Saturday, 08 February 2020 15:27

“የነፃነት ፀሐፊዎች” - ለዩኒቨርሲቲዎቻችን ችግሮች

Written by  ተመስገን.ታ
Rate this item
(1 Vote)


           “--ነገር ግን ሁሉም መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች የግጭቶች ተሳታፊ ባለመሆናቸው፤ ዩኒቨርሲቲዎች ለቆሙለት የነፃነት፣ የወንድማማችነት፣ የእኩልነትና የሰብአዊነት መርሆች ተገዢ የሆኑ ምሁራን እንዳሉ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡--”
             ተመስገን.ታ

              “የነፃነት ፀሀፊዎች” (Freedom Writers) የድራማ ዘውግ ያለው፣ በ2007 እ.ኤ.ኣ በአሜሪካ ለእይታ የበቃ ፊልም ነው፡፡ ፊልሙ The Freedom Writers Diary by Erin Gruwell በሚል በ1999 እ.ኤ.አ በወጣ መጽሐፍ ላይ ተመስርቶ  የተሰራ ሲሆን ፤ በዚህ ፊልም ላይ የተነሱት ጭብጦች በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ዩኒቨርሲቲዎች ከሚታዩት ችግሮች ጋር ተመሳሳይነት ያላቸው በመሆኑ ብዙ ልንማርባቸው የምንችላቸው  ቁም ነገሮችን ያዘለ ነው፡፡
ፊልሙ የሚያጠነጥነው፣ በ1994 እ.ኤ.አ በሎስ አንጀለስ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ውስጥ በተቀጠረች አዲስ አስተማሪ ዙሪያ ነው፡፡ የፊልሙ መሪ ተዋናይ Erin Gruwell (Hilary Swank) ማስተማር በምትጀምርበት ት/ቤት፤ በባህሪያቸው አስቸጋሪ ከሚባሉ፣ በወንጀል ተሳትፈው እስር ቤት ገብተው የሚያውቁ፤ እንዲሁም በአደንዛዥ ዕፅና በማፊያ ቡድኖች ውስጥ የሚሳተፉ ተማሪዎች ጋር ትጋፈጣለች:: ከዚህም የሚከፋው ደግሞ በት/ቤት ግቢ ውስጥና በክፍል ውስጥ በዘር (በቆዳ ቀለም) እና በማፊያ ቡድኖች ላይ ተመስርተውና ድንበር አስምረው፣ በጎሪጥ የሚተያዩ መሆናቸው ነው፡፡  
መምህርት ኤሪን በመጀመሪያ ቀን የክፍል ቆይታዋ፣ ከተማሪዎቿ ጋር ትውውቅ ለማድረግ ስትሞክር፣ ነጭ ስለሆነች ብቻ ተማሪዎቿ እንደሚጠሏትና እንደማያምኗት ይነግሯቷል፡፡ በትምህርት ክፍለ ጊዜም ቢሆን  ሊያዳምጣትም ሆነ ከእሷ ለመማር ፈቃደኛ የሆነ ተማሪ አልነበረም፡፡  በዚህ ምክንያት ለቀናት በክፍሏ ውስጥ ምንም ነገር ሳትሰራ ለመዋል ትገደዳለች:: በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለች በአንደኛው ቀን፣ አንድ ተማሪ በጣም አስጠሊታ የሆነ የካርቶን ስዕል በክፍል ውስጥ በሚገኝ ጥቁር አሜሪካዊ ፊት አስመስሎ በመሳል፣ በክፍል ውስጥ እንዲዞርና እንዲሳቅበት ያደርጋል፡፡ ይህንን ምስል ያየችው መምህርቷም፣ እንደዚህ አይነት ስዕሎች ናዚ ጀርመኖች፣ አይሁዶችን ለማስጠላትና ከሰው የሚያንሱ ለመሆናቸው እንደ ማሳያ ከተጠቀሙበት ምስሎች ጋር እንደሚመሳሰልና  ምን ያህል አሰቃቂ ሰብዐዊ ፍጅት እንዳስከተለ በምትነግራቸው ወቅት በአስገራሚ ሁኔታ የተረዳችው ነገር፣ በክፍል ውስጥ በአይሁዶች ላይ የደረሰውን የዘር ማጥፋት ፍጅት የሚያውቅ አንድም ተማሪ አለመኖሩን  ነው፡፡
መምህርቷ በመጀመሪያ ያደረገችው፣ ለሁሉም ተማሪዎች ማስታወሻ ደብተር በመስጠት፣ ከዚህ በፊት ያጋጠሟቸውና ከአእምሮአቸው ሊጠፉ ያልቻሉ ሁነቶችን፣ በየቀኑ የሚያጋጥማቸውንና የሚሰማቸውን  እንዲፅፉ ማበረታታት ሲሆን  እነሱ ካልፈቀዱላት በስተቀር ማስታወሻቸውን እንደማታነብ በመጠቆምም፣ ሃሳቦቻቸውንና ስሜቶቻቸውን በነጻነት እንዲገልፁ አነሳሳቻቸው፡፡  አብዛኛዎቹ ተማሪዎች ማስታወሻቸውን እንድታነብ በመፍቀዳቸውም፣ የተማሪዎችን የልጅነት ወቅት፣ የአስተዳደግ ሁኔታ እንዲሁም ለጥላቻና ግጭት የሚያነሳሷቸውን ስሜቶች ለይታ ለመረዳት ቻለች፡፡  
በመቀጠልም  በጎዳና ላይ ስላደገ ህፃን የሚተርክና “የአና ማስታወሻ” የተሰኙ መጽሐፍትን እንዲያነቡና በሎስ አንጀለስ የሚገኘውን ‹‹የአይሁዶች የእልቂት ሙዚየም›› እንዲጎበኙ አድርጋለች፡፡ ከዚህም በተጨማሪ፣ ከእልቂቱ ከተረፉ ሰዎች ጋር እራት አብሮ በመብላት ከጥላቻ፣ ካለመቻቻልና ከአመጽ የተፈጠረውን አሳዛኝ ክስተትና እነሱ ያሳለፉትን መከራና ስቃይ ሊያጋሯቸው ችለዋል፡፡ የመምህርቷ ጥረት በዚህ ሳያበቃ፣ አና ፍራንክና ቤተሰቦቿን መደበቂያ ስፍራ በመስጠት የረዷትን የደች ተወላጅ የሆኑትን ‹‹Miep Gies›› ከተማሪዎቹ ጋር እንዲገናኙ በማድረግ፣ በጊዜው ስለነበረው ሁኔታ እንዲወያዩ አድርጋለች:: እዚህ ጋ ልብ የሚነካው ትዕይንት ደግሞ ከተማሪዎቹ መሀከል አንዱ በመነሳት፣ የእርሱ ጀግና እንደሆኑ ሲነግራቸው፣ ያንን ያደረጉት ጀግና በመሆናቸው ሳይሆን  ትክክለኛው ነገር ስለሆነ ብቻ መሆኑን የገለጹበት  መንገድ ነው፡፡
መምህርቷ  እኒህ ተማሪዎች እንዲለወጡ ብዙ መስዋዕትነትን ከፍላለች፡፡ ከወግ አጥባቂዋ የት/ቤቱ ርዕሰ መምህር ጋር እልህ አስጨራሽ ክርክርና ተቃውሞ ገጥሟቷል፤ ተባባሪና አጋዥ መምህርም አጥታለች፡፡ ለተማሪዎች የመጽሐፍትና የጉብኝት ወጪዎችን ለመሸፈን ተጨማሪ ስራዎችን ለመስራት ተገዳለች፡፡ ባለቤቷ የምትሰራውን ስራ በመቃወሙ ትዳሯን አፍርሳለች፡፡ ለዚህ ሁሉ ልፋቷና መስዋዕትነቷ ያገኘችው ክፍያ ደግሞ የተማሪዎቿ የአመለካከት ለውጥና  ፍቅር ነው፡፡
ይህ ታሪክ አስደናቂ፣ መንፈስ አነቃቂና ለለውጥ መንገድ ከፋች ነው፡፡ ታሪኩ ስለ አንድ አስደናቂ አስተማሪና ለለውጥ ስለከፈለችው መስዋዕትነት ብቻ ሳይሆን፤ አንድነት ከልዩነት ውስጥ ሊመጣ እንደሚችልና ግለሰቦች ብቻ በመካከላቸው የተገነባውን የጥላቻ ግንብ በምክንያታዊነትና በእውቀት ማፍረስ እንደሚችሉ ማሳየትም ነው፡፡ ልዩነትን በማክበርና በመረዳት፣ ውበትም አንድነትም መሆን እንደሚችል ያስረዳናል፡፡ ለውጥ በማንኛውም እድሜና ጊዜ ላይ ሊመጣ እንደሚችል ይህ ፊልም ማሳያ ነው፡፡
ተማሪዎች በማንኛውም ወቅት ዕድሉ ከተመቻቸላቸው፣ ለለውጥ ዝግጁ በመሆናቸው፣ ከመምህራኖቻቸው የሚጠበቀው የለውጡን መንገድ በቀናነት ማሳየት ብቻ ነው፡፡ የእኛ ሀገር ዩኒቨርሲቲዎች በአብዛኛው የግጭት መነሻ በመሆን ላይ ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን በግጭት መነሻነት ከሚጠቀሱት ፖለቲከኞች ይልቅ በግቢ ውስጥ የሚገኙ መምህራን፣ በቅርበት ተማሪዎቻቸውን  ሊያውቋቸው፣ሊያስተባብሯቸውና ሊለውጧቸው እንደሚችሉ እገምታለሁ::
በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ከአደረጃጀትና መዋቅራዊ ችግሮች በተጨማሪ ሌሎች ተግዳሮቶችም አሉ፡፡
የመጀመሪያው፣ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ጎጥን መሰረት ባደረጉ የዘውጌ ድርጅቶች ውስጥ በመሪነትና በአባልነት መገኘታቸው ነው:: እንደነዚህ አይነት የዩኒቨርሲቲ መምህራን  ሁሉንም ተማሪዎቻቸውን በእኩል ዐይን መመልከታቸውን እጠራጠራለሁ፡፡
ሁለተኛው፤ በአብዛኛው ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በተነሱት ግጭቶች፣ የመምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች ተሳታፊ መሆናቸው፣ ተማሪዎች በልዩነት አጥር ስር ቆመው ለመቅረታቸው ጉልህ አስተዋጽኦ ማድረጉ  ነው፡፡ ነገር ግን ሁሉም መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች የግጭቶች ተሳታፊ ባለመሆናቸው፤ ዩኒቨርሲቲዎች ለቆሙለት የነፃነት፣ የወንድማማችነት፣ የእኩልነትና የሰብአዊነት መርሆች ተገዢ የሆኑ ምሁራን እንዳሉ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡ ለውጥ በግለሰቦች ጥረት የሚመጣ እንደመሆኑ፣ እነዚህ ምሁራን ፣ እንደ መምህርት Erin Gruwell የተማሪዎቻቸውን የአስተዳደግ ሁኔታና ስሜቶቻቸውን በመረዳት፣ የአስተሳሰብ፣ የእውቀትና የምክንያታዊነት ባህል ለማምጣት በትጋት ቢሰሩ፣ ችግሮችን ከስሩ ለማድረቅ እንደሚችሉ እገምታለሁ፡፡  

Read 677 times