Saturday, 08 February 2020 14:42

ጥምር ተግባር ለሰላም በምዕራብ ጐጂና ጌዲዮ ዞን

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(2 votes)

     “እሳትን በእሳት ለማጥፋት መሞከር ነበልባሉን ያብሰዋል እንጂ እሳቱን አያጠፋውም”
                          
        በ2010 የተደረገውን የመንግስት ለውጥ ተከትሎ በተቀሰቀሱ ግጭቶች በርካታ ወገኖች ለሞት፣ ለአካል ጉዳትና ለስደት ከተዳረጉባቸው አካባቢዎች አንዱና ዋንኛው ነው፤ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል፡፡ በዚህ ክልል በ2010 መጨረሻና በ2011 መግቢያ ወራት ላይ በጉጂ ኦሮሞና በጌዲዮ ብሔረሰብ አባላት መካከል በተቀሰቀሱ ግጭቶች፣ ከሁለት መቶ ሃያ በላይ ሰዎች ህይወታቸው ሲያልፍ፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወገኖች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ለስደት ተዳርገዋል፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ ቤቶች ተቃጥለዋል፤ ስፍር ቁጥር የሌለው ንብረት ወድሟል፡፡ በርካቶች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡
ትምህርት ቤቶች፣ የገበያ ስፍራዎችና የእምነት ተቋማት ሳይቀሩ የተለመደ አገልግሎታቸውን አቋርጠው ለወራት ዘልቀዋል:: በዚህ ለወራት በዘለቀ ግጭትና የሰላም ማጣት፣ ከሁለቱም ወገን በርካታ በተለይም ሴቶች፣ ህፃናትና አቅመ ደካሞች እጅግ ለከፋ ችግርና እንግልት ተዳርገዋል፡፡
ይህንን ወራት ያስቆጠረ ግጭትና አለመግባባት ለማስወገድና በሁለቱ ብሔር ህዝቦች መካከል ሰላምና ፍቅር ለማምጣት በተለያዩ መንገዶች ሙከራ ሲደረግ ቆይቷል፡፡ መንግስት ተፈናቃዮች ወደ መኖሪያ ቀዬአቸው ይምለሱ ዘንድ ከተለያዩ በጐ አድራጊ ተቋማት ጋር በቅንጅት ባከናወናቸው ተግባራት፣ ተፈናቃዮቹ ወደቀደመው የመኖሪያ ቀዬአቸው እንዲመለሱ ተደርጓል፡፡
ወደ መኖሪያ ቀዬአቸው የተመለሱት ወገኖች፣ ቤት ንብረታቸው በመውደሙና ባዶ እጃቸውን የቀሩ በመሆናቸ፣ው ህይወት እጅግ ፈታኝ ሆኖባቸዋለች፡፡ ምግብ፣ መጠለያ ልብስና ህክምና የእነዚሁ ተፈናቃይ ወገኖች የየዕለት ጥያቄያቸው ነው፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ግን እነዚህን ተፈናቃይ ወገኖች ይበልጥ የሚያሳስባቸው ጉዳይ ቢኖር፣ የደፈረሰው ሠላማቸው ነው፡፡ ከዛሬ ነገ ምን ይከሰት ይሆን? በሚል ስጋትና ጥርጣሬ የተሞላው የዕለት ተዕለት ኑሮአቸው ሰቀቀን ሆኖባቸዋል፡፡
በደቡብ ክልል ጌዲዮ ዞንና በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን ውስጥ የሚኖሩ በርካታ ወገኖች፣ የሠላም እጦት ያስከፈላቸውን ዋጋ ፈጽሞ አይዘነጉትም፡፡ በዘመናቸው አይተው የማያውቁትን መከራና ሰቆቃ፣ ወገን በወገኑ ላይ ሲፈጽም ቆመው የማየት ክፉ እጣ ፈንታ ገጥሟቸው ነበርና፡፡ ሁኔታው ከአዕምሮአቸው የሚጠፋም አይደለም፡፡ እናም ዛሬ የእነዚህ ወገኖች ዋንኛ ፍላጐትና ቀዳሚ ጥያቄ ሠላም ነው፡፡ በአካባቢው የአገር ሽማግሌዎች፣ በአባገዳዎችና በመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጥረት እርቅ ፈጽመው ዳግመኛ ወደ ጥፋት መንገድ ላይገቡ ቃል የተግባቡ ቢሆንም፣ ይህ ቃል ለሁለቱ ወገን ህዝቦች ሠላማዊ ኑሮ መረጋገጥ ዋስትና ሊሆን አልቻለም፡፡
ይህንን ሁኔታ ለመቀየር የሚያስችል አንድ ፕሮጀክት ይፋ የተደረገበት ፕሮግራም ሰሞኑን በደቡብ ክልል ጌዲኦ ዞን ዲላ ከተማና በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን ቡሌሆራ ከተማ ውስጥ ተካሂዶ ነበር፡፡ በወርልድቪዥን ኢትዮጵያና በአጋር ድርጅቶች በይፋ የተጀመረው ይኸው ፕሮጀክት፤ ለ18 ወራት የሚዘልቅና ወደ 3.3 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጐችን ተጠቃሚ የሚያደርግ  ነው፡፡
በፕሮጀክቱ ሰላም ርቋቸው ለወራት የዘለቁትንና በእርስበርስ ግጭት ሳቢያ ለሞት፣ ለአካል ጉዳት፣ ከቤት ንብረት ለመፈናቀልና ለንብረት ውድመት የተዳረጉትን ወገኖች ለማቋቋምና የሁለቱን ክልል ህዝቦች ወደ ሠላምና እርቅ ለመመለስ የሚያስችል የእርቅና ሠላም ግንባታ ሥራዎች ይከናወኑበታል፡፡
በደቡብ ክልል ጌዲዮ ዞን ዲላ ወረዳን ጨምሮ በዲላ ዙሪያ ወረዳዎች፣ ኮቸሬ፣ ገደብና ይርጋጨፌ፤ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን ቡሌሆራ፣ ቀርጫ፣ ገላን፣ አባያ፣ አምባላና ዋመያ ወረዳዎች ውስጥ ተግባራዊ በሚደረገው በዚህ የእርቅና ሠላም ፕሮጀክት ማስጀመሪያ ፕሮግራም ላይ የየክልሎቹ የፀጥታና ሠላም ቢሮ ኃላፊዎች፣ የወረዳ አስተዳዳሪዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎችና፣ የየአካባቢው ወጣቶች ተሣታፊ ሆነውበታል፡፡
ከአውሮፓ ዩኒየን በተገኘ የአንድ ነጥብ ሃያ አምስት ሚሊዮን ዩሮ የገንዘብ ድጋፍ በወርልድቪዥን ኢትዮጵያና አጋር ድርጅቶች ተግባራዊ የሚደረገው ይኸው ፕሮጀክት በይፋ በተደመረበት ወቅት የደቡብ ክልል የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊና የዘላቂ ሠላምና ግጭት አፈታት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አንድነት አሸናፊ እንደተናሩት፤ በአካባቢው ከ2010 ዓ.ም ማጠናቀቂያ ጀምሮ በተቀሰቀሱ ግጭቶች በሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች መካከል እጅግ ዘግናኝና አሰቃቂ ድርጊቶች ሲፈፀሙ ቆይተዋል:: የአካባቢው ነዋሪ ህዝብ በዘመኑ አይቶ የማያውቃቸውን አስከፊ ድርጊቶች አስናግዷል፡፡
በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጐች በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል፤ በአስርሺዎች የሚቆጠሩ ቤቶች ተቃጥለዋል፣ ሚሊዮኖች ከመኖሪያ ቤታቸው ተፈናቅለዋል፡፡ በወቅቱ በአካባቢው ላይ የተፈፀሙት ነገሮች እጅግ ዘግናኝና አሳዛኝ ነበሩ ያሉት የፀጥታና ሰላም ቢሮ ምክትል ኃላፊው፣ ሰው ሞቶ አስከሬኑ መሬት መሬት ለመሬት ሲጐተትና ሲቃጠል፣ ነፍሰጡር ሴት ከቤቷ ተፈናቅላ ዛፍ ስር ስትወልድ፣ ሴቶችና ህፃናት በአሰቃቂ ሁኔታ ሲገደሉ ያየንበት እጅግ አስከፊ ጊዜን ማሳለፋቸውን ተናግረዋል፡፡ ይህ ሁኔታ ዳግመኛ እንዳይፈጠርና የሁለቱም ክልል ህዝቦች በፍቅርና በሠላም አብረው ለመኖር እንዲችሉ ለማድረግ የሚያስችለውንና እርቅና ሠላም በሁለቱ ክልል ህዝቦች መሀል የሚፈጥረውን ይህን ፕሮጀክት በምንችለው አቅም ለመደገፍ የበኩላችንን ጥረት እናደርጋለን ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በአካባቢው አንፃራዊ ሠላም መስፈኑንና ይህንን ሠላም በተሻለ ሁኔታና በዘላቂነት እንዲቀጥል ለማድረግ፣ የሁለቱም ክልል ህዝቦች ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ችሮታው አየለ በበኩላቸው፤ ቀደም ሲል በአካባቢው ይከሰቱ የነበሩ ግጭቶችና አለመግባባቶች በአካባቢው የአገር ሽማግሌዎችና አባገዳዎች ይፈቱ ነበር፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በዓይነቱ የተለየና ሰፊውን ህብረተሰብ የጐዳ፣ ሰብአዊ እርዳታዎችን ለማቅረብ እንኳን አስቸጋሪ ሁኔታዎችን የፈጠረ ግጭት ተቀስቅሶ ብዙዎችን ለሞት ለአካል ጉዳትና መፈናቀል ዳርጓል፡፡
ማንም ሰው ይህንን ሁኔታ ለማየትና ለመቋቋም አቅም አልነበረውም፡፡ ዩኒቨርሲቲው በወቅቱ በተፈጠረው የእርስበርስ ግጭት የተጐዱ ወገኖችን ለመርዳት ከፍተኛ እንቅስቃሴ ማድረጉን የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ፤ አሁን በአካባቢው እየታየ ያለውን ሠላም ለማስቀጠልና በሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች መካከል የበለጠ ሰላም እንዲሰፍን ለማድረግ የበኩሉን ይወጣል ብለዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል የምዕራብ ጉጂ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ሆቴሎ ገልገሎ በዚሁ የጥምር ተግባር ለሰላምና እርቅ ፕሮጀክት ጅማሮ ፕሮግራም ላይ ተገኝተው እንደተናገሩት፤ በወቅቱ ተከስቶ በነበረው የእርስ በርስ ግጭት በመቶዎች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ሞተዋል፤ ሺዎች ከመኖሪያ ቀዬአቸው ተፈናቅለዋል፤ እጅግ ከፍተኛ ንብረት ወድሟል፡፡ ይህ ድርጊት በሁለቱም ህዝቦች መሀል ከፍተኛ ጠባሳ ጥሎ ያለፈ ድርጊት ነው፡፡ ይህን ሁኔታ ለመቀየርና የሁለቱን ህዝቦች የቀደመ ሰላም ለመመለስ በሚደረገው ጥረት የጉጂ ህዝብ ግንባር ቀደም ተዋናይ ይሆናል ብለዋል፡፡
የቡሌሆራ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጌታቸው ጐዳና በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ የአካባቢውን ሠላም በዘላቂነት ለማሻሻልና የሁለቱን ክልል ህዝቦች ሠላም የተረጋገጠ ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት ዩኒቨርሲቲው በሚቻለው ሁሉ ለማገዝ ዝግጁ ነው ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች የግጭት መነሻ ወይም መቀስቀሻ ቦታዎች እንዳይሆኑ በበኩላቸው፤ የምንችለውን ሁሉ ለማድረግ ቁርጠኞች ነን ሲሉም ጨምረው ገልፀዋል፡፡
የወርልድቪዥን ኢትዮጵያ ካንትሪ ዳይሬክተር ሚስተር ኤዲ ብራውን በበኩላቸው በዚሁ የፕሮጀክት ማስጀመሪያ ፕሮግራም ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ኢትዮጵያውያን ለሰላም ያላቸው አክብሮትና ስሜት ከሁሉም አገር ዜጐች ለየት ያደርጋቸዋል፡፡ እርስበርስ ሲገናኙ እንኳን ሠላምታቸውን የሚለዋወጡት ሠላም ነው እየተባባሉ ነው፤ ይህ ደግሞ ለሠላም ያላቸውን ፍላጐት የሚያሳይ ነው፡፡ ሠላም የሚመጣው ደግሞ እርስበርስ መከባበር ሲኖር ነው” ብለዋል፡፡
አያይዘውም፤ እሳትን በእሳት ለማጥፋት መሞከር ነበልባሉን ያብሰዋል እንጂ እሳቱን አያጠፋውም፡፡ እሳት የሚጠፋው በውሃ ነው፤ ጥላቻም የሚጠፋው በፍቅር ነው፤ በወንድማማች ህዝቦች መካከል በጊዜ አጋጣሚ የተነሳውን ፀብና ጥላቻ በፍቅር ማሸነፍ ይገባል:: ለዚህ ደግሞ የሁለቱም ህዝቦች አባላት፣ ወጣት አዛውንቱ ወንድና ሴቱ ሁሉ ኃላፊነት አለበት እኛም እዚህ ያለነው ይህንኑ ለማገዝና ሁለቱን ህዝቦች ወደቀደመው ሠላምና ፍቅር ለመመለስ የሚያስችል እርቅ እንዲፈጽሙ ለማድረግ ነው ብለዋል፡፡
ለ18 ወራት ተግባራዊ በሚደረገው በዚህ ፕሮጀክት በሁለቱ ክልሎች ውስጥ በሚገኙ ዞኖችና ወረዳዎች ውስጥ የሚኖሩ ህዝቦችን፣ በተለይም የግጭቱ ዋና ተሳታፊና የጉዳቱም ዋንኛ ተጠቂ የሆነውን ወጣቱን ክፍል በስፋት የሚያሳትፍ የተለያዩ ተግባራት እንደሚከናወኑበትና ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ ሥራዎች እንደሚሰሩበት በዚሁ የፕሮጀክት ማስጀመሪያ ፕሮግራም ላይ ተገልጿል፡፡    

Read 593 times