Monday, 03 February 2020 11:29

ኦፌኮ በአቶ ጀዋር ጉዳይ ከጥር 29 በፊት ምላሽ እሰጣለሁ አለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

   ኦፌኮ በአባልነት የተቀበላቸውን የአቶ ጀዋር መሀመድ የዜግነት ጉዳይ አስመልክቶ ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለቀረበለት ጥያቄ ሕጋዊ ምላሽ ማዘጋጀቱን አስታወቀ፡፡
ምርጫ ቦርድ ተገቢና ሕጋዊ መሠረት ያለው ጥያቄ ነው ያቀረበልን ያሉት የፓርቲው ጽ/ቤት ኃላፊ፣ አቶ ጥሩነህ ገምታ፤ እኛም ሕግን አጣቅሰን ሕጋዊ ምላሽ አዘጋጅተናል ብለዋል፡፡
በአዋጅ 278/96 አንቀጽ 22 ላይ፡-
‹‹የኢትዮጵያ ዜግነትን መልሶ ስለማግኘት›› በሚለው ድንጋጌ ላይ በንኡስ አንቀጽ፤  አስቀድሞ ኢትዮጵያዊ የነበረና በሕግ የሌላ አገር ዜግነት አግኝቶ የነበረ ሰው፡-
ሀ. ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ በመምጣት መደበኛ ኑሮውን በኢትዮጵያ ከመሰረተ፤
ለ. ይዞት የነበረውን የሌላ አገር ‹ዜግነት ከተወ እንዲሁም በተራ ቁጥር ሐ. ዜግነት እንዲመለስለት ካመለከተ፣ ኢትዮጵያዊ ዜግነቱን መልሶ ያገኛል› ይላል፡፡
በዚህ መሠረት ግለሰቡ ኢትዮጵያ ውስጥ መኖሪያውን ማድረጉን፣ አሜሪካዊ ዜግነቱን መመለሱን እንዲሁም ጥር 13 ቀን ለኢምግሬሽንና ዜግነት ጉዳይ ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ኢትዮጵያዊነቱ እንዲመለስም ማመልከቱን፣ ማመልከቻውን የተቀበለው ኃላፊም ‹‹ማመልከቻው ደርሶን ተቀብለናል›› የሚል ማረጋገጫ ፊርማ መስጠቱን አረጋግጠናል ብለዋል - ኃላፊው፡፡  በዚህ መሰረት ግለሰቡ ኢትዮጵያዊ ዜግነቱን መልሶ የማግኘት ሕጋዊ አካሄዱን ማጠናቀቁን ስላረጋገጥን ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይህን አብራርተን ለመመለስ ደብዳቤ አዘጋጅተናል ብለዋል - ለአዲስ አድማስ በሰጡት ማብራሪያ፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ለኦፌኮ ለሁለተኛ ጊዜ የጻፈው ደብዳቤ፤ ‹‹እስከ ጥር 29 ቀን 2012 የግለሰቡን ዜግነት አረጋግጣችሁ ምላሽ ስጡ›› የሚል ሲሆን የፓርቲው ኃላፊ፣ ደብዳቤው ከጥር 29 ቀን 2012 በፊት የሊቀመንበሩ ፊርማ ተደርጎበት ለቦርዱ እንደሚቀርብ አስታውቀዋል፡፡ በሌላ በኩል፣ ቦርዱ ሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶችም በአዲሱ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የምርጫ ሕግ መሠረት በአባልነት የመዘገቧቸውን ግለሰቦች ዝርዝር መረጃ እንዲያቀርቡ መጠየቁን የቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ አስታውቀዋል፡፡  


Read 9438 times