Saturday, 08 February 2020 16:06

እኔ ተጎድቼ

Written by  ነ.መ
Rate this item
(11 votes)

   እኔ ተጎድቼ
          ነ.መ

ትዝ ይልሻል ውዴ ሆዴ፣
አንቺ የልቤ ሁዳዴ!
ፆም እንያዝ ተባብለን
እንዳቅማችን ተሟሙተን
አንድ ሆቴል “በልተን ጠጥተን”
“ቦዩን አልጋ አለ ወይ?” ብለን
ትዝ ይልሻል ምን እንዳለን?
“ይቀልዳሉ እንዴ ጋሼ?
እንኳን አልጋው ይቅርና
ጨለማው ተይዟልኮ!” አለን፡፡
ዕውነትም ዙሪያውን ብናይ፤
ጨለማው በመኪና ሞልቶ
መኪናው በጥንዶች ትንፋሽ፣ የፍቅር ምጥ ሳግ
አግቶ
ዕውር ጨለማ በዕውር ሰው፣ ፆም እየያዘ ነው
ተግቶ!
በመቀደማችን ነዶን
ከወሲብ ጦሩ ራቅ እንዳልን
እንዳቅሜ አበባ ሸልሜ፣ ለፆም መያዣሽ ሰጠሁሽ
የፆም መያዣ ቀለበት፣ በጣትሽ ላይ አሰርኩልሽ
በወርቅ ይሁን ባርቲፊሻል፣ ፆም ከያዝሽ ምን
ቸገረሽ!!
የፆም መያዣ ፍቅር፣ ጭፈራውን ጋብዤሻለሁ
በቃ አለቀ ውዴ ሆይ! ፆም ይዘሻል፤ ፆም ይዣለሁ!
እግረ መንገዳችንንም፡- ሥጋ መግዛቱን ፆመናል
ቅቤ ማሽተትን ገድፈናል
ዶሮን ከነባልትናዋ፣ በሰላም ተገላግለናል
“እንዳካሄድ” ሳስበው፣
የኢኮኖሚያችን መፍትሔ፣ በርትቶ ፆምን መያዝ
ነው፡፡
ዛሬ ደግሞ እዚህ ደረስን፣ ሥጋ መቼም ያው ሥጋ
ነው
በእኔው ቆርጠሸ ብትፈስኪ፣ ብትፀድቂ ነው
እሚሻለው!
የፆመ ባልፆመ አጣማጅ፣ ከፈሰከ ፋሲካ ነው፡፡
ከሁለት ወር ቆይታ ዳር፣ ደሞ ዛሬ ስንገናኝ
በሬው ፆሟል፣ እኔ አልፆምኩም፤ ብዙው የፍስክ
እኔ ነኝ
አንቺ ውስጥ የከረምኩትን፣ ዕውን ረስተሸኝ ከሆነ
አዲስ ፋሲካ አግኝተሻል፣ በአካል በነብስ የዘበነ!!
እናም ያልፆምኩት ላንቺው ነው፣ ፍስክ ገላ ሆኜ
እንድገኝ
ባልፆመ ሥጋ ፈስከሽ፣ ከልብሽ እንድትፀድቂልኝ፡፡
አንቺም አንቺን ሰጥተሽኛል፣ እኔም እኔን ሰጥቻለሁ፤
አንቺም በእኔ ፈስከሻል፣ እኔም ባንቺ ፆም ይዣለሁ!!
ምንም ትርጉሙ ባይገባኝ፣ “ፆም ማኪያቶ”
እንደሚሉት
ፍቅርም ማኪያቶ አያጣ፤ ቢያንስ ባይን የሚገበዩት!
ይህንን ብጠራጠርም
ዕውን ከፆምሽ ፈስኪብኝ
ሥጋ ለሥጋ የሄደ፣ ጥይት አይጎዳም ይላሉና፤
እኔስ አላንቺ ማን አለኝ፡፡
ባንቺ ልፅደቅ በቃ ሆዴ፣ አንቺም በኔ ፅደቂብኝ፡፡
“እኔ ተጎድቼ! ይላል፣ ያገሬ ነጋዴ ሲቀኝ!
በቃ “እኔ ተጎድቼ”፣ በመጣሁበት ውሰጂኝ”!!
(ለፆም መያዣ እና ለፍስክ ፍቅረኞች)
በ2006 ሁዳዴ ፆም መያዣ ተጀምሮ

Read 3164 times