Saturday, 30 June 2012 11:17

30ኛው ኦሎምፒያድ በሁሉም ረገድ ገዝፏል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በለንደን አስተናጋጅነት የሚጀመረው 30ኛው ኦሎምፒያድ በሚደረግለት ከፍተኛ ጥበቃ፤ በወጣበት ወጭ፤ በተዘጋጁለት የመወዳደርያ ስፍራዎች የጥራት ደረጃ፤ በኢንተርኔት የማህበረሰብ ድረገፆች እና በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች በሚኖረው ሰፊ ሽፋን እና በስፖንሰሮች እና ንግዳቸውን በሚያጧጡፉ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ፉክክር በታሪክ አዳዲስ ምእራፎች የሚከፍትና የላቀ ደረጃ እንደሚኖረው እየተጠበቀ ነው፡፡ታላቁን የኦሎምፒክ መድረክ በታሪኳ ለሶስተኛ ጊዜ በማስተናገድ ብቸኛ ለመሆን የበቃችው የለንደን ከተማ የ30ኛው ኦሎምፒያድ አዘጋጅነቷን ከ7 አመት በፊት ያስገኘችው የፓሪስ እና የኒውዮርክ ከተሞችን ፉክክር በማሸነፍ ነበር፡፡ እንግሊዝ በኢኮኖሚ ቀውስ ዘመን የምታስተናግደው ኦሎምፒክ ከትርፉ ይልቅ ኪሳራው ያመዝናል በሚል በአንዳንድ የለንደን ከተማ ነዋሪዎች መጠነ ሰፊ ምሬት እያሰሙ ናቸው፡፡

ኦሎምፒኩ እንግሊዝ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ወዳጅነት በማጠናከር፤ በአውሮፓ ያላትን ጉርብትና በማጎልበት፤ አገሪቱ በቱሪስት መስህብነት ያላትን አቅም በማሟሟቅ እና ከፍተኛ የጥራት ደረጃ ያላቸውን የስፖርት መሰረተ ልማቶች በማስገኘት ከፍተኛ ውጤት እንደሚኖረው ግን ታምኖበታል፡፡ ለንደን ኦሎምፒኩን ለማስተናገድ ላለፉት ሰባት ዓመታት ስትንቀሳቀሳቀስ ከመነሻው የያዘችው በጀት በአጥፍ አድጎ 9.3 ቢሊዮን ፓውንድ ደርሷል፡፡ ይሄው በጀት 30ኛው ኦሎምፒያድን በታሪክ ከፍተኛው ወጭ የወጣበት የኦሎምፒክ መድረክ አድርጎታል፡፡ ከ205 ተሳታፊ አገራት የተውጣጡ 10500 አትሌቶች ለሚወዳደሩበት 30ኛው ኦሎምፒያድ 8.8 ሚሊዮን ትኬቶች ለገበያ ቀርበዋል፡፡ ከመላው ዓለም እስከ 28ሺ የሚዲያ የብሮድካስት ባለሙያዎች ይገኙበታል፡፡ ቢቢሲ በሚያሳማራቸው 765 ባለሙያዎች የ2500 ሰዓታት የቀጥታ ስርጭት ይሰራታል፡፡ የኦሎምፒክ ችቦ 8ሺ ማይሎችን በብሪታኒያ እና አየርላንድ ሲጓዝ 8ሺ ስፖርተኞች ኃይሌ ገብረስላሴን ጨምሮ አንግበውት ሮጠዋል፡፡ በ30ኛው ኦሎምፒያድ ለንደንን የሚጎበኙት ብዛታቸው 1 ሚሊዮን  ይደርሳል የተባለ ሲሆን ከ70ሺ በላይ የበጎ አገልግሎት ሰጭዎች እንደሚያስተናግዷቸው ይጠበቃል፡፡ በኦሎምፒኩ ሳቢያ ለንደንን የሚጎበኙ ቱሪስቶች መብዛት ከተማዋ በዓመት የምታስተናግደውን የጎብኝዎች ብዛት ወደ 31 ሚሊዮን ያሳደገው ሲሆን ይህም የቱሪስት ፍሰት እስከ 103 ሚሊዮን ፓውንድ ገቢ ይኖረዋል ተብሏል፡፡

 

በ26 የስፖርት አይነቶች እና 39 የውድድር መደቦች የሚካሄዱ 302 የሜዳልያ ሽልማት የቀረበባቸውን ውድድሮችን በ1 ወር ውስጥ የሚያስተናግደው የለንደን ኦሎምፒክ ከ1 ሚሊዮን በላይ የስፖርት ቁሳቁሶችን የያዙ 34 የመወዳደርያ ስፍራዎች ይጠቀማል፡፡

800ሚ. ዶላር የፈጀ ጥበቃ

30ኛው ኦሎምፒያድ በሚደረግለት የፀጥታ ጥበቃና ቁጥጥር በኦሎምፒክ ታሪክ ከፍተኛውን ደረጃ የሚያሳይ ይሆናል፡፡ ለኦሎምፒኩ አስተማማኝ ፀጥታና ደህንነት እስከ 800 ሚሊዮን ዶላር በጀት ወጭ መደረጉ በውድደሩ ታሪክ ከፍተኛው እየተባለ ሲሆን እንግሊዝ በዚህ ዝግጅቷ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ የፖሊስ እና የጦር ሃይሏን በከፍተኛ ተጠንቀቅ አዘጋጅታለች፡፡ በኦሎምፒኩ ፀጥታና ሰላም አስተማማኝ ጥበቃና ቁጥጥር ለማድረግ ከአሜሪካ የጦር ሃይል፤ የስለላ ድርጅቶችና የደህንነት ተቋማት ጋር በትብብር እየሰራች የምትገኘው እንግሊዝ 12ሺ ፖሊሶች፤ ከ23ሺ በላይ የፀጥታና የደህነነት ሰራተኞች፤ እስከ 20ሺ የግል ጥበቃ ሰራተኞች እንዲሁም እስከ 13ሺ የ0ር ሃይሏን ወታደሮች ለኦሎምፒኩ ጥበቃ ታሰማራለች፡፡ የለንደን ኦሎምፒክ በሽብር ጥቃት ሊደርስበት ይችላል የሚለው ስጋት ከቢንላደን መሞት እና የአልቃኢዳ ከፍተኛ አመራሮች በመሳደድ ላይ ከመሆናቸው ጋር በተያያዘ ቀንሶ ነበር፡፡ ይሄው ፍራቻ በኦሎምፒኩ ሰሞን ሊያጋጥም መቻሉ በተጨባጭ ደረጃ ከመታየቱም በላይ ያልታሰቡ ሽብር ፈጣሪ ክስተቶች እንዳይከሰቱ ለመከላከል ከፍተኛ ጥበቃ መደረጉ አስፈላጊ እንደሆነ ታምኖ ሁሉም ሃይል በተጠንቀቅ ላይ ይገኛል፡፡ አሜሪካ በመቶዎች የሚቆጠሩ የስለላ እና የደህነነት ባለሙያዎቿን ለኦሎምፒኩ የምትልክ ስትሆን ኢንተርፖልም በከፍተኛ ክትትል ለእንግሊዝ ድጋፍ እንደሚያደርግም ታውቋል፡፡ እስራኤል በሳምንት ሰባት ቀን ለ24 ሰዓታት ማንኛውንም እንቅስቃሴ የሚቆጣጠሩ 4ሚሊዮን የስለላ ካሜራዎችን በለንደን ከተማ እና በሌሎች የእንግሊዝ ከተሞች በመስቀል  እና በመግጠም ከፍተኛ እሰተዋፅኦ አድርጋለች፡፡ እንግሊዝ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ከፍተኛ ተጠንቀቅ አድርገበታለች የተባለው የለንደን ኦሎምፒክ ጥበቃዋ ላይ በለንደን ከተማ ዋና ዋና ስፍራዎች የአየር መቃዋሚያ ሚሳዬሎች፤ አርኤኤፍ ታይፎን የተባሉ ተዋጊ ጀቶችና እና ከፍተኛ የክትትል አቅም ያላቸውን ራዳሮች በመትከል እየሰራች ነው፡፡

የኬብል መኪኖች

በለንደን ከተማ ከተደረጉ መሰናዶዎች የተሟላ ግልጋሎት እንደሚገኝበት የተጠበቀው በትራንስፖርት አቅርቦት የተደረገው ከፍተኛ ዝግጅት ነው፡፡ ለውድደሩ የ24 ሰዓት የመጓጓዣ አገልግሎት የሚሰጡ 10 የባቡር ጣቢያዎች መዘጋጀታቸው ሲታወቅ በሰዓት እስከ 240ሺ ተሳፋሪዎችን የማስተናገድ አቅም ይኖራቸዋል፡፡ በልዩ ሁኔታ ለስፖርተኞች፤ ለስፖርት አፍቃሪዎችና ለቱሪስቶች የተቃና የለንደን ቆይታ የጉብኝት ምቹነት የተዘጋጁት በአየር ላይ ተንጠልጣይ የኬብል መኪናዎች አቅርቦትም ኦሎምፒኩ ማራኪ መሰናዶ ተደርጎለታል፡፡ በለንደን ከተማ በሚገኘውና ሁሉንም የመወዳደርያ ስፍራዎች በሚያካልለው የቴምስ ወንዝ  አናት በ100 ጫማዎች ከፍታ ላይ የተዘረጋው የኬብል መኪናዎች መጓጓዣ መስመር በ50 ሚሊዮን ፓውንድ ወጭ ተሰርቶ ተዘጋጅቷል፡፡ በብዛታቸው 34 የሆኑትና ጎንደለስ የሚል ስያሜ ያላቸው እነዚህ በአየር ላይ  በተዘረጉ የኬብል መስመሮች የሚያጓጉዙ ተሽከርካሪዎች ከኦሎምፒኩ በተያያዘ በለንደን ከተማ ሲሰሩ ለመጀመርያ ጊዜ ሲሆን የዱባዩ ኤምሬትስ ኤርላይንስ ለ10 ዓመታት በሚቆይ የ36 ሚሊዮን ፓውንድ የስፖንሰርሺፕ ድጋፍ የተዘጋጁ ናቸው፡፡ ለኦሎምፒኩ ተሳታፊዎች ለንደን ከተማን ከአየር ላይ ለመጎብኘት ማራኪ እድል ፈጥረዋል የተባሉት እነዚህ የኬብል መኪኖች በደቂቃ እስከ 2500 ተሳፋሪዎችን በማስተናገድ ይንቀሳቀሳሉ፡፡

የስፖንሰሮች ሩጫ

የለንደን ኦሎምፒክን ስኬታማነት አጓጊ ያደረገው ሌላው መሰናዶ ደግሞ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በስፖንሰርሺፕ እና በምርቶቻቸው አቅርቦት ገያቸውን ለማስፋፋት እና ገፅታቸውን ለመገንባት በሚያደርጉት እንቅስቃሴ የገቡት ፍጥጫ ነው፡፡ 30ኛው ኦሎምፒያድ በልዩ ፕሮግራም 11 ትልልቅ ኩባንያዎችን በስፖንሰርሺፕ አጋርነት ያሰባሰበ ሲሆን ዋና ዋናዎቹ ኮካኮላ፤ቪዛ ካርድ እና ፕሮክተር ኤንድ ጋምብል ናቸው፡፡ በታላቁ የኦሎምፒክ መድረክ በአጋር ስፖንሰርነት ሲሰራ 84ኛ ዓመቱን የያዘው የለስላሳ መጠጥ አምራቹ ኮካኮላ በ30ኛው ኦሎምፒያድ በ110 አገራት ያለውን ገበያ ለለማጧጧፍ ሲያቅድ ቪዛ ካርድ በ70 አገራት እንዲሁም ፕሮክተር ኤንድ ጋምብል በ80 አገራት የምርቶቻቸውን ገበያ ለማስፋት በያዙት እቅድ ሰፊ የማስተዋወቅ ዘመቻ የሚያደርጉ ይሆናል፡፡30ኛው ኦሎምፒያድ ባለማችን ታላላቅ የስፖርት ትጥቅ አምራች እና አቅራቢዎች የገበያ ትንቅንቅም ልዩ ትኩረት ያገኘ ነው፡፡ በተለይ የአሜሪካው ናይኪ፤ የጀርመኑ አዲዳዳስ እና የጃፓኑ ፑማ ኩባንያዎች በኦሎምፒኩ በወቅቱ የቴክኖሎጂ አቅምና የጥራት ደረጃ ያመረቷቸውን የስፖርት ትጥቆችና ቁሳቁሶች ለኦሎምፒክ ተሳታፊ አገራት በሚያደርጉት አቅርቦትና በማስተዋወቅ ዘመቻቸው የዓለም ገበያን ለመቆጣጠር በሚኖራቸው ፉክክር ይፎካከሩበታል፡፡ የጀርመኑ አዲዳስ በኦሎምፒኮ ኦፊሴላዊ የትጥቅ አቅራቢነት የተለየ ድርሻ ሲኖረው ኩባንያው በኦሎምፒኩ የሚሳተፉ 5ሺ አትሌቶችን ሙሉ ትጥቅ በማቅረብ፤ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለሚሰማሩ በ10ሺዎች ለሚገመቱ ስፖርት አፍቃሪዎች የአዲዳስ ቱታዎችን በማስታጠቅና በአጠቃላይ ከ3 ሚሊዮን በላይ የስፖርት ትጥቅ እና ቁሳቁሶችን በማቅረብ ሰፊ አስተዋፅኦ ይኖረዋል፡፡ አዲዳስ ለለንደን ኦሎምፒክ በልዩ ዝግጅት ካቀረባቸው ምርቶች በ25 የውድድር አይነቶች ለሚሳተፉ አትሌቶች ያቀረባቸው 41 የውድድር ጫማዎች ዋንኞቹ ሲሆኑ እነዚህ ጫማዎች ከ4 ዓመት በፊት ቤጂንግ ላይ ካቀረባቸው ምርቶች ክብደታቸው በ25 በመቶ የቀነሱ ቀላልና ምቹ ምርቶች እነደሆኑ ታውቋል፡፡ የአሜሪካው ናይኪ ኩባንያ በበኩሉ በዋናነት በ2016 ብራዚል የምታስተናግደውን 31ኛው ኦሎምፒያድ በኦፊሴላዊ ስፖንሰርነት ለማጀብ ትኩረቱን ቢያደርግም በኦሎምፒክ መድረክ ከፍተኛው የሜዳልያ ውጤት ለሚያስመዘግበው የአሜሪካ ቡድን ሙሉ ትጥቅ በማቅረብ ይሰራል፡፡ ናይኪ በለንደን ኦሎምፒክ የጎላ ተሳትፎ ባይኖርም በዘንድሮ የዓለም ገበያ እሰከ 21 ቢሊዮን ዶላር ገቢ በመሰብሰብ ከስፖርት ትጥቅ አምራችና አቅራቢ ኩባንያዎች የመጀመርያውን ደረጃ በመያዝ ገበያውን ሲመራ የቅርብ ተቀናቃኙ አዲዳስ በ17 ቢሊዮን ዶላር ዓመታዊ ገቢው ይከተላል፡፡ በዓለም አቀፍ ገበያ 3.8 ቢሊዮን ዶላር የዓመት ገቢ በመሰብሰብ 3ኛ ደረጃ የያዘው ፑማ ደግሞ ለንደን ኦሎምፒክ ላይ አስደናቂና የላቀ ተሳትፎ ይኖረዋል ተብሎ ለተጠበቀው ለዓለም ፈጣኑ ሯጭ ዩሴያን ቦልት ሙሉ ትጥቅ በማቅረብ የገበያ ፉክክሩን እንደሚያጠናክር ይጠበቃል፡፡

የሬስቶራንቶች ገበያ

የለንደን ኦሎምፒክ ለሬስቶራንቶች እና ለሆቴሎች ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኝ ገበያ በመፍጠርም ይነሳል፡፡ ኦሎምፒኩ ምናልባት ኪሳራ ይፈጥራል ተብሎ የተሰጋው ለሆቴሎች አገልግሎት ሲሆን ዋናው ምክንያት ደግሞ የመኝታዎች ዋጋ በ2 እና 3 እጥፍ ከመጨመሩ ጋር በተያያዘ ነው፡፡ በብዙዎቹ የእንግሊዝ ከተሞች በተለይ በለንደን ከተማ የሚገኙት ሆቴሎች የዋጋ ጭማሪ አገሪቱን ለሚጎበኙ ጎብኝዎች መጨናነቅና ምቹ ያልሆነ ቆይታ ምክንያት ሲሆኑ ሁኔታው ምናልባትም ሲሶ ያህሉን የሆቴል መኝታ ቤቶች ያለእንግዳ ወና ያስቀራቸዋል ተብሎ ተሰግቷል፡፡ ይሁንና 30ኛው ኦሎምፒያድ በምግብና የለስላሳ መጠጦች አቅርቦት ለሚሰሩ የለንደን ከተማ ሬስቶራንቶች ከፍተኛ ገቢ ሊያስገኝ ይችላል፡፡ በምግብና ለስላሳ መጠጦች አቅርቦት በኦሎምፒኩ ሰሞን እስከ 46 ሚሊዮን ፓውንድ ገቢ ሊሰበሰብ እንደሚችል ተገምቷል፡፡ ለኦሎምፒኩ በሚሰሩ ከ40 በላይ ኦፊሴላዊ ሬስቶራንቶች እስከ 14 ሚሊዮን የምግብ ትዛዞች፤ 75ሺ ሊትር ወተት እና 330 ቶን ድንቾች እንደሚቀርቡ ሲተነበይ የኦሎምፒክ ተሳታፊ አገራት በሚያርፉበት የኦሎምፒክ መንደር በቀን 45ሺ የምግብ ትዛዞች ይስተናገዳሉ፡፡

የትኩስ ምግቦች አቅራቢ በሆነው ዓለም አቀፉ የማክዶናልድ ኩባንያ ለኦሎምፒኩ የተደረገው ዝግጅትም አስደናቂ ነው፡፡ በለንደን ኦሎምፒክ ለ6 ሳምንታት አገልግሎት የሚሰጥበትን ባለሁለት ፎቅ ህንፃ ከዋናው የኦሎምፒክ ስታድዬም 300 ሜትር ርቀት ላይ ያስገነባው ማክዶናልድ በቀን 1200 ደንበኞችን በ50ሺ የቢግ ማርክ በርገሮችና በ180ሺ የድንች ጥብስ ለማስተናገድ እየተጠባበቀ ነው፡፡

 

 

Read 2124 times Last modified on Saturday, 30 June 2012 11:22