Print this page
Monday, 03 February 2020 11:41

ኢትዮጵያዊ ንቃ፣ ድንቁርና ይብቃ!

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 “-- በቅድሚያ ማወቅ ያለበት ሐቅ ግን በዙሪያው ቆራጥና ጀግና አብሮ አደሮች እንዳሉ ነው፡፡ ከእነርሱ ጋር በመተባበር ዲሞክራሲን ማስረጽ ይጠበቅብናል። ዲሞክራሲ ከተዘፈቅንበት መሻኮትና መቆራቆዝ ያላቅቀናል፡፡ --”

             እግዚአብሔር ከሁሉም ፍጡራን አብልጦ ለሰዎች እውቀትና ፍቅር ሰጥቶናል፡፡ እውቀት ነገር ለመለየት ይጠቅማል፡፡ ፍቅር ተግባብቶ ለመኖር ይረዳል፡፡ የዘመኑ ስልጣኔ የሰረፀውም በእነዚህ ፀጋዎች እንደሆነ ይታሰባል፡፡ ተፈጥሮ ሚስጥር ነች፤ ተለዋዋጭ ነች፣ ዘላለማዊም ነች ይባላል፡፡ የለውጥ ምንጩ ፀሐይና ኮከቦች ውስጥ ያለው ሀይድሮጅን በከፍተኛ ሙቀት ሲቃጠል የሚሰርፀው ጨረር (ኢነርጂ) እንደሆነ ይታመናል፡፡ አንዳንድ ሰዎች ግን ለውጥ የሚመጣው በጊዜ ተፅእኖ ይመስላቸዋል፡፡ እናም “አወይ ጊዜ” እያሉ ያንጐራጉራሉ፡፡ ጨረር ቁስ አካልን እየወዘወዘ ይቀያይረዋል፡፡ ውሁዶች ይፈጥራል ያፈርሳል፣ ሕይወትም ይገነባል፡፡
እኛ ሰዎች ስንሞት ገነት ለመግባት እንመኛለን፡፡ ከሞት በፊት ግን የሕይወትን ፀጋ በደንብ ብናጣጥመው ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ሕይወት ልዩ የተፈጥሮ ፀጋ ናት፡፡ ራሷን በራሷ ታውቃለች፣ ነገር ትለያለች፣ ምግብ እየበላች፣ ቆሻሻ እያስወገደች፣ እየተዋለደች ትዘልቃለች፣ ትንሽ ቆይታም ትከስማለች፡፡ ከሞት በኋላ ስለ ጽድቅ ወይም ኩነኔ ከማሰባችን በፊት ግን “በእጅ የያዙትን ወርቅ ላለመጣል” ብለን ሕልውናን ለማዝለቅ ብንጥር ትክክል ይመስለኛል:: ብቃቱም አለን፤ ከእግዜር ተሰጥቶናል፡፡ በዚች ምድር ብዙ ዓይነት ፍጡር አለ፡፡ አንዱ የሚለያዩበት ነገር እድሜ ነው፡፡ ዝንብ አንድ ቀን ትኖራለች፣ ውሻ 25 ዓመት፣ ኤሊ 200፣ ሰኮያ ዛፍ 4600 (አሜሪካ)፣ ሌላ ዓይነት ዛፍ (ደ/አፍሪካ) 6000 ዓመት ይኖራሉ ይባላል፡፡ ይህ የሕይወት ፀጋ ነው፡፡ በሰው ዘንድ ፀጋውን ብናዳብረው የበለጠ ተጠቃሚ እንሆናለን፡፡ ከዚያ በኋላ ብንፀድቅ ደግሞ ድርብ ፀጋ ይሆናል ማለት ነው፡፡ አምላክ መቼም ዝም ብላችሁ ሙቱ የሚል አይመስለኝም፡፡ ፍጡራን እድሜያችን የተለያየው እንደ ብቃታችን ሊሆን ይችላል፡፡
በዚች ተፈጥሮ አምላክ ራሱ ለዘላለም እንዴት እንደሚኖር ግራ ይገባል፡፡ እኛ ሰዎች አንድ ነገር ደጋግመን ስናደርግ ይሰለቸናል:: ማር እንኳን ሲደጋገም “ቋቅ ይላል” ይባላል:: እኛ ይህን ስሜት የምናንፀባርቀው በውዴታ ሳይሆን ተፈጥሯዊ ስለሆነ ነው፡፡ አምላክ ኑሮው “ቋቅ” እንዳይለው ምን ይሆን የሚያደርገው? ምናልባት በእለታዊው ለውጥ ውስጥ አብሮ ይለዋወጥ ይሆን?
የኛ እድሜ ምጥን ነው፡፡ በጊዜ ሒደት ነገር ስለሚቀያየር ደግሞ ፍጡርም ይቀያየራል ይባላል፡፡ በአለፈው 4½ ቢሊየን የሕይወት ዓመት ብዙ ዓይነት ፍጡራን ሰርፀዋል፣ አብዛኛው ግን ከስመዋል ይባላል፡፡ ጨረር ሲጠፋ ሕይወት ራሱ እንደሚከስም ይታሰባል፡፡ እውቀት ካለንና እስከዚያም ድረስ ከዘለቅን ሒደቱን መከታተል ይቻል ይሆናል፡፡ በእውቀት ግን ውሱን ነን፡፡ ስለ ውሱንነታችን ለማወቅ ለምሳሌ አንዱን ተራ ዜጋ ድንጋይ ከመሬት አንስተን፣ ይህ ምንድነው? ብንለው ድንጋይ ነው ይለናል፡፡ ድንጋይ ምንድነው? ካልነው ደግሞ “ድንጋይ ነዋ” ነው የሚለን፡፡ ስለ ድንጋይ ያለን እውቀት እዚህ ላይ አበቃ ማለት ነው፡፡ ስለ አምላክም ያለን እውቀት ተመሳሳይ ሊሆን ይችላል፡፡
ስለ ፍቅር ያለን ግንዛቤ ፈሩን ሳይለቅ አይቀርም፡፡ ፍቅር በሰው ዘንድ የሰረፀው በሴትና ወንድ ግንኙነት እንደሆነ ይታሰባል፡፡ ዓላማውም ረጅም እንክብካቤ የሚፈልገውን ሕፃን ልጃችንን ለአቅመ - መዋለድ ለማድረስ እንደሆነ ይነገራል:: አንዳንድ ሰዎች ለልጆች ፍቅር ስጧቸው ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ ፍቅር እንደ ብር ለሰው አይሰጥም:: በፍቅር ያደገ ልጅ ግን ከቤተሰቡ ይወርሳል፡፡ ሰው ይወዳል፣ ከሰው ይግባባል፣ የጋራ ችግርን ለመወጣትም ይተባበራል፡፡ በአንፃሩ ፍቅር ያጣ ልጅ ሰው አይወድም፤ ከሰው አይግባባም፣ አይተባበርም፡፡ እንዲያውም ማሕበረሰቡን ለመጉዳት በቀል ያደርጋል ይባላል፡፡ እናም ሰላማዊ ኑሮ ለመቋደስ በፍቅር መጋባትና ልጅን ተንከባክቦ ማሳደግ ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡
የፍቅር ዓላማው ቢገባን ኖሮ የክርስቶስን ትምህርት ተከትለን፣ ሴትና ወንድ በፍቅር አንድ ለአንድ ተወስነን እንኖር ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ የልጅ ብዛትንና የምርት መጠንን ማጣጣም ያስፈልጋል፡፡ እንደሚታወቀው መዋለድና ማምረት እኩል አይሄዱም፡፡ መዋለድ ፈጣን፣ ማምረት ግን ዘገምተኛ ነው:: ሕዝብ ሲበዛ ደግሞ ትርፉ ድህነት፣ የተፈጥሮ ሀብት ብክነትና የእርስ በርስ ግጭት እንደሆነ ይታወቃል:: ይህን ሒደት ባለማወቃችን አለገደብ እየተባዛን ድህነትን ተከናንበን፣ እርስ በርስ እየተጋጨን እንኖራለን፡፡ የችግሩ መፍትሔ (ከ1-2 ልጅ በቤተሰብ መውለድ) በሰለጠኑ ሀገሮች ቢታወቅም፣ እኛ ግን በአጉል ባህል ተተብትበን መኮረጅ እንኳን ተቸግረናል:: መሪዎቻችንም ስለ ሕዝብ ብዛት ትንፍሽ አይሉም፡፡ ይህን የግጭት ምንጭ ካልፈቱልን እንዴት ሰላምና መረጋጋት ያመጡልናል? ከድሮ መሪዎቻችንስ በምንድነው የሚለዩት?
እኛ ኢትዮጵያውያን በረጅም የአብሮነት ታሪካችን፣ እርስ በርስ በእጅጉ ተካሰናል፡፡ የግራኝ አህመድ ወረራ፣ የኦሮሞ ፍልሰት፣ የአፄ ምኒልክ ግዛት ማስፋፋትና የአድዋ ጦርነት ድል እንዲሁም የአፄ ኃይለስላሴና የደርግ የአንድነት አስተዳደር፤ በዚህ አቅጣጫ ጥሩ አስተዋጽኦ እንዳደረጉ ይታወቃል፡፡ ሆኖም ግን በሕወሓት ከፋፋይነት እንዲሁም በጊዜ ሒደት፣ የሕዝብ ብዛትና የኑሮ ፍላጐት ባለመጣጣሙ፣ እውቀትና ፍቅር የጐደላቸው “እንግዴ ልጆች” በሚቀሰቅሱት ነገር ግንኙነታችን እየሻከረ መጥቷል፡፡
እንደ ማሕብረተሰብ ስንኖር ማወቅ ያለብን ጉዳይ፣ በፍጡራን መካከል ስለሚከሰተው ሽሚያ ነው፡፡ የባዮሎጂ ሊቆች እንደሚሉን፤ ፍጡር ሁሉ ለምግብና ውሃ፣ ለፍቅርና ለቦታ ወዘተ… እርስ በርሱ ይሻማል ይሻኮታል፡፡ ሽሚያው ደግሞ በቅርብ ዘመዳሞች መካከል ይግላል ይባላል፡፡ ይህም ማለት በሰው ዘንድ ወንድም ከወንድሙ፣ እህት ከእህቷ፤ የበለጠ ይሻኮታሉ ማለት ነው፡፡ እኛ ሰዎች በዚች ምድር ስንኖር ደግሞ ዋና ፀጋ ብለን የምናስበው ተወልደንና አድገን፣ ልጆች ወልደንና አሳድገን ማለፍን ነው፡፡ ታድያ ይህን ምኞት እንዴት ልናሳካው እንችላለን? ለዚህ ችግር ግልጽ መፍትሔው ዲሞክራሲ ወይም የእኩልነትና የነፃነት ስርዓት ነው፡፡ እኩልነት አንድነትን ያጠናክራል፣ ምርታማነትንና ራስ መቻልን ያበለፅጋል፡፡ ነፃነት፤ ግልፅ ያልሆነችውን ተፈጥሮ በአግባቡ እየዳሰስን እንድናውቃትና እንድንጠቀምባት፣ የእርስ በርስ ግንኙነታችንንም በእውነተኛ መንገድ እንድናሰርፅ ይጠቅመናል:: በጥቅም ምክንያት የሚደርስ ግጭትን ደግሞ የፍትሕ አካሉ (ፍርድ ቤት) ይፈታዋል፡፡ ቂም በቀል ግን አይኖርም፡፡
እኛ በባህላችን የለመድነው ስርዓት የበላይነት ወይም ሌሎችን መግዛት ነው፡፡ ገዢው አካል የኑሮ ፍላጐቱን በሌሎች ጉልበትና ልፋት ያሳካል:: በዚህ ስርዓት ለረጅም ጊዜ ስለቆየን በግልጽ ያካበትናቸው ባህሪዎች ውሸት፣ ማታለል፣ ማስመሰል፣ መስረቅ፣ መንጠቅ፣ መክላትና ቂም በቀል ናቸው፡፡ ባህሪዎቹ በማንኛውም ዓይነት ግንኙነታችን (ለምሳሌ፡- በምርት፣ በንግድ፣ በፍቅር፣ በሀዘን፣ በጦርነት ወዘተ…) በግልጽ ይንፀባረቃሉ፡፡ ችግሮቹ በተለይ በፍቅር፣ በጦርነት፣ በሀዘን ወዘተ-- ላይ ሲንፀባረቁ የበለጠ ይመርራሉ፡፡ በዚህ ዓይነት ጉዞ ለረጅም ጊዜ ስንገጫገጭ በመቆየታችን ከስልጣኔ ጎዳና ከሞላ ጎደል ወጥተናል። ምክንያቱም ስልጣኔ የሚሰርፀው እውነትና መልካም ግንኙነት ሲኖር ነው፡፡
እንስት እንደ አንዳንድ ወንድ ‹‹እውነትን ተናግሮ እመሸበት ማደር›› እምብዛም አትልም ይባላል፡፡ እንደ ሁኔታው ግን ታድራለች:: ልጅ ወልዳ ተንከባክባ በማሳደግ ደግሞ ስኬታማ እንደሆነች ይታወቃል፡፡ ዘመኑ ለነጋዴ ይመቻል፤ ከሰለጠኑ አገሮች የኢንዱስትሪ ውጤቶች ይጎርፍለታል፡፡ ነጋዴው ግን ጥሩ ያልሆነውን እቃ ጥሩ ነው እያለ፣ ከዋጋው በላይ እያስከፈለ ይበዘብዘናል፡፡ በእንቡጥ ሴቶችም እያማለለ ያታልለናል፡፡ ጥሩ ሰው ለመምሰል ግን የማያደርገው  የለም፡፡ በአለባበሱና በአነጋገሩ ቅዱስ ይመስላል፡፡ ለድሆች ይመፀውታል። በእምነት ቤት ዙሪያም ሽር ጉድ ሲል ይታያል:: ድርጊቱ ግን እኛን ብቻ ሳይሆን ራሱ አምላክንም ጭምር እንደ ማታለል ይቆጠራል:: በድንቁርናችን በተዘፈቅንበት የበላይነት ሥርዓት እነሆ በፍሬቢስ ግንኙነት ዘወትር እንታመሳለን፡፡ ስርዓቱ ልዩ የተፈጥሮ ፀጋ የሆነችውን ሕይወታችንን ከእነ ጭራሹ እንዳያሳጣን ያሳስባል፡፡
ኢትዮጵያዊነት የሰፈነው በጥቂት አርቆ አሳቢ ገዢዎቻችንና የአንድነቱ ጥቅም በገባቸው ንቁ ብሔር ብሔረሰቦች ትብብር ይመስለኛል፡፡ በቅድሚያ አፄ ቴዎድሮስ ተበታትኖ የቆየውን የመሳፍንት ግዛት በወቅቱ አሰባሰቡት፡፡ ብልሁ አፄ ምኒልክ የአንድነት በትሩን ከአፄ ቴዎድሮስ ወርሰው ግዛቶችን አስፋፍተውና ሕዝቡን አስተባብረው፣
የኢጣሊያን የቅኝ ግዛት ጦርነት አድዋ ላይ መክተን፣ ከባርነት እንድንድን በቆራጥነት መርተውናል፡፡ በአሁኑ ዘመን ደግሞ ተመሳሳይ ችግር እየመጣ ሳይሆን አይቀርም፡፡ በአለም ደረጃ በካርቦን ልቀት ምክንያት የአየር ሙቀት እየጨመረ መጥቷል፡፡
ዝናብ በዝቷል፣ በየዋልታው ያለው በረዶ ይቀልጣል፤ የባህር ወለልም እያደገ ነው፡፡ ችግሩ እየተባባሰ ከሄደ የአንዳንድ የሰለጠኑ አገሮች መሬት በውሃ ስለሚሸረሸር፣ ውድ አገራችንን እናት ኢትዮጵያን በከፍታ ቦታነቷ ምናልባት ለቅኝ ግዛት ያጯት ይሆን? ማን ያውቃል? ለማንኛውም ጊዜው አሳሳቢ ነው:: ሕብረታችንን እንደ ልማዳችን አጠናክረን፣ የአድዋን ድል እንደገና መድገም ያስፈልገን ይሆናል፡፡
አሁን ‹‹ተረኛ›› መጥቷል ይባላል፡፡ ተረኛ የመጣው ለመግዛት ይሆን? መግዛት ረሀብንና ጥማትን ለጊዜው ያስታግስ እንደሆነ እንጂ ለዘለቄታው አያዋጣም:: በታሪካችን ገዢዎቻችን ሁሉ (ንጉሶች፣ ወታደሮች፣ ታጋዮች) ለጊዜው አለሁ አለሁ ቢሉም በስተመጨረሻ ግን ፈርሰዋል:: እኛንም ረግጠውናል፡፡ ተረኛው፤ አፍራሽነትን ትቶ ‹‹ኢትዮጵያዊነት›› ላይ ቢያተኩርና የራሱን የለውጥ አሻራ ቢያሳርፍ ለሁላችንም ይጠቅመናል፡፡ በቅድሚያ ማወቅ ያለበት ሐቅ ግን በዙሪያው ቆራጥና ጀግና አብሮ አደሮች እንዳሉ ነው፡፡ ከእነርሱ ጋር በመተባበር ዲሞክራሲን ማስረጽ ይጠበቅብናል። ዲሞክራሲ ከተዘፈቅንበት መሻኮትና መቆራቆዝ ያላቅቀናል::
ተረጋግቶ በመኖር ስልጣኔ ይሰርጻል:: በሒደቱም 1/ ለኑሮ አስፈላጊ የሆኑትን ምግብ፣ ውሃ፣ እቃና ልብስ ማምረት ወይም ማቅረብ 2/ ከሰውነት ከቤትና ከስራ ቦታ የሚወጣውን ቆሻሻ በአግባቡ ማስወገድ 3/ በጀርም የሚመጡ በሽታዎችን እንዲሁም ተውሳኮችን መከላከል 4/ የኑሮ ተቀናቃኝን በዘመናዊ ዘዴ መመከት ያስችላል:: በአንድ በኩል፣ ስልጣኔ ሊሰርጽ በሌላ በኩል ደግሞ ችግርም ይከማች ይሆናል:: ችግር ሲበዛም ስልጣኔው ይሰናከላል:: ታሪክ እንደሚናገረው፤ ብዙ ስልጣኔዎች ከስመዋል፡፡ አሁን ከተረኛው የምንፈልገው ቁም ነገር፣ ስልጣኔን ተንቀሳቅሶ ከመኖር ጋር እንዲያዛምድልን ነው፡፡ እንደሚታወቀው፤ በተፈጥሮ ሁሉም ነገር ይንቀሳቀሳል ይባላል:: በሰው ዘንድ ደግሞ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ ሰውነትን ያፍታታል፤ ሕሊናንም ያድሳል:: በመንቀሳቀስ የሕዝቦች ግንኙነት ይሻሻላል፣ ስልጣኔውም እያደር ይታደሳል፡፡ ዘዴው አዲስ ነው፤ እንሞክረው፡፡ በእንቅስቃሴ ባሕላችን ሕልውናችንን እናድስ!!
እናት ኢትዮጵያ በስኬት ትገስግስ!!    

Read 2502 times
Administrator

Latest from Administrator