Saturday, 30 June 2012 11:10

ላሮጃ ወይስ አዙሪ?

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

በ14ኛው የአውሮፓ ዋንጫ የሞት ምድብ በተባለው ምድብ 3 1ኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ይዘው ወደ ጥሎ ማለፍ ምእራፍ የገቡት ስፔንና ጣሊያን ለፍፃሜ ጨዋታ ደረሱ፡፡ ስፔን ረቡዕ እለት በተደረገው የግማሽ ፍፃሜ ጎረቤቷን ፖርቱጋልን በመለያ ምቶች 4ለ2 ስታሸነፍ፤ ጣሊያን ደግሞ ከትናንት በስቲያ ለዋንጫው ከፍተኛ ግምት ተሰጥቷት የነበረችውን ጀርመን በማርዮ ባላቶሊ ጎሎች  2ለ0 በመርታት ለነገው የዋንጫ ጨዋታ ደርሰዋል፡፡ በአውሮፓ ዋንጫው ከፍፃሜው በፊት በተደረጉት 31 ጨዋታዎች 72 ጎሎች ከመረብ አርፈዋል፡፡ በአማካይ በየጨዋታው 2.38 ጎሎች ስለተመዘገቡበት ከባለፉት ሁለት የአውሮፓ ዋንጫዎች ያነሰ የግብ እድል አሳይቷል፡፡ ማርዮ ባላቶሊ በ3 ጎሎች ማርዮ ጎሜዝና ክርስትያኖ ሮናልዶ በገቡበት የኮከብ ግብ አግቢዎች ፉክክር የተቀላቀለ ሲሆን በዋንጫው ጨዋታ ካገባ የውድድሩ ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ የመጨረስ እድል ይኖረዋል፡፡ በአንድ ጨዋታ በአማካይ እስከ 46ሺ ተመልካች የነበረውን 14ኛው የአውሮፓ ዋንጫን ከፍፃሜው በፊት 1.5 ሚሊዮን ተመልካቾች በሁለቱ አዘጋጅ አገራት በነበሩ ስምንት ስታድዬሞች በመገኘት ተመልክተውታል፡፡

የዋንጫ  ጨዋታው ነገ በስፔንና ጣሊያን መካከል በዩክሬን ዋና ከተማ በሚገኘው ኦሎምፒክ ስታድዬም ሲደረግ ለሻምፒዮኑ ቡድን ዋንጫና 7.5 ሚሊዮን ዩሮ የገንዘብ ሽልማት እንዲሁም ሁለተኛ ደረጃ ለሚያገኘው 4.5 ሚሊዮን ዩሮ እንደሚበረከት ታውቋል፡፡ ስፔንና ጣሊያን እስከዋንጫው ጨዋታው በነበራቸው ውጤታማነት በአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ከቀረበው ሽልማት እያንዳንዳቸው 15.5 ሚሊዮን ዩሮ ታስቦላቸዋል፡፡ በነገው ጨዋታ በስፔን ብሄራዊ ቡድን በኩል አምበሉ ኢከር ካስያስ፤ አንድሬዬስ ኢንዬስታና ሴስክ ፋብሪጋዝ እንዲሁም በጣሊያን ብሄራዊ ቡድን አምበሉ ጂያንሉጂ ቡፎን፤ አንድሪያ ፒርሎና ማርዮ ባላቶሊ በሚኖራቸው ወሳኝ ብቃት ይጠበቃሉ፡፡ ስፔንና ጣሊያን በምድብ ማጣርያው ተገናኝተው 1 እኩል አቻ ተለያይተዋል፡፡

ከ14ኛው የአውሮፓ ዋንጫ በፊት በ13 የአውሮፓ ዋንጫ ድሎች 9 አገራት ያሸነፉ ሲሆን ጀርመን 6 ግዜ ለፍፃሜ ቀርባ 3 በማሸነፍ ከፍተኛ ውጤት ክብረወሰንን ይዛለች፡፡ በአውሮፓ ዋንጫ ለፍፃሜ ስትደርስ ነገ በታሪኳ ለአራተኛ ጊዜዋ የሚሆነው ስፔን በ1964 እና በ2008 እኤአ ሁለት ዋንጫዎችን ስተውስድ በ1984 ደግሞ ሁለተኛ ደረጃ አግኝታለች፡፡ በ1968 እኤአ ላይ ብቸኛውን የአውሮፓ ዋንጫ የወሰደችው ጣሊያን ደግሞ በ2000 እኤአ ላይ ሁለተኛ ደረጃ ያገኘች ሲሆን የነገው ፍፃሜ በታሪክ ለ3 ግዜ የምትቀርብበት የዋንጫ ፍልሚያ ይሆናል፡፡ በአውሮፓ ዋንጫው የተሳተፉ 16 ብሄራዊ ቡድኖች በቡድን ስብስባቸው የያዟቸውን 23 ተጨዋቾች ወቅታዊ የዝውውር ሂሳብ በማስላት በስፖርት ኢንተለጀንስ የተሰራ አንድ ሪፖርት የስፔን ብሄራዊ ቡድን በ579.7 ሚሊዮን ፓውንድ ተተምኖ 1ኛ ደረጃን አግኝቷል፡፡

በ404.1 ሚሊዮን ፓውንድ  ጀርመን፤ በ345.23 ሚሊዮን ፓውንድ እንግሊዝ፤ በ299.9 ሚሊዮን ፓውንድ ፈረንሳይ፤ በ290 ሚሊዮን ፓውንድ ፖርቱጋል በቡድናቸው የዋጋ ተመን ከ3 እስከ 5 ያለውን ደረጃ ሲወስዱ ነገ ከስፔን ጋር ለዋንጫ የምትቀርበው ጣሊያን በተጨዋቾች ስብስቧ 260 ሚሊዮን ፓውንድ የዋጋ ተመን ኖሯት ስድስተኛ ደረጃ ተሰጥቷታል፡፡

ጣሊያን በ1982 እና በ2006 እኤአ ላይ ያሸነፈቻቸው ሁለት ዓለም ዋንጫዎች በአገሪቱ እግር ኳስ የጨወታ ቅየራ ቅሌቶች ባጋጠሙበት ሁኔታ መሆኑን የሚታወስ ነው ዘንድሮም ተመሳሳይ የቅሌት ድራማ በአገሪቱ መፈጠሩ ለዋንጫ አሸናፊነቷ ፍንጭ የሰጠ ተብሏል፡፡

በ2008 እኤአ ላይ 13ኛውን የአውሮፓ ዋንጫ እንዲሁም በ2010 እኤአ 19ኛውን የዓለም ዋንጫ ያሸነፈችው ስፔን በነገው የ14ኛው የአውሮፓ ዋንጫ ላይ ድል ከቀናት በ3 ትልልቅ ውድደሮች አከታትላ በማሸነፍ በእግር ኳስ ታሪክ አዲስ እና ብቸኛ የውጤት ክብረወስን ታስመዘግባለች፡፡ ይህ አይነቱን ደማቅ ታሪክ ለማሳካት ሞክረው ያልታሳካላቸው ታላላቅ ብሄራዊ ቡድኖች ነበሩ፡፡

በ1972 በአውሮፓ ዋንጫ በ1974 እኤአ ደግሞ የዓለም ዋንጫን አሸንፋ በ1976 እኤአ ለአውሮፓ ዋንጫ የቀረበችው ጀርመን በቼኮስሎቫኪያ 2ለ0 ተሸንፋ ዋንጫውን ተነጥቃለች፡፡ አርጀንቲና በዲያጎ ማራዶና ፊት አውራሪነት በ1991 እና በ1993 እኤአ የደቡብ አሜሪካ ሻምፒዮን ሆና በ1994 እኤአ በአሜሪካ ለተካሄደው የዓለም ዋንጫ ብትደርስም ከምድብ ማጣርያው ወድቃለች፡፡

በ1998 እኤአ የዓለም ዋንጫን በ200 እኤአ ደግሞ የአውሮፓ ዋንጫን አሸንፋ በ2002 ጃፓንና ኮርያ ባስተናገዱት የዓለም ዋንጣ የቀረበችው ፈረንሳይም ከምድብ ማጣርያ ለመሰናበት ግድ ሆኖባታል፡፡ በ2002 እኤአ የዓለም ዋንጫን አሸንፋ ከዚያም የደቡብ አሜሪካ ሻምፒዮን የሆነችው ብራዚል በ2006 እኤአ በተሳተፈችበት የዓለም ዋንጫ ለ3 ተከታታይ ድል ብትጠበቅም ሩጫዋ የተገታው በሩብ ፍፃሜ ነበር፡፡

=====

የአውሮፓ ዋንጫው ሲጀመር በስታድዬም ዘረኛ ስድብ ከገጠመኝ ሜዳውን ለቅቄ እወጣለሁ ከሜዳ ውጭ ደግሞ ሊሰድበኝ የሞከረን ሰው ገድዬ ወህኒ እገባለሁ ሲል የነበረው ማርዮ ባላቶሊ በጣሊያንም ተመሳሳይ የዘረኝነት ዘለፋዎችን ሲጋፈጥ ኖሯል፡፡ ጣሊያን በሩብ ፍፃሜ እንግሊዝን በመለያ ምቶች አሸንፋ ወደ ግማሽ ፍፃሜ ስትገባ ደግሞ በጣሊያኑ ትልቅ የስፖርት ሚዲያ ጋዜታ ዴሎ ስፖርት ላይ የወጣው የካርቱን ስእል ደግሞ ሰሞኑን አወዛጋቢ ሆኗል፡፡ የካርቱን ምስሉ ማርዮ ባላቶሊን በታዋቂው ፊልም ኪንግ ኮንግ ላይ ላይ ያለውን የጎሪላ ገፀባህርይ በመመሰል በለንደኑ የቢግ ቤን ታወር ላይ ተሰቅሎ ከየአቅጣጫው የሚመጡበትን ኳሶች ሲመታ የሚያሳይ ነበር፡፡ የማርዮ ባላቶሊ ኤጀንት በጋዜታ ዴሎ ስፖርት የወጣውን የካርቱን ምስል ከተቃወመ በኋላ በይፋ ይቅርታ የጠየቀው ጋዜጣው ካርቱኒስታችን ምስሉን በጣም ተጠብቦ ባላቶሊን ለማድነቅ የሰራው ነበር በሚል የደረሰበትን ትችት ሊያበርድ ሞክሯል፡፡

 

 

 

Read 2309 times Last modified on Saturday, 30 June 2012 11:22