዱስትሪ ቢዝነስ “መመቸት” ማለት፣ ከእርሻና ከእንስሳት እርባታ፣ ከንግድና ከኮንስትራክሽን፣ ከባንክና ከኢንሹራንስ፣ ከትራንስፖርትና ከኪነጥበብ ቢዝነሶች የበለጠ፣ ልዩ ምቾት ለኢንዱስትሪ ማቅረብ ያስፈጋል ማለት አይደለም፡፡ “ለኢንዱስትሪ ቢዝነስ የተመቸ አገር፣ ለሌሎች የቢዝነስና የኢኮኖሚ መስኮች ሁሉ፣ እጅግ የሚመች አገር ይሆናል” የሚለውን ትክክለኛ መርህ ልብ እንበል ለማለት ፈልጌ ነው፡፡
የፋብሪካ ስራ፣ የስልጡን ኢኮኖሚ “አስኳል”፣ ዋና የብልጽግና “ኃይል” ነው ሲባልም፣ “መንግስት ድጐማና በጀት ይመድብለት” ማለት አይደለም፡፡ ለፋብሪካ ኢንቨስትመንት “ቅድሚያ” ትኩረት፣ ድጋፍና ማበረታቻ መስጠት ማለትም አይደለም፡፡
ይልቅስ፣ የኢንዱስትሪ እድገት፣ ለሌሎች የኢኮኖሚና የኑሮ መስኮች ሁሉ፣ ሰፋፊ የእድገት እድሎችን የመፍጠር ከፍተኛ ኃይል አለው ለማለት ነው፤ ኢንዱስትሪ አስኳል ነው የሚባለው፡፡
የዘይት ፋብሪካና የዘይት መደብር ይለያያሉ፡፡
የኢንዱስትሪ መስክ፣ ከስልጣኔ እመርታ ጋር የመጣ ከፍተኛ የብልጽግና ኃይል እንደመሆኑ መጠን፣ ከፍ ያለ ስልጡን አሰራርን ይጠይቃል፡፡
ዘይት ማምረትንና ዘይት መነገድን በማነፃፀር ልዩነቱን በቀላሉ መገንዘብ  ትችላላችሁ፡፡ ሁለቱም፣ ኑሮን ለማሻሻል፣ ህይወትን ለማለምለም የሚጠቅሙ፣ ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸው የእውቀትና የሙያ፣ የስራና የቢዝነስ መስኮች ናቸው፡፡ ነገር ግን፣ ፋብሪካ ከመትከልና ከማምረት ይልቅ፣ መደብር ለመክፈትና ለመነገድ የሚመርጡ ሰዎች ይበዛሉ፡፡ በብዙ እጥፍ ይበልጣሉ፡፡ ለምን?
ነገርዬው ያን ያህልም ረቂቅ ሚስጥር አይደለም፡፡
መንግስት፣ ድንገት በሲሚንቶ ላይ የዋጋ ተመን የሚያውጅ ከሆነ፣ ከፍተኛ ጉዳት የሚደርሰው ማን ላይ ነው ብላችሁ አስቡት:: በሲሚንቶ ፋብሪካ ላይ ወይስ በሲሚንቶ ነጋዴ ላይ? ምን ይጠየቃል? የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ላይ፣ የቢሊዮን ብሮች ኪሳራ ይወርድባቸዋል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፡፡
የፋብሪካ ስራ ከባድ ነው፡፡ የዘይት አምራች እና የዘይት ነጋዴ፣ ሁለቱም፣ ጥሪታቸውን አውጥተው፣ ሰፊ መጋዘን መገንባት ቢኖርባቸውም እንኳ፣ ዘይት ለማምረት መጋዘን መገንባት በቂ አይደለም:: መጋዘኑ እንዲሁ ፋብሪካ አይሆንም፡፡
እጅግ የከበዱ ብዙ ተጨማሪ ስራዎች ይኖሩታል - ማሽኖችን መትከል፡፡ የፋብሪካ ስራ  ህንፃ ገንብቶ ከማከራየት ይለያል፡፡ ፋብሪካው አንዴ ተገንብቶ የሚያልቅ ነገር አይደለም፡፡ በየእለቱና በየሰዓቱ፣ ያለማቋረጥ የሚካሄድ ግንባታ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በየቀኑ፣ በብዛትና በጥራት ማምረት፣ እጅግ ፈታኝ የፋብሪካ ስራ ነው - ከግንባታም የከበደ፡፡ ከዚያስ?
የመንግስት አደናቃፊነት፣ እና ነውጠኛ ስርዓት አልበኝነት
መንግስት፣ በዘፈቀደ ተራራ የሚያክል ታክስ፣ በዘይት ገበያ ላይ ቢጭን፣ ወይም “ህዝቡን ለመጥቀም”፣ “የሸማቾችን መብት ለማረጋገጥ”፣ “የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት” በሚሉ ሰበቦች፣ “የዘይት ዋጋ በግማሽ እንዲቀንስ ወስኛለሁ” ብሎ ቢያውጅ አስቡት፡፡ አሁን አሁንማ፣ “የካርቦን ልቀትን ለመቀነስ”፣ “የሰሜን ዋልታ በረዶ እንዳይሳሳ ለመከላከል” የሚሉ ወገኛ ሰበቦች ተጨምረዋል፡፡
የመንግስት ባለስልጣናትና ቢሮክራቶች፣ ባሰኛቸው ጊዜ የዋጋ ተመንና ቁጥጥር ሲያውጁ፣ ዘይት አምራቾችና ዘይት ነጋዴዎች፣ ብዙ ጉዳት እንደሚደርስባቸው አያከራክርም፡፡ ኪሳራ ይደርስባቸዋል፡፡
ልዩነቱ ምንድነው? ዘይት ነጋዴዎች፣ እንደገና እንዳይከስሩ የመሸሽ፣ ወይም ወደሌላ ንግድ የመግባት እድል አላቸው፡፡ ሌሎች ሸቀጦችና ምርቶች ላይ በማተኮር፣ ከኪሳራ ለመውጣትና ለማገገም ሊሞክሩ፣ “የዘይት ነገር እርም ብያለሁ” ሊሉ ይችላሉ፡፡
የዘይት ፋብሪካ ለመትከል አስቦ፣ ያጠራቀመውን ሃብት ሁሉ ኢንቨስት ያደረገ አምራች ግን፣ ፋብሪካውን እንደዘበት መቀየር አይችልም፡፡ አምና የተተከለ የዘይት ፋብሪካ፣ ዘንድሮ የመስተዋት፣ የሳሙና፣ የኤሌክትሮኒክስ ማምረቻ ፋብሪካ እንዲሆንለት የማድረግ እድል የለውም፡፡
እና ምን ይሻለዋል? በአንድ በኩል፣ ስራውን መቀየር አይችልም፡፡ በሌላ በኩል፣ እለት በእለት ዘይት ባመረተ ቁጥር ደግሞ፣ በመንግስት የዋጋ ቁጥጥር ሳቢያ፣ ኪሳራው እየጨመረ፣ እዳው እየከፋ ይሄዳል እንጂ፣ ከኪሳራ የማንሰራራት እድል አይኖረውም:: ምናለፋችሁ፤ የፋብሪካ ኢንቨስትመንት፣ ከንግድና ከኮንስትራክሽን ኢንቨስትመንት ይከብዳል፡፡
የፋብሪካ ስራ፣ ዋነኛ የብልጽግና “ኃይል” እንደመሆኑ መጠን፣ በዚያው ልክ ስልጡን አሰራርን የሚፈልግ ከባድ ስራ እንደሆነ ለማረጋገጥና ለመገንዘብ የሚያግዙ ሌሎች ቁምነገሮችም አሉ፡፡ የስርዓት አልበኝነት ጉዳትን ማነፃፀር ትችላላችሁ፡፡
“የማከፋፈያ መጋዘንህን፣ የችርቻሮ መደብርህን ከዚህ አካባቢ ንቀል” የሚል ስርዓት አልበኝነት፣ የንግድ ስራን ለኪሳራ ይዳርጋል፡፡
“ፋብሪካህን ከዚህ አካባቢ ነቅለህ ጥፋ” የሚል ተመሳይ ስርዓት አልበኝነትስ? ያኔ፣ ጉዳቱ የትየለሌ ይሆናል - አገርን የሚያጨልም ጉዳት፡፡ 

Read 3149 times