Saturday, 08 February 2020 15:17

ክቡር ሚኒስትር፤ እኛም ጥያቄ አለን

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(3 votes)

  “አሁን በሥልጣን ላይ ያለው የሀበሻ መንግሥት ከምን ጊዜውም የተሻለ ነው:: ዘሩ ከምኒልክና ከኃይለሥላሴ ስላልሆነ ለእኛ ለአረቦች በጣም ቅርብ ነው፡፡ ሆኖም ግን መሠረቱ በቁጥር አናሳ ከሆነው ከትግራይ ብሔረሰብ የመጣ ስለሆነ በሥልጣን ለመቆየት እድሉ አስተማማኝ አይደለም፡፡ እኛም እድሜው አጭር ይሆናል የሚል ግምት ስለአለን፤ ሰፊ መሠረት ያለውን የኦሮሞ ብሔር ተቃዋሚ ኃይል ጠንክሮ እንዲወጣ ድጋፍ እናደርጋለን፡፡ ኦሮሞዎች ከትግሬዎች እጅግ ሰፊ የሕዝብ ብዛትና ፀረ ምኒልክ አመለካከት ስላላቸው ልንደግፍቸው ግድ ይለናል፡፡ አንድ ጊዜ ሥልጣኑን እንዲይዙ ከረዳናቸው የረጅም ጊዜ ወዳጆቻችን ይሆናሉ፡፡” -
ኡመር ሙሳ
(የግብፁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፤
(እ.ኤ.አ 2003)
እርስዎ የአሜሪካውን ፕሬዚዳንት የዶናልድ ትራምፕን ጉትጐታና ማግባባት ተቋቁመው፣ ስምምነት እየተደረሰባቸው ያሉ ጉዳዮች ከመጽደቃቸውና ከመፈራረማቸው በፊት የማሰቢያ ጊዜ መጠየቅዎ፣ ለእኛም በዜግነታችንና በጉዳዩም ባለን ባለቤትነት የማሰቢያ ጊዜ አስገኝተውልናል፤ አጥብቄ አመሰግናለሁ፡፡
ከ1930-1934 (እ.ኤ.አ) ባለው ጊዜ በአስራ አምስት ሚሊዮን ዶላር ጣና ላይ ኢትዮጵያ ግድብ ለመሥራት አስባ በእንግሊዞች ሴራ ሳይሳካ መቅረቱን እናስታውሳለን፡፡ ከ1956 -1964 እ.ኤ.አ በአባይ ሸለቆ ላይ አሜሪካኖች ባካሄዱት ጥናት መሠረት፣ ሊሠሩ ከታሰቡት 32 ፕሮጀክቶች ውስጥ ተግባራዊ የሆነው አንድ የፊንጫ ግድብና የስኳር ልማት መሆኑ የሚረሳ አይደለም፡፡ ፕሮጀክቶቹ ዳዋ በልቷቸው የቀረው ኢትዮጵያዊያን አገራቸውን የማልማት ፍላጐት ሳይኖራቸው ቀርቶ ሳይሆን፣ ግብፆችና ወዳጆቻቸው ከጀርባ ሆነው ሲደግፉት በኖሩት የእርስ  ጦርነት እንዲሁም በሶማሌ ወረራ አገራችን በመጠመዷ መሆኑ የሚዘነጋ አይደለም፡፡ ሌላው የማይዘነጋው የግብፆች ሥራ፣ ኢትዮጵያ ብድር እንዳገኝ ያለ መታከት ያደረጉት ጥረት ነው፡፡
ኢትዮጵያና ግብጽ እ.ኤ.አ በ1993 ካይሮ ላይ የፈረሙትን የመግባቢያ ሰነድ እዚህ ላይ ማስታወስ ይገባል፡፡ አቶ መለስና ፕሬዚዳንት ሙባረክ በፈረሙት በዚህ ሰነድ ሁለት መሠረታዊ ጉዳዮች ቦታና ዋጋ አግኝተዋል፡፡ አንደኛው፤ አንዱ አገር በሌላው አገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ላለመግባት መስማማታቸው  ሲሆን፤ ሁለተኛው በናይል ተፋሰስ አገሮች መካከል በውሃ ሃብት የወል ተጠቃሚነት ማስፋፋትን ግብፆች መቀበላቸው ነው፡፡     
ውሉ ግብፆችን ያላገዳቸው መሆኑንና በውስጥ ጉዳያችን ጣልቃ ስለመግባታቸው መግቢያዬ ላይ ካቀረቡት  የኡመር ሙሳ ንግግር በላይ ማስረጃ ማቅረብ የሚያስፈልግ አይመስለኝም፡፡ ዛሬም ቢሆን በሀገር ውስጥ ባለው የሰላም መደፍረስ  የግብፆች እጅ የለም ብዬ ለማሰብ ይቸግረኛል፡፡ ግብፆች፤ አሜሪካንንና የአለም ባንክን ወደ ጉዳዩ ጐትተው ያስገቡት፣ ድርድሩ በጀት ፍጥነት ወደአንድ መደምደሚያ ይደርስ ዘንድ በእጅጉ የሚያጣድፉት፣ በእነሱ እምነትና አስተሳሰብ “ዛሬ በኢትዮጵያ የመንግሥት ሥልጣን ላይ ያሉት ኦሮሞዎች ናቸው፡፡ ኦሮሞዎች ፀረ ምኒልክና ለኢትዮጵያ ጥቅም የማይቆረቀሩ ናቸው፡፡ አገሪቱም በውስጥ አለመረጋጋት ተጠምዳለች፡፡ ግብጽ ጥቅሟን ለማስጠበቅ ከዚህ የተሻለ ጊዜ የላትም” ብለው እንደሆነ ለመገመት ነብይ መሆን አይጠይቅም፡፡
አሜሪካ የግብጽ የነፍስ አባት ናት፡፡ በስዊዝ ካናል ላይ ያላትን ተጠቃሚነት ለማስጠበቅ በየዓመቱ በብዙ ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ወታደራዊ እርዳታ ለግብጽ ትሰጣለች:: አሜሪካ የእስራኤልን ጥቅም ለማስጠበቅ በተንቀሳቀሰች ቁጥር የአረቡን አለም ቁጣ ማብረጃ ወይም የስሜት ሙቀት መለኪያ አድርጋ የምትጠቀመው ግብጽን ነው፡፡ ግብጽ ለአሜሪካ የቤተ ሙከራ አይጥ ናት፡፡ በአንፃሩ ኢትዮጵያ እንደ ግብጽ ልትሆንላት አትችልም፡፡
ስለዚህም አሜሪካ ለራሷ ስትል የኢትዮጵያን ጥቅም መርገጥ የሚጨንቃት ጉዳይ እንዳልሆነ ሊሠመርበት ይገባል፡፡ አሜሪካ እየተዘጋጀች ያለችው ኢትዮጵያን የጦስ ዶሮ ለማድረግ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ራሷን በራሷ ማዳን አለባት፡፡     
ከአስር ዓመት በላይ የወሰደው የናይል ትብብር ማዕቀፍ በተፈረመ ጊዜ፣ ፈራሚ አገሮችን በማውገዝ መግለጫ ያወጣችው አሜሪካ ናት፡፡ በግልፅ የጠየቀችው ደግሞ የናይል ተፋሰስ አባል አገራት እ.ኤ.አ በ1929 እና በ1959 በሱዳንና በግብጽ መካከል የተደረገውን የውኃ ስምምነት እንዲቀበሉ ነው፡፡ ይሄ ማለት ደግሞ የቅኝ ግዛት ውሎችን ማስቀጠል ማለት ነው፡፡ ይህን ኢትዮጵያ እንደማትቀበል የታወቀ ነው፡፡ (አሜሪካን በዳኝነት መቀበል ማለት፣ የመታረጃ ቢላዋን አሳልፎ ለአራጅ ከመስጠት በምን ይለያል?ዓ
ግብፆች  ውሃ ሲሉ ከባሮ ከአኮቦ ከጊሎ ወዘተ ወንዞች የሚያገኙት ውሃ ከኢትዮጵያ የሚፈልቅ መሆኑ በደረቅ አማርኛ ሊነገራቸው ይገባል:: ስለ ድርቅም ቢሆን፣ የድርቅ ውሃ መታየትና መወሰን ያለበት በኢትዮጵያ መሬት ለዚያውም በአባይ ተፋሰስ ውስጥ እንጂ ሱዳን ወይም ግብጽ ውስጥ መሆን የለበትም፡፡ ግብፆች ከፍ ያለ የውሃ መጠን ለማግኘት ከልብ የሚፈልጉ ከሆነ፣ ይህን በኢትዮጵያ ኪሣራ እንደማያገኙ ረገጥ አድርጐ መንገር የግድ ነው፡፡
መንግሥት ለግብፆች ይህን መንገር አለበት “ብዙ ውሃ ትፈልጋላችሁ?፤ እንግዲያውስ ኢትዮጵያ እያደረገች ያለውን የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም አስርና አስራ አምስት ቢሊዮን ዶላር ገንዘብ በመመደብ አግዙ” በማለት፡፡
አንድ ነገር እናስታውስ፡- አሜሪካ፤ ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብን መገንባት ስትጀምር፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቢሮዋ ውስጥ የግድቡን ሥራ የሚከታተል ሰው የመደበች አገር ናት፡፡
በማን ችሎት ማን ይዳኛል? እንዴትስ ፍትህ ይጠበቃል? ጥያቄያችን ነው፤ ክቡር ሚኒስትር፡፡  
ከአዘጋጁ፡- በፅሁፉ የተንፀባረቀው አቋም ፀሐፊውን ብቻ የሚወክል መሆኑን ለመግለፅ እንወዳለን


Read 11809 times