Saturday, 08 February 2020 15:20

‹‹ገ/ሥላሴ ኢትዮጵያ››

Written by  ጌጡ ተመስገን
Rate this item
(1 Vote)


           36ኛው የበርሊን ማራቶንን ለመመልከት በዶክተር ስቴፋን ካፕለር ጋባዥነት በርሊን ከተማ ገብቻለሁ - ሴፕቴምበር 20 ቀን 2009 ዓ.ም.፡፡ ከአንድ ጀርመናዊ ጋር ከበርሊን ግንብ አቅራቢያ ቡና እየጠጣን ነበር፡፡
ጀርመናዊው ‹‹ኢትዮጵያን አላውቃትም!›› ሲለኝ በንዴት ጨስኩ፡፡
‹‹እንዴት አገሬን አያውቃትም?!›› አልኩና፣ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ የምትታወቅባቸውን ነገሮች ሁሉ ዘረዘርኩለት፡፡
እሱ እቴ! ድርቅ አለ፡፡
 አገሬን፤ ኢትዮጵያን አያውቃትም፡፡  
ይህ አውሮፓዊ ንዴቴን አፍለቀለቀው፡፡
 ‹‹ለምቦጭህን አትጣል!›› አለኝ፤ በጠራ አማርኛ፡፡
ደነገጥኩኝ፡፡ ከአንደበቱ አማርኛ ቋንቋ በመስማቴ፡፡
ኢትዮጵያን አላውቃትም  ያለኝ ፈረንጅ፤ በጀርመን ላይፕዚግ ዩኒቨርሲቲ የአማርኛ መምህር ነው፡፡     ‹‹ኢትዮጵያን የማውቃት በአትሌት ገ/ሥላሴ ነው›› አለኝ፤ ጀርመኑ በአማርኛ …
ይኼኔ ከንዴት ስሜት ወጣሁ፡፡ አትሌት ኃይሌ ገ/ሥላሴ፣ የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ መታወቂያ መሆኑ አስደሰተኝ፡፡ ፈረንጆቹ ኃይሌን ‹‹የማይዝገው ብረት›› /Stainless Steel/ ይሉታል፡፡ እነ ቢቢሲ ደግሞ “Unearthly, He is not from our planet.”  ‹‹እርሱ ከምድራችን የተገኘ አይደለም፤ ከሌላ ፕላኔት የመጣ ነው›› እያሉ የሚያሞካሹት አትሌት ነው፡፡
***
የበርሊን ማራቶን ተጀመረ፡፡ በበርሊን ጎዳና የጀርመን ባንዲራ የሚያውለበልቡ፤ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ቱታ የለበሱ የኃይሌ አድናቂዎች አያሌ ነበሩ፡፡
‹‹ገ/ሥላሴ ኢትዮጵያ!›› እያሉ ሲጮኹለትና ሲያብዱለት ተደነቅሁ፡፡
በበርሊን ማራቶን ላይ ሃምሳ ሺህ ተወዳዳሪዎች ተካፍለዋል፡፡ በዚህ ውድድር ኃይሌ ለሦስተኛ ጊዜ የበርሊን ማራቶንን አሸነፈ፡፡ በሴቶች ማራቶንም ያሸነፈችው ኢትዮጵያዊቷ አትሌት አፀደ በስዬ ነበረች፡፡
በማራቶን ከተቀዳጀነው አስደማሚ ድል ባልተናነሰ ትኩረቴን የሳበው አንድ ነገር ነበር፡፡ ይኸውም  ለበርሊን ማራቶን ሃምሳ ሺህ ተወዳዳሪዎች የተበረከተው ሜዳሊያ ፊትና ጀርባው የኃይሌ ገ/ሥላሴን ምስል የያዘ መሆኑ ነው፡፡ የሜዳሊያው  ማንጠልጠያ የጀርመን ባንዲራ ነበር፡፡
ከበርሊን ማራቶን በኋላ ጋዜጣዊ መግለጫ ለመከታተል ወደ ማሪዮት ሆቴል አመራሁ፡፡ የጀርመን ድምፅ አንጋፋው ጋዜጠኛ ይልማ ኃ/ሚካኤልን አገኘሁት:: ስለ አገር ቤት ጥቂት አወጋን፡፡ የሞስኮ ኦሎምፒክ ጀግናው (ማርሽ ቀያሪው) ምሩጽ ይፍጠር ወደ ሞስኮ ከመሄዱ በፊት ልምምድ ያደረገው ላይፕዚግ ከተማ ሴንትራል ስታዲየም እንደነበረ ጋዜጠኛው ነገረኝ፡፡
ኃይሌ ከሁለት ቀናት በኋላ ወደ ላይፕዚግ ከተማ አመራ፡፡ ጉዞው በሰባት ሞተር ብስክሌቶች ታጅቦ ነበር፡፡ አጀቡን በቅርብ ርቀት ተከተልነው፡፡ ላይፕዚግ ከተማ የከንቲባው መቀመጫ ሕንፃ ጋ ሲደርስ ከሦስት ሺህ እስከ አምስት ሺህ በሚገመቱ አድናቂዎቹ የተደረገለት ደማቅ አቀባበል እሱን ብቻ ሳይሆን መላ ኢትዮጵያውያንን የሚያኮራ ነበር፡፡ አጃኢብ ያሰኛል!!
ኃይሌ በላይፕዚግ ጎዳና ከአድናቂዎቹ ጋር የሦስት ኪሎ ሜትር የመታሰቢያ ሩጫ አድርጎ ዝግጅቱ ተጠናቀቀ፡፡
ከዚያም አትሌቱ ወደ ላይፕዚገር ታዋቂ የስፖርት ትጥቅ መሸጫ ሱቅ አመራ፡፡ አድናቂዎቹም ተከተሉት፡፡ ለአንድ ሰዓት ተኩል ያህል ተሰልፈው የጀግናውን የክብር ፊርማ በማኀደራቸው (በተለያዩ ቁሳቁሶች፤ በኩባያ፣ በባርኔጣ …ወዘተ ተቀበሉት:: ኃይሌ በጀርመን አገር ተወዳጅና ዝነኛ (Celebrity) አትሌት መሆኑን አረጋገጥኩ:: (በነገራችን ላይ ኃይሌ አራት ጊዜ የበርሊን ማራቶንን አሸንፏል፡፡)
አትሌቶቻችን የድል አክሊል የደፉባት አገር ናት - ጀርመን፡፡ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በአምስት ሺህና በአሥር ሺህ የዓለም ሻምፒዮና በመሆን አብረቅራቂ የድል አክሊል የደፋው በጀርመን ነው፡፡
በ110 አገራት የሚካሄዱ 410 የሩጫ መድረኮች በአባልነት የሚገኙበት ዓለም አቀፉ የማራቶንና የረዥም ርቀት ሩጫዎች ማኅበር፤ አትሌት ኃይሌ ገ/ሥላሴን በ2016 ‹‹የሕይወት ዘመን ተሸላሚ›› አድርጎታል፡፡
*    *    *
 አትሌት ኃይሌ ገ/ሥላሴን በአካል ሳገኘው እግሮቹን አይቼ አልጠግብም:: ምክንያቱም በፈጣን አእምሮው የሚታዘዙት እግሮቹን ሲምዘገዘጉ ማየት ያስደስተኛል፡፡ ሃያ ሰባት የዓለም ሪከርዶችን እንዲሰብር ያስቻሉት ቀጫጭን ግን ጠንካራ ምስማር እግሮቹ፣ ወርቃማ ታሪክ የከተበባቸው ብዕሮቹ ናቸው፡፡
በመንገድ ላይ ጉልበታችሁ ዝሎ፣ አዕምሯችሁ ደክሞ፣ ተስፋ ቆርጣችሁ፣ ኃይሌን ብታገኙት ጽናቱና አሸናፊነቱ ብርታት ይሆናችኋል፤ በተስፋ ይሞላችኋል፡፡ የዛለው አእምሮአችሁ አዲስ አቅምና ጉልበት ይጎናፀፋል፡፡ የራደው ጉልበታችሁ በአዲስ ጉልበትና ኃይል እየተቀጣጠለ ጉዟችሁን ትቀጥላላችሁ፡፡ አሸናፊነትን፤ ድል አድራጊነትን፤ ይቻላልን እያዜማችሁ፡፡
ደራሲ ስዩም ገ/ሕይወት ‹‹ሚክሎል - የመቻል ሚዛን›› በተሰኘው ልቦለድ መጽሐፉ፤ ‹‹የእውነቱ ‹ይቻላል› ከልብ ውስጥ ከተንጠለጠለ ረመጥ ላይ የተጣደ የእልክ ቁሌት ነው›› ይላል፡፡
አዎ… ይቻላል!
ምንጭ፡- (በቅርቡ ለህትመት ከሚበቃው የጋዜጠኛ ጌጡ ተመስገን መጽሐፍ የተወሰደ)


Read 1606 times