Saturday, 15 February 2020 11:01

ምክር ቤቱን ያወዛገበው የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃ ማሰራጨትን የሚከለክለው አዋጅ ፀደቀ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

  - ከመሰረቱ የተበላሸውንና በማሻሻያ ስም ተቀባብቶ የቀረበውን ረቂቅ ሕግ ምክር ቤቱ ሊያጸድቀው አይገባም፡፡
    - ከመሰረቱ የተበላሸው የፀረ ሽብር ሕግ አውጥተን የዜጎችን ጥፍር ስንነቅል ዜጎችን ወደ እስር ስንወረውር ነው፡፡
    - ይህ ምክር ቤት የአንድን ሰው ጥቃት ለመከላከልና በተቃራኒው ደግሞ የአንድን ሰው ጥቅም ለማስከበር ሕግ ያወጣ ምክር ቤት ነው፡፡
    - ብሮድካስት ባለሥልጣን የማህበራዊ ሚዲያ አገልግሎት ሰጪዎችን እንዲቆጣጠር ኃላፊነት ተሰጠው፡፡
    - ከ5 ሺ በላይ ተከታይ ባለው ማህበራዊ ሚዲያ ሕዝብን የሚያጋጭ ሀሰተኛ መረጃን ማሰራጨት በ3 ዓመት እስርና በመቶ ሺ ብር የገንዘብ ቅጣት
ያስቀጣል፡፡
                        የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን ባልተለመደ ሁኔታ ያወዛገበው የጥላቻ ንግግርና የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣው ረቂቅ አዋጅ ፀደቀ፡፡ አዋጁ በ23 የተቃውሞ ድምጽ፣ በሁለት ድምጽ ተአቅቦና በአብላጫ ድምጽ ድጋፍ ጸድቋል፡፡
አዋጁ በምክር ቤቱ ከትናንት በስቲያ በፀደቀበት ወቅት አዋጁ ሕገ መንግሥቱን የሚቃረንና ፀረ ዴሞክራሲያዊ የሆነ አዋጅ ነው የሚል ተቃውሞ ደርሶበታል። በአገራችን ሀሰተኛ መረጃ ማሰራጨትን የሚከለክሉ ሕጎች ቀድሞውንም ያሉን በመሆኑ አሁን የዚህ አዋጅ መጽደቅ ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 29 ለዜጎች የሰጠውን ሀሳብን በነፃ የመግለጽ መብት የሚጻረር ነው ተብሏል፡፡
ዶ/ር አድሃኖም ኃይሌ የተባሉ የምክር ቤቱ አባል ባቀረቡት የተቃውሞ ሀሳብ የምክር ቤቱ የሕግ ፍትህና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር እይታ የተመራለትን ረቂቅ አዋጅ ተመልክቶ ያቀረበው የማሻሻያዎች የውሳኔ ሀሳብ ተቀባይነት ሊኖረው አይገባም ብለዋል፡። ከመሰረቱ የተበላሸን ነገር ምንም ያህል ቢቀባቡት ለውጥ አያመጣም፡፡ ተደረገ የተባለው ማሻሻያም በዋናው ሀሳብ ላይ ለውጥ የሚያመጣ አይደለም ብለዋል፡፡ አዋጁ የአገሪቱን ሕገ መንግሥት የሚፃረርና የዜጎችን ነፃነት የሚጋፋ ነው ያሉት ዶ/ር አድሃኖም አካል ጉዳተኞችን በፆታና በብሔር የተወሰኑ ወገኖችን ከጥቃት ለመከላከል በሚል ሰበብ የወጣው አዋጅ አዛኝ ቅቤ አንጓችነት ነው ብለዋል፡፡ አዋጁ ለፖለቲካ አመራሮች፣ ለሚዲያ ባለሙያዎች፣ እና ለተለዩ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ቢወጣ ሊያስማማን ይችላል በዚህ መልኩ ግን በዜጎች ላይ ሁሉ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል አዋጅ ማጽደቁ ተቀባይነት ሊኖረው አይገባም ብለዋል፡፡
ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን በመገደብ እውነትን ማግኘት አይቻልም ያሉትና የአዋጁን መጽደቅ በጥብቅ የተቃወሙት ወገኖች አዋጁ ሕገመንግሥቱን የሚፃረር በመሆኑ መጽደቅ የለበትም ሲሉ ተሟግተዋል፡፡
የጥላቻ ንግግርንና ጉዳት አድራሽ የሀሰተኛ መረጃዎችን ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣው አዋጅ የዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅና የአገሪቱን ሰላምና ፀጥታ ለማስከበር የሚኖረው አስተዋ    ጽኦ ከፍተኛ ነው ተብሏል፡፡
በሕገ መንግሥቱ የተሰጠን ሀሳብን በነፃ የመግለጽ መብት ከዚህኛው ሕግ ጋር የሚያገናኘቸው አንዳችም ጉዳይ የለም ይህ አዋጅ የጥላቻ ንግግርንና ጉዳት አድራሽ ሀሰተኛ መረጃዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ማህበራዊ ሚዲያዎችን ጨምሮ በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን የሚታዩት ይፋዊ የጦርነት ቅስቀሳዎችና በየዘፈኖቻችን የሚታዩት ግጭት ቀስቃሽ ጉዳዮች እጅግ ለከፋ የእርስ በርስ ግጭት የሚዳርጉና ለመቆጣጠር የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ የሚያስፈልጋቸው ናቸው ተብሏል፡፡
ከመሰረቱ የተበላሸውን ነገር እየቀባቡ ለማሳመር መሞከር ተገቢ አይደለም በሚል ከምክር ቤቱ አባል ከዶ/ር አድሃኖም ኃይሌ የተሰጠውን አስተያየት መነሻ አድርገው ሀሳባቸውን የገለፁት የሕግና ፍትህ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢው አቶ ተስፋዬ ዳባ ከመሰረቱ መበላሸቱ እሙን ነው ጥያቄው ግን መሰረቱ መቼ ነበር የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ መሰረቱ የተባላሸው በሽብር ሕጉ ሰበብ የዜጎችን ጥፍር እየነቀልን ስናሰቃይ ዜጎችን ወደ እስር ቤት ስንወረውር ነው፡፡ መሰረቱ የተበላሸው ያኔ ነው፡፡ ዛሬ የተበላሸውን መሰረት ማስተካከል የምንችልበትን ሥራ እየሰራን ነው፡፡ ይህ ምክር ቤት እኮ በዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ጉዳይ የአንድን ሰው ጥቅም ለማሳጣት አዋጅ ያወጣ በተቃራኒው ደግሞ የአንድን ሰው ጥቅም ለማስጠበቅ አዋጅ ያሻሻለ ምክር ቤት ነው፡፡ አሁን የአገርንና የሕዝብን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ የሚያስችል አዋጅ ለማውጣት እንዲህ መቃወሙ አስገራሚ ጉዳይ ነው ብለዋል ጉዳዩ ለምክር ቤቱ ይህን ያህል ተቃውሞ ይገጥመዋል የሚል ግምት እንዳልነበራቸው የተናገሩት አቶ ተስፋዬ አዋጁ መውጣት ከነበረበት ጊዜ እጅግ ዘግይቶ የወጣ ቢሆንም አሁንም ነገሮችን ለማስተካከልና አገርና ሕዝብን ከጥፋት ለማዳን ጊዜው አልረፈደም ብለዋል፡፡
የአዋጁን መጽደቅ አስመልክቶ ከምክር ቤቱ አባላት የተነሳው ተቃውሞ መሰረቱ ፈጽሞ እንዳልገባቸውና ምክር ቤቱ አዋጁን በማፅደቁና የጥላቻ ንግግሮችንና ፀብ አጫሪና ጉዳት አድራሽ የሀሰተኛ መረጃዎችን ስርጭት የመቆጣጠሪያ አዋጅ ማውጣቱ ሊጎዳ የሚችለው የኢትዮጵያን መፍረስ የሚናፍቁና ይህ እንዲሆን ከፍተኛ በጀት መድበው የሚንቀሳቀሱ ወገኖችን ብቻ ነው ብለዋል፡፡
ግጭትን መቀስቀስና ማነሳሳት ቀደም ሲልም በፀደቁ የኢትዮጵያ ሕግጋት የተከለከለ መሆኑን ያስታወሱት የምክር ቤቱ አባላት ማህበራዊ ሚዲያዎችን የመሳሰሉ ዘመን ወለድ የመገናኛ ብዙሃን ባልነበሩበት ጊዜ የወጣውን አዋጅ ከዘመኑ ጋር እያጣጣሙ መሄድና ዘመኑን መከተል ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ለዚህም እንደ ማሳያ በቅርቡ በተለያዩ አካባቢዎች በተቀሰቀሱ ግጭቶች ሳቢያ ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎችና ግጭቱ እንዲቀሰቀስ መልዕክት የተላለፈባቸውን መንገዶች ማየቱ ብቻ በቂ እንደሆነም የምክር ቤቱ አባላት በዚሁ ረቂቅ ሕጉን ባፀደቁበት አስቸኳይ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገልጿል፡፡
የንግግር መብት ፍፁማዊ አይደለም ያሉት የምክር ቤቱ አባላት ለአገርና ለሕዝብ ደህንነት ስጋት በሚሆንበት ጊዜ ሀሳብን የመግለጽ መብት ሊገደብ ይችላል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የሚታየውንና ብሔሮችን ለጥቃት የሚያጋልጠው፣ ግለሰቦች በስም እየተጠቀሱ አደጋን እንዲጋፈጡ የሚያደርገው እንዲሁም በደቦ በሚፈፀሙ ጥቃቶች የሰዎች ሕይወት ለአደጋ እንዲጋለጥ የሚዳርገው ልጓም ባልተበጀለትና ሀሳብን በነፃነት በመግለጽ መብት በተሸፈነ ሕገወጥነት ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ከትናንት በስቲያ በ23 የተቃውሞ ድምጽ፣ በ2 ድምፀ ተአቅቦና በአብላጫ የድጋፍ ድምጽ አዋጅ ቁጥር 1/85/201 ሆኖ የፀደቀው የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣው አዋጅ ከ5 ሺ በላይ ተከታይ ባላቸው እንደ ፌስቡክ ባሉ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይም ተፈፃሚ ይሆናል ተብሏል፡፡
የጥላቻ ንግግሩ ወይም ጉዳት አድራሽ ሀሰተኛ መረጃው የተሰራጨው ከ5 ሺ በላይ ተከታዮች ባሉት የማህበራዊ ሚዲያ ገጽ ላይ ከሆነ እስከ ሶስት ዓመት በሚደርስ የእስርና እስከ አንድ መቶ ሺህ ብር በሚደርስ የገንዘብ ቅጣት እንደሚያስቀጣም አዲሱ አዋጅ ይደነግጋል፡፡ የኢትዮፕያ ብሮድካስት ባለሥልጣንም የማህበራዊ ሚዲያ አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች ግዴታቸውን በአግባቡ መወጣታቸውን እየተከታተለ ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርግም በፀደቀው አዋጅ ላይ ተቀምጧል፡፡


Read 481 times