Saturday, 15 February 2020 11:24

ጠ/ሚኒስትሩ በተባበሩት አረብ ኢምሬት ከኢትዮጵያውያን ጋር ተወያይተዋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(22 votes)

  - ለቤተክርስቲያን መስሪያ ቦታ ጠይቀው በጐ ምላሽ ተገኝቷል

            ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ከሀሙስ ጀምሮ ሲያደርጉት የነበረውን ጉብኝት ዛሬ የሚያጠናቅቁ ሲሆን በሦስት ቀናት ቆይታቸው እዚያ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር በስፋት ተወያይተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመጀመሪያ ቀን ቆይታቸው፣ ከ3 መቶ በላይ ከሚሆኑ የኢትዮጵያውያን ተወካዮች ጋር በአዳራሽ የተወያዩ ሲሆን በትላንትናው እለትም ከተለያዩ የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ዱባይ ለተሰባሰቡ 15 ሺህ ያህል ኢትዮጵያውያን ንግግር አድርገዋል፡፡
በዚህ ንግግራቸውም ጠ/ሚኒስትሩ ኢትዮጵያውያን ከጥላቻና ከመከፋፈል እንዲርቁና በአንድነት ለክብራቸው እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
‹‹ከጥላቻና ከመከፋፈል ርቀን በአንድነት ወደ ብልጽግና መጓዝ አለብን›› ያሉት ዶ/ር ዐቢይ፤ በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን መብት ለማስከበር መንግስታቸው ጥረት እያደረገ መሆኑን አብራርተዋል፡፡  ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአደባባይ ስብሰባ ባሻገር ከ3 መቶ በላይ ከሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ተወካዮች ጋር በአዳራሽ ባደረጉት ውይይት የተለያዩ ጥያቄዎች ቀርበውላቸዋል፡፡
ከጥያቄዎቹም መካከል የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መስሪያ ቦታ በዱባይ እንዲፈቀድ የሚል ሲሆን ጠ/ሚኒስትሩም ጥያቄውን ለአገሪቱ መንግሥት አቅርበው በጎ ምላሽ ማግኘታቸውን አስታውቀዋል፡፡
‹‹በአጠቃላይ የኢትዮጵያውያን መብትና ክብር የሚጠበቀው ወደ ብልጽግና የምናደርገው ጉዞ ሲሳካ ነው›› ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች ለአገራቸው ብልጽግና የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ጠይቀዋል፡፡
በአገር ውስጥ ከሕግ ማስከበር ጋር ተያይዞ፣ “የኔ ብሄር አባል ተነካብኝ›› የሚለው አመለካከት እንቅፋት እንደሆነም አስረድተዋል - ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፡፡


Read 12545 times