Monday, 03 February 2020 11:44

“እናት ፓርቲ” በሴቶች የሚመራ ፓርቲ ይሆን?

Written by  (ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል)
Rate this item
(2 votes)

   የዛሬ 15 ቀን በወጣው የአዲስ አድማስ ጋዜጣ እትም ላይ “ወጣቱ የፖለቲከኞች መጠቀሚያ እንዳይሆን” በሚል ርእስ መጣጥፍ ማቅረቤ ይታወቃል፡፡ ያቺን መጣጥፍ ያነበቡ ሰዎች “በነካ ብዕርህ ስለ ሴቶች አንድ ነገር ብትልስ?” የሚል አስተያየት ልከውልኛል፡፡ ተገቢ አስተያየት መሆኑን ስላመንኩበት፣ በዚህ ሳምንት በማቀርባት በዚች አስተያየት ትኩረት የማደርገው በሴቶች ዙሪያ እንዲሆን ወደድኩ፡፡
ጽሑፌን የምጀምረው “በጥንታዊ የጋርዮሽ ስርዓተ ማህበር” የነበረውን ሁኔታ በወፍ በረር በማስታወስ ነው… በጥቅል አጠራር “ጥንት” በሚሰኘው ዘመን የሴቶች የበላይነት የገነነበት ወቅት እንደነበር “ተረት መሰል” መላምት ይነገራል፡፡ ያ ወቅት በብዙ ምሁራን “የእማዊ ዘመን” በሚል ስያሜ ይገለጻል:: በዚያ ዘመን ሴቶች ከእናትነት፣ ከልጅነትና ከሚስትነት ወግ ማዕረጋቸው በተጨማሪ የቤት ዋልታ ነበሩ፡፡ በ“እማ-ወራነት” የቤተሰብ መሪ ነበሩ:: የሚወልዷቸው ልጆች የሚጠሩትም በእናታቸው ስም ነበር - ያኔ፡፡ ሴቶች የቤተሰብን ብቻ ሳይሆን የማህበረሰብን የእለት ጉርስና የዓመት ቀለብ በማምረት ረገድ ከፍተኛ ድርሻ እንደነበራቸውም ይገመታል፡፡ የግብርናን ሙያ ቀድመው የተካኑት ሴቶች ስለ መሆናቸውም የሰውን ልጅ ታሪክ ያጠኑ ቀደምት ምሁራን ያስረዳሉ፡፡
ያ “የእማ-ወራነት” ዘመን አክትሞ እንስሳትን የማላመዱና የሴቶች የእርሻ ግኝት በወንዶች የመከናወኑ ሂደት ሲጎለብትና የወንዶች ተሳትፎ ከአዳኝነት ወደ አምራችነት (አራሽነት) ሲሸጋገር የሴቶች ሚና በቤት ውስጥ እየተወሰነና እየተዳከመ ይሄድ ጀመር ይላሉ ምሁራኑ፡፡ ልጅ ወልዶ የማሳደጉ ኃላፊነት እየጎላ ሲመጣና የቤተሰብ ቁጥር ሲጨምር በቤት ውስጥ የሚከናወነው ሥራ ጨመረ፡፡ በዚህም ሰበብ የሴቷ ወደ ውጭ የመውጣትና በአደባባይ የመዋል እድሏ ከእለት ወደ እለት ቀነሰ፡፡ በዋሻ ውስጥ መወሰኗ ይፋ ሆነ፡፡ አስተዳደራዊ ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚያዊና ማህበረሰባዊ ተሳትፎዋም ዝቅ አለ፡፡
በየጊዜው የሚገኘው ምርት ከእጅ ወደ አፍ የነበረውንና በአደንና በፍራፍሬ ለቀማ የተወሰነውን ህይወት ለውጦ ሀብት ማካበት ሲጀምር፤ ወንዱ ያጠራቀመውን ንብረት የሚያወርሰው በስሙ የሚጠራ ልጅ እንዲኖረው ፈለገ፡፡ ማህበረሰቡም አንዲት ሴት ለብዙ ወንዶች “ህጋዊ ሚስት” እንዳትሆን ወሰነ፡፡ የሰው ልጅ ያለው ሰብአዊ ክብርና ከእንስሳት የሚለይበት የእድገት ደረጃ ላይም ተደረሰ:: በዚህ መልኩ “የአባዊ ዘመን” እያስገመገመ መጣ፡፡ ወንድ የበላይነቱን ሲጨብጥ፤ እየጠበበ የመጣው የዋሻ በር በሴቷ ላይ ጨርሶ ተጠረቀመ፡፡ ከልጅ መውለድ በተጨማሪ ያለው የሴቷ የየእለት ተግባርም በምግብ ማብሰልና መሰል የቤት ውስጥ ሥራ ተወሰነ፡፡ ሰብአዊ ተሳትፎዋ በማጀት ቀረ፡፡
ዛሬ ዘመን ተለውጧል፡፡ ጊዜ ተሻሽሏል:: የሴቷ ሰብአዊ ተሳትፎ “ከዚህ እንዳያልፍ” ተብሎ ድካ የሚበጅለት፣ ወሰን የሚከለልለትና ድንበር የሚቸከልለት አልሆነም፡፡ ሴቷ ልጅ ወልዳ ማሳደግና አብስላ ማጉረስ ብቻ ሳይሆን ወንድ በተሰማራበት የሥራ መስክ ሁሉ ትሰማራለች፡፡ ለቤተሰቧ ተጨማሪ ገቢን ለማስገኘት ትታትራለች፡፡ ከዚህ አኳያ ቅን አሳቢዎች ሁሉ የሴቶችን እናትነት፣ እመቤትነትና ሰብአዊ ክብር ግምት ውስጥ በማስገባት ዙሪያ ሳይወሰኑ አጋርነታቸው እንዲያድግና ሁለገብ የሴቶች ተሳትፎ የሚጎለብትበት አጋጣሚ ሁሉ እንዲመቻች እየጣሩ መሆኑ ይስተዋላል፡፡ ይህ ቀናነት፣ ይህ መተሳሰብና መተጋገዝ አብቦ ሲያፈራ ማየት ስለ ስርዓተ-ፆታ ግንዛቤ ያለው ሰው ሁሉ ምኞት ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡
በዚህ ዘመን ያለን ሰዎች የምንኖርባት ዘመናዊቷ ዓለማችን በሳይንስና በቴክኖሎጂ ሽቅብ እየመጠቀች ነው፡፡ በዚያው ልክ ሥራ አጥነት ማስታገሻ እንኳ ያልተገኘለት የዓለማችን ራስ ምታት ሆኗል፡፡ የመንግስታት ፈተና ሆኗል፡፡ ለማመን በሚያስቸግር መልኩ እያደገ የመጣው የህዝብ ቁጥር፣ እየተመናመነ በመሄድ ላይ ያለው የተፈጥሮ ሀብትና የምድራችን የማስተናገድ አቅም፤ ካለንበት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውስ ጋር ተዳምሮ የመኖርን ተስፋ ከድጡ ወደ ማጡ እየጎተተው መሆኑን ማስተዋል ይቻላል፡፡ ይህንን ሁኔታ ያነሳሁት ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ይህንን ወደ ድህነት አረንቋ የሚደረግ መንደርደር ለመመከት የሚቻለው ሰዎች ሁሉ (የፆታ ልዩነት ሳይኖር) በሚያደርጉት ሁለገብ ተሳትፎና ትጋት መሆኑን ለማመላከት ነው፡፡
በየትኛውም ዓለም የሴቶች ቁጥር ከአጠቃላዩ ሀገራዊ የህዝብ ብዛት ከግማሽ እንደማያንስ በተለያዩ ሀገራት የተደረጉ የሕዝብ ቆጠራ ውጤቶች ያመለክታሉ፡፡ በእኛም ሀገር ተመሳሳይ ገጽታ ያለው የህዝብ ቁጥርና የፆታ ስብጥር መኖሩን ማስተዋል ይቻላል፡፡ እናም ይህ ግማሽ የሰው ኃይል በልማት ሥራ ላይ የሚያደርገው ተሳትፎ እጅግ ወሳኝ መሆኑ ይታመናል፡፡
በሀገራችን ሴቶችን በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ሊያሳትፍ የሚችል “ብሔራዊ የሴቶች ፖሊሲ ተቀርጿል” የሚለውን መረጃ ተደጋግሞ ሲነገር ሰምተናል፡፡ ሚኒስቴር መስሪያ ቤትም አለ፡፡ በተዋረድ በየክልሉ መዋቅር ተዘርግቶ የሴቶችን ተጠቃሚነትና ተሳታፊነት እንደሚከታተልም ይነገራል፡፡ ግን ምን ለውጥ ተገኘ? የሚለው ጥያቄ በወጉ መፈተሽ አለበት፡፡
በመሰረቱ  ሀገራችን እቅድ የማውጣት፣ ደንብና መመሪያን የማዘጋጀት፣ መስሪያ ቤት የማቋቋም ወዘተ. ችግር የለባትም፡፡ ዋነኛው ችግር እቅዱን ወደ ተግባር መለወጥ፣ መመሪያና ደንብን የማስፈጸም ነው፡፡ በተግባር የተተረጎመ ህልም፣ ፍሬ ያፈራ ራዕይ ግን እምብዛም ለውጤት በቅቶ አይታይም፡፡ እናም “ከህፃንነት ዘመኗ አንስቶ ሁለት ፀጉር እስክታወጣ ድረስ በጉሊት ገበያ ሀሩርና ቁር እየተፈራረቀባት የተከፈተ ጉሮሮን ለመዝጋት ቃሪያና ሽንኩርት፣ ድንችና ቲማቲም፣ ሰላጣና ጎመን፣… ለምትቸረችረው እናት/እህት/ልጅ ኑሮ መሻሻልና ለህይወቷ መቃናት የተቋቋመው የሴቶች ጉዳይ ሚኒስቴር መ/ቤት ምን ምን ተግባራትን አከናወነ?” የሚለው ጥያቄ ተደጋግሞ ሲነሳ ይደመጣል፡፡
አዎ! በሴቶች ስም በርካታ እርዳታ እንደሚሰበሰብ፣ ብዙ የፕሮጀክት ዓይነት እንደሚዘጋጅ፣ ወርክ ሾፕና ስልጠና እየተባለ ድግስና ሪሴፕሽን እንደሚዘወተርና የአስረሽ ምቺው ዳንኪራ እንደሚወረድ ይታወቃል:: የሴቶች ህይወት ግን ዛሬም ካለበት ንቅንቅ አላለም፡፡ ሴቶች ከጉሊት ተራ አልተለዩም፡፡ ከእንጀራ ጋገራና በየበረንዳው ቡና ከማፍላት አልተላቀቁም፡፡ ከኮብል ስቶን ፈለጣና ከባሬላ ተሸካሚነት አልወጡም፡፡ መቼ ይሆን የሴቶችን ህይወት የሚቀይር ሥራ የሚሰራው?
እንደኔ እንደኔ መፍትሄው ሴቶች የፖለቲካ ተሳትፏቸውን ከፍ በማድረግ የፖለቲካ ፓርቲ እስከ መመስረት ድረስ መጠናከራቸው ብቻ ነው! በዚህ ረገድ ሰሞኑን በተባራሪ ወሬ እየሰማነው ያለው በመቋቋም ላይ እንደሆነ የሚነገርለት “እናት ፓርቲ” በሴቶች አስተባባሪነት የሚቋቋምና በሴቶች የሚመራ ፓርቲ ነው? ከሆነ የሴቶችን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ለውጤት እንዲያበቃ አስፈላጊው ድጋፍና እገዛ ሊደረግለትና ሊበረታታ የሚገባው ነው እላለሁ፡፡
 ጸሐፊውን Email: This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡


Read 8706 times