Monday, 03 February 2020 12:03

‹‹ራይድ›› አሽከርካሪና መኪናን ከዝርፊያ የሚታደግ አዲስ ቴክኖሎጂ አስተዋወቀ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

     ራይድን የሚያስተዳድረው “ሀይብሪድ ዲዛይንስ” ከሌሎች ሀገር በቀል ተቋማት ጋር በመተባበር ያሰራውን “ዱካ ሁሉ” ተሰኘ የተሳፋሪን፣ አሽከርካሪንና መኪናን ከዝርፊያ የሚጠብቅ ቴክኖሎጂ ሰሞኑን አስተዋውቋል፡፡
ራይድ ከትላንት በስቲያ ሀሙስ ጥር 21 ቀን 2012 ዓ.ም በሸራተን አዲስ ላሊበላ አዳራሽ ይፋ ያደረገው “ዱካ ሁሉ” የተሰኘው ቴክኖሎጂ፤ በሆራይዘን ኤክስፕረስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር እባ በሀገር ልጆች የተሰራ ሲሆን፤ “ለፋይዳ” ብድርና ቁጠባ ተቋም ፕሮጀክቱን በፋይናንስ መደገፉም በዕለቱ ሶስቱ ድርጅቶች በጋራ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
“ዱካ ሁሉ” የተሰኘው ቴክኖሎጂ በዋናነት የመኪናንና የአሽከርካሪን ዘረፋ የሚታደግ ሲሆን፤ በተጨማሪም በአደጋ ጊዜ የድረሱልኝ ጥሪ ለተለያዩ ባለድርሻ አካላት ለማሰማት ዕድል ይሰጣል ተብሏል፡፡ በመኪና ውስጥ በድብቅ ቦታ ላይ የሚገጠመው መተግበሪያው፤ አደጋ ባጋጠመ ጊዜ ለራይድ ለዋናው ማዕከል፣ በአካባቢው ላሉ የራይድ አሽከርካሪ ቤተሰቦችና ለፖሊስ በተመሳሳይ ሰዓት ጥሪ እንደሚያቀርብ ተገልጿል፡፡ በጂፒኤስ አቅጣጫ የሚጠቁመው ይሄው ቴክኖሎጂ፤ አሽከርካሪዎችንም ሆነ መኪናን ከዝርፊያና ከአደጋ የመጠበቅና የማስጣል ዕድሉ ከፍተኛ ነው ያሉት የራይድ መስራችና ዋና ስራ አስኪያጅ ወይዘሪት ሳምራዊት ፍቅሩ፤ ለዚህ ቴክኖሎጂ ትግበራና ቅድመ ጥናት ድርጅታቸው 2.6 ሚ ብር ወጪ ማድረጉንና ይህም ከፕሮጀክቱ አጠቃላይ ወጪ 40 በመቶ ያህሉ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
እንደ ስራ አስኪያጇ ገለፃ፤ በቀጣይነት የቴክኖሎጂው የጠቅላላ ምርት ቅድመ ክፍያ “ለፋይዳ” ብድርና ቁጠባ ተቋም እንዲሸፍን አሰራር የተነደፈ ሲሆን ከአንድ ሳምንት በኋላ ለትግበራ አሽከርካሪዎች ወረፋ መያዝ እንደሚጀምሩ፣ ከኤፕሪል 1 ጀምሮ በያዙት ወረፋ መሰረት ማስገጠም እንደሚጀምሩና የዚህን ቴክኖሎጂ ክፍያ በአንዴ ከፍለው መጨረስ ለማይችሉ አሽከርካሪዎች በወር 1345 ብር እየከፈሉ በ6 ወር እንዲያጠናቅቁ ለፋይዳ ብድር ማመቻቸቱን እንዲሁም ለቴክኖሎጂው አገልግሎት ክፍያ በየወሩ 650 ብር ሊከፍሉ የነበረውም ወደ 350 ብር ዝቅ ማለቱን ተናግረዋል፡፡
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በራይድ ታክሲዎች ላይ የሚፈፀመ ዘረፋና ጉዳት እየጨመረ መምጣቱ መዘገቡ አይዘነጋም፡፡ ቴክኖሎጂው ዝርፊያን  ከመከላከል በተጨማሪ፣ መኪናቸውን ለሚያከራዩ ባለንብረቶችም እፎይታን የሚሰጥ ሲሆን፤ የመኪና ጉዞ ክትትል፣ የፍጥነት መቆጣጠሪያ ጥቆማ፣ የነዳጅና የመኪና ወጪ መከታተያ፣ የስራ ክልል መገደቢያ፣ የተበላሸ መንገድ ላይ ሲነዳ የመናጥ ችግር ጥቆማና መሰል አገልግሎቶችን ያካትታል ተብሏል፡፡
ምንም እንኳን ራይድ እነዚህን ሁሉ እሴቶች በአገልግሎቱ ላይ ቢጨምርም በተሳፋሪ ላይ የዋጋ ጭማሪ እንደማያደርግ ወይዘሪት ሳምራዊት ጨምረው ገልፀዋል፡፡


Read 2137 times