Saturday, 08 February 2020 15:14

‹‹ኮረና›› ቫይረስ እና ገናሌ የኤሌክትሪክ ግድብ (ከቻይና)፤

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)

   ከሦስት ሳምንት በፊት፣ በቻይና የ‹‹ኮረና›› ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር፣ ገና 300 አልሞላም ነበር፡፡ ትናንት አርብ የቫይረሱ ስርጭት ከ30ሺ በላይ ሆኗል፡፡ ወደ 30 አገራት ገደማ ተዛምቷል፡፡ ያስፈራል፡፡ በእርግጥ እስካሁን ድረስ፣ የአፍሪካ አገራትን አልነካም ማለት ይቻላል - ከአንድ ሁለት ደሴቶች በስተቀር፡፡
ከቻይናም ሆነ ከሌላው አለም ጋር፣ ያን ያህልም የኢኮኖሚ እና የጉዞ ግንኙነት የሌላቸው የአፍሪካ ድሃ አገራት፣ የኮረና ቫይረስ ገና አልደረሰባቸውም፡፡
ተስፋ ሰጪ ወይም አስደሳች ‹‹ዜና›› ይመስላል፡፡ ነገር ግን፣ የአፍሪካ አገራት፣ በደካማ ኢኮኖሚ አማካኝነት፣ ከኮረና ቫይረስ ያመልጣሉ ማለት አይደለም፡፡ የድህነት ኑሮ፣ አስተማማኝ የኑሮ ደህንነትን አያስገኝም፡፡
ጠንካራ ኢኮኖሚና የበለፀገ ኑሮ ባላቸው አገራት ውስጥ፣ በንግድ እና በጉዞ ብዛት ሳቢያ፣ ለኮረና ቫይረስ የሚያጋልጥ መንገድ መስፋፋቱ፣ ስርጭቱን የሚያባብስ አጋጣሚ መብዛቱ አያከራክርም፡፡ ነገር ግን፣ የዚያኑ ያህል፣ ቫይረሱን የመከላከልና በሽታውን የማከም አቅማቸውም በጣም ከፍተኛ ነው::
የአሜሪካና የእንግሊዝ የጤና ባለሙያዎችና ሳይንቲስቶችን የተመለከቱ:: ህክምና በመስጠት ህመምተኞችን የማዳንና መከላከያ ክትባት ለመፍጠርም በጥልቀት የመመራመር ብቃታቸው ወደር የለውም:: በቻይናም፣ ሁለት ሆስፒታሎች በሁለት ሳምንት ተገንብተው ስራ ሲጀምሩ አይተናል፡፡ የኢኮኖሚ እድገት ጠቀማት፡፡
ድሃ አገራት ግን፣ ይሄ ሁሉ አቅም የላቸውም፡፡ የበለፀጉ አገራት፣ እንዲህ አይነቱን ቫይረስ መቆጣጠርና ስርጭቱን መግታት ካልቻሉ፣ የጊዜ ጉዳይ እንጂ፣ ወደ አፍሪካ አገራትም መዛመቱ አይቀርም፡፡ ያኔ፣ በሌሎች አገራት ውስጥ ያልታየ፣ እጅግ የከፋ ጥፋት በአፍሪካውያን ዘንድ ይደርሳል:: በኤችአይቪ ሳቢያ አፍሪካ ላይ የደረሰው አሳዛኝ ጥፋትና ሰቆቃ፣ አንድ ምሳሌ ነው፡፡
‹‹የድህነት ኑሮ፣ መቼም ቢሆን፣ የኑሮ ደህንነትን አያስገኝም›› የሚባለው፣ ዞሮ ዞሮ፣ ውሎ አድሮ፣ ለአለማቀፍ የበሽታ ስርጭት መጋለጡ ስለማይቀርለትና በአቅመ ቢስነት ለከፋ እልቂት ስለሚዳረግ ብቻ አይደለም፡፡
ስር የሰደደና የማይሻሻል የኑሮ ድህነት፣… የክፋቱ ክፋት፣ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ፣ የጤና ብቻ ሳይሆን የህልውናም ጠንቅ ነው፡፡ ከአገር ውስጥና ከውጭ አሰፍስፈው የሚጠብቁ፣ የክፋትና የጥፋት አራጋቢዎችንና የሰላም ጠንቅ ነውጠኞችን ይጋብዛል - ‹‹ተስፋ አስቆራጭ ድህነት››፡፡
በሌላ አነጋገር፣ የኢኮኖሚ እድገት፣ የእለት ጉርስን የማምረት፣ ከረሃብና ከተመጽዋችነት እየተገላገሉ፣ ቀስ በቀስ ኑሮን የማሻሻልና የማደላደል ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡  ፋይዳው ብዙ ነው፡፡ በሁሉም የሕይወት መስክ፣ ተጨማሪ አቅም ይሆንልናል - የኢኮኖሚ እድገት፡፡ ታዲያ ‹‹ካወቅንበት›› ብቻ ነው፡፡
ከኢኮኖሚ እድገት ጎን ለጎን፣ በእውቀትና በስነ ምግባርም የምንመነደግ፣ በሙያና በሰብዕና ብቃትም የምንታነጽ፣ በነፃነትና በሕግ የበላይነት አክባሪነትም የምንሻሻል፣ ከሆነ፤ እያንዳንዱ ነገር ለሌሎቹ ተጨማሪ አቅምና ፀጋ ይሆንልናል፡፡
ኢኮኖሚ ሲያድግና ኑሮ ሲሻሻል፤ ልጆቻቸውን በጥራት የማስተማር የወላጆች አቅም ይጨምራል፡፡ የምርምር ግኝቶችን ወደ ቴክኖሎጂ ፈጠራ የማሸጋገር፣ በላቀ ጥራት በአነስተኛ ዋጋ የተትረፈረፈ ምርት የመፈብረክ፣ ማለትም የኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንትና የሥራ ዕድልን የማስፋፋት አቅም ያስገኛል - የኢኮኖሚ እድገት፡፡
ይህም ብቻ አይደለም። የኢኮኖሚ እድገት፣ ስነ ምግባርንና መንፈሳዊ ፋይዳም አለው፡፡ ልጆች፣ እውነትን ከመካድና ሰውን በሃሰት ከመወንጀል እንዲታቀቡ ብቻ ሳይሆን፣ ለእውነት የመታመንና እውቀትን የመውደድ ስነ ምግባርን በጥልቀት እንዲገነዘቡ የማስተማር አቅም ይሰጠናል - የኢኮኖሚ እድገት፡፡ የማይሸፍጥና የማይዘርፍ፣ የሌሎች ሰዎችን ንብረት ለመውሰድ ጨርሶ የማይመኝ ብቻ ሳይሆን፣ ኑሮን ለማሻሻልና የሩቅ አላማውን ለማሳካት እለት በእለት በንቁ አእምሮ እያገናዘበ፣ በሙያ እየተካነ፣ ለስራ መትጋትን ከምር እንድናፈቀር አንፈልግም? የምንፈልግ ከሆነ፣ የስኬት ስነ ምግባርን ይበልጥ ለማስተማር ይጠቅማል - የኢኮኖሚ ስኬት፡፡
ሌሎች ሰዎችን የማይመቀኝ፣ የማያጠቃና ህይወትን የማያጠፋ ብቻ ሳይሆን፣ ‹‹የእያንዳንዱ ሰው፣ ምትክ የለሽ፣ እጅግ ውድ ሕይወት፣ ጥቃት ሊቃጣበት እንደማይገባ›› በጽኑ የሚገነዘብ፣ ለሕይወት ዋጋ የሚሰጥ ባህል ለማዳበርም፣ የኢኮኖሚ እድገት ጥሩ ነው፡፡
ጥቃት የሚፈጽም ማንኛውም ሰው፣ በዘፈቀደ ሳይሆን፣ የሰውን ነፃነት በሚያስከብርና ወንጀልን በሚከላከል ሕግ፣ በአስተማማኝና በተጣራ ሕጋዊ ስርዓት እየተዳኘ፣ የጥፋቱ ያህል ፍትህ ተፈጻሚ እንዲሆንስ እንፈልጋለን? እንግዲያውስ፣ ሕግ አክባሪና ፍትህ አፍቃሪ ስብዕናን ለመገንባት፣ ተቋማትን ለማጠናከር የሚያገለግል ተጨማሪ አቅም ከኢኮኖሚ ዕድገት ማግኘት ይቻላል፡፡
ከምቀኝነትና ከክፋት መታቀብን ብቻ ሳይሆን፣ ሰዎችን እንደየ ብቃታቸው የማድነቅ፣ በሁሉም የሙያ መስክ የላቀ ብቃትንና ጀግንነትን ሲመለከት ከልብ የማወደስ የቅንነትና የፍትህ መንፈስን ለማለምለም የምንፈልግና የምንጥር እስከሆነ ድረስ፣ የኢኮኖሚ እድገት መንገዳችንን ለማቃናት ጉዟችንን ለማፍጠን ይረዳናል፡፡  
የኢኮኖሚ እድገት ሲኖር፣ ስነ ምግባርን ለማስተማር፣ የላቀ የግል ብቃታቸውን በተግባር ያስመሰከሩ ሰዎችን ለመሸለም፤ አንቸገርም፡፡ የአእምሮ ብሩህነትን፣ የስነ ምግባር ጥንካሬንና የላቀ ብቃትን በእውን የሚያሳዩ ምርጥ የኪነጥበብ ስራዎችን የማዘጋጀትና በስፋት የማሰራጨት አቅምንም ያበረክትልናል - የኢኮኖሚ እድገት፡፡ በሌላ አነጋገር፣ የመንፈስ ምግብን ለማስፋፋት ይጠቅማል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፡፡
ወረራን ለማስቀረት፣ ለመግታትና ለማሸነፍ፣… ወንጀልን ለመከላከል፣ በአስተማማኝና በተጣራ አሰራር ለዳኝነት አቅርቦ ፍትህን ለማስፈጸም ያግዛል - ከኢኮኖሚ እድገት፡፡ ነፃነትን ለመጠበቅና መብትን ለማክበር፣ ሰላምን ለማስፈንና የሕግ የበላይነትን ለማጠናከር፣ በአጠቃላይ የአገር ሕልውናን በሕግና ስርዓት ላይ ለማጽናት ያገለግላል - የኢኮኖሚ እድገት፡፡
በአጭሩ፣ እውነትና እውቀት፣ ስራና ሙያ፣ ኑሮና ሕልውና፣ ስነ ምግባርና ሰብዕና፣ ነፃነትና የሕግ የበላይነት፣ ፍቅርና ፍትህ… እነዚህን የመሳሰሉ መልካም ነገሮች ሁሉ፣ እርስ በርስ በቅጡ ሲሰናሰሉ፣ እጥፍ ድርብ ዋጋና ክብር ያስገኛሉ፡፡
በቁንጽል ሲነጣጠሉ ግን፣ አንዱ ነገር ሌላኛውን ያዳክማል፣ ያሰናክላል፣ ያጠፋል:: … ከነዳጅ ወይም ከእርዳታ ጋር ተያይዞ በአንዳች አጋጣሚ የሚፈጠር የኢኮኖሚ እድገት፣ ስንት መዘዝ እንደሚያስከትል፣ በበርካታ አገራት በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡
ለኢኮኖሚ እድገት በሚመጥን መንገድ፣ ጎን ለጎን ትንሽ በትንሽ፣ በአእምሮና በእውቀት ሳናድግ፣ በሙያና በስራ ሳንመነደግ፣ በስነ ምግባርና በሰብዕና ሳንታነጽ፣ በቁንፅል ኢኮኖሚው ቢያድግ ወይም ገንዘብ ቢገኝ፣ የጥፋት መሳሪያ ለመግዛት፣ የክፋት ተግባር ለመፈጸም ይውላል፡፡
ሌላ ሌላውን እንተወውና፣ በሞባይል ስልክ የመጠቀም እድል ሲፈጠር፤ የሃሰት ውንጀላንና ጥላቻን፣ የእልቂት ቅስቀሳንና ዘመቻን ለማራባት የሚያገለግል ተጨማሪ የጥፋት አቅም ይሆናል፡፡
እውቀትን፣ ምርታማነትንና ሥነ ምግባርን በቁንፅል ሳይሆን፤ አሰናስለን እያዋደድን የምናድግ ከሆነስ? ያኔ፣ የኢኮኖሚ እድገት፣ ለሁሉም ነገር… ለጤናም፣ ለሰላምም፣ ለኑሮም፣ ለአገርም የሚበጅ ይሆናል:: ለዚህም ነው፣ ከቻይና በተቀሰቀሰው የኮረና ቫይረስ ስንሰጋና ስንጠነቀቅ፣ ከዚሁ ጎን ለጎን፣ በቻይና ብድር ተገንብቶ ከሰሞኑ የተመረቀውን የገናሌ ዳዋ የኤሌክትሪክ ግድብንም ማሰላሰል የሚገባን፡፡
በ450 ሚሊዮን ዶላር (አሁን ባለው ምንዛሬ በ14.4 ቢሊዮን ብር) የተገነባው ግድብ፣ በዓመት 1670 ጊጋ ዋት አወር የኤሌክትሪክ ሀይል ያመነጫል፡፡
እንደ ሌሎቹ የኤሌክትሪክ ግድቦች፣ ይሄኛውም፣ በአነስተኛ ወጪ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ሀይል ለማመንጨት የሚችል ፕሮጀክት ነው፡፡ ከፈለጋችሁ፣ ከነፋስ ተርባይኖች ጋር ልታነፃጽሩት ትችላላችሁ፡፡
770 ሚሊዮን ዶላር የፈጁ የነፋስ ተርባይኖች፣ በዓመት 700 ጊጋ ዋት አወር የኤሌክትሪክ ሀይል ያመነጫሉ፡፡
450 ሚሊዮን ዶላር የወጣበት የኤሌክትሪክ ግድብ ግን፣ ወደ 1700 ጊጋ ዋት አወር የሚጠጋ የኤሌክትሪክ ሀይል በየአመቱ ያመነጫል፡፡ (700 ጊጋ ሀዋት አወር ከ200 ሚሊዮን ዶላር ባነሰ ሂሳብ ማለት ነው)፡፡
በዚህ አይን ካየነው፣ ለነፋስ ተርባይኖች ከፈሰሰው 770 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ፣ 570 ሚሊዮን ዶላር ያህሉ፣ ከንቱ ብክነት ነው ማለት ይቻላል፡፡ (አሁን ባለው ምንዛሬ፣ ወደ 17 ቢሊዮን ብር ገደማ የድሃ አገር ሃብት፣ በብላሽ ባክኗል)፡፡ የድሃ አገር ሀብትን ለብክነት የሚዳርጉ፣ ተጨማሪ የነፋስ ተርባይን፣ የፀሐይና  የእንፋሎት ሀይል ፕሮጀክቶች በግንባታ ላይ መሆናቸው ደግሞ፣ ጉዳቱን ያባብሳል፡፡
በአንድ በኩል፣ በአነስተኛ ወጪ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ሀይል የሚያመነጩ ግድቦች፣ ለመኖሪያ ቤቶች ብርሃን ናቸው፡፡ ከዚያ በላይ ደግሞ፣ ለፋብሪካዎች ዋነኛ የመንቀሳቀሻ ሀይል በማቅረብ፣ የኢኮኖሚ እድገትና የስራ እድል እንዲስፋፋ፣ ከዚህም ጋር ለጤናም ይሁን ለሰላም፣ ለአገር ህልውናም ሆነ ለሕግ የበላይነት ጠቃሚ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ፡፡
በሌላ በኩል፣ ሀብት በከንቱ ሲባክን ደግሞ፣ አዳዲስ ፋብሪካዎች ሊከፈቱ ይቅርና፣ ነባሮቹም በኤሌክትሪክ እጦት ይቸገራሉ፡፡ አገር ላይ የውጭ እዳ ይቆለላል፡፡ በዓመት ውስጥ 500 ሚሊዮን ዶላር ለብድር ወለድ ብቻ መገፍገፍ ምን ማለት እንደሆነ አስቡት፡፡ የሃብት ብክነት፣ ለተጨማሪ የሃብት ብክነት ይዳርጋል፡፡ ስራ አጥነትን ያስፋፋል፡፡ ጤናንና ሰላምን ያሳጣል፡፡ ሕግና ስርዓትን ያዳክማል፡፡ ከውስጥም ከውጭም፣ የአገር ሕልውናን ለትርምስ፣ የሚሊዮኖችን ሕይወት ለእልቂት ያጋልጣል፡፡    


Read 2819 times