Saturday, 15 February 2020 11:03

ኢዴፓ በቢሮ ጉዳይ በኢዜማ ላይ ክስ መሰረተ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

ሁለት ቢሮዎቼ በኢዜማ ያለ አግባብ ተወስደውብኛል የሚለው የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) በፍ/ቤት ክስ መሰረተ፡፡
በአዲስ አበባ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 እና 9 (ግሎባልና ስታዲየም አካባቢ) የሚገኙ ቢሮዎቹ እንዲመለሱለት ነው ኢዴፓ ክሰ የመሠረተው፡፡
ጽ/ቤቱን ከ1992 ዓ.ም ጀምሮ ከመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ ጋር ውል ፈጽሞ ሲጠቀምባቸው እንደነበር ጠቁሞ፤ ሆኖም በኢዴፓ ውስጥ የተፈጠረውን ችግር ተከትሎ፣ ከኢዜማ ጋር ተደርጓል በተባለ ውህደት፣ ቢሮዎቹ እንደተወሰደበት የገለፀው ኢዴፓ፤ ጽ/ቤቶቹ እንዲመለሱለት ያቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት በማጣቱ ወደ ፍ/ቤት ለመሄድ መገደዱን የፓርቲው ፕሬዚዳንት አቶ አዳነ ታደሰ ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡
ባለ 14 ገጽ የፍትሃ ብሄር ክስ በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ቂርቆስ ምድብ 2ኛ ፍ/ብሄር ችሎት ክስ የተመሰረተበት ኢዜማ፤ ምላሹን የካቲት 19 ቀን 2012 ዓ.ም እንዲያቀርብ እንዲሁም ክሱን ለመስማት ለመጋቢት 2 ቀን 2012 ቀጠሮ ተሰጥቶታል፡፡
በኢዴፓና ኢዜማ መካከል ሌላኛው የንብረት ውዝግብ የኢዴፓ ተቀማጭ ገንዘብ ጉዳይ ሲሆን ይህንን ለመፍታትም ከባንኩና ከኢዜማ ጋር ውይይት እየተደረገ መሆኑንና በውይይት የማይፈታ ከሆነ ግን ፓርቲው ተመሳሳይ ክስ ለመመስረት እንደሚገደድ አቶ አዳነ አስረድተዋል፡፡
በአጠቃላይ ኢዴፓ እንዲመለስለት እየጠየቀ ያለው ገንዘብም 1 ሚሊዮን ብር ገደማ እንደሆነ ታውቋል፡፡ አቶ አዳነ ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡


Read 1139 times