Print this page
Saturday, 08 February 2020 14:54

ለሁለት ወጣቶች ሞት ምክንያት የሆነው የቤተ እምነት ቦታ ከ4 ዓመት በፊት ጥያቄ የቀረበበት ነው ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(18 votes)

ሁሉም አካል የቤተክርስቲያኒቱን ስም ከሚያጐድፍ መረጃ ሊታቀብ ይገባል ተብሏል

               ባለፈው ማክሰኞ ለሁለት ወጣቶች ህልፈት ምክንያት የሆነው የቤተ ክርስቲያን ቦታ ጉዳይ ከ4 ዓመት ጀምሮ ለአስተዳደሩ ጥያቄ ሲቀርብበት የነበረ መሆኑን “ጴጥሮሳውያን ሕብረት” ለአዲስ አድማስ አስታውቋል፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን፣ ጴጥሮሳውያን የቤተ ክርስቲያን ክብርና መብት አስጠባቂ ሕብረት ዋና ጸሐፊ አቶ ግርማ ተስፋ፣ ስለተፈጠረው ችግር ሕብረቱ ከስር መሰረቱ እያጣራ መሆኑንና ግኝቱን ለሕዝብ በዝርዝር እንደሚያቀርብ ገልጸው፤ በተለምዶ 24 ቀበሌ በተባለውና አሁን ለሁለት ወጣቶች ህልፈትና ከ17 በላይ ወጣቶች ጉዳት መነሻ በሆነው አካባቢ፣ ለቤተ ክርስቲያን ግንባታ የሚሆን ቦታ በይፋ ሲጠየቅ የነበረው፣ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ መሆኑን አስረድተዋል፡፡  
በአካባቢው ምንም አይነት ቤተ ክርስቲያን አለመኖሩን መነሻ በማድረግ፣ ምዕመናን ከ1998 ዓ.ም አንስቶ ለቤተ ክርስቲያን ቦታ እንዲመራላቸው ጥያቄ ማቅረብ መጀመራቸው አስታውሰው፤ በ2009 ዓ.ም ከንቲባ ድሪባ ኩማ ከተማዋን በሚያስተዳድሩበት ወቅትም፣ ጥያቄው በይፋ በደብዳቤ መቅረቡን ተናግረዋል፤ አቶ ግርማ፡፡
‹‹ቄሶች ራዕይ ታይቶን ነው ብለው ቦታውን ያዙ የሚባለው ፍፁም ሃሰትና የቤተ ክርስቲያኒቱን ክብር የሚያጎድፍ ነው›› ያሉት ዋና ጸሐፊው፤ “በቦታው ላይ የረጅም ጊዜ ጥያቄ መኖሩን የክፍለ ከተማው አስተዳደርም በሚገባ ያውቃል” ብለዋል፡፡
ጴጥሮሳውያን ህብረት፤ የቤተ ክርስቲያንን መብት ለማስጠበቅና ስለ ቤተ ክርስቲያኒቱ ለመሟገት የተቋቋመ እንደመሆኑ፣ ሕብረቱ ጉዳዩን ከስረ መሰረቱ አጣርቶ፣ለሕዝብ ተገቢውን መረጃ ያደርሳል ብለዋል፤ ዋና ጸሐፊው፡፡
የአካባቢው ነዋሪዎች በበኩላቸው፤ ማክሰኞ ለረቡዕ አጥቢያ፣ ከሌሊቱ 7 ሰዓት አካባቢ፣ 22 ቅዱስ ገብርኤል ሆስፒታል አካባቢ፣ የፀጥታ ሃይሎች፣ ሕገ ወጥ ነው ያሉትንና ከተመሰረተ ከሁለት ሳምንት ያልዘለለ ዕድሜ ያለውን ቤተ ክርስቲያን ለማፍረስ በተንቀሳቀሱበት ወቅት ግጭቱ መፈጠሩን ይናገራሉ፡፡
በወቅቱ ቁጥራቸው በርከት ያሉ የፀጥታ ሀይሎች አካባቢውን መቆጣጠራቸውን፤ በቤተ ክርስቲያኑ ግቢ ውስጥ የነበሩ ካህናትም ለአካባቢው ሰዎች የድረሱልን ጥሪ ማስተላለፋቸውን፣ ይህን ተከትሎም በተለይ የአካባቢው ወጣቶች መሰባሰባቸውን የአዲስ አድማስ  ምንጮች  አስረድተዋል፡፡
የፀጥታ ሀይሎች በአካባቢው ወጣቶች ላይ አስለቃሽ ጭስና ጥይት መተኮሳቸውን፤ በዚህም ወጣቶች   ሜዳ ላይ መውደቃቸውን የተናገሩ የአይን እማኞች፤ አምቡላንሶችም የወድቁትን እያነሱ ወደ ሆስፒታል መውሰዳቸውን ገልጸዋል፡፡ ሚካኤል ፋኖስና ሚሊዮን ድንበሩ የተባሉ ሁለት ወጣቶችም በፖሊስ ጥይት ተመተው ህይወታቸው ሊያልፍ ችሏል፡፡
ባለፈው ረቡዕ ድርጊቱን አስመልክቶ የአዲስ አበባ አስተዳደር ም/ከንቲባ ኢ/ር ታከለ ኡማ በሰጡት መግለጫ፤ በፀጥታ ሀይሎች የተፈፀመው ድርጊት ከአስተዳደራቸው እውቅና ውጪ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ከንቲባው በፌስቡክ ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ “ከየትኛውም ጊዜ በተለየ ከሃይማኖት ተቋማት ጋር ተቀራርበን እየሰራን በምንገኝበት ወቅት፣ በሃይማኖት ተቋማት ጥያቄዎች ምክንያት የአንድም ሰው ሕይወት ይጠፋል ብለን አስበን አናውቅም›› ብለዋል፡፡
‹‹በተለይ ከይዞታ ጥያቄዎች ጋር በተያያዘ ረጅም ርቀት ሄደን ጥያቄዎችን ስንመልስ ቆይተናል›› ያሉት ከንቲባው፤ ‹‹ይሁን እንጂ በመንግሥትና በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ በሚገኙ ጥቂት አጥፊዎች ምክንያት በከተማችን ይሆናል ያላልነው፤ እንዳይሆን የለፋንበት ድርጊት ተፈጽሟል›› ብለዋል፡፡
የወጣቶች ሕይወት እንዲጠፋ ያደረጉ ከሁለቱም ወገን ያሉ የጥፋት አካላት፣ በሕግ እንዲጠየቁ እናደርጋለን ያሉት ከንቲባው፤ ሰባት ተጠርጣሪዎች መታሰራቸውን እንዲሁም በወቅቱ በፀጥታ ሃይሎች ታስረው የነበሩና እንዲለቀቁ የሕዝብ ግፊት የቀረበባቸው ወጣቶች እንዲፈቱ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡
በፀጥታ ሃይሎች ህይወታቸው ያለፈው ሁለቱ ወጣቶች የቀብር ሥነ ስርዓት፣ ባለፈው ሀሙስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ በተገኙበት በቦሌ መድሃኒዓለም ፀሎተ ፍትሃት ከተደረገ በኋላ በገርጂ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ተከናውኗል፡፡   
ኢዜማና አብን ባወጡት መግለጫ፤ ድርጊቱን በጽኑ ያወገዙ ሲሆን መንግሥት ግድያ የፈፀሙ አካላትንና አጥፊዎችን በአፋጣኝ ለሕግ እንዲያቀርብ፣ ለተጎጂ ቤተሰቦች አስፈላጊውን ካሳ እንዲከፍልና ስለ ሁኔታው ዝርዝር መረጃ ለሕዝብ እንዲያቀርብ ጠይቀዋል፡፡

Read 13528 times