Saturday, 15 February 2020 11:07

በኦሮሚያ፣ ደቡብ እና ሶማሌ ክልል ኮሌራ በወረርሽኝ መልክ እየተዛመተ ነው ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

    እስካሁን 76 ሰዎች ሞተዋል

          በኦሮሚያ፣ ደቡብ እና ሶማሌ ክልል እየተሰራጨ ነው በተባለው የኮሌራ ወረርሽኝ 76 ሰዎች መሞታቸውን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ያስታወቀ ሲሆን አለማቀፍ ተቋማት፣ መንግስት ለወረርሽኙ ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡
ካለፈው አመት ሚያዚያ ወር ጀምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተከሰተው የኮሌራ በሽታ ከጊዜ ወደ ጊዜ አድማሱን እያሰፋ ነው ብሏል - የኢንስቲትዩቱ ሪፖርት፡፡
ወረርሽኙ በአሁኑ ወቅት በደቡብ ክልል 11 ወረዳዎች፣ በኦሮሚያ ሶስት ወረዳዎችና በሶማሌ ክልል ሁለት ወረዳዎች በጠቅላላ በ16 ወረዳዎች ከ4 ሺህ በላይ ሰዎችን ማጥቃቱን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ ወረርሽኙን ለመቋቋም የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ነው ብሏል፡፡
የኮሌራ በሽታ “ቫይብሮ ኮሌራ” በተባለ ተህዋስ ምክንያት የሚከሰት አንጀትን የሚያጠቃ በሽታ ሲሆን በባህሪው አጣዳፊ በመሆኑ ተገቢውን የህክምና ክትትል ካላገኘ በአምስት ቀናት ውስጥ ለሞት የሚዳርግ በሽታ ነው ተብሏል፡፡
በአሁኑ ወቅት በሽታው በወረርሽኝ ደረጃ ከተከሰተባቸው አካባቢዎች፣ በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን አዶላ ሬዴ እና አባያ ወረዳዎች፣ በደቡብ ክልል በጐፋ ዞን ደብረፀሐይና ዛላ ወረዳዎች፣ በጋሞ ዞን ጋራ መርታና ከምባ ወረዳ፣ በደቡብ ኦሞ ዞን ሰላማጐ፣ ማሌና አሌ ወረዳ እንዲሁም በኮንሶ ዞንና ጌዲኣ ዞን ወናጐ፣ እንዲሁም በሶማሌ ክልል ሞያሌ ወረዳ ይገኙባቸዋል፡፡

Read 11427 times