Print this page
Saturday, 08 February 2020 15:35

ተማሪዎችን መመገብ ሃጢአት ነው?

Written by  ደ.በ
Rate this item
(3 votes)

   የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የነበሩት ሊንደን ቢ. ጆንሰን ስለ ድህነት ሲናገሩ፤ ‹‹ድህነት ማለት ምን ማለት እንደሆነ ስሜቱ ይገባኛል፤ ስራ አጥ ነበርኩ፤ ዳቦ ለመብላት የሰዎች ጫማ ጠርጌያለሁ፤ ከማለዳ እስከ ምሽት አንዲት ዶላር ለማግኘት ዳክሬያለሁ›› ይላሉ፡፡ ከዚያም ባለፈ ከቆሻሻ ገንዳ ውስጥ የሚበላ ነገር ፍለጋ የሚባዝኑትን ሕጻናት ሕይወት ያስታውሳሉ:: ይህን ያሉት ትውልድን ለመለወጥ ሕጻናትን ማሰብ እንደሚያስፈልግ ለማሳሰብ ነው፡፡
እኔም ያስታወስኳቸው በዋዛ አይደለም፣ በቅርቡ አነጋጋሪ አጀንዳ ስለሆነው የሕጻናት ምገባ ለማንሳት አስቤ ነው፡፡ እኛ ሀገር ጥሩ ሰርቶ ከመመስገን ይልቅ ስድብና ነቀፋ መጥገብ የተለመደ ነው፡፡ ቀደም ሲል ያዳበርናቸው ባህሎች፣ ለዚህ ጎጂ ምግባራችን አስተዋጽኦ ያደረጉ ይመስለኛል፡፡ ምናልባት አንድ ሰው ብዙ በጎ ነገር ቢሰራ እንኳ የተሳሳታት ጥቂት ነገር  ጎልታ፣ ከዓመት እስከ ዓመት ልታስተቸው ትችላለች፡፡ ለዚህ ችግራችን ጥሩ ማሳያ የሚሆነው ብዙ መልካምና አስደናቂ ድሎችን ያጎናጸፉን ጠቅላይ ሚኒስትራችንን የምናይበት መንገድ ነው፡፡ ሀገራችንን በሚገርም ሁኔታ ከመከፋፈልና ከመገፋፋት ለማውጣት ከመስራታቸው ጎን ለጎን፣ በርካታ ፕሮጀክቶችን በመምራት ተጠምደው እያየን፣ የሚፈጠሩ ጥቃቅን ችግሮችን እየፈለፈልን መተቸት ይቀናናል፡፡ ይህ የቆየ ባሕላችን ውጤት ነው፡፡
እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ ፎቅ የጋረዳቸው፣ በሺህ የሚቆጠሩ ሕጻናት ረሃብተኞች አሉ፡፡ ይህንን ችግር በይበልጥ ያወቅሁት መምህርት የሆነች ጓደኛዬ፣ ገጠመኞችዋን ከነገረቺኝ በኋላ ነው፡፡ እናም ባሰብኩት ቁጥር ነገሩ ያሳዝነኛል:: መምህርቷ ያስተማረችው በከተማችን እምብርት በሚባልና በኢኮኖሚ አቅሙ በእጅጉ የተጎዳ አካባቢ ነበር፡፡ ይሁንና ይህቺ መምህርት ስሰና አዛኝ ስሜት ያላት በመሆኗ የምታየው ነገር  ከአቅሟ በላይ ሆኖባት ስራዋን ለመተው ተገዳለች፡፡ “ማበድ አልፈልግም” ስትል ከሥራ የለቀቀችበትን ምክንያት ነግራኛለች:: ምንም ስሜት የማይሰጣቸው ጨካኞች የሞሉትን ያህል ስለ ሌሎች እንቅልፍ የሚያጡና የሚሰቀቁ ጥቂቶችም አሉ፡፡ ዓለም ሚዛንዋን የጠበቀችውም በዚህ ይመስለኛል፡፡
ጓደኛዬ እንደነገረችኝ፤ የምታስተምርበት ትምህርት ቤት ሕጻናቱ ብዙ ጊዜ እንቅልፍ ሲያዳፋቸው ግራ ይገባት ነበር፡፡ በኋላ ግን ነገሩን ጠይቃ ስትረዳ ጉዳዩ ሌላ ነው፡፡ ልጆቹ የማይጫወቱት፣ መምህር እያስተማረ የሚተኙት ረሃብ እያንገበገባቸው ብቻ ሳይሆን ሰውነታቸውን አዝሎት ነው፡፡ ይሁንና ካወቀች በኋላም ምንም ማድረግ አልቻለችም፤ አንዳንዴ የባሰባቸውን ሕጻናት ክበብ እየወሰደች ብታበላም ልትዘልቀውና ሁሉንም ልታግዝ አልሆነላትም::  በዚህም የተነሳ ሥራዋን በመተው ስቃዩን ለመሸሽ መረጠች፡፡ ስለ አንድ ተማሪዋ የአንድ ቀን ገጠመኝ ያወራችኝ አይረሳኝም፡፡ ልጁ አንድ ቀን ጧት እየፈገገ መጥቶ ‹‹ቲችር፤ ትናንትና ቤት የገጠመኝን ብነግርሽ…›› አላት፡፡
‹‹ምን አገኘህ?›› አለችው፡፡
‹‹ቤት ስሄድ የድንች ወጥ በእንጀራ በላሁ›› አላት፡፡
ማመን አልቻለችም፤ ያሰበችው ስጋ በላሁ ሊለኝ ነው ብላ ነበር፡፡ ግን አይደለም፤ ድንች ወጥ ነው፡፡ ያንን አይነት ወጥ ከበላ ስድስት ወሩ ነበር፡፡ እንግዲህ ውቧ አዲስ አበባ ይህንን የመሰለ ሰቆቃ ይዛለች፡፡ ለአንዳንዶቻችን ይህ ሊገባን አይችልም፡፡ ዉሻውን በግ አርዶ ለሚቀልብ ቱጃር፤ ይህ ተረት ተረት ነው:: ለዚህም ነው አንዳንዶች ማህበራዊ ሚድያ ላይ ተጥደው፣ “ታከለ ዑማ ሕጻናትን መመገብ ብሎ ፖለቲካ ይሰራል” እያሉ የሚጽፉት፡፡ በጎ ስራ በመስራት ለፖለቲካ መጠቀም አዲስ ነገር አይደለም፤ ይኸኛው ግን ከዚያ በላይ ነው፡፡ የሰው ልጅ ከፖለቲካው በፊት ዳቦ መብላት አለበት፡፡ ሕጻናትን መመገብ ደግሞ የነገዪቱን ሀገር ዕድል የሚወስን ስራ መስራት ነው፡፡ በየቦታው ለአገር አሳቢ መስሎ የሚንጫጫው ሁሉ፣ ትናንት ሃገር ሲዘርፍ፣ ያለ ቀረጥ እቃ ሲያስገባ፣ የሀገር ሀብት ሲሰርቅ የነበረ ነው፡፡ አንዳንዱም ሳይገባው ነገሩን በብሄር ስሌት እያሰላ ያወራል፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ሕጻናት ብሔር የላቸውም፤ ምስኪን የኢትዮጵያ ልጆች ናቸው፡፡
እንግዲህ እነዚህ የኢኮኖሚ ችግር ያለባቸው ልጆች ዩኒፎርም መልበሳቸውና ጦማቸውን ያለመዋላቸው፣ በአንዳንድ ለሃገር አሳቢ መሳዮች ዘንድ መቆርቆር የፈጠረ ይመስላል፡፡ እንደ አስቆርቱ ይሁዳ የሚባክነው ገንዘብ አሳዘናቸው:: እነርሱ ለቁርስ የማትበቃቸው ሳንቲም ለሕጻናቱ የወር ቀለብ መሰጠቱ የሃገራቸውን ኢኮኖሚ እንዳይጎዳው አሳሰባቸው፡፡ የስላቁ መጨረሻ ይህ ነው፡፡ “ኢንጂነር ታከለ ዑማ ሊወደድበት ነው” ብለው ሙሾ አወረዱ፡፡ እርሱ ከሚመሰገን ሕጻናቱ በረሃብ ቢሞቱ፣ በረንዳ ቢጣሉ ይሻላል፡፡ ደጋግ ኢትዮጵያውያን ነን የሚሉ ናቸው እንዲህ የሚያስቡት፡፡
እነዚህ ዳቦ ለምን ተሰጣቸው የሚባሉ ልጆች፤ ነገ የሀገሪቱ ጥያቄ መልሶች ሊሆኑ እንደሚችሉ ተዘንግቷል፤ ወይም የደሃ ልጆች ትልቅ ቦታ አይደርሱም፣ የሚል ኋላ ቀር አስተሳሰብ ሰፍኗል፡፡ ለዚህ ግን የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጥሩ መልስ ይሰጡናል፤ ማንም ሰው ታላቅ ሆኖ አይወለድምና!!
ስለ ሃገራችን ሕጻናት ፈተና ለመረዳት፣ በቅርቡ ወይዘሮ ፍሬአለም ሺባባው በጻፉት መጽሐፍ ውስጥ የተጠቀሰውና ባዶ የምሳ ዕቃ ይዞ ት/ቤት የሚመጣው ህጻን አሳዛኝ ሕይወት በቂ ነው፡፡ ታዲያ ይህንን አሰቃቂ ሕይወት ያየ ሰው በተቻለ መጠን የልጆቹ ስቃይ የሚቀየርበትን አጋጣሚ ይናፍቃል እንጂ፣ “ለምን በረሃብ አይቆሉም” ብሎ ምላሱን የሚመዝ አይመስለኝም፡፡ ምናልባት ጤና ማጣት ካልሆነ በቀር፡፡
እንዲያውም መንግስት ከዘረፋና ሃብት በውጭ አገራት ከማከማቸት አባዜ ወጥቶ፣ በልጆች ላይ ኢንቨስት ሲያደርግ ሊመሰገንና ከጎኑ ሊቆም ይገባ ነበር፡፡ ግን ጠማማነቱስ የት ይሂድ! ይልቅስ የድሃው ጉዳይ ትዝ የሚላቸው መሪዎች መገኘታቸው ለምስጋና የሚያነሳሳ በሆነ ነበር፡፡ ግን ለዚህ አልታደልንም፤ ዝቅ ብሎ የሚያከብር ሰው ማክበር አልለመድንም:: ፊት የሚነሳ እንጂ ፊት የሚሰጥ መሪ አይተን አናውቅም፡፡ የገረፉንን እንጂ ያቀፉንን ማድነቅ አልሆን ብሎናል፡፡ እንዲያውም ትናንት ፍርግርግ ውስጥ ያሰሩንን፣ እስከ መናፈቅ ደርሰናል፡፡
እኛ የምንወደው ለብቻቸው በልተው ሲጠግቡ አጥራቸውን ሰማይ አስነክተው፣ በኤሌክትሪክ ሽቦ የሚያጥሩ መሪዎችና ፖለቲከኞችን ነው፡፡ ከድሆች ይልቅ ክብራቸውና ሃብታቸው የሚያቃዣቸው ባለሥልጣናት:: የዚህ መልካም ስራ ተቃዋሚዎች፣ ከፊሉ ለውጡን አጋጣሚ አድርገው ሹመት የቋመጡ፣ አማካሪ እንሆናለን በሚል ቃዥተው ሳይሳካላቸው የቀሩ፣ በህዝብ ስም መንገስ የቋመጡ ናቸው፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ሽግግሩን ለየራሳቸው ብሄር ጥቅም ማስጠበቂያ፣ ግርግሩን ወሰን ማስፊያ ማድረግ፣ እንደተለመደው ሃብቱን ወደ አንድ ሰፈር የማግበስበስ ቅዠት ውስጥ መግባት የፈለጉ ነበሩ፡፡ ጠቅላዩ ግን ሁሉም እኩል የሚሆንባት፣ እኩል የሚጠቀምባትን ሃገር ካልፈጠርን ማንም ለብቻው አይነግስባትም ብለው በመፈጠማቸው ያልተመዘዘባቸው ጦር፣ ያልተዘመተባቸው ዘመቻ የለም፡፡ ድሃ ሕጻናት ለምን ይመገባሉ! እስከ ማለት፡፡ ይህ ግን ብዙዎችን አስኮረፈ፤ ለውጡን ቁልቁል ለመድፈቅ ሌት ተቀን ሰሩ፡፡ አሁንም እየሰሩ ነው:: ትናንት በህዝብ ደምና እንባ እየቀለዱ የኖሩ ዓይናውጣዎች የነገሯቸውን የጥላቻ መርዝ እየረጩ ነው፡፡ ተዋናዮቹም እነዚሁ በሃገርና በህዝብ ሲቀልዱ የነበሩ አረመኔዎች ናቸው፡፡
ይባስ ብለው ሕጻናት ለምን ዳቦ ይበላሉ!! የሚሉት እነዚሁ ትናንት ሕጻናትን በጥይት የደበደቡ ናቸው፡፡ ይህም አውሬነታቸውን የሚያሳይና የትናንት ማንነታቸውን የሚያጋልጥ ነው፡፡ የዚህ አይነት ለምን ሕጻናት ዳቦ በሉ ጫጫታ ከሌላም አቅጣጫ እየተሰማ እንደሆነ አስተውለናል፡፡ በቅርቡ አገልጋይ ዮናታን አክሊሉ ለልጆች ምገባ የሠጡት ገንዘብ አንዳንዶችን አንገብግቧል፡፡ ከሁሉ የሚገርመው ደግሞ ጫጫታው ስለ ወንጌል ያገባናል ከሚሉ ወገኖች አካባቢ መሆኑ ነው፡፡ ለመሆኑ ክርስቶስ ችግረኞችን አታግዙ ብሏል? ድሆችና ሕጻናት እየተራቡ ሃብት አከማቹ የሚል ቃል ወጥቶታል? ፈጽሞ!! ይልቁንም እኔ የገባኝ በርሱ ዓይነት ተመሳሳይ አገልግሎት ያሉና ሀብት ያከማቹ ሰዎች፤ ‹‹እነርሱስ ለምን አይሰጡም!›› በሚል እንዳይወቀሱና ካከማቹት ገንዘብ እንዳይነካባቸው በመስጋት ይመስላል፡፡ ሌሎች ደግሞ ሰውዬውን በግል መቃወም በመፈለግ ብቻ ነው፡፡ ይህም ደግሞ አንድ ሰው ሲሳካለት፣ ለምን ተሳካለት ብሎ እንደመነጫነጭ ነው፡፡
ይሁን እንጂ የዮናታን ተግባር የሚያስመሰግን እንጂ የሚያሰድብ አይደለም፡፡ ለራሳቸው ቅንጦት ሃብት እንደሚያከማቹት የባንክ አካውንቱን ሊያሳብጥ ሲገባ፣ የሃገሬ ጉዳይ ያገባኛል ማለቱ መልካም አርአያነት ያለው ተግባር ነው፡፡ የዶክተር ዐቢይ አህመድ አስተዳደር ለችግረኞች የሚራራ፣ አዛውንቶችን ለመርዳት ላይ ታች የሚል መሆኑ የማይዋጥላቸው ቢኖሩም፣ ለአዲስ አበባ ወላጆችና ልጆች የዋሉት ውለታ የማይረሳና በነገው ትውልድ ላይ ከፍተኛ አሻራ የሚያሳርፍ ነው፡፡ በምንም መለኪያ ለሃገር ልጆችና ለትውልድ መስራት ሊያስወቅስ አይገባም ባይ ነኝ፡፡ ይልቅስ በተመሳሳይ አገልግሎት ላይ ያሉ ወገኖች፣ በተመሳሳይ መንገድ፣ ልጆችና ሕጻናትን መርዳት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ምናልባትም ሌሎችም ቤተ-እምነቶች ተመሳሳይ ስራ መስራት ይገባቸዋል፡፡
እኛም በተለያዩ ስራዎች ላይ የተሰማራንና የሃገሪቱ ጉዳይ ያገባናል የምንል ሁሉ፣ የሕጻናቱን ጉዳይ አብረን ልንሰራና መንግስትንና በጎ አድራጊዎችን ልናግዝ ይገባናል፡፡ በተለይ በተለይ ሕጻናት ለምን በረሃብ አልሞቱም! በሚል የሚቃወሙትን ማውገዝና መቃወም  የግድ ነው፡፡ በሌላ በኩል፤ ይህንን መልካም ስራ የሚሰሩት የመንግስት አካላት የጀመሩትን በተሻለ ሁኔታ መቀጠል አለባቸው፡፡ በተለይም ለነርሱ የሚሆን አንድ ታሪክ ላካፍላችሁ እወዳለሁ፡፡
በአንድ ስፍራ የተራራ መውጣት ውድድር ፕሮግራም ይካሄድ ነበር፡፡ በውድድሩም በርካታ የዱር እንስሳት ተሳትፈዋል፡፡ ሆኖም በውድድሩ ብዙዎቹ አልተሳካላቸውም፡፡ በኋላ ግን ጦጢት አሸናፊ ሆነች፡፡ አንድ ጋዜጠኛ ጥያቄ ያቀርብላታል፡-
“እነዚያ ሁሉ ሳይሳካላቸው አንቺ እንዴት ተሳካልሽ?”
ይሄኔ ጦጣዋም መመለስ አልቻለችም፡፡ ጋዜጠኞች ግራ ተጋብተው ሲያስተውሉ፣ ጦጢት ጆሮዋን በጥጥ ደፍናለች፡፡ እናም ያንን ተራራ ለመውጣት የሞከሩ ሁሉ ያልተሳካላቸው፣ ከያቅጣጫው የሚጮኸውን ጩኸት እያዳመጡ ግራ በመጋባታቸው ነበር፡፡ ጦጢት ግን ድምጹን ላለመስማት ጆሮዋን በመድፈንዋ ድል ልትቀዳጅ ቻለች፡፡
ዛሬም መልካም ስራ በመስራት ላይ የሚገኙ የመንግስት ሃላፊዎች፣ ክፉ የማይጠቅሙ ወሬ ላለመስማት ጆሯቸውን መድፈን አለባቸው፡፡ ድል የሚገኘው እውነተኛ ሕልምን ለመከወን በመጣር እንጂ ክፉ ወሬና ጫጫታ በማዳመጥ አይደለም፡፡ ስለዚህ መልካሙ ተግባር ሁሌም ይቀጥል፡፡ ታከለ ዑማ በርታ! አገልጋይ ዮናታን ይልመድብህ! እኛም ማመስገን እንልመድ!!

Read 1205 times