Saturday, 15 February 2020 11:18

ጠ/ሚኒስትሩን የሚደግፍ ጥላቻን የሚያወግዝ ሰልፍ በጅማና አጋሮ ተካሄደ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(6 votes)

   ‹‹መሳደብ የኦሮሞ ሕዝብ ባህል አይደለም››

              ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድን፣ እንዲሁም መላውን የለውጥ አመራርና ብልጽግና ፓርቲን ለማበረታታት ያለመ ሰላማዊ ሰልፍ ሰሞኑን በጅማ ተካሄደ፡፡
ከትናንት በስቲያ ሀሙስ ከጠዋቱ 2፡30 ጀምሮ የጅማ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች በጅማ ከተማ ስታዲየም እንዲሁም የአጋሮና አካባቢው ነዋሪዎች በአጋሮ ከተማ አደባባይ የድጋፍ ሰልፍ ባደረጉበት ወቅት፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ጎን መቆማቸውን በተለያዩ መፈክሮች ገልጸዋል፡፡
አዲስ አድማስ ያነጋገራቸው የሰልፉ ተሳታፊዎች እንደገለፁት፤ ሰልፉ በዋናነት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ድጋፍ ለመስጠትና የጀመሩትን ለውጥ ለማበረታታት ያለመ ሲሆን የተዘጋጀውም በከተማዋ ወጣቶች እንደሆነ ታውቋል፡፡ በዚህ ሰልፍ ላይ ከጅማ በተጨማሪ ከአጐራባች የከፋ ዞንም የመጡ ተሳታፊዎች የሰልፉ አካል እንደነበሩ ታውቋል፡፡
በሰላማዊ ሰልፉ ላይ ከተሰሙ መፈክሮች መካከልም ‹‹በተጀመረው ለውጥና የዲሞክራሲ ጉዞ ጽኑ እምነት አለን!›› ‹‹መሳደብ የኦሮሞ ሕዝብ ባህል አይደለም!›› ‹‹ጅማ መሬትም ሰውም ጀግናም አላት!››፤ ‹‹ሰዎች በፖለቲካ አመለካከታቸው ሊሰደቡ አይገባም!››፤ “ከመንግሥት ጎን በመቆም ሰላማችንን አስጠብቀን ብልፅግናችንን እናረጋግጣለን!›› የሚሉት ይገኙባቸዋል፡፡
በዚህ የድጋፍ ሰልፍ ላይ የተገኙት የጅማ ከተማ ከንቲባ አቶ መኪዩ መሀመድ፣ ባደረጉት ንግግር፤ በግልፅ የሚታይን ለውጥ መካድ ለማንም አይጠቅምም መንግስት ሀገሪቱን ከገባችበት ችግር ለማውጣት ቀን ከሌት እየሠራ ነው፤ ይሄን ጥረት መካድ በፈጣሪ ዘንድም ያስጠይቃል ብለዋል፡፡
አንድ የሠልፉ መድረክ መሪ በበኩላቸው “ጅማ ላይ ያልተገባ ነገር የምታደርጉ ከድርጊታቸው ታቀቡ፤ እኛ እንደ ኦሮሞ ስድብን ተምረን አላደግንም፤ ጨዋነት ነው መገለጫችን እኛ የአባጅፋር ልጆች ስድብን አልተማርንም አንሳደብም” ብለዋል፡፡
የሠላማዊ ሠልፉ ተሣታፊዎች በበኩላቸው ጠ/ሚኒስትሩ ለሀገሪቱ ፖለቲካዊ ለውጥ የጀግንነት ተግባር ማከናወናቸውን ለመገናኛ ብዙሃን አስረድተዋል፡፡
አንድ የአካባቢው የሀገር ሽማግሌ “ዐብይን በአካል አውቀዋለሁ፤ እነ ፕ/ር መረራ በታሠሩበት ወቅት እባካችሁ እነዚህን ሰዎች አስፈቷቸው ብለን የሀገር ሽማግሌዎች ቢሮው ሄደን አነጋግረነው ነበር፤ እሱም የመለሰልን መልስ እኔም የእነ ፕ/ር መረራ እስር የስጨንቀኛል እንቅልፍ ይነሳኛል ለእነሱ መፈታት ነው የምንታገለው ብሎኝ ነበር፤ ቃሉን ጠብቆ አግኝቸዋለሁ” ሲሉ ጠ/ሚኒስትሩ በኦሮሞ ህዝብ ትግል ውስጥ ወሳኝ ሚና እንደነበራቸው አስረድተዋል፡፡
ሌላው የሠላማዊ ሰልፉ ተሳታፊ በበኩላቸው ዶ/ር ዐቢይ እና የለውጥ ሃይሉ ዋጋ ከፍሎ ብዙዎችን ከእስር ማስፈታቱን፣ ተሠደው የነበሩ እንዲመለሱ ማስቻሉን በመጥቀስ እንዲህ ላደረገ መሪ ስድብና ዘለፋ አይገባም ስድብና ዘለፋ የኦሮሞ ህዝብ መገለጫ አይደለም ብሏል፡፡
አንዲት የዚሁ ሰልፍ ተሣታፊ ወጣት በበኩሏ በጋራ ታግሎ ነፃነቱን ያገኘው የኦሮሞ ህዝብ እርስ በእርሱ ሊቃረን አይገባውም፡፡ “ዶ/ር ዐቢይን መደገፍ እንኳ ባንፈልግ መስደብ አይገባንም ለሀገሩ ለውጥ ሙሉ ጊዜውን የሰጠ መሪ ነው” ብላለች፡፡
በማህበራዊ ሚዲያ እየተዘላለፉ ከአንድነት ይልቅ ልዩነትን መስበክ ለማንም አይጠቅምም ያሉት ሌላው የሠልፉ ተሳታፊ የፖለቲካ ልዩነት በመከባበር ውስጥ ሊታይ ይገባዋል ብለዋል፡፡

Read 11687 times