Saturday, 30 June 2012 11:07

“ትኩስ ድንች አንወራወር!”

Written by  ነቢይ መኮንን
Rate this item
(0 votes)

አዋሳ ለተመሳሳይ ዓላማ ከጄክዶ (ኢህማልድ) ጋር ሄጄ ከኦያሲስ ሆቴል በመስኮት ያየሁዋትን አረንጓዴ አዋሳ ለማስታወስ የሚከተለውን ግጥም ፅፌ ነበር፡፡ ድሬዳዋንም በዚያ ዐይኔ አይቻታለሁ!!

ተራህን ፍጠራት

መከነች … ነጠፈች

ደረቀች … ተዛባች

ጎረፈች … ተናደች፣ ወይ በረዶ ዋጣት

ውሃ አጥለቀለቃት … እሳት ገሞር በላት

እያልክ የለት ዜና፣ … ከምትጠርቅባት

ልሣንህን ዘግተህ፣ ጡንቻህን አሳያት

ውበቷን አስበህ

ዐይኗን ባይንህ አይተህ

አዕምሮህን ከፍተህ

ተፈጥሮን ዕቀፋት!

ብታምንም ባታምንም፤ እናትህ እሷ ናት!

አንዴ ፈጥራሃለች፣ ተራህን ፍጠራት!

ለልጅህ አቆያት!

(ለአዋሳ ጥረት፣ ለሙሌና ለእኔ)

 

ከሆቴሉ ወጥቼ ሻይ ቡና እያልኩ ልቆዝም አንዲት ትንሽ መሸታ ቤት ተቀምጬ፣ አንድ አዛውንት ለማኝ መጡ፡፡

“የለበሱት ያልቃል

የሰጡት ያጠድቃል” አሉና ለመኑኝ፡፡ ልስጣቸው አልስጣቸው ሳልወስን ቀና ብዬ ሳያቸው፤ ያንድ አፍንጫቸውን ቀዳዳ በአንድ አውራ ጣታቸው ከድነው “እንፍ” ብለው ተናፈጡና መንገድ ቀጠሉ፡፡ “የለማኙ ነገር” የምትለው ግጥሜ በዚች ቅፅበት ተወለደች!

የለማኙ ነገር

አዛውንቱ ለማኝ

“የለበሱት ያልቃል

የሰጡት ያጠድቃል”

ሲሉ ሰማሁዋቸው

ዕውነት ነው ልብስማ፣ ከለበሱት ያልቃል

ለማኙም ሲጠቅቀሰው፣ ቃሉ ሆድ ያባባል

ማለቅ ያሳዝናል፣ ያራራም ይሆናል!

የሰጡት ማፅደቁ፣ ግን ያጠራጥራል

ምነው ለምን ቢባል?

ለዚህ የምንሰጠው፣ ከዚያ ነጥቀን እንደሁ፤

በምን ይታወቃል?

ይህን ልመራመር፣ ገና ሳብሰለስል

አንድ ሀሳብ መጣና፣ ገላገለኝ በውል፡፡

“አልመፀወትካቸው፣ ሣንቲም አላወጣህ

ቢያፀድቅ ባያፀድቅ፣ አንተ ምን አገባህ?!

ወቸ ጉድ! አሁን ለኒህ ለማኝ

ይህ ቢሆን ያ ቢሆን፣ ብዬ ባስረዳቸው

የኔ ፍልስፍና፣ ዳቦ አይሆንላቸው?

ምነው ፈጠን ብዬ የእጄን ብሰጣቸው?”

ብዬ ተፀፀትኩኝ !

እንቅልፌ ሲመጣ፣ ሳልፀልይ ለጥ አልኩኝ!!

ግንቦት 16 2004

(ለምንለምን ሁሉ)

 

“አሪፍ ያለው ህዝብ ውስጥ ነው!”

“ገመድ ጉተታና ልማት አብሮ አይሄድም!”

መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሦስት ዓይነት ናቸው ወይም አንድም ሶስትም ናቸው፡-

ወይ Missionary (ሚሲዮናዊ)

ወይ Mercenary (ቅጥረኛዊ)

ወይ Visionary (ራዕያዊ)”

- ከተሳታፊዎች አንደበት

***

በነጋታው ወደ ኢየሩሳሌም ህፃናትና ማኅበረሰብ ልማት ድርጅት የሄድነው ስብሰባው በሚጀመርበት ሰዓት ነው፡፡

ወደ ቢሮው አዳራሽ መግቢያ ላይ የፎቶግራፍ ኤግዚቢሽን አለ፡-

የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ፣ መደበኛ ትምህርት ማጠናከሪያ (Tutorial)፣ የጤና ጥበቃ፣ የመንገድ ደህንነት ሥልጠና፣ የአየር ንብረት ለውጥ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት እና የአካባቢ ጥበቃ በሚሉ ጥቃቅን ርዕሶች ሥር የተቀመጡ ልዩ ልዩ ፎቶግራፎችን አየሁ፡፡

በጎሮና ቡቲጂ ሁለገብ ኃላፊነቱ የተወሰነ የህብረት ሥራ ማህበርና በኢየሩሳሌም ህፃናት ማህበረሰብ ልማት ድርጅት (ኢህልማድ) መካከል የሚደረገው የፕሮጀክት ርክክብ ሥነ ስርዓት ሊከናወን ነው፡፡ ቤቱ ጢም ብሎ ሞልቷል፡፡

ሲስተር ትዕግሥት የፕሮግራሙን መጀመር ካሳወቀች በኋላ የኢየሩሳሌም ህፃናትና ማህበረሰብ ልማት ድርጅትና የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ቢሮ ሥራ አስኪያጅ አቶ አበበ መኰንን ጋበዘች፡፡ አቤ እንደተለመደው በፓወር ፖይንት (ማሣያ ሰሌዳ) እየታገዘ የበሰለ ዕውቀት ይሰጠን ጀመር፡፡

አቤን ከዚህ ቀደም ሳገኘው የሚገርም ዓይነት ክስተት ነበር የተፈጠረው፡፡ እኔንና የኢየሩሳሌም ህፃናትና ማህበረሰብ ልማት ድርጅት ዋና መ/ቤት አባል የሆነውን ሰው ከኤርፖርት የተቀበለን አቤ ነበር፡፡ ጥቂት ካረፍን በኋላ ወደ አቤ ቢሮ ሄድኩኝ፡፡ አቤ እንደ አበሻ ሥራ አስኪያጅ ሁሉ ግራፉ፣ ዶክመንቶችና፣ የቪዲዮ ምስሎችን ሁሉ፤ ታጥቆ፤ “ይሄን ካዲሳባ የመጣ ጋዜጠኛ በደምብ አስረዳዋለሁ” ብሎ ተዘጋጅቶልኛል፡፡ “አበበ መኮንን እባላለሁ፡፡ ስለድርጅታችን ምን ለማወቅ ትፈልጋለህ?” አለኝ፡፡ “ምን መሰለህ አቤ፤ እንዳየሁህ የመከላከያ (ማብራሪያ) መሣሪያዎችህን ሁሉ ይዘህ፤ በዶክመንትና በሠንጠረዥ የተደገፈ ከባድ ኢንተርቪው ልትሰጥ መሰለኝ የተዘጋጀኸው፡፡ ችግሩ ግን እኔ መደበኛውን (Formal) ቃለ መጠይቅ ላደርግልህ አልመጣሁም፡፡ የአንድ ድርጅት ህልውናም ሆነ የሥራ ባህሪ ያለው መሬት ላይ ነው፡፡ ህዝቡ ጋ ነው፡፡ ስለዚህ ሰው ሰው የሚሸት ነገር እንዳይ፤ እንድሰማና እንዳሸት፤ አድርገኝ - Impress me!” አልኩት፡፡

ላፕቶፑን አጥፎ፣ ዶክመንቶቹን በየሰገባቸው ከቶ፤ “በል ና መኪና ውስጥ ግባ” ብሎ ሾፈረኝ - የድሬዳዋ ጐርፍ ወደ ሸረሸረው ጋራ! ወደ አፈሩ! መሬት ወዳለው ገበሬ! ተመቸኝ! ብዙ ትምህርት ቀሰምኩ! የአንድን ህዝብ ልማት ጥፋቱን ለማየትና አንድ ከህዝብ ጋር የሚሠራ ድርጅት ከልቡ መሆን አለመሆኑን ለመለየት፤ አፈሩን ማሽተት ያስፈልጋል! ጋራው ሲያነባ የፈጠረውን ተርተር አይቶ መፍረድ ይጠይቃል፡፡ “ከንፈር ከሌለ ምራቅ አይሰበሰብም - ለዚህ ነው እርከን የምንሠራው” ያሉኝን የትግራይ ገበሬ አስታወሰኝ የጋራው ላይ እርከን፡፡

ዛሬ በርክክብ ሥርዓቱ ላይ አቤ የሚገልፅልን የድርጅቱን የአምስት ዓመት ስትራቴጂ የሥራ ፍሬ ነው! ደስ ይላል አገላለፁ፡፡ ጉዳዩን እንደ እጁ መዳፍ ነው የሚያውቀው፡፡

“በአምስት ዋና ዋና ከተሞች የልማት ሥራ ሠርተናል በኦሮሚያ፣ በአማራ ክልል፣ በደቡብ ክልል ውስጥ!

ችግሮችን ለመፍታት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ማበረሰቦችን መንከባከብ፣ ኑሮ እንዲቀላቸው ማድረግ ነው ሥራችን፡፡

የማይላቀቁት ዕቅድ (Inevitable Plan) መቅረፅ

ማስገንዘብ፡- ማብሰል፣ መቅረፅ፣ መተግበር፣ አቅም መገንባት፣ የተማከለ መፍትሔ መስጠት ነው ዋና ተግባራችን ይላል፡፡ የሴቶችና ህፃናት ነገር፣ የትምህርት፣ የጤና፣ የመፀዳጃ፣ የመንገድ ወዘተ. እጭቅ ችግሮችን መፍታት! ዘርፈ-ብዙ ምላሽ መስጠት!

አቅምና ጊዜ ካልተቀዳጀ ልማት የለም ይላል አቤ፡፡

የሾቀውን ህብረተሰብ ማገዝ የኢላማችን ማነጣጠሪያ ነው!

ለአንድ ቤተሰብ መሀለቅ ማለትም እስከ 2000 ብር በመስጠት ነገ ተተኪ የሆነ ተሽከርካሪ ገንዘብ እንሰጣለን!

ሥልጠና መስጠትና መሀለቅ መስጠት ለእኛ አንድ ነው!

የእኛ ዋንኛ መርህ፡-

“ሲመቱ መጮህ ሳይሆን፣ ሳይመቱ መሸሽ! ነው” በዚያ ላይ፤ “ጥሩ ተመክሮ ከትንሽ መንደር እንደሚነሳ እናውቃለን!”

የከተማ ግብርና ምርጥ የስትራቴጂ አማራጭ ነው (Best alternative Strategy)

መንግሥት ቦታ ሰጥቶን በከተማ ግብርና ተዓምር እንሰራለን ብለን እናምናለን!

መርሆአችን፡-

ሀ. ንቃት - አዘል

ለ. ግንዛቤ - ገብ እና

ሐ. ግብ - ተኮር

ተደርጎ የተቀረፀ ነው፡፡ 4,300 ተማሪዎች የልምምድ/የማጠናከሪያ ትምህርት፣ በ8 ክፍሎች እንሰጣለን፡፡ ልማት ማለት የነዚህ ተማሪዎች አንደኛ መውጣት ነው - በዐይናችን አይተነዋልና ምሥክር ነን!

የካሳቫ ቴክኖሎጂን ማስፋፋት አንዱ ትልቁ ሥራችን ነው፡፡”

ይገርማል! አቤ ሲያወራ የሚያነብ እንጂ የመጣለትን የሚናገር አይመስልም፡፡ የሀሳቡ ስምረትና ፍሰት፣ ነገርን ቅልል አድርጎ የማቅረቡ ክህሎት ሲታይ፤ እንኳን አሰልቺውን የ5 ዓመት ስትራቴጂክ ሪፖርት እጅግ የሚያዝናና ቀልድም እንዲህ አያምርም! ከደሰኮሩ አይቀር እንዲህ ነው እንጂ ያሰኛል! ዱሮ የቃል-ጥናት ጎበዝ ነው የሚባልን ተማሪ ለማድነቅ “ትምህርቷን ፉት ይላታል!” እንደምንለው ማለት ነው!

አንኳር አንኳሮቹን ማራኪ አባባሎቹን ልጥቀስላችሁ!

“ድርጅታችን Hit and Run” ዓይነት አይደለም፡፡ ጠቅ ጠቅ አድርጎ እልም ማለት አያውቅም! የጎሮ ማህበር ደግሞ በባህሪው ዕውነት ያልሆነ ነገር የማይቀበል ማህበር ነው፡፡ `ዕውሸት ከ4 ሰዓት በላይ አይቆይም!` የሚል የኦሮሞ ተረት አለ፡፡ ያ የገባው ነው የጎሮ ማህበር!

እኛ ድርጅታችንን አሪፍ ድርጅት ነው አንልም! አሪፍ ያለው ህዝብ ውስጥ ነው!” ሥራውን የሚሠራውን ሰው ሥራው” ይላሉ ፈረንጆች! መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ገንዘብ (የNGO መሀለቅ) የጠፍ ገንዘብ አይደለም! ከመንግሥት፣ ከመንግሥታዊ ድርጅትና ከፈንድ የመጣን መሀለቅ አንድ ፖስታ ውስጥ ያለ ገንዘብ አድርገን ነው የምናየው!

ልማትን ተሸሽቶ የትም አይደረስም!

ለመስቀል የደነቆረ በጥምቀት እዮሃ አበባዬ ይላል! የያዝነውን መልቀቅ አለመቻል አንዱ ፈተናችን ነበር! የግንዛቤ ማነስ፣ የህጋዊነት ችግር፣ የሹሞች መቀያየር ወዘተ.. ሲታሰብ ያለብን ችግር ከምናየው በላይ መሆኑን እናስተውላለን! ሥራ በትብብር እንጂ በገንዘብ ኃይል ብቻ አይሄድም! የሹሞች መቀያየር የሚቸግረው፤ አንዱ ሲቀየር ጅኒ ሌላው ሲመጣ ፍቅር እየሆነብን ነው!” አለ አቤ፡፡ ጢቅ ያለ ዕውቀቱን በአማረ አንደበቱ እጭቅ አርጎ ነግሮን አመስግኖን አበቃ! አጨበጨብንለት!

የጎሮና ቡቲጂ ሁለገብ ኃላፊነቱ የተወሰነ የህብረት ሥራ ማህበር ሊቀመንበር አቶ ግዑሽ ገ/እግዚዕ ነው ቀጥሎ የቀረበው፡ ድርጅቱን አመስግኖ፤ ያለውን ቆራጥ አቋም ገልጦ፣ ያለችግር ማህበሩ እዚህ እንዳልደረሰ አስረዳ!

ብዙ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን አልፈናል! ዋና እገዛ ያደረገልን ጄክዶ ነው፡፡ ዋናው ሀብታችን የህብረተሰባችንን ዝቅ ያለ ግንዛቤ ማሻሻል ነው! ድርጅቱ ይህንን አስተምሮናል፡፡ ምን መሥራት እንዳለብን መስመሩን አስጨብጦናል፡፡ ሀብታችንን እንድንጠቀምና ተፈጥሮን እንድንለውጥ ትልቅ እርዳታ አድርጎልናል፡፡ በጤና በኩል፡ በትምህርት በኩል፣ በአካባቢ ጥበቃ በኩልም አግዞናል፡፡ ለዚህ ለዛሬ ቀን በመብቃታችንና ህዝባችንን የሀብቱ ባለቤት ሆኖ በማየቴ ትልቅ ደስታ ይሰማኛል! ድጋፋችሁ አይለየን እንጂ እኛም አደራችንን ተቀብለን ያለ ጥርጥር ኃላፊነታችንን እንወጣለን! (ተጨበጨበ)

የሻይ እረፍት ሲሆን አንድ ፎጠናና አንደበተ-ቀና ልጅ (elegant and eloquent) አግኝቼ አነጋገርኩ! ወንድዬ ሙሉጌታ ይባላል፡፡ የልማቱ ነገረ-ሥራ የገባው ነው-በእኔ ሚዛን!

ይሄ ልጅ ትክክለኛ የቢሮ ማዕረጉ የክልሉ የፋናይንስና ኢኮኖሚ ቢሮ የውጪ ሀብትና ዝግጅት አስተዳደር ዋና ሥራ ሂደት ከፍተኛ ኤክስፐርት ነው፡፡ (እንደ ጓድ ሊቀመንበር ረጅም ነው ማዕረጉ፡፡ ሥራቸው ግን ለየቅል ነው - ያ ጥፋት! ይሄ ልፋት! አልኩኝ በሆዴ)

ከጎሮና ቡቲጂ ማህበር ጋር ያለውን ግንኙት ሲገልፅልኝ፡-

“የጎሮና ቡቲጂ ማህበር የጄክዶ ፕሮጀክት ተጠቃሚ በመሆን ራሱን አብቅቶ ማህበረሰቡን ለማቀፍ የቻለ ማህበር ነው፡፡ እኛ ደሞ በፋይናንስና ኢኮኖሚው የውጪ ሀብትን የምናስተዳደርና የምንቆጣጠር እንደመሆናችን፤ በአዋጅ 621 መሠረት አጠቃላይ ድጋፍና ክትትሎችን ስለምናደርግ ህብረተሰቡ የራሱ ልማት ተጠቃሚ መሆኑን በሚያረጋግጠው በዛሬው የርክክብ ቀን ተገናኝተናል፡፡”

“ማህበሩ Sustainable (ዘላቂ) የሚሆን ይመስልሃል ወይ?” አልኩት፡፡

“ነቢይ ይሄ ወሳኝና ተገቢ ጥያቄ ነው” ብሎ ጀመረ፡፡ “ትልቁ ተግባራችን የህብረተሰቡ የታችኛው ክፍል በልማቱ ተሳታፊ እንዲሆንና የይገባኛል ስሜት ይዞ እንዲዘልቅ ነው! ተከታታይ ሥራ እንዲቀጥል ነው! የ2015 የተቀመጠ ግብ አለ፡፡ ከዚያ እንዲጣጣም ነው - ልማትና በጎ አድራጎቱ፡፡ በተለይ ቀበሌን ዋነኛ አካል በማድረግ ነው ጉዟችን! ሁሉንም ባለድርሻ አካላት (Stake holders) ለማሳተፍ እናጥራለን - አቀናጅተን ለመሄድ ነው ኃላፊነታችን! በቅርቡ  ስምንት ሴክተር ቢሮዎች ተገናኝተን የማህበሩ ዘላቂነትና ባለቤትነት ላይ ተወያይተንበታል፡፡

ለመጪው ትውልድ ልማቱን ማስረከብ ነው ዓላማችን - ዛሬም እዚህ ስብሰባ ላይ ተገኝተን ምናልባት ያላለቁ መሬት ነክ ጉዳዮችን ያካባቢ ጥበቃን እንደ ካርታና የመሣሠሉ ሥራዎች ቢኖሩ ቢሮአችን እየተከታተለ እንዲቀላጠፍላቸው ይጥራል! የቅርብ አጋር ሆነን እንቀጥላለን፡፡ ለቀጣይ 6 ወር ጄክዶ ለማህበሩ በጀት አስቀምጦለታል፡፡ በየ3 ወሩ ክትትል እናደርጋለን Sustain ያደርጋል በእርግጠኝነት!

ትውልድ የሚረካከበው እንዴት ነው? እንዴት ያስረክባል ለወጣቱ? አስባችሁበታል?

ማንኛውም ልማት መሠረቱ ህዝብ ነው፡፡ በተለይም ደግሞ ወጣቱ! ይሄ ድርጅት ከወጣቱ በተጨማሪ ሴቶችና ህፃናት ላይ ነው ትኩረት ያደረገው! ጐሮና ቡቲጂም ይሄንኑ መሥመር ነው የሚከተለው -  ወጣቱ ክፍል የራሱን ሚና መጫወት አለበት፡፡ በበጎ ፈቃደኝነት የሚሠሩ የተማሩ ወጣቶች አሉን፡ በአንድ ዣንጥላ ሥር ናቸው፡፡ ዛሬ ዓለማችን መንደር ሆናለች፡፡ የጎሮና ቡቲጂ ማህበር በሠለጠነ መንገድ መመራት አለበት፡፡

ለዚህ የተማረው ኃይል ማገዝ አለበት፡፡ በዚህ ዓይነት ወጣቱ እየተዋሃደና አመራር እየለመደ ይዘልቃል፡፡ ህብረተሰቡ የራሱ ዕውቀት እንዳለው አውቃለሁ - ከኑሮው የተማረው! ሀብቱን እንዴት እንደሚገለገልበት የእኛም እገዛ በዚህ 6 ወር ይቀጥላል!

አግብተሃል?

አላገባሁም በቅርብ አገባለሁ

ይሄም የስትራቴጂው አካል ነው?

የራሴ ቪዥን አለኝ - አሳካዋለሁ ባይ ነኝ! ለአገርም ለመትረፍ ያ ይሻላል!

አንዱ ሥጋቴ ቮለንታሪዝም (በጎ ፈቃደኝነት) ይሰለቻል፣ ይደክማል ብዬ ነው፡፡ ይታክታል ብዬ እሠጋለሁ፡፡ እስከ መቼ በበጎ-ፈቃደኝነት ይዘለቃል?

ይሄን አስባችሁበታል ወይ? በምን ታስፋፉታላችሁ!

በአፍሪካ፣ ሰብሰሀራን አካባቢ ቮለንተሪዝም ደካማ ነው! በተለይ እኛ አገር ደሞ ዝቅ ያለ ነው! ባህሉም ብዙ የለም፡፡ ግን አሁን ልንገርህ ነቢይ፤ እዚህ ቤት ካለው ¼ኛው በበጎ ፈቃድ የሚንቀሳቀስ ነው! እኔን ራሴን ብትወስደኝ ጎርፍ ሲመጣ የመጀመሪያው ደዋይ ነበርኩኝ - ህዝቤን ለማዳን ነው! የበጎ ፈቃድ ኔትወርክ ውስጥ አለሁበት፡፡ ለልማቱ የበጎ ፈቃደኝነት የአስተሳሰብ ለውጥ መኖር አለበት፡፡ የለውጥ ስሜቱን ማዳበር ያስፈልጋል፡፡ ብዙ አደራጅተናል፡፡   ዕውነቴን ነው የምልህ ሰው ለዘለዓለም በበጎ ፈቃደኝነት አይሠራም - የሰው ባህሪ ነው፡፡  ኢንተረስት አለው፡፡ ብዙ ሴቶች እናቶች አሉ፡፡ ግን አንድ ቀን እንዳልከው ይደክማቸዋል! አገር ሲለወጥ ሰው መሻሻል አለበት፡፡ ማህበሩ ዛሬ በበጎ ፈቃድ ያሠራል፡፡ ነገ ግን ሲያድግና ሀብት ሲያፈራ አቅም ሲያዳብር ፕሮፌሽናል ቀጥሮ ነው ማሠራት ያለበት! ሰው ሲጠቀም ማኅበረሰቡን ይጠቅማልና! ይሄ የበለጠ ጥንካሬ ነው!”

አመስግኜው ወደ ስብሰባው አዳራሽ ተመለስን፡፡ ከቀረቡት ሰዎች ሁሉ የቀበሌ የጤና ተጠሪዋ እጅግ አድርጋ አስገርማኛለች፡፡ ማርካኛለች ብል ነው የሚሻለው፡፡ ቆንጆ ናት፡፡ ብዙ ቆንጆ ጥሩ ተናጋሪ አይደለም፡፡ እሷ ግን ተሳክቶላታል፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ በህዝቡም በድርጅቱ ሠራተኞችም የቀረበው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እርከን በእርከን፣ ከቀበሌ እስከ ላይኛው መዋቅር በ5ቱ ዓመት ውስጥ እንቅፋት ፈጥረውባቸው እንደነበር ብዙ ተናጋሪዎች ቅሬታቸውን አሰምተው ነበር፡፡ ታዲያ የቀበሌዋ ተጠሪ ይህንኑ በማስረገጥ ነበር ንግግሩን የጀመረችው፡፡

“ጎበዝ! ገመድ ጉተታው ይቅር! ገመድ ጉተታና ልማት አብሮ አይሄድም፡፡ ትኩስ ድንች አንወራወር! ዕውነቷን ፍርጥርጥ ብናደርጋት ይሻላል!” ብላ ጀመረች፡፡ በጣም ነው የገረመችኝ፡፡ ሶስቱም አረፍተ-ነገሮች እጭቅ ያለ ሀቅ የያዙ ናቸው! “ነገሩን በአንድ ወቅታዊ ቀልድ ላስረዳችሁ፡፡” አለች ቀጥላ፡፡

“ሠይጣን ለአቤቱታ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሄዳል አሉ፡፡“ምነው ምን እግር ጣለህ?” ይሉታል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡

“በደል ደርሶብኛል ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር”

“ምን ሆነህ ነው የተበደልክ?” አሉት፡፡

“እዚህ አገር መኖር መሮኛል! ስለዚህ መልቀቂያ ቪዛ (exit visa) እንዲሰጠኝ ያድርጉልኝ!”

“እኮ ለምን? የተበደልከውን ነገር ንገረኝና እንዳካሄድ ልንፈታው የምንችለው ነገር ከሆነ ይፈታል፡፡ ምንድን ነው የቸገረህ?”

“ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር! ቢሮዎችዎ ውስጥ ያሉት ሰዎች የእኔን ሥራ ወስደውብኛል! ስለዚህ ሥራ ፍለጋ ከኢትዮጵያ ውጪ ሌላ አገር መሄድ አለብኝ!” አላቸው…

ብላ ጨረሰች፡፡  እኔም በሆዴ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “አዪ! ይህ የሥራ አጥ ቁጥር በጣም እየጨመረ ነው ማለት ነው!” ብለው ሲያዝኑ ታዩኝና አዘንኩ!

“ስለዚህ” አለች የቀበሌዋ ተጠሪ “ዛሬ ቃል መግባት አለብን፡፡

ህዝብ ፊት እንማማል! በምንም ዓይነት በየቢሮአችን የሚመጣውን ባለ ጉዳይ ከእንግዲህ አናስቸግር - ከመንግሥት ቢሮ የመጣን ሁሉ ኑ ወደዚህ መድረክ! እንቅፋት እንደማንሆን ለህዝቡ እናረጋግጥ! ይህን ሳንጨርስ ከዚህ ንቅንቅ አንልም ዛሬ!” ከፍተኛ ጭብጨባ ተደረገላት!

የስብሰባው መንፈስ በአጠቃላይ በጣም አስገራሚ ነው፡፡ ከመንግሥትም፣ መንግሥታዊ ድርጅት ካልሆነም፣ ከህዝብም የሚሰጠው አስተያየት እጅግ አስደምሞኛል! የበሰለ፣ ሙሉ - ልባዊ እና ቀና አስተያየት ተሰንዝሯል፡፡ እንዲህ ዓይነት ውይይት አይቼ የማውቀው ምናልባት ማዕከላዊ እሥር ቤት ይመስለኛል! ለምሳሌ የመንግሥት ሴክተር ቢሮዎች ቃል እንግባ ብላ የቀበሌዋ ልጅ ስትናገር ከህዝቡ መካከል አንዱ ተነስቶ “ለምን የመንግሥት ቢሮዎች ብቻ እኛም ህዝቦቹ ሁለተኛ የለማውን ላናጠፋ፣ የተተከለውን ላንነቅል፣ የተሠራውን ላናፈርስ ቃል እንግባ!” አለ፡

“ዋና የሥራ ምሣሌ የጎርፉ አደጋ ጊዜ ያየነው ነው” አለ ሌላው ድርጅቱንም በማድነቅ!

“ፕሮጀክት ማለት ወር-ተረኝነት ነው! እኛ የድርጅቱን ፕሮጀክት የምንረከበው በዚህ መንፈስ ነው”

“ጄክዶ የተባው ድርጅት ህብረተሰብ በራሱ መቆም መቻሉን ብቻ ሳይሆን በሁለት እግሩ መሄድ መቻሉን አስመስክሯል!” አለች አንዷ፡፡

“መካሪ፣ ሥራ ፈጣሪ፣ ታታሪ ወጣት በመፍጠር፤ ጎርፍ በመከላከል፤ ድህነት በመቀነስ፣ ሠርቶ በማደር ድሬዳዋ ትለወጣለች!” አሉ ሌላው፡፡

“ሰውን መለወጥን ያህል ከባድ ሥራ የለም”!

“በየቢሮው ያሉት አፍራሾች የወሰዱትን አቋም የመንግሥት አቋም አናድርገው!” አለ አንድ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ፡፡ “መንግሥታዊ ቢሮ ሄደን ፈርተን አንመለስ፤ ድፍረት ይኑረን ሀሞት ይኑረን”

አንዲት ልበ-ሙሉ ሴት ደሞ ተነሳችና፤ “እኛን የኢኮኖሚ ቁጠባ ያስተማረን ድርጅት ዛሬ ለጎሮ ቡቲጂ ማህበር አስረክቧል፡ ጎሮ ቡቲጂ ደግሞ ነገ ለእኛ ያስረክበናል!” “ጭብጨባው ቀለጠ!

አንድ የሴክተር ኃላፊ ተነስቶ “መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት የማይተካ ሚና አላቸው” ብሎ ነው የሚያምነው መንግሥት! NGOዎች የልቀት ማዕከል መሆን አለባቸው! (Center of excellence)” በጣም ረዥምና ጣፋጭ ስብሰባ ነው ያጋጠመኝ! ብዙ ሀሳቦች ተብላልተዋል፡፡ ስብሰባውን የመራው የፋይናንስና ኢኮኖሚው ወንድየ ሙሉጌታ እንዲህ አጠቃለለው፡-

መንግሥት፣ NGO እና የግል ሴክተሩ በአንድነት ልማትን ያረጋግጡ! ችግሮቻችን መማሪያ ይሁኑ! መንግሥትም NGOም በአገራችን ለውጥ አምጥተዋል! እንደ ጄክዶ ያለ አርአያ ድርጅት ራዕይን፣ ቁርጠኝነትን፣ እያደረጃጀን ያስተማረን ት/ቤት ነው! ህዝብን የልማት ባለቤት ማድረግ ፈታኝና የአመለካከት ለውጥ የሚጠይቅ ትልቅ ጉዳይ ነው! አንድ ቤት የሚሠራ ሰው ሣር አይሻማም - የኦሮሚኛ ተረት! ጐሮና ቡቲጂ ልማቱን ዘላቂ እንዲያደርግ የ6 ወር በጀት ልማት ተደርጎለታል! ነገ ነፃ ሆኖ መቀጠል አለበት! ውጊያው ካሁን ይጀምራል! ትልቁ ሥልጣን የቀበሌ ስለሆነ ከሱ ጋር ተጣጥሞ መሥራት አስፈላጊ ነው - ያላለቀው የጋራ ነገር ክትትሉ አይዘንጋ! አንድነትን መሬት አውርደን ስናየው ልማት ማለት ምን እንደሆነ እንገነዘባለን!

የርክክብ መፈራረሙ ሥነስርዓት ተጀመረ፡፡ ግብርና፣ ፋይናንስ፣ ኢኮኖሚ እና ቀበሌ በታሳቢነት ተሰደሩ፡፡ ፊርማ ሰፈረ፡፡ ርክክቡ አበቃ!

የመታሰቢያና የሽልማት ፕሮግራም ለቀበሌ 02 ተወካይ እና በኋላም ለጄክዶ ተካሄደ - ዕልልታው ቀለጠ! የኢህማልድ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሙሉጌታ ገብሩ የመቋጫውን ንግግር አደረገ፡፡

ዋና ዋናው ሀሳቦቹ እነሆ፡- “ምሥጋና ለሁላችሁ” ሲል ጀመረ፡፡ “ስለ ድርጅቱ 26 ዓመት ዕድሜ መሆን፣ ለዚህ አገር የሚገባውን ሥራ እንደሠራ፣ ህፃናት ላይ እናተኩራለን፡፡ ሦስት መስኮች አሉን - መሠረታዊ አገልግሎት አየር ንብረትና የሚያስከትለው የአቅም ግንባታ ማካሄድ ሁለት ቦታዎች ላይ እየሠራን ነው - ባህር ዳር ላይና ቢሾፍቱ ላይ፤ በባህር ዳር 170ሺ ካ.ሜ ቦታ፡፡ በቢሾፍቱ ላይ 55ሺ ካሬ ቦታ አለ፡፡ ደብረ ብርሃን ላይ 22ሺ ካ.ሜ ቦታ አለን - መንግሥት የሰጠን፡፡ ይሄ የብዙ ሚሊዮን ብር ድጋፍ ነው በገንዘብ ቢተመን! 155 ሠራተኞች አሉት፤ ከዚያ ውስጥ 80 የሚሆኑት የመጀመሪያ ዲግሪና ማስተርስ አላቸው፡፡

ሠራተኞቻችን በጣም ጎበዝና ታታሪ መሆናቸውን እመሰክራለሁ! የቡድን ሥራ ይሠራሉ - commitment አለ፡፡ እንደዛው ሁሉ ኃይለኛ ግጭትም አለ!

አንዱ እዚህ ድርጅት ውስጥ የሚያቆየኝ የሠራተኞቼ መበርታት ነው! ምክር አለ መተማመን አለ! ብዙና ሠፊ ግንኙነት አለን፤ ከውጪው ዓለም! ያገር ውስጥ ኤምባሲዎች ጋር አብረን እንሠራለን! የአገር ልማት የዛሬ 16 ዓመት ባህርዳ ዳር ላይ ሥራ ስንጀምር፤ Outreach ፕሮግራም ማለት ነው፤ ኮሚቴዎች አቋቋምን… የትምህርት፣ የጤና - በሰባት ዓመት ውስጥ

1ኛ የባለቤትነት ስሜቱ ኃይለኛ ነው፡፡

2ኛ. ወጪው አነስተኛ ነው፡፡

3ኛ. ቀጣይነቱ አስተማማኝ ነው፡፡

ስለዚህ ከማህበረሰብ ጋር መሥራት አዋጪ እንደሆነ ተገነዘብንና ዛሬ ከ145 ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር እንሠራለን - በ15 ቦታዎች የአቅም ግንባታ፣ የልምድ ልውውጥና የቴክኒካል ድጋፍ እናደርጋለን! ጐሮ ቡቲጂ አንዱ ነው! ጥሩ የዳበሩ ልምድ አለን ብዬ በጣም አረጋግጣለሁ!”

እስካሁን 10 ፕሮጀክቶች በተለያየ ቦታዎች አስረክበናል - እንደዛሬው! በህግና በገንዘብ ብዙ ለመሥራት ይቻላል … ብዙ ማለት አልፈልግም … ግን ከሁሉም ነገር በላይ ግን ያለኝ አስተያየት አንድ ቴክኒካል ኮሚቴ ቢቋቋም የሚል ነው! በሀገር በቀል ሀብት ላይ እናተኩር፤ መሬት ገንዘብ የሰው ኃይል አለን! ወረቀት ፅፈን ሀሳብ አፍልቀን ሸጠን (ለዓለም አቀፍ ውድድር) የምናገኘው ገንዘብ ነው! ለሀገር ለወገን አስተዋፅኦ እናረጋለን - ጎሮ ቡቲጂ እዚህ ማህ ነው ያለው!

የስዊድንን አምባሳደር ደብረዘይት አግኝቼው ነበር - ከ3 ዓመት በፊት፡፡ ስዊድን የዛሬ 200 ዓመት ከ6 ሚሊየን ህዝብ 1 ሚሊየኑ ተሰደደ፡፡ ረሀብ ነው ጥማት ነው፤ ስለዚህ ተሰደደ የሚበላ የለም የሚጠጣ የለም - ወደ አሜሪካን፡፡ ወንዱ ሥራ አይሠራም - አልኮሊስም ሆነ! ቮድካ ነበር የሚጠጣው፤ ስለዚህ መንግሥት መጠጥ እንዳይጠጣ አዋጅ አወጣ፡፡ የሴቶች እንቅስቃሴ ጀመሩ ለዚህ ነው እኛም ሴቶች ላይ የምናተኩረው፡፡

ሠራተኛ ፈጠሩ፡፡

ዲሞክራሲ አስፋፉ፡፡ ለዚህ ነው - ዛሬ ስዊድን በዓለም ከፍተኛ ገቢ ካላቸው አገሮች አንዱ የሆነችው፡፡

አሁን ራሱን ችሏል ማህበራችሁ ለአቅመ-አዳም ደርሷል! ከጎኑ እንደምንቆም አረጋግጣለሁ፣ የድሬዳዋ ሰው አቀባበል ነው የማረከን - አብረን እንቀጥላለን! ሁላችሁንም አመሰናግለሁ!

ዋናው ሥራ አስኪያጅ አንድ ቴክኒካል ኮሚቴ መቋቋም አለበት ባሉን መሠረት፣ አቤ “ይሄን ኮሚቴ አቋቁመን ነገሩን አሥረን መሄድ ነው ያለብን!” አለና “እኔ መነሻ ሀሳብ ልስጥ … ፋይናንስና ኢኮኖሚ አንዱ ቢሆን ልዩነት አለ?” ሲል ጠየቀ፡፡ “የለም!” አለ ተሰብሳቢው፡፡

“ግብርና አንዱ ቢሆን … የአካባቢ አደጋ መከላከል አንዱ ቢሆን … ቀበሌ መስተዳድሩ አንዱ ቢሆን… በዋናነት እኛም አለንበት … ጄዲካና አኮርድን ብንጨምረው? ወዘተ ... ተቃውሞ አለ?”

“የለም!”

“ስለዚህ ጉንጭ ሞልቶ ሌላ ነገር አይጐረስም ነውር ነው አደል?” ይሄን ይሰራል ኮሚቴው! የልማት ፍላጐት አለን - ዋናው ነገር ነው!” በዚሁ አመስግነን እንለያያለን - አንድ የኦሮሞ ተረት አለ - በቅጡ የተቋጠረ አይተረተርም! - ዛሬ ቋጥረናታል አመሰናግለሁ፡፡

ቀጥሎ የምሣ ግብዣ ስለተደረገልን ያ ደግና ሥራህ - ብዙ ሾፌር እየሾፈረ ፓራዲዞ ሆቴል አደረሰን!

በገበታው ዙሪያ ተደረደርን … ከፊሉ ዶሮ አሮስቶ ከፊሉ ፓስታ፣ ሌላው የፍየል አሮስቶ፣ ከፊሉ ክትፎ …. አዘዘ፡፡ “የፍየል አሮስቶ አልቋል!” አለና ቦዩ ዋናውን ምግብ ነሳን! ወደ ዶሮ አሮስቶ ተጋባን! እሱም ብዙ አላማረን! አንዷ አብራን ያለች፡-

“ምነው ባቢሌ ውሃ በዛ? አዳሜ በይሉኝታ ታጥሮ ነው እንዴ? ለእኔ ቢራ ስጠኝ ባክህ?” አለች፡፡ የልጅቷ ልበ-ሙሉነት ላይ የድሬዳዋ ልጅነት ተጨምሮ ዕውነትን ፀሀይ ላይ አወጣው፡፡

የበዓሉ ግርማ “ከአድማስ ባሻገር” ላይ አውሮራ ቡና ቤት ገና እንደቆሙ ቦዩ ትኩስ ቡና ይዞላቸው ሲመጣ፤

“የልብ አውቃ!” ትላለች ሉሊት ታደሰ፤ በተለይ ቡና ስትል የታችኛው ከንፈሯ የልብ ቅርፅ የሚሠራው ጠይሟ ጣዖት! እኔም ቢራ ያዘዘችውን ቀይ ልጅ፤ “የልብ አውቃ!” ብያታለሁ በልቤ!

የዕለት ቢራዬን አዝዤ ጠጣሁ! የዕለት ቢራዎቿን አዛ  ጠጣች፡፡ ከዛ አንዳንዱ ማዘዝ ጀመረ፡፡

ቀዩዋ ልጅ እግዚሃር ይስጣት ከሰዓት በኋላ ሆቴል ቁጭ ብዬ የሚከተለውን ግጥም ፃፍኩ፡-

የወፍ ጫጩት

በቀኗ ተወልዳ፣ አንዲት የወፍ ጫጩት

ዛፍ ላይ፣ ጎጆዋ ውስጥ፣ እናቷ አስቀምጣት

ስትሰጣት ሰንብታ፣ የጉያዋን ሙቀት፡፡

አንድ ቀን ማለዳ

አገሬውን ጠርታ፡-

“እኔ ልበር ነው፤ ሣር ውሃ ፍለጋ፤ ለሌሎች ልጆች

ደሞ እንደልማዴ፣ ልሩጥ ከላይ እስከ እታች

ይቺ ልጄ ግና፣ ይቺ ድንቢጥ ተስፋ

የናንተው ሀብት ናት፤

ተረከቡኝና

ከፊላችሁ ሰማይ፤ ከፊላችሁ መሬት

ሁኑና ጠብቋት!

ከጎጆዋ ብትወድቅ፣ አንሷትና አክሟት

አሥር ጊዜ ብትወድቅ

አሥር ጊዜ አቅፋችሁ

ቦታዋ መልሷት!

ህዝብ ያቀፈው ገላ በዋዛ አይቀጭም

አጥንተ - ጥኑ ናት!

እግሮቿ እስኪቆሙ ክንፎቿ እስኪበሩ

አሳድጓትና፤ አብራችሁ ብረሩ!

(ለጐሮ ቡቲጂ፣ ለጄክዶና ለድሬዳዋ ሰው)

ሰኔ 09 2004 ድሬዳዋ

 

 

Read 2119 times Last modified on Saturday, 30 June 2012 11:15