Saturday, 15 February 2020 11:07

የመንግስትና ፓርቲ መዋቅር ግልጽ ድንበር እንዲበጅለት ተጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

   “ገዥው ፓርቲ የመንግስትን መዋቅር ተጠቅሞ ገቢ እያሰባሰበ ነው”

           የፓርቲና የመንግስት ድርሻዎች በግልጽ በተግባር እንዲለዩ “ነፃነት እና እኩልነት ፓርቲ” የጠየቀ ሲሆን ገዥው ፓርቲ የመንግስትን መዋቅር በመጠቀም፣ አሁንም የፓርቲ ገቢ እየሰበሰበ ነው ሲል ከሷል፡፡
“ባለፉት ሶስት አስርት አመታት በሀገራችን ከታዩ መሠረታዊ የፖለቲካ ችግሮች አንዱ፣ የፓርቲና የመንግስት መቀላቀል የፈጠረው ውስብስብ ሂደት ነው ያለው የፓርቲው መግለጫ ፤ከለውጡ በኋላም ይኸው አሠራር መቀጠሉን በተጨባጭ ማስረጃ አረጋግጫለሁ - ብሏል በጊዜ ሊታረም እንደሚገባ በመግለጽ፡፡
ባለፉት ጥቂት ሣምንታት ብቻ ገዥው ፓርቲ ከባለሀብቶች ገንዘብ ለመሰብሰብ የተለያዩ አስፈፃሚ መስሪያ ቤቶችን በመጠቀም ጥሪ ማካሄዱንና የስብሰባውን አጀንዳ ሳያውቁ የተሠበሰቡ ባለሀብቶችም ለፓርቲው ገንዘብ እንዲያዋጡ መጠየቃቸውን “ነፃነትና እኩልነት ፓርቲ” ጠቁሟል፡፡
ይህ አይነቱ አሠራር በተለያዩ ክልሎችም በስፋት እየተፈፀመ መሆኑን መገንዘቡን፣ በፌደራልና  በክልል መስሪያ ቤቶች የሚሠሩ የመንግስት ሠራተኞች የፓርቲ አባልነት መዋጮ  ከደመወዛቸው ላይ የመቁረጥ አሠራር ዛሬም መቀጠሉን ማረጋገጡን ጠቁሞ፤ ይህ ሁኔታ በአስቸኳይ ሊቆም ይገባዋል ብሏል፡፡
ፓርቲው በመግለጫው፤ ለፓርቲ ሃብት የማሰባሰብ ስራ ላይ የሚሠማሩ ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ የመንግስት ስልጣናቸውን ተጠቅመው ጫና ከማሳደር እንዲቆጠቡ፣ ፓርቲው ገቢዎቹን ከመንግስት መዋቅር ውጪ እንዲሰበስብ፣ እንዲሁም በአጠቃላይ ገዥው በፓርቲ ድርጅታዊ መዋቅሩን ከመንግስት መዋቅር በግልጽ እንዲለይ “ነፃነትና እኩልነት ፓርቲ” ጠይቋል፡፡ 

Read 10866 times