Monday, 03 February 2020 11:31

በቻይና የሚማሩ ኢትዮጵያውያን፣ መንግስት እንዲደርስላቸው ተማፀኑ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(13 votes)

        - ቫይረሱ በተቀሰቀሰበት ከተማ ከ300 በላይ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች አሉ
                  - ኬኒያን ጨምሮ 5 የአፍሪካና በርካታ አገራት ወደ ቻይና በረራ አቁመዋል
                  - የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ቻይና የሚያደርገውን በረራ ቀጥሏል
                  - በሽታው የወቅቱ አሳሳቢ የምድራችን የጤና ስጋት ተብሏል
                       
             የዓለም የጤና ድርጅት የወቅቱ አሳሳቢ የምድራችን የጤና ስጋት በሚል በፈረጀው የኮርኖ ቫይረስ በተጠቃችው ሁዋን ከተማ የሚኖሩ ከ300 በላይ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች፣ መንግስት ወደ አገራቸው እንዲመልሳቸውና ከበሽታው እንዲታደጋቸው ተማጽነዋል፡፡
በቻይና የተቋቋመው የኢትዮጵያ ተማሪዎች ህብረት ባወጣው መግለጫ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች የሚገኙበትና የበሽታው መነሻ የሆነችው ሁዋን ከተማ ከማንኛውም የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ ታግዳለች፡፡ ተማሪዎቹ ከዩኒቨርስቲዎቹና ከመኖሪያ ክፍሎቻቸው እንዳይወጡና ከማንኛውም የእርስበርስ ግንኙነት ታቅበው እንዲቆዩ ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ምግብና መጠጥ ከዩኒቨርሲቲው የሚያገኙ ቢሆንም፣ በበሽታው የመያዝ ስጋታቸው ለከፍተኛ ጭንቀትና ውጥረት እንደዳረጋቸው አስታውቋል፡፡
የህብረቱ መግለጫ እንደሚያመለክተው፤ እስከአሁን ድረስ በቫይረሱ የተያዘም ሆነ የተጠረጠረ ኢትዮጵያዊ ተማሪ የለም፡፡ ይህ ሁኔታ ለጊዜው ከበሽታው ነፃ መሆናችንን የሚጠቁም ቢሆንም፤ በዚህ ሁኔታ እዚህ ከተማ የምንቆይ ከሆነ ግን ለበሽታው መጋለጣችን አይቀርም፤ አሁን ዋንኛው ጥያቄያችን ያለንበት ሁኔታ ከፍተኛ የጤና ስጋት የፈጠረብን በመሆኑ በአስቸኳይ ወደ አገራችን መመለስ የምንችልበትን ሁኔታ  መንግስት እንዲያመቻችልን ነው ሲሉ ተማጽኖአቸውን በህብረቱ አቅርበዋል፡፡ ተማሪዎቹ ጥያቄያቸውን ለኤምባሲውና ለቆንስላ ጽ/ቤቱ እንዳቀረቡ ገልፀው፤ ምላሽ በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የአለም ጤና ድርጅት፣ የወቅቱ አሳሳቢ የምድራችን የጤና ስጋት ነው ያለው የኮርኖ ቫይረስ፤ ዝቅተኛ የጤና ሽፋን ባላቸው አገራት ቢከሰት ጉዳቱ ከባድ እንደሚሆን የአለም ጤና ድርጅት ገልጿል፡፡ የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ይፋ እንዳደረጉት፤ ኮርኖ ቫይረስ የአለም ስድስተኛው የወረርሽኝ ስጋት ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ ከዚህ ቀደም ኤችዋንኤንዋን የተባለው ኢንፍሉዌንዛ፣ ኢቦላ፣ ፖሊዮና ዚካ በተመሳሳይ ሁኔታ የወቅቱ አሳሳቢ የምድራችን የጤና ስጋት ሆነው ተመዝግበው ነበር፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም “ታይቶ የማይታወቅ ወረርሽኝ” ሲሉ የገለፁት ኮርኖ ቫይረስ፤ እስካሁን 213 ሰዎችን የቀጠፈ ሲሆን 10ሺ የሚደርሱ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን፣ እንዲሁም በሌሎች 18 አገራት 98 የቫይረሱ ተጠቂዎች መገኘታቸውን የአለም ጤና ድርጅት ይፋ አድርጓል፡፡ በሽታው የተለያየ ፈጣን ምላሽ የሚያስፈልገው እንደሆነም ዶ/ር ቴዎድሮስ ተናግረዋል፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት የዚህን ዓይነት አዋጅ የሚያውጀው የበሽታው ወረርሽኝ የተለየ ሲሆንና በዓለም አቀፋዊ ስርጭት መጠኑ ለሌሎች አገራትም ከፍተኛ ስጋት ሲሆን ነው - ዓለም ከኮርኖ ቫይረስ የሰጠው ምላሽ፡፡
የተለያዩ አገራት ዜጐቻቸውን ከቻይና እያስወጡና በተለየ የማቆያ ስፍራ እንዲቆዩ በማድረግ ምርመራ እያካሄዱ እንደሚገኑ እየተዘገበ ነው፡፡ እንግሊዝ፣ አውስትራሊያ፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ሲንጋፖር፣ ኒውዘርላንድ… ዜጐቻቸውን ከቻይና እያስወጡ ይገኛሉ፡፡
አውስትራሊያ በቻይና የነበሩና በበሽታው ተይዘው ሊሆን ይችላል ያለቻቸውን ዜጐቿን ከከተማዋ 2ሺ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ አስፍራ ምርመራ ለማድረግ ወስናለች፡፡
ኢጣሊያ ወደ ቻይና የምታደርገውን በረራ አቋርጣለች፡፡
አሜሪካ ከሁዋን ከተማ ያስወጣቻቸውን 200 ዜጎቿን በፍሎሪዳ ለብቻቸው ተገልለው የሚቆዩበት ስፍራ በማዘጋጀት ምርመራ እያደረገች ነው፡፡
ሩሲያ ከቻይና ጋር የሚያዋስናትን 4 ሺ 3 መቶ ኪሎ ሜትር ድንበር ዘግታለች፡፡
ከአፍሪካ ማዳጋስካር፣ ሞሮኮ፣ ሴኒጋል፣ ኬኒያና ሩዋንዳ ወደ ቻይና የሚደረጉ በረራዎችን ሙሉ በሙሉ ሰርዘዋል፡፡ አየር መንገዶች ትኬት የቆረጡ ደንበኞቻቸውን ገንዘብ ለመመለስ መወሰናቸውን ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ቻይና ግዛቶች ቤይጂንግ፣ ሆንግኮንግ፣ ሻንጋይ፣ ቻንዱና ጓንዡ የሚያደርጋቸውን በረራዎች እንደቀጠለ መሆኑ ታውቋል፡፡
ከሁዋን ከተማ ወደ አዲስ አበባ የገቡ አራት ሰዎች በቫይረሱ ተጠርጥረው ምርመራ የተደረገላቸው ሲሆን ከበሽታው ነፃ መሆናቸውም ተረጋግጧል፡፡ በቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል ቅጥር ግቢ ውስጥም በበሽታው የተጠረጠሩ ሰዎችን ለማቆየት የሚያስችል ጊዜያዊ የማቆያ ጣቢያ ተዘጋጅቷል፡፡
ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ከቻይና ጋር በገነባችው ጠንካራ ግንኙነት በርካታ ኢትዮጵያውያን ለንግድ፣ ለሥራና ትምህርት ወደተለያዩ የቻይና ግዛቶች ይጓዛሉ፡፡ እነዚህ ዜጎች በአሁኑ ወቅት እጅግ አሳሳቢ በሆነ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ መሆኑንና መንግሥት እንደ ሌሎች አገራት ሁሉ ለዜጎቹ ደህንነት ቅድሚያ በመስጠት በከፍተኛ ሥጋት ያሉትን ኢትዮጵያውያን ሊታደግ እንደሚገባ ልጆቻቸው በቻይና የተለያዩ ግዛቶች ውስጥ በትምህርት ላይ የሚገኙ ተማሪዎች ወላጆች ተናግረዋል፡፡
የኮርኖ ቫይረስ ስርጭት በአስደንጋጭ ሁኔታ እየጨመረ ሲሆን በአንድ ቀን ብቻ የበሽታው ስርጭት ከ2 ሺ ሰዎች በላይ መጨመሩን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ በሽታውን የሚያድን መድሃኒትም ሆነ መከላከያ ክትባት እስካሁን ድረስ አለመገኘቱም በሽታውን እጅግ አሳሳቢ ያደርገዋል ተብሏል፡፡  እንደ ሆንክኮንግ ባሉ አገራት ደግሞ ነዋሪዎች የሁለትና ሦስት ሰዓት ወረፋ እየጠበቁ የፊት መሸፈኛ ማስኮችን እየገዙ መሆኑ ተዘግቧል፡፡

Read 11407 times